Latest

የአቶ አለነ ማህፀንቱ የፍርድ ቤት ውሎ ከእዮዔል ፍሰሃ

የአቶ አለነ ማህፀንቱ የፍርድ ቤት ውሎ ከእዮዔል ፍሰሃ

  • የፓርቲው የቀድሞ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል
  • ተከሳሹም ለፍርድ ቤቱ የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጥተዋል
‹‹ስብሰባን በማወክ ወንጀል›› የተከሰሱት የቀድሞ አንድነት ፓርቲ ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊና ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ አለነ ማህፀንቱ፣ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት በመቅረብ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ፡፡

ችሎቱ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ላይ የአቶ አለነ ማህፀንቱን መከላከያ ምስክሮች ለማዳመጥ የተሰየመ ሲሆን፤ በችሎቱ የተሰየሙት ዳኛ፣ ተከሳሹ የተከሳሽነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ አቶ አለነ ማህፀንቱም የተከሳሽነት ቃላቸውን በሚከተለው መልኩ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

‹‹ስሜ አለነ ማህፀንቱ ይባላል፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነኝ፡፡ በትምህርቴ የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት ነኝ፡፡ በሙያዬ የተለያዩ ቦታዎች ሰርቼያለሁ፤ በተለያዩ ኮሌጆች ላይ ዲን ሆኜ ሰርቼያለሁ፡፡ በትምህርት ቤቶችም በርዕሰ መምህርነት አገልግያለሁ፡፡ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖሊሲና ፕሮግራም ኃላፊ ሆኜ ሰርቼያለሁ፡፡ ሀገሬን ወክዬ በተለያዩ ሀገራት በመጓዝ ተከራክሬያለሁ፡፡ 


የሀገሬን ጥቅምም አስከብሬያለሁ፡፡ በፖለቲካ ዘርፍ የ11 ዓመት ልምድ አለኝ፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመቅረብ አንስቶ፤ በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ብሔራዊ የስራ አስፈፃሚ አባል፣ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ ሆኜ እስከተያዝኩበት ቀን ድረስ አገልግያለሁ፡፡ የታሰርኩበትና የተያዝኩበት ምክንያትም በፖለቲካ አመለካከቴ ነው፡፡  

የተቃውሞ ጎራ አባል በመሆኔና እኔም ስታገል የነበርኩት በሀገሬ ላይ ዲሞክራሲን ለማስፈን፤ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኛና ነፃ ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ፤ ዜጎች ያለምንም ምክንያት የማይታሰሩባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ፣ ትክክለኛ ፍትህ በሀገሪቱ እንዲሰፍን፣ ትክክለኛ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን ነው፡፡ 

እንደ ተማሩ ወጣቶች ሁሉ ለሀገሬ ሰርቼያለሁ፡፡ በዚህ ስብእናዬ፣ በአካዳሚክ ባክግራውንዴ፣ ባለኝ ማህበራዊ ኃላፊነት አሁን የተከሰስኩበትን ክስ ማለትም አቃቤ ሕግ ያቀረበውን ‹‹አይኤስን ምክንያት በማድረግ መንግስትን በሀይል ለመናድ….›› ወዘት የሚሉ ነገሮች፤ የቀረቡብኝ ባለኝ የፖለቲካ አመለካከት ነው፡፡  

በክሱ ላይ የተዘረዘሩት ነገሮች ሁሉ ባለኝ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ኃላፊነቴ ልፈፅማቸው የማልችላቸው መሆኔን አረጋግጬ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ከቤቴ በማይታወቁ ሰዎች ታፍኜ ተወስጄያለሁ፤ ከምኖርበት አካባቢ በአራት ደህንነቶች ታፍኜ ተወስጄ ክስ ተመስርቶብኝ፤ በሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግርም ሆነ የሌሎችን ንግግር ለመግታት፣ ‹‹ጉባኤ አውከሃል›› በሚል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 490/3 በመናገሻ ፍርድ ቤት ቀርቤ፤ የአቃቤ ሕግ ምስክር በፖለቲካ ሴራና በተንኮል የተደራጀ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ስላረጋገጠ በነፃ አሰናብቶኛል፡፡

