Latest

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 1፡- ከልዩነት ወደ ጦርነት - ስዩም ተሾመ

ከልዩነት ወደ ጦርነት

“የሰቆቃ ልጆች” በሚል ርዕስ ያቀረብናቸው አምስት ተከታታይ ፅሁፎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጀርመንና ጃፓን ወታደራዊ ፋሽስት፣ እንዲሁም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በእስራኤልና በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት የተመሰረቱበትን ሁኔታ በዝርዝር ለመዳሰስ ሞክረናል።  


 ከዚህ በመቀጠል “የዘር/ብሔር አፓርታይድ” በሚል ርዕስ በምናቀርባቸው ተከታታይ ፅሁፎች የኢትዮጲያና የደቡብ አፍሪካ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረትን በዝርዝር ለመዳሰስ እንሞክራለን። በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ለዜጎች የመብትና ነፃነት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ እንዴት ወደ ብሔርተኝነት እና ጦርነት እንደሚቀየር እንመለከታለን።

1. የዘር/ብሔር ልዩነት
እ.አ.አ. በ1950 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ያወጣው የሕዝብ ምዝገባ አዋጅ (Population Registration Act) የሀገሪቱን ዜጎች “ነጭ፥ ጥቁር፥ “ከለርድ” (colored) እና ህንዳዊያን” በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። በተመሣሣይ፣ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀፅ 39(5) የሀገሪቱን ዜጎች በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነ ልቦናን መሰረት በብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ይከፋፍላቸዋል።

በመሰረቱ “አፓርታይድ” (Apartheid) የሚለው ቃል “መለየት” (Separatedness) ወይም “መለያየት” (the state of being apart) ማለት ነው። ዜጎች የሚከፋፈሉት በዘር ሆነ በብሔር በመካከላቸው የሚኖረውን ልዩነት አይቀይረውም ወይም መለያየቱን አያስቀረውም። ስለዚህ፣ “አፓርታይድ” ማለት የአንድ ሀገር ዜጎችን በዘር/ብሔር በመለየትና በመለያየት የሚያስተዳድር ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረትን ከማየታችን በፊት ግን የዘር/ብሔር ልዩነት እንዴት ለፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ እንደሚውል እንመልከት።

በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዘር ሀረግ፥ በቆዳ ቀለም፣ በብሔር፥ በቋንቋ፥ በባህል፥ በልማድ፣ በሥነ-ልቦና፣ በሃማኖት፣…ወዘተ ይለያያሉ። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፥ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብሎ የሚያምን፥ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር ማኅበረሰብ እንደ ሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

ምንግዜም ቢሆን በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እና በሌላ መካከል ልዩነት ይኖራል። ከፖለቲካ አንፃር ሲታይ፣ ልዩነት የሰላም ወይም ጦርነት፣ የዴሞክራሲ ወይም ጭቆና መኖርና አለመኖር መለያ ነው። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሃማኖት፥ ሕልውና (ማንነት)፣…ወዘተ “እኩል” በሚከበርበት፣ ሁሉም ዜጎች የራሳቸውን አመለካከት ያለማንም ጣልቃ-ገብነት የመያዝና ሃሳባቸውን “በነፃነት” መግለፅ በሚችሉበት፣ እንዲሁም ከሀገሪቱ ልማትና እድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚ ከሆኑ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ መኖሩን ያረጋግጣል።

በተቃራኒው፣ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ባልተረጋገጠበት ሀገር ጭቆና መኖሩና ጦርነት ማስከተሉ እርግጥ ነው። በአንድ አከባቢ የሚኖር ማኅብረሰብ ጭቆና ሲደርስበት በቅድሚያ መብቱና ነፃነቱ እንዲከበር በአመፅና ተቃውሞ ብሶትና አቤቱታውን በአደባባይ ይገልፃል። ሆኖም ግን፣ መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የሕዝቡ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ ግጭትና ጦርነት ይቀየራል።

በመሰረቱ በአንድ አከባቢ የሚኖር ማኅብረሰብ የራሱን መንግስት የሚመሰረተው ሕግና ስርዓት እንዲያስከብር፣ በዚሁም የሁሉንም መብትና ነፃነት እንዲያረጋግጥ ነው። የተወሰነ ሕብረተሰብ ክፍል የእኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ሲያነሳ መንግስት በምላሹ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ለእስራት፣ እንግልትና አካል ጉዳት የሚዳረግ ከሆነ እንደ መንግስት መሰረታዊ ዓላማውን ስቷል። መሰረታዊ ዓላማውን የሳተ ነገር ሁሉ ፋይዳ-ቢስ ነው። ስለዚህ፣ ከሕዝቡ የሚነሳን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚሞክር መንግስት ሕጋዊ መሰረት የለውም።

