Latest

ያልታበሰው የላሊበላ እንባ - ቢቢሲ

የሰሜን ወሎ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ
የሰሜን ወሎ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ
«ታሪክ መስራት ካልቻልን ታሪክ እንጠብቅ!»

«UNESCO የበላይ ጠባቂ ነኝ ካለ አደጋውን እያየ ለምን ዝም አለ?»

«ታሪክና ቅርስ እየፈረሰ አዲስ ታሪክ አይሰራም!»

እሁድ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ. ም. በላሊበላ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከተነበቡ መፈክሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የላሊበላ ነዋሪዎች ሀይማኖትና እድሜ ሳይለዩ አደባባይ ወጥተው እሮሯቸውን አሰምተዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከተፈጥሯዊ አደጋ ለመከላከል በሚል ግዙፍ የብረት ምሰሶ በቤተክርስቲያኖቹ ጣሪያ ከተተከለ ዓመታት ተቆጠሩ።

ሆኖም ምሰሶው እንደታሰበው ቅርሱን ከአደጋ የሚከላለል ሳይሆን፤ እያደር ቅርሱን የሚደመስስ ሆነ። ይህንን ያስተዋሉ የላሊበላ ነዋሪዎችም የሰሚ ያለህ እያሉ ነው።

የላሊበላ ቀሳውስት፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ህጻናትም አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠን ሲሉ ይጠይቃሉ። ሙስሊሙ ማህበረሰብም «ላሊበላ የኛም ቅርስ ነው፤ ይጠበቅልን!» ሲሉ ተደምጠዋል።

ከቤተክርስቲያኖቹ አንዱን የሚወክል መጠነኛ ቅርጽ ሰርተውና ከላዩ ግዙፍ ምሰሶ አቁመው አደባባይ የወጡ የአካባቢው ነዋሪዎችና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ከሰልፈኞቹ መካከል ይገኙበታል።

ከምሰሶው በላይ «ልጆቼ፤ ይህን የብረት ሸክም ከላዬ አውርዱልኝ» የሚል ጽሁፍ ይነበባል።

በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተተከለው ምሰሶ እንዲነሳ ጥያቄ ሲቀርብ የመጀመሪያው አይደለም። የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ደጋግመው ብለውታል። የቅርስ ተቆርቋሪዎችም ከአንድም ሁለት ሶስቴ አሳስበዋል።

ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናቶችም ቅርሱ ሊጠፋ ስለመቃረቡ ማስረጃ አቅርበዋል። አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከሚገኙት መካከል ቤተ መድኃኔአለም ይገኝበታል።

የሰሜን ወሎ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ
ታዲያ ለምን አፋጣኝ ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ?

ሒሩት ወልደማርያም(ዶ/ር) የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሳሉ በአብያተ ክርስቲያናቱ ጣሪያ ላይ ያለው የብረት ጥላ ሊነሳ ነው ተብሎ ነበር።

የብረት ምሰሶው ቅርሱን ከዝናብና ንፋስ ይከላከላል በሚል ቢዘረጋም፤ ቅርሱን ስለተጫነው ከእለት ወደ እለት እየተሰነጣጠቀ፣ እየፈራረሰ ነው።

የብረት ጣሪያው ሊነሳ ነው ከተባለ በኋላ የቀድሞዋ ሚንስትር ሒሩት (ዶ/ር) ቅርሱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ ለተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ማሳወቃቸውን ተናግረው ነበር።

ቅርሱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም እንደመሆኑ የተቋሙ ውሳኔ እንደሚጠበቅም አመልክተው ነበር። ምላሹ የዘገየበት ህዝብ በአንጻሩ ጉዳዩን ወደ አደባባይ አወጥቶታል።

መምህር አባ ጽጌስላሴ መዝገቡ የደብረ ሮሀ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ገዳም አስተዳዳሪ ናቸው። «በየእለቱ ቢታዩ የማይጠገቡ» የሚሏቸው አብያተ ክርስቲያኖች ጉዳይ እንቅልፍ ከነሳቸው ውሎ አድሯል።


ቤተ መድኃኔአለምና ቤተ አማኑኤል በ1920ዎቹ በግብጻውያን በ1950ዎቹ ደግሞ በጣልያናውያን አማካይነት ሲታደሱ የደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት፤ ቅርሶቹ አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለመድረሳቸው ምክንያት ነው ይላሉ።

የቅርስ ጥገና እውቀት የሌላቸው ግለሰቦች በመዶሻና በመሮ አብያተ ክርስቲያናቱን አጎሳቁለዋል። አስከትሎም ቅርሶቹ ላይ አንዴ የቆርቆሮ ሌላ ጊዜ ደግሞ የእንጨት ጣሪያ ተደርጎ ጫና ደርሶባቸዋል።