ይህንንም የተከበረው ፍርድ ቤት አምጥቶ ያረጋገጠ ይመስለኛል፡፡ የመናገሻ ፍርድ ቤት በነፃ ካሰናበተኝ በኋላ፤ የኢህአዴግ መንግስት እኔን ማሰር አላማው አድርጎ ስለተንቀሳቀሰ ብቻ በሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ከሶኝ የነበረውን ክስ ሰርዞ፤ ‹‹በሚያዚያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ለቅሶ ቦታ ላይ ተገኝተህ አመፅ ለማነሳሳት ሞክረሃል›› በማለት ክስ አቅርቦብኛል፡፡ ይህ ክስ እኔንም ሆነ ፍርድ ቤቱን የማይመጥን ክስ ነው፡፡ 

‹‹ወጣቶችን አደራጅትህ በሪቼ አድርገህ፣ ወደ መስቀል አደባባይ ወስደሃል›› የሚል ክስ ነው የቀረበብኝ፡፡ የሀሰት ምስክሮች ማለትም፡- የቀበሌ አመራሮች፣ የፎረም አባሎች፣ ሰብስቦ በማምጣት በሀሰት ተመስክሮብኝ እንዲህ አይነት ክስ ሊመሰረትብኝ ተችሏል፡፡ በዚህች ሀገር ላይ የመኖር ዋስትናዬ አልተከበረልኝም፤ እየተከበረልኝም አይደለም፡፡

ስለዚህም የተከበረው ፍርድ ቤት ጭብጥ ማስያዝ የምፈልገው በወቅቱ እኔ ከ2፡30 እስከ 3፡00 ባለው ግምታዊ ሰአት ከጓደኞቼ ጋር ማለትም ከአቶ ግርማ ሰይፉ ቢሮ መገኘቴን ነው፡፡ ‹‹ሙሾ እያወረደ ሲያሳምፅ ነበር›› የሚለው የፈጠራ ክስ በጭራሽ የማይገናኝ ነው፡፡ ከእነዚህው ጓደኞቼ ጋር እስከ ምሳ ሰዓት አብሬ ነበርኩ፡፡›› በማለት የተከሳሽነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ የተሰየሙት ዳኛ ለአቶ አለነ ማህፀንቱ የተወሰኑ የማጣሪያ ጥያቄዎችን ካቀረቡ በኋላ የተከሳሹን መከላከያ ምስክሮች አድምጠዋል፡፡ 1ኛ ምስክር አቶ ግርማ ሰይፉ ከተከሳሹ ጋር በነበራቸው ቀጠሮ መሰረት ሚያዚያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 አካባቢ ቄራ በሚገኘው ቢሯቸው መገናኘታቸውንና ዮናስ ጨርጨር፣ ተብሎ በሚጠራው ሥጋ ቤት አብረው ምሳ መብላታቸውንና እስከ 9፡00 ድረስ አንድ ላይ እንደነበሩ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

በመጨረሻም ስቴዲየም አካባቢ መለያየታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ከአቃቤ ሕግ በኩል ለተነሱ መስቀለኛ ጥያቄዎችም ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከፍርድ ቤቱ በኩልም ለተነሳላቸው የማጣሪያ ጥያቄ ምላሻቸውን አስከትለዋል፡፡ በተመሳሳይ 2ኛው ምስክር አቶ ተክሌ በቀለና 3ኛው ምስክር አቶ ስዩም መንገሻ ተመሳሳይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡  

አቃቤ ሕግ ለአቶ ተክሌም ሆነ ለአቶ ስዩም መንገሻ መስቀለኛ ጥያቄን አንስቷል፡፡ አቶ ተክሌ በቀለም ሆነ አቶ ስዩም መንገሻ ከፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ አልቀረበላቸውም፡፡

የፓርቲው የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክሌ በቀለና የፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ ስዩም መንገሻ፣ መከላከያ ምስክር በመሆን የምስክርነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አለነ በመከላከያ ምስክርነት አራት ሰዎችን ቢያስመዘግቡም፤ አራተኛ ምስክራቸው የነበሩት የፓርቲው የቀድሞ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም፣ የምስክርነት ቃላቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡  

የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ፣ ‹‹ሶስቱ የመከላከያ ምስክሮች ከሰጡት የምስክርነት ቃል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ሊናገሩ ስለማይችሉ፤ ሶስቱ ምስክሮች በቂ ናቸው፡፡›› በማለት ጠበቃው አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ የምስክርነት ቃላቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠ ሲሆን፤ ብይን ለማስተላለፍ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡

No comments