በዚህ ምክንያት በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ውስጥ እንዲህ ያለ ቅሬታ ሲፈጠር የለውጥ አብዮት ማስነሳት ለሚሹ ልሂቃን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ልሂቃን በማህብረሰቡ ውስጥ የለውጥ አብዮት ለመቀስቀስ ከሚጠቀሟቸው ስልቶች ውስጥ ዋናዋናዎቹ የብሔርተኝነት ስሜት እና በራስ-የመወሰን መብት ናቸው። በዚህ መልኩ በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እና በሌላ መካከል ያለ ልዩነት በሂደት ወደ ግጭትና ጦርነት ያድጋል። የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት – TPLF) መስራችና የቀድሞ አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ድርጅቱ የትግል አጀማመር በሰጠው ትንታኔ እንዲህ ይላል፡-

“Discontent can be caused by a variety of intervening factors but often is articulated in relation to the state that claims to possess the moral and legal authority to manage the affairs of the populace. Once discontent has been created, it can be easily politicized by the elite who seek change and civil disorder may follow. In this circumstance ‘loss of government legitimacy is an important if not critical factor in explaining civil strife events.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Ch.2, Page 24.
2. ብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት
ፖለቲካዊ ስርዓቱ የአንድን ማህብረሰብ እኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማያረጋገጥ ከሆነ የማህብረሰቡ ልሂቃን የተለያየ ዓይነት የለውጥ እርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ። በተለይ መንግስታዊ ስርዓቱ የዜጎቹን መብትና ነፃነት ማረጋገጥ ሲሳነው በቅድሚያ አስፈላጊ የሚሏቸውን የሕግና ፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ ይጎተጉታሉ።

የሀገሪቱ መንግስት ስራና አሰራሩን በመቀየር ከሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ከተሳነው አመፅና ተቃውሞ ይቀሰቀሳል። መንግስት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ብሶትና አብቱታውን በአደባባይ እንዳይገልፅ የሚያፍነው ከሆነ የለውጥ ንቅናቄው ወደ ትጥቅ ትግልና ጦርነት ያመራል።

በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የለውጥ ፍላጎት ወደ “አብዮት” (revolution) ለመቀየር እና የትግል ስልቱን ከአደባባይ አመፅና ተቃውሞ ወደ ውጊያና ጦርነት ለማሸጋገር የፖለቲካ ልሂቃኑ ሁለት ነገር መፍጠር አለባቸው። እነሱም፣  
  1. በብሔሩ፥ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የወገንተኝነትና የአንድነት ስሜት ለመፍጠር ብሔርተኝነትን ማስረጽ፣ 
  2. የትግሉን ዓላማና ግብ ደግሞ የብሔሩን፥ ብሔረሰቡን ወይም ሕዝቡን በራስ-የመወሰን መብት ማረጋገጥ እንዲሆነ ማሳመን አለባቸው።
ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት በሚደረጉ የሕዝብ ንቅናቄዎች ውስጥ ያለው መሰረታዊ ጥያቄ በራስ የመወሰን መብትን (right of self-determination) ነው። በራስ የመወሰን መበት አንድ ብሔር ወይም ሕዝብ የወደፊት ዕድሉን በራሱ የመወሰን፣ በራሱ ሕግና ደንብ የመተዳደር እና ከእሱ ፍቃድና ምርጫ ውጪ በሆኑ መሪዎች አለመመራት ነው። በዚህ መሰረት፣ ማህብረሰቡ ልዩነቱን በራሱ ማስከበር ይችላል።  

ከዚህ በፊት ሲያነሳቸው የነበሩት የእኩልነት፥ የነፃነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በራሱ ለራሱ መመለስ ይችላል። ብሔርተኝነት ደግሞ የማህብረሰቡን አባላት በትግሉ ዓላማና ግብ ዙሪያ አንድነትና ቁርጠኝነት እንዲኖረው ያስችላል። በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች እና በኢትዮጲያ ትግራይ የትጥቅ ትግል የተጀመረው በብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት ላይ ተመስርቶ ነው።