ከአስር ዓመት በፊት «የጥገና ቴክኖሎጂው ተፈልጎ እስኪገኝ» ተብሎ የብረት ጣሪያ ተዘረጋላቸው። ጣሪያው ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይነሳል ተብሎ ነበር።

«ቤተ መድኃኔአለም፣ ቤተ አማኑል፣ ቤተ ማሪያም እና ቤተ አባ ሊባኖስ ተጠግነው ወደቀደመ ይዘታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ቃል ተገብቶልን ነበር፤» ይላሉ አስተዳዳሪው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራንን አጣቅሰው «የንፋስ መጠኑ 28 አካባቢ ደርሷል ተብሏል፤ ከባድ ንፋስ ተነስቶ መጠለያው ቢወድቅና ቅርሱ ቢጠፋስ?» ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የብረት ምሰሶው ቅርሱን እየተጫነው ነው

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አማካይነት ቤተ ገብርኤል ሩፋኤል እንዲሁም ቤተ ጎለጎታ ተጠግነው ጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን ተናግረውም የተቀሩት ቅርሶችም ሳይውል ሳያድር መፍትሄ እንደሚሹ ይጠቁማሉ።

የደብረ ሮሀ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ገዳም አገልጋይ እና የላሊበላ አካባቢ የቅርስ ማህበር አመራር አቶ ይሄነው መልኩ ሀሳባቸውን ይጋራሉ።

ከ1997 ዓ. ም. ጀምሮ በተደጋጋሚ የሰነዘሩት ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ አዝነዋል። ኢትዮጵያን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች አብዛኞቹ ላሊበላን ይጎበኛሉ። ከጎብኚዎቹ የሚገኘው ገቢም ቀላል አይደለም።

«የሚያስገኘው ገቢና የተሰጠው ትኩረት አይመጣጠንም» ይላሉ አቶ ይሄነው። ተጠያቂ የሚያደርጉት የኢትዮጵያን መንግስት ብቻ ሳይሆን ዩኔስኮንም ጭምር ነው።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስላጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፤ ቅርሱ ለ37 ዓመታት በተለያየ አይነት ጣሪያ ስር መዝለቁን «ለኮንሰርቬሽን [ጥበቃ] የሚሆን የምንተማመንበት ቴክኖሎጂ ስላልነበረ ነው» ሲሉ ይገልጻሉ።

አሁን ላይ ከጊዜያዊ መጠለያ የሚያላቅቅ ቴክኖሎጂ መገኘቱን ያስረዳሉ። ዩኔስኮን ጨምሮ ከሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ተቋሞች ጋር የጥገና ፕሮጀክቶች ነበሯቸው። የቤተ ገብርኤል ሩፋኤል እድሳትን እንዲሁም በቤተ ገብርኤል ሩፋኤል (47 ሚሊየን ብር የወጣበት) ተሞክሮ ቤተ ጎለጎታ ሚካኤል መሰራቱንም ይጠቅሳሉ።

የቀደሙትን ፕሮጀክቶች መነሻ አድርገው አጠቃላይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን ለዩኔስኮ ያቀረቡት ፕሮጀክት ተቀባይነት አግኝቷል። በቀደመው ወጪ ስሌት መሰረት አጠቃላይ አብያተ ክርስቲያናቱን ለማደስ 300 ሚሊዮን ብር በጀት ያስፈልጋል።

«ገንዘቡን አግኝተን ቅርሱ ከተጠገነ ጣሪያውን [በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ በ11 ሚሊየን ዩሮ የተሰራው] በማግስቱ እናነሳዋለን፤» ይላሉ ዳይሬክተሩ።

አቶ ዮናስ ቅድሚያ የሚሰጠው ለቅርሱ እድሳት መሆኑን ይናገራሉ። ለዓመታት በመጠለያ ውስጥ ከቆየው ቅርስ ላይ የብረት ምሰሶው ሲነሳ ቅርሱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ይጠቁማሉ።

ጣሪያውን ያለበሰው ድርጅት እንዲያነሳው የሚያስችል ዲዛይን ቀርቦለት እንደተደራደሩ ገልጸው፤ ቅርሱ ታድሶ ጣሪያው እስከሚነሳ ባለው ጊዜ ቅርሱ ላይ ጎዳት እንዳይደርስ «ሱፐርዚዥን [ቁጥጥር] እንሰራለን» ብለዋል።

በዘንድሮው በጀት አመት ለቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን ከተመደበው 29 ሚሊዮን ብር፤ 20 ሚሊዮኑን ለላሊበላ እንደመደቡ ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ ለእድሳት የሚሆነውን ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ስራውን ከማስጀመር ወደኋላ እንደማይሉ አስረግጠዋል።

የመምህር አባ ጽጌስላሴ፣ የአቶ ይሄነው እንዲሁም የተቀረው የቅርስ ተቆርቋሪ ማህበረሰብ ጥያቄ ግን ጊዜ አለን ወይ? ነው።

No comments