Latest

ከንግስተ ሳባ እስከ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ (መስቀሉ አየለ)

ከንግስተ ሳባ እስከ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ (መስቀሉ አየለ)

ታምሪን ከተባለ ባህር ተሻጋሪ ነጋዴ ስለ ሰሎሞን ጠቢቡ ታላቅነት ብዙ ሰማች። ልቧም ቆርጦ ለመሄድ ተነሳሳ። ወደዚያውም አቀናች። ባየችውም ነገር ተደመመች።


"በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የከበርክ አንተ ታላቅ ሰው ከህዝቡ መካከል መርጦ ያከበረህ እግዚአብሔር ታላቅ ነው። እኔ እንኳን የጥበብህን ነገር ሰምቸ ከምድር ዳርቻ መጥቻለሁና" አለች። ሰሎሞንም መልሶ "ጥበብን ለማድነቅ ጥበበኛ መሆን ይጠይቃል" ማለቱ ከዋለበት እየዋሉ፤ ካደረበት እያደሩ ነገር ግን የቃሉን ጥልቀት የእጁን ጥበብ አይተው መረዳት ያልቻሉ በርካቶች ነበሩና ስለነርሱ መናገሩ ነው።

ከነክብሯ የኖረችው ንግስት ግን በዚህ አጋጣሚ በእንግድነት በቆየችባቸው ወራቶች ሳይታሰብ ሰሎሞን አወቃትና ወንድ ልጅም ጸነሰች። በዚህም ንጉሱን አንድ ነገር ለመነችው። እንዲህም አለች። "ባገሬ የምትነግሰው ሴት ልጅ ስትሆን ነገር ግን በዙፋኑ ላይ በኖረችበት ዘመን ሁሉ ድንግል እንድትሆን ስርዓቱ ያዛል። 

እኔ ደግሞ ዛሬ ከድንግልና ጸጋዬ ወርጃለሁ። ስለሆነም በአገሬ በኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ ሴት ልጅ ዙፋን ላይ እንዳትቀመጥ ስርዓት ስራልኝ" አለችው ይላል ክብረ ነገስት። ጠቢቡም ስርዓቱን ሰራ።በዚህም የተነሳ ከእርሱ ለሚወለደው የወደፊቱ ቀዳማዊ ሚኒሊክ የንግስናውን እርካብ አጸናለት።
 

"ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ" እየተባለ የሰሎሞን ስርዎ መንግስት በአገራችን የተተከለው እንዲህ ነበር። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሁለት መቶ አምሳ አራተኛው የሰሎሞን ስርዎ መንግስት ተብለው በነገሱ በአራባኛው ዓመት በጥቂት አስር አለቆች ተገልብጠው የስርዎ መንግስቱ ፍጻሜ እዚያ ላይ ያበቃ እስከመሰለበት ግዜ ድረስ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ንግስት ዘውዲቱ ከተሾመችበት አጋጣሚ በስተቀር 

በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት ልጅ ወደ ዙፋን እንዳትወጣ የሚከለክለውና በመንግስታትና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚወስነው ክብረ ነግሰት የየዲት ጉዲትን የአርባ አመት የአመጻ ሩጫ, ሳይወለድ የጨነገፈውን የአዜብ ጎላን ከንቱ ምኞት ሳይጨምር ለሶስት ሽህ ዘመን ያህል ሳይፋለስ ተጠብቆ ቆይቷል ማለት ይቻላል።
 

የዛሬዋ ሳህለወርቅ ዘውዴ ደግሞ ክብረነገስቱን በመሻገር ሁለተኛዋ ሴት እንዳንላት የምታዘው ወታደር፣ የምትሰፍረው በጀት የሌላት ሆነችብን። ያም ሆኖ ግን ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ካየናቸው ሶስት ጝዑዛን ለራሷ ክብር ያላት ለመሆኗ ደም ግባቷ ይናገራል። ምን ስልጣን ባይኖራትም ቢያንስ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሻለ ትሰራ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

No comments