ሳትደምር ይሆናል አትበል! ሌሊሳ ግርማ
በቢጫዋ የ”ታሪክና ምሳሌ” መጽሐፍ ውስጥ “ፋኖስ እና ብርጭቆ”፣ “አውራ ዶሮ እና የአይጥ ግልገል”፣ “ብረት ድስት እና ሸክላ ድስት” ወዘተ-- የሚሉ ተረቶች ተካተውበታል፡፡ አሁን አድጌ ትልቅ ከሆንኩ በኋላም -- በአንዳች ምክንያት ወይም ያለ ምክንያት አንዳንዱ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡
ዛሬ ትዝ ያለኝ “ሁለት ራስ ያለው ወፍ” የሚለው ነው፡፡ የከበደ ሚካኤል ተረቶች ብዙ ጊዜ በግጥም ቅርጽ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ “ሁለት ራስ ያለው ወፍ” ም በግጥም የሚተረክ ቢሆንም ግጥሙ ስለተዘነጋኝ፣ በዝርው፣ በአጭሩ ልንገራችሁ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ራስ ያለው ወፍ ይኖር ነበር፡፡ ከወፉ እራሶች አንደኛው ጠንካራና በጉልበቱ የሚመካ--የተገኘውን እህል ጥሬም ሆነ ሌላ ለቀም አድርጎ የሚበላ ነው፡፡ ሁለተኛው እራስ ደካማና ከጉልበተኛው እራስ ጋር እኩል መፎካከር የማይችል ቀሰስተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ከጉልበተኛው እራስ ጋር ልምምጥ ውስጥ ገብቶ አቤቱታውን አቀረበ።
“ለራስህ ብቻ ሁሌ ለምን ትስገበገባለህ -- ተካፍለን እንብላ --- አንዳንዴም ለእኔ እዘንልኝ እንጂ” ብሎ ጥያቄውን ሰነዘረ፡፡ ግን ጉልበተኛው እራስ ደካማው ላይ አላገጠበት እንጂ እሮሮውን አልሰማውም፡፡ በእንዲህ ሁኔታ አንዱ ቀምቶ ሲበላ --- ሌላው ጦሙን ሲያድር፣ለብዙ ጊዜ አብረው ኖሩ፡፡
ጉልበተኛው እራስ የራሱን ፍላጎት ማሟላትን እንጂ በደካማው እራስ በኩል ቂምና ጥላቻ እያደገ መምጣቱን አላስተዋለም፡፡ ወይም ቢያስተውልም ምንም የሚያመጣ ስላልመሰለው፣ ንቆ ትቶታል፡፡ ሁሌ የእሱ እጣ ፈንታ የማሸነፍ፣ የደካማው ደግሞ መሸነፍ ነው ብሎ፣ የማይደራደርበት የድምዳሜ ትዕቢት ላይ ተደላድሎ ተቀምጧል፡፡
በእንደዚህ ባለ ሁኔታ፣ እነዚህ በአንድ የወፍ አካል ላይ ተዳብለው የተፈጠሩ እራሶች ሲኖሩ፣ ከዕለታት አንድ ቀን ወፉ፣ አንድ ዛፍ ላይ ያርፋል። ያረፈበት ዛፍ መርዘኛ ፍሬዎች የሚያፈራ መሆኑን አስቀድሞ የሚያውቀው ጉልበተኛው ራስ እንደለመደው፣ ተሽቀዳድሞ ከመጉረስ ራሱን ቆጠበ፡፡ ይኼንን ዕድል ተጠቅሞ ደካማው አፍ፣ የመርዘኛውን ዛፍ ፍሬ በመንቁሩ ለቀም አድርጎ፣ አስገባ፡፡
ጉልበተኛው ራስ ወደ አፉ ያስገባው ፍሬ “ሞትን ለሁለታችንም ስለሚያመጣ---እባክህ ትፋው” ብሎ ልምምጥ ውስጥ ገባ፡፡ ግን ደካማው አፍ፣ ቂም ስላለበት አልሰማም አለው፡፡ “እህል እንዳልበላ ስለከለከለከልከኝ፣ መርዙን በልቼ እሞታለሁ” ብሎ ወሰነ፡፡ የመርዙን ፍሬ ውጦ ወፉን ከእነ ሁለት እራሶቹ አዳብሎ ገደላቸው፡፡---የሚል ነው ተረቱ፡፡
