የዳች በሽታ! ኤርሚያስ ለገሰ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የነዳጅ ማግኘት ብስራት ስሰማ ቀኑን ሙሉ የተደበላለቀ ስሜት ተሰምቶኝ ዋለ። በኢህአዴግ ፓለቲካ ውስጥ ቆይታ የነበራችሁና አሁንም ያላችሁ ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት እንደሚሰማችሁ እገምታለሁ።
"የመለስ ልቃቂት" በሚለው ሁለተኛ መጽሐፌ ላይ ሰፊ ሽፋን የሰጠሁትም በዚህ ምክንያት ነው። በዚህ አጋጣሚ መጽሐፋ በእጃችሁ ላይ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን " የዳች በሽታ!" በሚል ርዕስ በምዕራፍ ስምንት ከገፅ 252 -324 ያለውን መልሳችሁ እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ።
ይሄ ከ70 ገጽ በላይ ሽፋን የተሰጠው ምእራፍ በፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ፍትጊያ ሲካሄድበት የነበረ የአይዲኦሎጂ እና የፓሊሲ ልዩነት የሚንፀባረቅበት ነው። አቶ መለስ በዚህ ዙሪያ የሚነሳበትን ጥያቄ መመለስ ስለማይችልና የተደበቀ አጀንዳ ስላለው ምላሽ ሲሰጥ በከፍተኛ ድንፋታ እና ስድብ ነበር። በ" የመለስ ልቃቂት" መጽሐፍ ላይ በፓርቲው የፓሊሲ ስልጠና ወቅት " ማዕድን ላይ ትኩረት እንስጥ" ብለው የተከራከሩ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች በአቶ መለስ የደረሰባቸውን የስድብ ናዳ ማየት ይቻላል።
ዛሬም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ እጅግ በጣም በጥንቃቄና በስጋት ውስጥ ሆኖ ብስራቱን ሲያሰማ የሁለት አስርተ አመቱ የውስጠ ድርጅት ፍትጊያ በገፅታው ላይ አንብቤያለሁ። ዶክተር አቢይ ነዳጅ ልናወጣ ነው ከሚለው ፍንደቃ በላይ ከነዳጅ ማውጣቱ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው አደጋ አስጨንቆታል።
ኪራይ ሰብሳቢ ከሚለው ቋንቋ ይልቅ " ስግብግብ ውሻ" የሚለውን አገላለጥ የተጠቀመው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። ምናልባትም የመለስ የተደበቀ አላማና ራዕይ አራማጆች ጋር በውስጠ ድርጅት ከፍተኛ ጭቅጭቅ አድርጐ ሳይቀበላቸው ይፋ አድርጐት ይሆናል። ምናልባት ሰሞኑን እያደረገው እንዳለው ጉዳዩን ወደ ፓርቲው እና ሚኒስትሮች ምክርቤት ሳይወስደው ከለውጥ ሀይሉ የቡድን አባላት ጋር ብቻ መክሮ አደባባይ አውጥቶት ይሆናል።
ይህ ከሆነ ደግሞ ምናልባትም በቀጣይ ቀናት ዶክተር አቢይ ከህውሓት ጋር ተጨማሪ ፍጥጫ ውስጥ ሊገባ ይችላል። ህውሓቶች እንደቀደመው የፕራይቬታይዜሽን ውሳኔዎች ለህዝብ ቀድሞ መገለፅ አልነበረበትም የሚል መግለጫ ወደ ማውጣት ባይሄዱም የተለያዩ እንቅፋቶች ሊፈጥሩ ይችላሉ።
ህውሓቶች ከሚፈጥሩት እንቅፋት የቅድሚያውን የሚይዘው ነዳጁ የሚወጣበት አካባቢ ህዝብ በተቃውሞ ማነሳሳት ነው። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችን የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ አካባቢውን የቀውስ ቀጠና ሊያደርጉት ይችላሉ። ከቡድን አሳስኔሽን ጀምሮ ቅልጥ ያለ የጦር ቀጠና በማድረግ ክልሉን የደም ጐርፍ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ህውሓቶች ሁለተኛ የሚያደርጉት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተገንጣዮችን ከማስታጠቅ አልፈው የመገንጠል ጥያቄያቸውን እንዲያነሱ የኃላ ሽፋን ይሰጣሉ። ተገንጣዮቹ የዶክተር አቢይን መንግስት የሚያስጠነቅቅ እና ለሚፈጠረው ቀውስ ሃላፊነት መውሰድ እንዳለበት የሚያመላክት መግለጫ እንዲያወጣ ያደርጋሉ።
