Latest

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (1832 – 1911 ዓ.ም.) (አበባው አያሌው እንደ ጻፈው)

እቴጌ ጣይቱ ብጡል

እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ታሪክ የጎላ ሥፍራ ካላቸው እጅግ ጥቂት አንስት በግምባር ቀደምትነት የሚጠሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ንጉሥ ምኒልክን (በኋላ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያን) በሕግ ጋብቻ ካገቡ በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ አስተዳደርና ሥልጣኔ ያበረከቱት አስተዋጽዖ ነው፡፡ ከበርካታ አስተዋጽዖዎቻቸው ጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡

የዐፄ ምኒልክ አስተዳደር እንዲመቻችና ሥልጣናቸው እንዲጠናከር አስተዋጽዖ ማድረግ
የዐፄ ምኒልክ የትውልድ ሐረግ ከሰሎሞናውያን ነገሥታት የሚመዘዝ ቢሆንም ከሸዋ አልፎ ከሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች መሳፍንት ጋር እምብዛም አይተሳሰርም፡፡ የእቴጌ ጣይቱ የትውልድ ዘር ሐረግ ግን አብዛኛውን የሰሜን ኢትዮጵያን ከሚገዙት ወይም ከሚያስተዳድሩ መሳፍንት በእጅጉ የተሣሠረ ነው፡፡

የትውልድ ሐረጋቸው ከደምቢያ በደጃች ማሩ (ማሩ ቀመስ ደምቢያ)፣ ከስሜን በደጃዝማች ኃይለ ማርያም፣ ከላስታና ዋግ በዋግ ሹም ክንፉ፣ ከትግራይ በደጃዝማች ገብረ ሚካኤል፣ ከጎጃም በደጃዝማች ዮሴደቅ፣ ከወሎ የጁ ደግሞ በቅደመ አያቷ ዕውቁ የዘመነ መሳፍንት የወረሴህ መስፍን በራስ ጉግሳ ሙርሳ የተዛመዱ ናቸው፡፡

የትውልድ ሐረጓ ከብዙ የሰሜን ኢትዮጵያ መሳፍንት መተሣሠሩ ለዐፄ ምኒልክ ሥልጣን መደላደልና ለአስተዳደሩ መመቻቸት ትልቅ አስተዋጽዖ ነበረው፡፡ የእቴጌ ጣይቱና የንጉሥ ምኒልክ በጋብቻ መተሣሠር በክብርም በፖለቲካም የጠቀመው ጣይቱን ሳይሆን ምኒልክን ነበር፡፡

የአዲስ አበባ መቆርቆር፡-


ዐፄ ምኒልክ ከመቅደላ አምባ አምልጠው ሸዋ ከገቡ በኋላ መቀመጫ ከተማቸውንና የአስተዳደር ማዕከላቸውን ከቦታ ቦታ ሲቀይሩ ነበር፡፡ መጀመሪያ አንኮበር፣ ቀጥሎ ወረ ኢሉ ከዚያም ልቼ (ደብረ ብርሃን አጠገብ) መቀመጫ ከተማቸውና የአስተዳደር ማዕከላቸው ነበሩ፡፡ 

ከ1873 እስከ 1875 ዓ.ም. ደግሞ መናገሻ፣ ሆለታና ፉሪ እንደ ጊዚያዊ ማዕከል ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1875 በኋላ እንጦጦን ከተማቸውና የአስተዳደር ማዕከላቸው አድርገዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ አየወረዱ ፍል ውኃ አጠገብ ድንኳን እያስተከሉ ሳምንትም ሁለት ሳምንትም ይነከሩ ነበር፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት የቂጥኝ ሕመም ተጠቂ ስለ ነበሩ ነው፡፡ በፍል ውኃ መነከር ለቂጥኝ ሕመም ጊዜያዊ ማስታገሻ ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ መካን የሆኑበት ዋናው ምክንያትም ይህ የቂጥኝ ሕመም ነበር፡፡  

ፍል ውኃ ለመነከር በተደጋጋሚ ከእንጦጦ በመውረዳቸው ምክንያት በኅዳር 1878 ዐፄ ምኒልክ ወደ ሐረርጌ በዘመቱበት አጋጣሚ አሁን ታላቁ ቤተ መንግሥት በሚገኝበት ቦታ ቤት እንዲሠራና አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ትእዛዝ ሰጡ፡፡

በዚህ መሠረት አዲስ አበባ ብለው ራሳቸው የሰየሙት ከተማ ከእንጦጦ ግርጌ ተመሠረተ፡፡ ምኒልክም ከሐረርጌ ዘመቻ ሲመለሱ የእቴጌን ሐሳብ ተቀብለው የቤተ መንግሥት ሥራው እንዲፋጠን አደረጉ አድባራትንም ተከሉ፡፡