እንግዲህ ይሄንን ተረት ይዘን፣ ዓይናችንን ወደ ጣራው ወይም ወደ ሀገራዊ መሬት መመለስ እንችላለን። ጥያቄዎችም መጠየቅ እንችላለን፡፡ እኔ ለምሳሌ -- በተረቱ ላይ እንደሚከተለው አስተያየት እሰጣለሁ፡፡ “ችኩሉ ወፍ ጉልበተኛ ሆኖ ተሻምቶ ቢበላም፣ ያው ምግቡ ወደ ወፉ አካል እስከሆነ የገባው፣ ደካማው አፍም፣ በሰውነት አሰራር ሥርዓት ምግቡ ይደርሰዋል።-- እና የህልውና ጥያቄ አይደለም ደካማው አፍ የጠየቀው፤ የፍትህ ጥያቄ ነው” ልል እችላለሁኝ፡፡
ግን ይኼ የእኔ አስተያየት፣ ከእኔ ምልከታ የመጣ እንጂ “እውነት ነው” ማለት አይደለም። እውነት በአንድ አንጻር ምልከታ ብቻ አይመጣም። ምክንያቱም፤ በእኔ አተያይ የደካማውን (ተበድያለሁ ያለውን) የወፉን እራስ ጥያቄ ወደ “integration” ጥያቄ አመጣሁት። ወፉ የጠየቀው ጥያቄ ግን የ”እኩልነት” ጥያቄ ነው።
የእኩልነትን ጥያቄ የሚወልደው ደግሞ ምርጫ የማድረግ አቅም ነው፡፡ ወፉ በተፈጥሮ ሳይመርጥ ሁለት ራስ ያለው ሆኖ ተፈጥሯል፡፡ እነዚያ በአንድ አካል ላይ የተፈጠሩ ሁለት እራሶች ደግሞ የተለያየ አቅም ያላቸውና እርስ በእርስ የሚፎካከሩ ናቸው፡፡--- ምግብ በራሳቸው አፍ እንዲገባ እንጂ፣ በአንዱ አፍ የተበላው የሌላውን ፍላጎት ወይም ረሃብ ያረካል ብለው የማያምኑ ናቸው፡፡ የምርጫ ተፈጥሮ ያላቸው ናቸው፡፡ ጠንካራው የወፍ አፍ “አቅም ያለው ይብላ” ብሎ የሚያምን ነው፡፡ ሁለተኛው ይሄንን አይቀበልም፤”እኩልነት” እንዲሰፍን ይፈልጋል፡፡
እንደ ተፈጥሮ ወይም ፈጣሪ ከፍ ብዬ ላስብ ካልኩኝ--የወፉ አካል ላይ ያሉ ራሶችን ጥያቄ፣ የ”አንድነት” ጉዳይ አደርገዋለሁኝ፡፡ ትልቁ እውነት ጥቅሉ ነው፡፡-- ልል እችላለሁኝ፡፡ ግልጽ ነው፤ የወፉ ሁለት እራሶች ከአካሉ ተለይተው በራሳቸው አቅጣጫ ሊለያዩ እንደማይችሉ።-- ደካማው ወፍ አርፎ ይቀመጥ፣ ጉልበተኛው ለሁሉም ይመግብ ማለትም ይቻላል፡፡
ጠንካራው አፍ እንደዚያም ብሎ ነበር፤ ግን መጨረሻ ላይ የደካማው አፍ ውሳኔ ነው የጥቅሉን የወፍ እጣ ፈንታ የወሰነው፡፡ ምርጫ ባለበት ስለ አንድነት “integration” አስቀድሞ ማስብ --- የታሰበውንም እንደ ድምዳሜ አድርጎ መውሰድም የሚከብደው ለዚህ ነው፡፡
ምርጫ ማድረግ የሚችሉ የአካል ክፍሎችን ወደ አንድነት ማምጣት የሚቻለው በድርድር ብቻ ነው። በተፈጥሮ እኩል መሆናቸው በሳይንሳዊ/ምክንያታዊ ትንተና ግልጽ አድርጎ ማሳየቱ ጥያቄ አቅራቢዎቹን ካላሳመናቸው፣ ቅሬታ መውለዱ አይቀርም፡፡ የጨቋኝና ተጨቋኝ፣ የመደብም ሆነ የብሔር ትርክት መፈጠሩ አይቀርም፡፡
ደካማው የወፍ አፍ ጠንካራው እንደበደለው ከተረዳ፣ ይሄ ጥያቄ ለጠያቂው አግባብ ነው።
