Latest

ብአዴን የሕወሃት ወኪሎችን የማጥራት ስራ እሰራለሁ አለ (ኢሳት ዲሲ)


 የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ በመጪው ሃምሌ በሚካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ በማዕከላዊ ኮሚቴና በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የሚገኙ የሕወሃት ወኪሎችን የማጥራት ስራ እንደሚሰራ ምንጮች ገለጹ።

አቶ በረከት ስምኦንን ጨምሮ በለውጥ ሒደቱ እንቅፋት ሆነው የቆሙትን ብአዴኖች ሙሉ በሙሉ ከድርጅት አመራርነት ለመጥረግ መዘጋጀቱም ተመልክቷል።

እንደ ኢሳት ምንጮች ገለጽእ ብአዴን በአሁኑ ወቅት ካሉት 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የለውጡ እንቅፋትና የሕወሃት ድጋፊ ተብለው የሚታወቁት 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።

አቋማቸው የማይታወቅና የሃይል ሚዛን አይተው የሚንሸራተቱት ደግሞ ዘጠኝ ብቻ እንደሆኑም ተመልክቷል።

እነዚህ በጠቅላላ በአንድነት ቢቆሙ እንኳን ብአዴንን ከለውጡ ጉዞ መግታት የሚያስችል ድምጽ አይኖራቸውም ተብሏል።

አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣አቶ ተስፋዬ ጌታቸው፣ዶክተር አምባቸው መኮንን፣አቶ ብናልፍ አንዱአለምና አቶ ተፈራ ደርበውን ጨምሮ 37 የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት የለውጡን ሒደት በመደገፍ የቆሙ መሆናቸው ታውቋል።

በግልጽ ከለውጥ እንቅስቃሴው በተቃራኒ የቆሙትና የሕወሃትን የቀደመ የበላይነት ለማስጠበቅ ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉት አቶ በረከት ስምኦንን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።

እነሱም አቶ በረከት ስምኦን፣ወይዘሮ ዝማም አሰፋ፣አቶ አህመድ አብተው፣አቶ ጌታቸው አምባዬ፣አቶ ከበደ ጫኔ፣አቶ ምትኩ በየነ፣አቶ ታደሰ ካሳ ወይንም ታደሰ ጥንቅሹ፣ወይዘሮ ፍሬሕይወት አያሌው፣ወይዘሮ መአዛ ገብረመድህን፣አቶ ይልማ ወርቁ፣ወይዘሮ ነጻነት አበራ፣አቶ አወቀ ሃይለማርያም፣ወይዘሮ ገነት ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

እነዚህ 14 ሰዎች ከለውጥ ሒደቱ በተቃራኒ የቆሙ በመሆናቸው ብአዴን በሃምሌ በሚያካሂደው ጉባኤ ከማዕከላዊ አባልነት እንደሚያስወግዳቸውም ታውቋል።

ከነዚህ ከተዘረዘሩት 14 የለውጡ ተቀናቃኝ የብአዴን አባላት ከአቶ ጌታቸው አምባዬና ከአቶ አህመድ አብተው እንዲሁም ወይዘሮ ነጻነት አበራ ውጭ ያሉት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ለኢሳት የደረሰው ዝርዝር መረጃ ያስረዳል።

አቶ በረከት ስምኦን የኤርትራ ተወላጅ መሆናቸውም በዝርዝሩ ተመልክቷል። አቋም የላቸውም ተብለው ከተዘረዘሩት 9 የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ፣ወይዘሮ ምስራቅ ማሞ፣አቶ ወርቁ ሰሙ ማሞ፣አቶ ስዩም መኮንን፣ወይዘሮ ወለላ መብራቴ፣ወይዘሮ ብስራት ጋሻው ጠናና አቶ ባዘዘው ጫኔ እንደሆኑም ታውቋል።

አወዛጋቢ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን በአሁኑ ወቅት የለውጡ ደጋፊ ሆነው መቆማቸውንም የኢሳት ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

ኦህዴድ አመራሩን ሙሉ በሙሉ እንዳጸዳ በመግለጽ ላይ ነው። የብአዴንም ርምጃ የለውጥ ሃይሉን ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ታምኖበታል።

ደኢሕዴንም አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ከሊቀመንበርነት በፈቃዳቸው እንዲነሱ ማድረጉ በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።

No comments