Latest

ወፋ በፌስቡክ (በእውቀቱ ስዩም)

በእውቀቱ ስዩም

በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ ባንዳንድ ገጠሮች ውስጥ "ወፋ" የሚባል ልማድ ነበር:: ያንድ ቀበሌ ባላገሮች ከወንዝ ወዲህ ማዶ እና ወድያ ማዶ ተሰላልፈው በጩቤ በጦር በዱላ ይከሳከሳሉ::


አንድ ባላገር ከገበያ ሲመለስ የወፋ ጦርነት ሲካሄድ ከተመለከተ ቆም ብሎ ቅርጫቱን ያስቀምጣል:: ከዚያ በቅርብ ከሚያገኘው ጎራ ተቀላቅሎ ትንሽ ተደባድቦ መንገዱን ይቀጥላል:: የዱላ ጠበል ጠዲቅ እንደመቅመስ ነው::

ጦርነቱ ለርስት ወይም ለክብር የሚደረግ አልነበረም:: በዛሬ አይን ስንመዝነው: ያለ ምንም አላማ የሚደረግ ውጊያ ነበር ማለት ይቻላል::

ይህንን ልማድ ያስቆሙት አራዳው ልጅ ኢያሱ ናቸው ይባላል:: ልኡሉ ባላገሮችን ሰብስበው ለምን እንደሚጋደሉ ሲጠይቁዋቸው:

" ሁሌም በበልግ ላይ ደም ካልፈሰሰ ቆሌዋ ትቆጣለች:: መሬቱም እህል አይለግስም" ብለው መለሱላቸው::

በዚህ ምላሽ የተገረሙት ልጅ ኢያሱ" ታድያ ደም ለማፍሰስ ከሆነ ይሄ ሁሉ አርሶ የሚያበላ ወጣት ለምን ያልቃል? ለቆሌዋ አንድ የጃጀ ሽማግሌ መርጣችሁ አታርዱላትም? "አሉ ይባላል::

የወፋ ልማድ በልጅ ኢያሱ ከተደመሰሰ ከብዙ ዘመን በሁዋላ በፌስቡክ ላይ ትንሳኤ ያገኘ ይመስላል:: ፌስቡክ ላይ ውይይት የለም:: ሙግት አይታሰብም:: ንግግር የለም:: ያለው አላማ የለሽ ክርክር ነው:: 

በመሰረቱ ክርክር የሚለው ቃል ራሱ በድሮ አማርኛ ጦርነት ማለት ነበር:: በእምባቦ ጦርነት ዋዜማ : የንጉስ ምኒልክ ገንቦ ተሸካሚ ሴቶች ለጠመንጃ የሚሆን ባሩድ( ዳሂራ) ሲቀምሙ:-

"ጎበዝ ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሂራ

ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ"

ብለው የዘፈኑትን ያስታውሱዋል::" ክርክር አይቀርም "ሲሉ ጦርነት አይቀርም ማለታቸው ነው::

ፌስቡክ ላይ ክርክር ነፍ ነው:: ማንኛውም አይነት ርእስ ህዝብን ወዲህና ወዲያ አቧድኖ የሚያፋልም የክርክር ምንጭ የመሆን አቅም አለው:: ለምሳሌ ሰኞ እለት ኢንጂነር ስመኘው የክርክር ምንጭ ሆኖ ይነሳል::
 

ዜጎች በጉዳዩ ላይ መላምታቸውን ሴራቸውን ግምታቸውን አልፎ አልፎም ሀሳባቸውን አቅርበው ይከራከርሉ:: እልል ያለ ፍረጃ እና ጠገራ ስድብ ከያቅጣጫው ይጎርፋል:: 

በመጨረሻ የጋራ ግንዛቤ ጠብ ሳይል ቀኑ ያልፋል:: ዜጎች በዘለፋ ቆስለው: ባይሞቱም የአእምሮ ሰላማቸውን ገድለው የቀን ራስ ምታታቸውን ተቀብለው ወደ ምኝታቸው ያዘግማሉ:: በማግስቱ ባዲስ ጉልበት ለአዲስ ክርክር ተዘጋጅተው ይነሳሉ::

የፌስቡክን አላማቢስ ጦርነት እንደ ወፋ ውጊያ ባዋጅ ማስቆም አይታሰብም:: ይሁን እንጂ በጦርነቱ በተዋጊነትም ሆነ በገላጋይነት ባለመሳተፍ ለሰላም አስተዋጽዖ ማድረግ ይቻላል::

በነገራችን ላይ በፅሁፌ መግቢያ ላይ የወፋ ልማድ ይዘወተርባቸው የነበሩት ቦታዎች በስም ከመጥቀስ የተቆጠብኩት ሆን ብየ ነው::
 

ሳር ቅጠሉ ከብሄር ኩራትና ውርደት አንፃር በሚመዘንበት በዚህ ዘመን የሆነ ቦታ መጥቀስ በራሱ እልም ላለ ጦርነት መነሻ ሊሆን ይችላል:: እና ክርክር የሚያወግዝ ፅሁፍ እንዴት የክርክር ሰበብ ያቀብላል? 🙂

No comments