ይሄ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከሰት ይመስለኛል። ተገንጣዮቹ ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሰአት የውጭ ዜጐቹንም ሆነ የነዳጅ ፋብሪካው ሰራተኞች ላይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። በሂደትም ናይጄሪያ ውስጥ የተለመደውን የነዳጅ ቧንቧዎች መቆራረጥና እሳት መለኮስ በኢትዮጵያም ተግባራዊ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ህውሓቶች ሶስተኛ የሚያደርጉት በራሳቸው እና በሚቀጥሯቸው ምሁራን ( አብዛኛው የትግራይ ስም የሌላቸው) የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ ማውገዝ ይሆናል። በምሁራን ስም የሚወጡት ሰነዶችና መጣጥፎች እንዲሁም የፕሮፐጋንዳ አቅጣጫዎች የዶክተር አቢይ እርምጃ ፀረ -አብዮታዊ ዲሞክራሲና ፀረ -ልማታዊ መንግስት መሆኑን የሚያስተጋቡ ይሆናሉ።
ውሳኔው ኪራይ ሰብሳቢነት የወለደው እንደሆነ ሊገልፁ ይችላሉ። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፓሊሲ ሰነዶችን እያጣቀሱ የመስመር ክህደት ተፈጽሟል ሊሉ ይችላሉ። ለምሳሌ " የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የልማት መስመሮችና ስትራቴጂዎች" በሚለው የፓርቲው ፓሊሲ ገፅ 212 -215 ላይ የሚከተለውን ይላል፣
"የማእድን ልማት እኛ ከምንፈልገው አስተማማኝ፣ ፈጣንና ዘላቂ ልማት ጋር የሚሄድ ባህሪያት የሉትም። የአገሪቱን የልማት አቅሞች የሚያመክን ነው። የማእድን ሀብት ልማት በተለምዶ የዳች በሽታ (Dutch Disease) እየተባለ የሚጠራውን ችግር ይፈጥራል።… የማዕድን ስራ እንደ ሁሉም ሁሉም የኪራይ የማሰባሰብ ስራ በመሰረታዊ የልማት አቅጣጫችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው።
የማዕድን ልማት ዋነኛ የልማት አቅማችንን በመሰባበር ኪራይ የማከፋፈል ባህሪ እንዲጐለብት ያደርጋል። ይህም የምርታማነት አቅማችንን በማሽመድመድ ወደ አጠቃላይ ፓለቲካ ችግር ሊወስደን ይችላል።"
እዚህ ላይ የህውሓት አመራሮች ከላይ የተቀመጡትን ሶስት አደገኛ ተግባራት የማይፈፅሙበት አንድ እድል ይኖራል። ይኸውም የኤፈርት "የፈረስ ስም" ነዳጁን የሚያወጣው የቻይና ድርጅት ከሆነ። አሊያም በቻይናው ድርጅት ውስጥ ኤፈርት የአንበሳ ድርሻ ካለው። ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ ከአየር ላይ የታፈሰ መላምት ሳይሆን በኤፈርት ኢምፓወርመንት ፕላን ውስጥ የተካተተ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ዶክተር አቢይ በኤፈርትና በቻይናው ድርጅት መካከል ግንኙነት መኖር እና አለመኖሩን አጣርተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
- የቻይናው ኩባንያ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ነው ወይ?
- ደረጃው በምን ይገለፃል?
- ከዚህ በፊት ያለው የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ይመስላል?
- ስለ ኩባንያው የተግባርና የፋይናንስ አቅም ምን ያህል ይታወቃል?
- ከቻይና መንግስት ጋር ትስስር አለው ወይ?
- ወደ ኢትዮጵያ ማን አመጣው?
- በአገረ ቻይና ከኩባንያው ጋር የተደራደረው የትኛው ባለስልጣን ነው?
- የቻይናው ኩባንያ ድርሻ ምን ያህል ነው?
- ፌዴራል እና የክልሉ መስተዳድር ምን ያህል ድርሻ አለው?
- ነዳጅ የሚወጣበት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ምን ጥቅም ያገኛል?
- ኩባንያው የሚጠቀመው ኬምካል(ካለ) የአካባቢ ብክለት ሊፈጥር ይችላል ወይ?…ወዘተ በግልፁ መስፈር ይኖርባቸዋል።
No comments