“በአፌ ምግብ አላምጬ በጉሮሮዬ ካላስገባሁ ተመገብኩ አልልም” ካለ፣ ጥያቄውን ቁብ ሰጥቶ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ “integration” የከፍታው እውነት ነው። ጥቅል የሚያደርጉን ነገሮች ይበዛሉ፡፡ ልዩነቶችን የመረዳት አቅም ያለው ንቃተ ህሊና ግን ወደ አንድነት የሚመጣው ልዩነቶችን በእኩልነት እየደመረ ነው፡፡ ወይም ልዩነቶችን እያከባበረ --- ካልሆነም እያቻቻለ፡፡
ሁሉም እኩልነትን የመጠበቅ ዘዴዎች ናቸው፡፡ልዩ ልዩ ነገሮችን እንደ ማንነታቸው በመቀበል ነው መደመር የሚቻለው፡፡ የተደማሪው ምርጫ--- ወይም ማንነት ከደማሪው ቅድመ እምነት ነጻ ካልሆነ፣ ያው የ”ጨፈለቅኸኝ” ለቅሶ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ “ከዚህ ውጭ አማራጭ የለም፡፡ አማራጭ አለ የሚልም አንድነቱን ለማፍረስ የሚሻ ነው” ብሎ የሚደመድም ደማሪ---ጉልበተኛ ነው፡፡
ለሀገር የሚጠቅመው ጉልበተኛው እራስ፤ ባህል፣ ሃይማኖት ወይም ትርክት የወፉን አካል ወክሎ እየተሻማ ሲበላ ነው፡፡ ከማለት አይተናነስም፡፡ግን እዚህ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ተፈጥሮን መረዳት የግድ ነው፡፡ ተፈጥሮ የሰው ልጆችን በማህበር እንዲኖሩ የመረጠችበት ምክንያት ሳይገባው፣ ማህበሩን ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ ብልጠት የሚመስል ጥፋት ነው፡፡-- የሰው ልጆች የባህልም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት በማህበር ለመኖር ባይጠቅም ተፈጥሮም ልዩነትን ባላበረታታችው ነበር፡፡
ከልዩነቶች የሚመጡ ጥያቄዎች አግባብ ባልሆነ ፍትህ ሰጪ ካልተሸፈኑ በስተቀር አብሮ መኖሩን ሊያጠፉ የሚችሉ አይደሉም። እኩልነት ባያስፈልግ ጥያቄም ሆኖ ባልተነሳ ነበር፡፡ “survival of the fittest” ማለት ጉልበተኛ በአንድነቱ ላይ ብቻውን ይወስን ማለት አይደለም፡፡ ደካማው የወፉ አፍ፣ በአንድነቱ ህልውና ላይ መወሰን ሲከለከል፣ ህልውና በማጥፋቱ ላይ ግን በእልህ መወሰን ችሏል፡፡
ደካማው እራስ በእልህ “ካልበላሁ ጭሬ ላፍስሰው” ማለቱ ወፉን ገድሎታል፡፡ ጉልበተኛው እራስ “በእኔ አፍ በኩል እህል ከገባ ነው ሀገር የምትኖረው” ማለቱም ጭቆናን በማይፈልጉት አቅመ ቢሶች ላይ ጭኖባቸዋል። ከራሱ (ራስ) ውጭ ባሉት ላይ፡፡ በአቅመ ቢሱ እራስ እና በአካሉም ላይ፡፡