እቴጌ ጣይቱ አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ከማዘዛቸው በፊት አሁን አዲስ አበባ የምንለው ከተማ ፍል ውኃ ለመነከር የሚመጡ ሕመምተኞች በተለይም የሥጋ ደዌ በሽተኞች ትንንሽ ጎጆ ሠርተው የሚቀመጡበት ሥፍራ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል አፈ ወርቅ ገብረ ኢየሱስ “ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው “ይህን የቆማጣና የድውይ መሰብሰቢያ ቀን አወጡለት” ሲል ያተቱት፡፡

የቅድመ ዐድዋ የዲፕሎማሲ አስተዋጽዖ፡-
በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል በውጫሌው ውል አንቀጽ 17 ትርጓሜ በተነሣው አለመግባባትና የዲፕሎማሲ ውዝግብ ከዐፄ ምኒልክ ይልቅ እቴጌ ጣይቱ የጎላ ሚና ነበራቸው፡፡ በወቅቱ ጣሊያኖች በኢትዮጵያ የሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ሁለት ነበሩ፡፡

1. ማስከዳት(Subversion) ይህ ማለት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ የሚገኙ መሳፍንትንና ባላባቶችን ምኒልክን እንዲከዱ ማድረግ ነው፡፡

2. ማሳመን(Persuasion) ይህ ማለት በመሐል ኢትዮጵያ ያሉትን የመንግሥት ታላላቅ ሰዎችን በተለይም ዐፄ ምኒልክ፣ ራስ መኮን፣ እና እቴጌ ጣይቱ የውጫሌን ውል ያለምንም ማስተካከያ እንዲቀበሉ ማሳመን ነው፡፡

ጣሊያኖች በሚከተሉትና በተደጋጋሚ ባደረጉት የማሳመን ፖሊሲ ጥረት ለኢጣሊያ መንግሥት ተወካይ ለኮንት ፔትሮ አንቶኔሊ የስብከትና የማስፈራሪያ እንዲሁም የሽንገላ የዲሎማሲ አክሮባት አልበገር ያሉትና ከዐፄ ምኒልክም ሆነ ከራስ መኮንን የበለጠ ጠንክረው የተከራከሩት እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ ለውጫሌው ውል ሙሉ ለሙሉ መሠረዝ ዋነኛ ተከራካሪ እቴጌ ጣይቱ ናቸው፡፡

በዐድዋ ዘመቻ ለዘመቻው መሳካትና ለዋናው ድል ያደረጉት አስተዋጽዖ፡-
በዐድዋ ዘመቻ ወቅት የእቴጌ ጣይቱ ዋና የሥራ ድርሻ የሠራዊቱን ስንቅ ማሰናዳት ነበር፡፡ ወቅቱ በአብዛኛው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ርሃብና ድርቅ የነበረበት በመሆኑ እንዲሁም የአባ ደስታ በሽታ የቀንድ ከብቱን ስለፈጀው ለሚዘምተው ሠራዊት ስንቅ ማደራጀት ከባድ ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ በየአካባቢው ያሉ የሥጋ ዘመዶቻቸውን በመጠቀም ለሠራዊቱ ስንቅ የሚሆን እህል መጀመሪያ ወረ ኢሉ እንዲከማች አደረጉ፡፡

ቀጥሎም ይህ ስንቅ የሚጓጓዝበትን መንገድ አመቻችተው እስከ አድዋ ድረስ በልክና በሚበቃ መልኩ ለሠራዊቱ እንዲደረስ ያደርጉ ነበር፡፡ ስንቅ ባነሰ ጊዜም ስሜን (ጎንደር) ያሉ ዘመዶቻቸው ይዘው እንዲመጡ ያደርጉ ነበር፡፡

የመቀሌው ከበባ በድል እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉትም እቴጌ ጣይቱ ናቸው፡፡ የጣሊያን ወታደሮች አሁን መቀሌ እንዳየሱስ ላይ ፎርቶ ዲ. ጋሊያኖ የሚባለው ቦታ መሽገው ለሁለት ሳምንት የኢትዮጵያን ጦር አላስጠጉም ነበር፡፡ 

እቴጌ ጣይቱ ባመጡት ብልሐትና በራሳቸው ከሚመራው እና ከሚታዘዘው ጦር ምርጥ ተዋጊዎችን በሌሊት ልከው ጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን ከምሽጋቸው በስተ ደቡብ ያለውን ማይንሽቲ የተባለውን ምንጭ በኢትዮጵያውያን እጅ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ይህ ወታደራዊ እርምጃ በጣሊያኖች ዘንድ ከፍተኛ የውኃ ችግር በመፍጠሩ ጣሊያኖች ምሽጋቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል፡፡

