Latest

በጦላይ ቆይታዬ የተማርኩት፣ የታዘብኩት፣ የተገነዘብኩት! (አፈወርቅ አምበሉ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ)

አፈወርቅ አምበሉ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ

  • "አንዷን ከእኛ ጋር ያዟትና የ10 ወር ህፃን ልጅ አለኝ አለቻቸው፤ ወደ ቤቷ ይዘዋት ሄዱ፡፡ ልጅዋን ሲያዩ፣ ይለቋታል ስንል፣ ከእነ ልጇ ይዘዋት ተመለሱ፤ ልጇን እዚያው ስታጠባ አደረች፡፡"
  • "የሰውን ልጅ በግድ በጉልበት ይዞ አካላዊና ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ይቻል ይሆናል፣ እንዴት አዕምሮውን እናሰለጥናለን ትላላችሁ፣ ያውም ይሄን ያህል የኖረ ሰው፣ በዚያ ላይ ያለ ፍላጎቱ እንዴት ይሆናል? ለመሆኑ ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ታውቁታላችሁ ወይ?--- እላቸው ነበር፡፡ እነሱ ደግሞ ከላይ ታዘን፣ ይህን ለማስተማር ነው የመጣነው፣ ለጥያቄያችሁ መልስ የለንም ይሉናል፡፡"
  • "የአቋም መግለጫው በጣም ያስቃል፤ በፌስ ቡክ የሚወራው እኛን አይወክልም ብቻ አይደለም፣ የተከሰስንባቸው ቀደም ብዬ የነገርኩሽ ጉዳዮች አሉ አይደለ መንግስት አልተሳሳተም፣ መታደስ ያለባቸውን ልጆች ነው የያዘው፣ በትክክል አድሷል፣ ተፀፅተን ህብረተሰቡን ለመካስ ነው የመጣነው ምናምን ይላል …. ይሄ እስካሁን በጣም በጣም ያስቀኛል፡፡"

ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተይዘው ጦላይ ማሰልጠኛ ከገቡት ወጣቶች አንዱ ነህ፡፡ እስኪ የትና እንዴት እንደተያዝክ ንገረኝ?

የተያዝነው ሺሻ ቤት ነው፡፡ እኔ መጠጥ ቤት ማምሸት ትቻለሁ፡፡ የምጠጣውን በውሃ ፕላስቲክ ይዤ ሺሻ ቤት ነው የምሆነው፡፡ መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ላይ ነው መጥተው ጠራርገው የወሰዱን፡፡

ለምንና የት እንደሚወስዷችሁ ለመጠየቅ ወይም ለመከራከር አሊያም ለማስረዳት አልሞከራችሁም?

እኔ ምንም አላልኩም፡፡ ለመከላከል ለመደባደብ የሞከሩ ነበሩ፡፡ እኔ ትፈለጋለህ ከተባልኩ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ራሴ ነኝ የምሄደው፤ ፈልጋችሁኛል ወይ እላለሁ፡፡ ደግሞም ነፃነቴ ታውቆ እስከምትለቁኝ ድረስ ለማምለጥ እንኳን አልሞክርም፤ ራሴን የማውቅ ሰው ነኝ ብያቸዋለሁ፡፡

ለማምለጥ የሚሞክሩ ነበሩ እንዴ?

ከተለያየ ቦታ ታፍሰው ከመጡ ልጆች ውስጥ ለማምለጥ፣ ፖሊስ ለመደብደብ ሁሉ የሞከሩ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ አያያዛቸው ያስፈራ ነበር፤ በኋላ መለየት ጀመሩ እንጂ፡፡ ለምሳሌ አንዷን ከእኛ ጋር ያዟትና የ10 ወር ህፃን ልጅ አለኝ አለቻቸው፤ ወደ ቤቷ ይዘዋት ሄዱ፡፡ ልጅዋን ሲያዩ፣ ይለቋታል ስንል፣ ከእነ ልጇ ይዘዋት ተመለሱ፤ ልጇን እዚያው ስታጠባ አደረች፡፡ በነጋታው ግን ሴቶችን መፍታት ጀመሩ፡፡

ወደ ጦላይ ማሰልጠኛ ካምፕ የተወሰዳችሁት በስንተኛው ቀን ነበር?