ይኼ የወፍ ተረትና ምሳሌን በደንብ ለተመለከተ ሦስተኛ እራሰ መኖር አለበት፡፡--- ብሎ ቢጠይቅ አይገርመኝም፡፡ ሦስተኛው እራስ ህግ ነው። ህገ መንግስት፡፡ ለደካማው ብቻ ሳይሆን ለአቅመ ቢሱም በእኩልነት የሚፈርድ እራስ፡፡ በጉልበት ሳይሆን በዲሞክራሲ ከሁሉም ጥያቄና ምርጫ የተመረጠ ሦስተኛ እራስ፡፡ መምረጥ ለሚችሉት እራሶች (ልሂቃን) ብቻ ሳይሆን መምረጥ ለማይችለው የወፉ አካል ክፍሎች በአጠቃላይ የሚያስብ ሦስተኛ እራስ። ሦስተኛው እራስ፣ ሥራውን በአግባቡ መሥራት እንዲችል፣ ቅርንጫፎች ሊፈጥር ይችላል፡፡
በተፈጥሮው የወፉ የአካል ክፍሎች ላይ አንድነትን በህግ ውክልና የሚያከናውን ሰው ሰራሽ አካል መቀጠል ይችላል፡፡-- ወፉ በተፈጥሮ የተሰጠውን አካል ለማኖር፣ ሰው/ወፍ ሰራሽ ጎጆ እንደሚቀልሰው፡፡ ወፉ ሦስተኛ እራስ ቢኖረው---ሦስተኛው እራስ በጠንካራ ተቋሞች ቢታነጽ ኖሮ---መርዝ በልቶ መሞትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ባልወሰደ ነበር። ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የወፉን ታሪክ የነገረን ታሪኩ በአሳዛኝ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑ---ለወፉ ባይጠቅመውም ለእኛ ሰዎች ግን የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ እንደ ወፉ እኛም በእራሶች መሃል ባለ ቂምና ግጭት እየተናጥን ያለበት ሁኔታ ላይ ነን፡፡
“እኔ ከሌለሁ አገር ትፈርሳለች” የሚሉ ብዙ ራሶች አብቅለናል፡፡ በአካሉ ላይ የተሰጠን ቦታ አይገባንም የሚሉ ናቸው፡፡ የጥቅሉ ውክልና በእኛ በኩል --- የሚሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ጥያቄ አላቸው፡፡ ጥያቄ ያላቸውን የሚያፍኑ እንዳለ ሁሉ--የራሱን ጉልበት ለማበርታት ጥያቄ እየፈጠረ እርስበርስ ለማጋጨት የሚለፋም ይኖራል፡፡ -- የራስ መኖር ወይም ራስ ማብቀል--”የራስ ብቻ” ለማለት ከሆነ፣ የመቻቻል ሂደቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
መፎካከር እንጂ መተባበር ያዳግታል፡፡ እኩልነት ለመፍጠር የሚሞክረውን የህግ አካልም ሥራ ያበዛበታል። የሀገር ሽማግሌ ሥራ ሲፈታና ሀገር ደግሞ በአዎንታዊ ሥራ ውስጥ ሲጠመድ፣ ያኔ ብልጽግና መፈጠሩ ግልጽ ነው፡፡
ያኔ ነው ልዩነት የማይጎላው፡፡ አሁን አገር አንድ የሆነችው በግጭት አማካኝነት ነው፡፡ እኔ ስለ ሶማሌም ሆነ ኮንሶ ያወቅሁት በግጭትና የሰው ጉዳት አማካኝነት ነው፡፡ ድሮ “ሀገርህን እወቅ” ሲባል በሽርሽር አማካኝነት ነበር፡፡
ያኔ ነው ልዩነት የማይጎላው፡፡ አሁን አገር አንድ የሆነችው በግጭት አማካኝነት ነው፡፡ እኔ ስለ ሶማሌም ሆነ ኮንሶ ያወቅሁት በግጭትና የሰው ጉዳት አማካኝነት ነው፡፡ ድሮ “ሀገርህን እወቅ” ሲባል በሽርሽር አማካኝነት ነበር፡፡
