Latest

“ፊንፊኔ” በሚል ስም የሚጨቃጨቅ የአዲስ አበባን ታሪክ አያውቅም (በፕሮፌሰር ሐብታሙ ተገኘ )

“ፊንፊኔ” በሚል ስም የሚጨቃጨቅ የአዲስ አበባን ታሪክ አያውቅም

የአዲስ አበባ የጥንት ስም “በረራ” ነው፡፡ በረራም ፣ የነገስታቱ ቀዳማዊ ዋና መቀመጫ ከተማ በመሆን ፣ ከአፄ ዳዊት ቀዳማዊ ዘመን ፣ (ከ1380-1413 ) ድረስ ፣ እንዲሁም በአፄ ልብን ድንግል ስርወ መንግስት ዘመን ፣ማለትም (ከ1408-1480) ፣ በረራ ከመቶ አመት በላይ አገልግላለች፡፡


በረራ ወረብ በሚባል አውራጃ ስር ትተዳደር እንደነበር ፣ የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ፡፡ ወረብ ታላላቅ አብያተክርስቲያኖች እና ቤተመንግስቶች የነበሩበት ፣ በጣም ሀብታም አውራጃ ነበር፡፡በዚሁ ዘመን ፣ የግራኝ አህመድን ጦርነትን ከግራኝ ወታደሮች ጋር እየተዘዋወረ ሲዘግብ ፣ ወረብንና በረራን ያየው ፣ ሻሀብ አደዲን እብዱልቃዲር ፤ “ፉቱህ አል ሃበሽ” በተሰኘው መፀሐፉ፣ “በረራን የሐበሾች ምድራዊ ገነት” ይላታል፡፡

የበረራን ታሪክ የፃፍነው ፣ አንዱን ነባር ፣ ሌላውን መጤ እና እንግዳ ለማድረግ አይደለም፡፡ ፅሑፉን ለማዘጋጀት የተፈለገው፣ ስለ አዲስ አበባ የኋላ ታሪክ ያለውን የታሪክ ክፍተት ፣ በተወሰነ መልኩ ለመድፈን ያግዛል ፣ እንዱሁም ስለቦታው ታሪክ ኢትዮጵያዊያን ትክክለኛ መረጃና እውነት እንዲኖራቸው በማሰብ ነው፡፡ 

የዚህ ፅሑፍ ይዘት ፣ ያልነበረን ፣ ወይም ያልተነገረን አዲስ ታሪክ ለማስተዋወቅ አይደለም፡፡ ለዚህ ፅሑፍ የተጠቀምናቸው ማስረጃዎችም ፣ ከዚህ በፊት ስለ በረራ ታሪክ መፃፋቸው የታወቁ ምንጮች ናቸው፡፡ ይህ ፅሑፍ ሁለት አላማዎች አሉት፡፡  

አንደኛው ፣ የበረራን ወይም የአዲስ አበባን የኋላ ታሪክ ባጭሩም ቢሆን ለመዳሰስ ነው፡፡ ሁለተኛው ስለ በረራ ፣ በኢትዮጵያዊያንም ሆኑ በውጪ አገር ፀሐፊዎች የተፃፉ ታሪኮችን ለአንባቢ ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በተለይም ፣ የቦታው ተወላጆች ስለበረራ በሰጡት ምስክርነት ላይ የተፃፉትን ለማካተት ይሞክራል፡፡ 

የበረራን ታሪክ ያጠኑ ተመራማሪዎች ፤ኦጂኤስ ክራውፎርድ ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሀርትዌትግ ብሪትሪት ፣ ሳሙኤል ዎከር እና ማርኮ ቪጋኖ ይገኙበታል፡፡በተጨማሪም ታዋቂው ጣሊያናዊ የካርታ ባለሞያ ፣ ፍራ ማውሮ፣ በረራንና ባካባቢው ያሉ ከተሞች ፣ ወንዞች ፣ ተራሮች እና ገዳማት ፣ በ1450 አመተ ምህረት ባዘጋጀው የአለም ካርታ ፣የቦታውን ተወላጆች በመጠየቅ አስፍሯቸዋል፡፡