ማክሰኞ ተያዝን፣ አርብ ቀን ተወሰድን፡፡ ማክሰኞ የተያዘ አለ፣ ረቡዕ የተያዘ፣ ሐሙስም አርብም የተያዘ አለ፡፡ ሁሉም በአንድ ቀን አልተያዘም፡፡ ከተለያየ ቦታ በተለያየ ቀን ነው ያንን ሁሉ ወጣት የያዙት፡፡ ብቻ አልሞላ ብሏቸው መከራቸውን ሲበሉ ነበር፡፡

አልሞላ ብሏቸው ስትል ምን ማለትህ ነው?

እኔ እጃ ከየአካባቢው ኮታ አለ ማለት ነው፡፡ ከእኛ ክፍለ ከተማም ብዙ ነው የያዙት፤ ከቂርቆስ ማለት ነው። እኔ አሁን የተያዝኩት ሳር ቤት አካባቢ ነው፡፡

ጦላይ ማሰልጠኛ ካምፕ ስትገባ ምን ተሰማህ ---- አልፈራህም?

ብዙዎች ፈርተው ነበር፡፡ ኡኡ ብለን እንጩህ፣ ህዝብ ይስማ እንለቀቃለን የሚል ሀሳብም ተነስቶ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ መጠን የመንግስት አስተሳሰብ ይወርዳል ብዬ ስላልገመትኩ፣ በግርምት ነበር የምጓዘው እንጂ አልፈራሁም፡፡ እንደውም ለመጀመሪያ ጊዜ የምኖርበትም የምሞትበትም ምክንያት የሰጡኝ ይመስለኛል፡፡

እንዴት ማለት --- አልገባኝም?

ምን ለማለት ነው? ከዚያ በፊት የምታወሪው በየመንደሩ ነው፡፡ የምታወሪው በመላምት ነው፡፡ ሁሉ ነገር በግምት ነው፡፡ አንደኛ ስለ መንግስት ችግር፣ በሰው ላይ ስለደረሰ ነገር ሳይሆን ያለ ምንም ጥፋት ታፍሼ ስሄድ በራሴ ላይ በደረሰ በደል ነው የማወራው፤ የሆንኩትን ያየሁትን ነው የምናገረው፡፡  

በሌላ በኩል፤ አዋቂም ይሁኑ አይሁኑ፣ ከመንግስት ተወክለው ለመጡ ሰዎች፣ አገሪቱ ላይ ያለውን አጠቃላይ ችግር በቀጥታ ለራሳቸው እንድናገር መድረክ አግኝቻለሁ፡፡ በእርግጥ በፊትም የሚሰማኝን ነገር በማንኛውም ቦታና ሁኔታ የመናገር፣ የመግለፅ ችግር የለብኝም፤ ግን እንደዚህ ለሚመለከተው አካል ፊት ለፊት መናገር ደግሞ ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡

በማሰልጠኛው ውስጥ ሆናችሁ የሚጎበኟችሁ የመንግስት ባለሥልጣናት ነበሩ?

ትልልቅ የምትያቸው የፖሊስ ኮሚሽነሮች በክፍለ ከተማ ደረጃም ከዚያም በላይ ያሉት ይመጡ ነበር፡፡ እንግዲህ ከሰሙን ብዙ ተናግረናል፡

በካምፑ ውስጥ አያያዛችሁ እንዴት ነበር? እስኪ ንረገኝ ---

ስልጠና የጀመርነው ከ10 ወይም ከ11 ቀን በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ጠዋት ለቁርስ ትወጫለሽ፣ ከዚያ ሽንት ቤት ከዚያ ወደ ቤት፡፡ ምሳ ሰዓትም ሆነ ራት ላይ እንደዚያው ነው፡፡ ውሃ ሲመጣ ገላ ለመታጠብ ወይ ልብስ ለማጠብ ብቻ የተወሰነ ሰዓት ትወጫለሽ፤ በቃ!