በዋናው የዐድዋ ጦርነት ቀን እቴጌ ጣይቱ የሚመሩት ጦር በውጊያ ከመሳተፉ ባሻገር የሚቆጣጠሯቸው የሥራ ቤት ሴቶች ውኃ በማቅረብ ቁስለኛ በማንሣትና በማከም ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡  

ጦርነቱ በብዙ ቦታዎች በመደረጉ አንዱን ክፍል የጣሊያን ጦር አሸንፎ የሚመጣውን ጦር እንዲሁም የደከመውን “አይዞህ በርታ ውጊያው አላለቀም ንጉሡም አልተመለሱም” እያሉ ሲያበረታቱ ውለዋል፡፡ የዐድዋ ጦርነት ጅግና አንስት እቴጌ ጣይቱና አዝማሪ ፃዲቄ ነበሩ፡፡

የዘመናዊ ትምህርት አስተዋጽዖ፡-
እቴጌ ጣይቱ በውጫሌ ውል ምክንያት በአስተርጓሚ ሲደረግ የነበረውን ችግር በመገንዘብ ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር ሂደው ቋንቋና ጥበብ እንዲማሩ ዐፄ ምኒልክን ይወተወቱ ነበር፡፡ ይህም ውትወታ ፍሬ አፍርቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተልከው የአውሮፓን ጥበብ በተለይም ቋንቋ እንዲማሩ እቴጌ ጣይቱ ግምባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡

ዘመናዊ ሆቴል እንዲቋቋም ማድረጋቸው፡-
እቴጌ ጣይቱ ኢትዮጵያውያን መሳፍንትን ባላባቶችንና ተራውን ሕዝብ በግብራቸውና በድግሳቸው ሁልጊዜም እንዳስደሰቱት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአውሮፓውያን እንግዶች ብዛት እየጨመረ ሲመጣ ለእነሱ የሚሆን የግብር ምግብ ማዘጋጀት አስቸጋሪ እየሆነ መጣ፡፡ ይህም በአመጋገብ ባህል ልዩነት የተነሣ ነው፡፡ 

ስለሆነም ለአውሮፓውያን (ለፈረንጆች) እንደ ባሕላቸውና እንደ አመላቸው ምግብና መጠጥ የሚቀርብበት ቤት (ሆቴል) እንዲሠራ ሐሳብ አፍልቀው ጣይቱ ተብሎ በስማቸው የሚጠራ ሆቴል ተከፈተ፡፡

ዘመናዊ ወፍጮ
እቴጌ ጣይቱ ዘመናዊ የእህል ወፍጮ ወደ ሀገራችን እንዲገባ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ ለግብር የሚሆን እህልን መፍጨት ከፍተኛ የሰው ኃይል እና ጊዜ ይወስድ ስለነበር ዐፄ ምኒልክን ዘመናዊ የእህል ወፍጮ ወደ ሀገራችን ገብቶ ሥራ እንዲጀምር በመወትወት አስፈጽመዋቸዋል፡፡

ዘመናዊ የውኃ መዘውር
የዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከፍተኛ የውኃ ፍጆታ ነበረው፡፡ በተለይም ለሥራ ቤቱ የዕለት ተግባር ብዙ ውኃ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ውኃ ከወንዝና ከምንጭ በሰው ኃይል በእንስራ ከማስቀዳት ዘመናዊ የውኃ መዘውር እንዲገባና ውኃ በቧንቧ ወደ ተፈለገው ክፍል እንዲሄድ ሐሳቡን ለምኒልክ አቅርበው አስተግብረውታል፡፡

እቴጌ ጣይቱ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በፖለቲካና በአስተዳደር ጉዳዮች ከምኒልክ ጎን ሆነው በሁሉም ውሳኔዎች ይሳተፉ ነበር፡፡ በእድሜ ዐፄ ምኒልክን አራት (4) ዓመት ስለሚበልጡ እንዲሁም በትውልድ ሀገራቸው ከዐፄ ምኒልክ ይልቅ እጅግ የተከበሩ በመሆናቸው በሁሉም ዓይነት ጉዳይና ምክር ተሳታፊ ነበሩ፡፡ 

በኢትዮጵያ ታሪክ የእርሳቸውን ዓይነት የፖለቲካ ቦታ ከነበራቸው አንስት በእጅጉ የሚለዩትም በትውልድ ሐረጋቸው፣ በአስተዳደርና በፖለቲካ በነበራቸው የላቀ ድርሻ ነው፡፡ “እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ” የሚል የራሳቸው ማኅተምም ነበራቸው፡፡ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ እቴጌዎች የግል ማኅተም አልነበራቸውም፡፡

No comments