የፍራ ማውሮ የአለም ካርታ ፣ በትክክለኛነቱ በአለም የተደነቀ ነው፡፡ ካርታው ፣ አውሮፓውያን ኢትዮጵያን ጨምሮ አለምን ለማሰስ በዘመኑ ባደረጓቸው ጥረቶች ውስጥ ፣ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶላቸዋል፡፡ ፍራማውሮ ለሳይንስ እውቀት እድገት ላደረገው አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት ፣ የጨረቃ የተወሰኑ አካላት በስሙ ተሰይመውለታል፡፡ የበረራ ታሪክ ፣ ከአፄ ዳዊት ፣ማለትም ከ1380-1413 – ቀጥሎም እስከ አፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት ፣ ከ1508-1540 ፤ ስለ በረራ የመጀመሪያው የታሪክ ማስረጃ ፣ በ1450 የተሳለ የአለም ካርታ ነው፡፡  

በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አፄ ዘረ-ያእቆብ ፣ከ1434-1468 ድረስ የገዙት ናቸው፡፡ ነገር ግን የበረራ ታሪክ ከዚህ ይጀምራል ማለት አይደለም፡፡ ከተማው ተመስርቶ ፣ አድጎ፣ ለነገስታቱ መቀመጫነት እስኪበቃ ድረስ ፣ ብዙ አመታት መፍጀቱ አይቀርም፡፡ የአፍቃል መረጃ እንደሚያስረዳው ፣“እንጦጦ ፣ ወይም በረራ” ፣ በዋናነት የአፄ ዳዊት ከተማ እንደነበር ነው፡፡ 

አፄ ዳዊት የዘረ ያእቆብ አባት ሲሆኑ ፣ የነገሱት ከ1380 አመት ጀምሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ከፍራማውሮ የአለም ካርታ መዘጋጀት በፊት ፣ በረራ የአምሳ አመት እድሜ አስቆጥራ ነበር ማለት ነው፡፡ ካርታው በያዘው መረጃ ብዛትና ጥልቀት ፣በዘመኑ ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡ የፍራማውሮ ካርታ የመጀመሪያው የሚታወቅ ሳይንሳዊ ካርታ ነው፡፡  

ሳይንሳዊ የሚያደርገው ፣ በመሬት ላይ ባሉ ተጨባጭ እውነታዎች ላይ እንጂ ካርታው ከሃይማኖታዊ ግብአቶች ይልቅ ፣ በመሬት ላይ ያሉ ነበር እውነታዎች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ በመሆኑ ነው፡፡ በካርታ ስራውም ብዙ ባለሞያዎች ተሳትፈዋል፡፡ የኢትዮጵያን ካርታ የሚያሳየውን የዚህን ካርታ ክፍል እንደ ማስረጃተጠቅመነዋል፡፡

መረጃውን የሰጡ ሰዎች ፣ በተለይም የአዋሽን ወንዝ ፣ በረራን እና የዝቋላን ገዳም የሚያውቁ መሆን ነበረባቸው፡፡ ካርታው በሚያስደንቅ ሁኔታ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ያንፀባርቃል፤ በረራንም በደንብ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም የንጉሱ ዋና መቀመጫ መሆኑንም በደንብ ይገልፃል፡፡ በበረራ አካባቢ ያሉ ከተሞችን ፣ወንዞችንና ፣ አድባራትን ያሳያል፡፡  

ከነዚህም ውስጥ የአዋሽ ወንዝ ፣ የዱከም ወንዝ ፣ የዝቋላ ገዳምና የአምባ ነገስት ተራራ ይገኙበታል፡፡ ሁሉም እስከዛሬ ድረስ በትክክለኛ ካርታው ላይ በተገለፁበት አቀማመጥ እንዳሉ ይገኛሉ፡፡ ዱከም ከየረር ተራራ የሚመነጭ አነስተኛ ወንዝ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ያሉ ስሞችን ኦሮሞዎች ከዘመናት በኋላ ስያሜዎቹን ቢቀያይሩትም ፣ “ዝቋላ” በጥንታዊ ስሙ እስካሁንም አለ፡፡

No comments