2.1 በደቡብ አፍርካ የነጭ ሰፋሪዎች (Boers) የትጥቅ ትግል
በደቡብ አፍሪካ ቀድመው የሰፈሩት ነጮች “Boers” የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ “Boers Republic” በሚል ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ነፃ ግዛቶች ነበሩ። ነገር ግን፣ እ.አ.አ. በ1866 የአልማዝ፣ እንዲሁም በ1886 ደግሞ የወርቅ ማዕድን በአከባቢው መገኘቱን ተከትሎ ብዙ የእንግሊዝና የሌሎች ሀገራት ዜጎች (utilanders) ወደ አከባቢው በብዛት መጉረፍ ጀመሩ።  

የአዲስ ሰፋሪዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄዶ በ1890ዎቹ የመጀመሪያ ላይ ከነባር ነጮች ”Boers” ጠቅላላ ብዛት በሁለት እጥፍ በለጠ። ይህ በነባር የደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብታቸውና ነፃነታቸው ላይ የሕልውና አደጋ ተጋረጠበት።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በራስ-የመወሰን መብታቸው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ አዲስ ረቂቅ አዋጅ በማውጣት ተግባራዊ አደረጉ። ይህ አዋጅ የነባር ሰፋሪዎችን በራስ-የመወሰን መብት የሚያረጋግጥ ሲሆን የአዲስ ሰፋሪዎችን ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት የሚገድብ ነበር።  

አብዛኞቹ አዲስ ሰፋሪዎች ከእንግሊዝ ወይም ከቅኝ-ግዛቶቿ የመጡ እንደመሆናቸው በእንግሊዞች እና በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች (Boers) መካከል አለመግባባት አለመግባባት ተፈጠረ። አለመግባባቱ ወደ ጦርነት ተሸጋገረና በሁለቱ መካከል “Second Boers War” የተባለው፣ በዓለም ታሪክ አሰቃቂ በደልና ጭቆና የተፈፀመበት ጦርነት ተካሄደ። ይህ አሰቃቂ በደልና ጭቆና ደግሞ እ.አ.አ. በ1948 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ለተመሰረተው አፓርታይድ ስርዓት ዋና ምክኒያት ነው።

2.2 በትግራይ የሕወሃት የትጥቅ ትግል 

በእርግጥ የትግራይ ሕዝብ በራስ የመወሰን ጥያቄን ማንሳት የጀመረው በቀዳማይ ወያኔ አማካኝነት ነው። በቀዳማይ ወያኔ የተካሄደው የአርሶ-አደሮች አመፅ ከባሌና ጎጃም የአርሶ-አደሮች አመፅ ጋር ተመሳሳይ ነው። የአርሶ-አደሮቹ አመፅና ተቃውሞ በዋናነት በእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ማዕከል ያደረገ ነበር። ሆኖም ግን፣ በወቅቱ የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ የወሰደው እርምጃ የአመፅ እንቅስቃሴውን በጦር ኃይል ማዳፈን ነበር።  

በዚህ መልኩ በወቅቱ የነበረው መንግስት ለሕዝቡ የመብትና ነፃነት ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ቀጣዩን የትግል ስልት በብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል።

በዚህ መሰረት፣ ዳግማዊ ወያነ – ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የማህብረሰቡን የብሔርተኝነት ስሜት በማቀጣጠል እና በራስ-የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የሕወሓት (TPLF) መስራችና የቀድሞ አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመር፣ የንቅናቄ ስልትና ድርጅታዊ አሰራር በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-

“…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one hand and the enforcement of strict internal discipline of its rank and file that able to take on rival forces decisively.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Ch.5, Page 151 – 152.
ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሁለቱ ወገኖች፤ በእንግሊዞች እና በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በደርግ መንግስት እና በሕውሃት ታጋዮች መካከል ጦርነት ተካሂዷል። በጦርነቱ ወቅት የእንግሊዝና የደርግ መንግስት እያንዳንዳቸው 22000 ወታደሮች በሦስት አመት ውስጥ ተገድሎባቸዋል። 

ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ነጮችና በትግራይ ሕዝብ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በሁለቱ ሀገራት የተፈፀመው አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ለዘር/ብሔር አፓርታይድ መመስረት ያለውን አስተዋፅዖ በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

No comments