አሁን ሀገሩን በጠቅላላ እያወቅነው ያለው፣ በሰቆቃ አስጎብኚ የሚዲያ ተቋማት ነው፡፡ ከቤት መውጣት ፈርተን፣ በሰበር ዜና የምንጎበኘው ሀገር ሆኗል፡፡ የሞተ --- ወይም የተሰደደ--- ወይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጣለበት-- ወይም ኢንተርኔት የተዘጋበት --- በሚል የተገለጹ ቦታዎችን በኢትዮጵያ ካርታ ላይ እየፈለግሁ ምልክት ሳደርግ፣ ሳልጎበኝ የቀረሁት ቦታ በጣም ጥቂት ብቻ ነው፡፡
“ሀገሬን አውቄአታለሁኝ” - በሰቆቃ ሰበር ዜና፡፡ ቤቴ ውስጥ ተቀምጬ፡፡ ሀገር እንዳይፈርስ እፈራለሁኝ፡፡ ግን የሰቆቃው ካርታ እንደሚያሳየው፤ ሀገር ያለችው “ድህረ ፍራሽ” ውስጥ ነው፡፡ ፈርሶ የማይፈርስ ህዝብ፣ ከልዩነቱ ይልቅ አብሮ የሚያኖረው ምክንያት፣ ከካቦ ሽቦ የጠነከረ መሆኑ ሊገለጽለት ይገባ ነበር፡፡ ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ ለመለያየት የሚሰራው ሥራ --- እና ሰሪዎቹ ተግተው ቀጥለዋል፡፡
ሊዮናርዶ ፒኮፍ የሚባል ፈላስፋ ከጥቂት ዓመታት በፊት ባወጣው “The Dim Hypothesis” የተሰኘ መጽሐፉ ላይ አንድ ምሳሌ ያነሳል፡፡ የ”integration” አስፈላጊነትን ለማሳየት ነው፣ በምሳሌው የሚሞክረው። በሃሳብና ነገራት መሃል ያለው ትስስር ሲረሳን ምንነታችን “ሰውነታችን” ይጠፋናል ባይ ነው - ፈላስፋው፡፡
እና አንዲት ህጻን ልጁን አባት ይጠይቃታል። ጥያቄው፤ “where is dady?” የሚል ነው። የአምስት ዓመት ህጻን ልጁ፣ የጠየቃት አባቷ ደረት ላይ ጣቷን ትጠቁማለች፡፡ አባት ጭንቅላቱን ይነቀንቅና፤ “No that’s dady’s chest, where is dady?” ህጻኗ ግራ ይገባታል፡፡ በመቀጠል ጭንቅላቱ ላይ ጣቷን ታመለክታለች፡፡
“No no—that’s dady’s head, so where is dady?” ህጻኗ ግራ ተጋብታ ማልቀስ ትጀምራለች፡፡ አባቴ የት ጠፋ ብላ ነው ያለቀሰችው፡፡ አዎ ዋናው ነገር ኢንተግሬሽን ነው፡፡ ኢንተግሬት ማድረግ ካልተቻለ፣ መልክአ ምድር እያለ ሀገር ይጠፋል፡፡ ሰዎች እያሉ ህዝብ ይጠፋል። ውጤቶች እያሉ ምክንያቱ ግልጽ አይሆንም።
“አንድ” የሚለው ቁጥር መኖሩን የማያውቅ፣ “መቶ ሚሊዮን” የሚለው አብስትራክት ብዛት ላይ ሊደርስ አይችልም፡፡ ልዩነቱ አንድነቱን እንዲሰራ አንድነቱን ስለ ልዩነቱ ምርጫ ካልሆነ፣ ያለ ነገር ወደ ሌለ ይለወጣል፡፡ ብዙ እራሶች እያሉ፣ ላይለያዩ መጠፋፋት፣ የዕለት ተዕለት የህልውና ግባቸው ይሆናል፡፡
ግባቸው፣ የሁሉንም ህልውና ማጥፋት መሆኑ የገባቸው አይመስልም፡፡ እራስ ስላለ ማመዛዘን አብሮ ይሰጣል ማለት አይቻልም።
No comments