Latest

በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ተስፋ የቆረጡ ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት እኩይ ሴራ ፈፅሞ አይደናቀፍም-ኢህአዴግ

በሀገሪቱ የተጀመረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ለውጥ ተስፋ የቆረጡ ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት እኩይ ሴራ ፈፅሞ አይደናቀፍም አለ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በዛሬው እለት “ለውጥን እንደግፍ፤ ዴሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በድርጅቱ ሊቀ መንበር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት በሀገሪቱ ለተጀመረው ለውጥ እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለማድነቅና ምስጋናን ለማቅረብ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በደረሰዉ ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል ብሏል በመግለጫው።  
ምክር ቤቱ ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለመላ ኢትዮጵያዊያንም መጽናናትን ተመኝቷል።
መግለጫው ኢሕአዴግ ይህን የተስፋ መቁረጥና የጥላቻ ፖለቲካ መገለጫ የሆነ አፀያፊ ድርጊት በፅኑ አወግዛለሁ ያለ ሲሆን፥ የተጀመረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ለውጥ ተስፋ የቆረጡ ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት እኩይ ሴራ ፈፅሞ ሊደናቀፍ እንደማይችል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አረጋግጣለሁ ብሏል።
የድርጅቱ ሊቀ መንበር ዶ/ር አብይ አህመድ በንግግራቸው ጥላቻና በቀልን ሳይሆን ፍቅርና አንድነትን፤ ዘረኝነትንና ሙስናን ሳይሆን መደመርንና ሀገር ወዳድነትን ባከበሩበት የሚሊዮን ንፁህ ኢትዮጵያዊያን መድረክ ላይ የተፈፀመው ይህ የተሸናፊዎች የወንጀል ድርጊት በመስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ለአፍታም ሳንዘናጋ ጠብቀን እንድንዘልቅ፤ የጀመርነውን የፍቅር፣ የእርቅና የአንድነት ጉዞ አጠናክረን እንድንቀጥልበት የሚገፋን እንጂ ወደኋላ የሚጎትተን አይደለም ነው ያለው።
መላው ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው አደባባይ በመውጣት ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገራዊ አንድነት ያላቸውን ፅኑ እምነት እንዲሁም ለመሪያቸው ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር የገለፁበትን መንገድ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት በማድነቅ ወደፊትም ከድርጅቱና ከመሪው ጎን ቆሞ ትግሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ለፍቅር፣ ለይቅርታና አንድነት የዘረጋችው እጅ መቼም የማይታጠፍ መሆኑን በመረዳት በተረጋጋ ሁኔታ መደበኛ ተግባራችሁን እንድትቀጥሉም ከአደራ ጋር አሳስባለሁ ነው ያለው ፅህፈት ቤቱ።

No comments