Latest

በ5 ወር ውስጥ ብቻ የ48 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው መንገድ - ቢቢሲ

በ5 ወር ውስጥ ብቻ የ48 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው መንገድ - ቢቢሲ

  • ደብረ ብርሃን አቅራቢያ አንጎለላና ጠራ ውስጥ በርካታ ሰዎች በትራፊክ አደጋ የሞቱበት መንገድ
በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ከደብረብርሃን ተሳፋሪዎችን ይዞ ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ የነበረ አንድ ዲ ፎር ዲ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ከድንጋይ ገልባጭ መኪና ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የ 12 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ሦስት ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሁለት ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

የወረዳው ፖሊስ በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ነገሩኝ እንዳለው መለስተኛ የህዝብ ማመላሻው ርቀቱን ሳይጠብቅ ለመቅደም ሲሞክር ከተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣው የጭነት መኪና ጋር ተጋጭቷል።

በአንጎለላ ጠራ ወረዳ ከግንቦት 21 ጀምሮ ብቻ ሦስት ከፍተኛ የትራፊክ አደጋዎች ደርሰዋል።

የአንጎለላ ጠራ ወረዳ ፓሊስ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዳግም አጣለ ለደረሱ አደጋዎች በዋናነት የሙያ ብቃት ማነስን እንደምክንያት ያነሳሉ።

በተጨማሪም መንገዱ የፍጥነት መቀነሻ እንደሚያስፈልገው የተናገሩ ሲሆን በቅርብ ጊዜ በደረሱት 2 የመኪና አደጋዎች ብቻ 1.2 ሚሊየን ብር አካባቢ የሚገመት የንብረት ውድመት ደርሷል ብለዋል።

እንደ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሠረት ላዕቀ ከሆነ በአምስት ወር ውስጥ ለደረሱት ሦስት ከባድ አደጋዎች መንስዔው ፍጥነት ነው።

"ስፍራው ሜዳማ ይምሰል እንጂ መታጠፊያዎች አሉት" ያሉት ምክትል ኮማንደር መሠረት አሽከርካሪዎች አደጋን ተከላክለው ማሽከርከር ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል። ያን ባለማድረጋቸው ብቻ እነዚህን ሦስት አደጋዎች አስተናግደናል ሲሉ ተናግረዋል።

የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት በስፍራው ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ያሉትን ነገር አጥንተው ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረባቸውን የተናገሩት ምክትል ኮማንደር መሰረት ላዕቀ ወደፊት ፍጥነትን የሚገቱ ነገሮችን እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። እስከዚያው ግን የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አስታውሰዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ዳግምም መንገዱን የሚያስተዳድረው የፌደራል መንግሥት መሆኑን አስታውሰው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ለማሰራት ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ መፃፋቸውን ተናግረዋል።

No comments