Latest

መንግስት ኦነግን በግዴታ ትጥቅ እንደሚያስፈታ አስታወቀ (ቢቢኤን)

መንግስት ኦነግን በግዴታ ትጥቅ እንደሚያስፈታ አስታወቀ (ቢቢኤን)

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ ወታደሮቹን ትጥቅ እንዲያስፈታ መንግስት አሳሰበ፡፡  


የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዛሬ በሰጠው መግለጫ፤ ኦነግ ትጥቅ ያልፈቱ ወታደሮቹን በአስቸኳይ ትጥቅ እንዲያስፈታ፤ በፈቃደኝነት ትጥቅ የማያስፈታ ከሆነም፤ መንግስት በግዴታ ትጥቅ የማስፈታት ስራ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ 

ጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በአስመራ በተደረጉ ሶስት ድርድሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ገብቶ ለመፎካከር ተስማምቷል፡፡ ሆኖም ግን በድርድሩ ወቅት ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ አልተነሳም፡፡›› ያለ ሲሆን፤ ‹‹ጉዳዩ ያልተነሳውም የመደራደሪያ ጉዳይ ስላልነበረ ነው፡፡›› በማለት በድርድሩ ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ገለጻ አድርጓል፡፡

ኦነግ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ 1 ሺህ 300 የሚሆኑ ወታደሮቹን ትጥቅ እንዳስፈታ የገለጸው መንግስት፤ ትጥቅ የፈቱት ወታደሮች በጦላይ የጦር ካምፕ ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነ አስታውቋል፡፡ 

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፡- ‹‹ሰላማዊ ትግል የሚደረገው በሀሳብ እንጅ በአፈሙዝ አይደለም፡፡ ስለዚህም ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበውና ቀይ መስመር ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ መንግስት ያቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ወታደሮቹን በአስቸኳይ ትጥቅ እንዲያስፈታ የተጠየቀ ሲሆን፤ አቋሙን እንደገና በመፈተሽ የሰላማዊ ትግል ብቻ እንዲያካሂድ ከመንግስት በኩል ጥሪ ቀርቦለታል፡፡  

ኦነግ ከመንግስት የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ትጥቅ የማይፈታ ከሆነ ግን፤ ‹‹መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገ መንግስታዊ ስርዐቱን ለመጠበቅ ሲል መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ በራሱ ይሰራል፡፡›› ተብሏል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በመግለጫው ማጠቃለያ፡- ‹‹መንግስት ህግን የማስከበር ስራውን በቆራጥነት ስለሚሰራ መላው ህዝብ የደህንነት ችግር ይገጥመኛል በማለት ስጋት ላይ እንዳይወድቅና እንዳይደናገር መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡›› ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡  

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ በአጠቃላይ ወደ 4 ሺህ 500 ወታደሮች ያሉት ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ትጥቅ የፈቱት 1 ሺህ 300 የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ 

ቀሪዎቹ ግን አሁንም እስከነትጥቃቸው በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እንደሚገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

No comments