ቅያሪ ልብስ አልያዛችሁም--- ምኑን ነበር የምታጥቡት? ወይስ ልብስ ሰጧችሁ?

እስከነገርኩሽ ቀን ድረስ ልብስ አልነበረንም፤ ከዚያ በኋላ ከየት እንደመጣ አናውቅም፣ ኖርማል ቱታና ማሊያ ቲ-ሸርት ቁምጣ ሰጡን፡፡ እንደየ እድልሽ ቁምጣም ቱታም ሊደርስሽ ይችላል፡፡ እኔ ቱታ ነበር የደረሰኝ፤ በግድ ልበሱ ተባለ ለበስን፤ 15ኛው ቀን ላይ ብርድ ልብስ ተሰጠን፤ ፍራሽ ላይ ትተኛለሽ፡፡

አመጋገባችሁ ምን ይመስል ነበር? የሰብአዊ መብት ጥሰት?

ምግብ ጠዋት ዳቦ በሻይ፣ ምሳ ዳቦ በወጥ፣ ራት ዳቦ በወጥ፤ አለቀ! ከዚህ ውጭ እንጀራ ምናምን ሌላ ነገር የለም፡፡ ሰብዓዊ መብት ላልሺው፣ እነሱ እንደውም በዋናነት እሱ ርዕስ ላይ ነው ማውራት የሚፈልጉት። መብታችሁን የነካ፣ የሰደባችሁ ካለ ተናገሩ ይላሉ፡፡ የእኔ ጥያቄ ግን ይሄ አይደለም፡፡ 

አውሮፓም ኖሬያለሁ፤ ጫፌን ነክቶኝ የሚያውቅ የለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ጦላይ በዚያ ሁኔታ የተገኘሁት፣ ሰብአዊ መብቴን ተነጥቄ ነው የሚለው ነው፤ ጥያቄዬ፡፡ ለምንድን ነው ከእድሜዬ ላይ አንዲትስ ሰከንድ ብትሆን፣ በሌላ ሰው የሚወሰነው? ነው ጥያቄዬ፡፡ እዚያ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ፤ ብዙዎችም የሚጠየቁ፡፡  

ምግቡ እንዲህ ቢሆን፣ ውሃ እንደዚህ ቢደረግ፣ ብርድ ልብስ ቢሰጠን ሌላም ሌላም ጥያቄዎች … የእኔ ጥያቄ ግን ለምን እዚያ ቦታ ላይ ተገኘሁ ነበር፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ደግሞ ይሄ ይመስለኛል፡፡ የመለሰልኝ ግን አልነበረም፤ ከዕድሜዬ ላይ 30 ቀናት ያለ ፍላጎቴ ተቀንሶ፣ በሰው ቁጥጥር ውስጥ ሆኜ ነው የከረምኩት፡፡ 

ይሄ ያለ ምንም ጥፋትና ወንጀል ሲሆን ደግሞ ያሳምማል፡፡ እርግጥ የሚሰደቡም የሚመቱም ልጆች ነበሩ፡፡ እኔን ማንም ነክቶኝ አያውቅም፤ ሁሌም ለፖሊሶቹ እነግራቸዋለሁ፤ እኔ ትዳር የለኝም፤ ልጅም የባንክ አካውንትም የለኝም፡፡ ያለኝ ስሜና ሰብዕናዬ ብቻ ነው፤ እሱ ላይ አልደራደርም፡፡ ይሄንን አስጠብቄ የወጣሁ ይመስለኛል፡፡

ስልጠናና ትምህርት በሚሰጣችሁ ጊዜ አጥብቀህ ትከራከርና ትሞግታቸው እንደነበር ሰምቻለሁ ለመሆኑ ትምህርትና ስልጠናው ምን ምን ያካተተ ነበር ስለመብት ስለ ህግ የበላይነት ስትሟገትስ የተለየ ጫና አያሳድሩብህም?

ስልጠናው በዋናነት በህገ መንግስቱና በህግ የበላይነት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ አንዳንዱ ትምህርት እንደሚገልፀው ከሆነ፤ እኛ እዚያ ቦታ ላይ መገኘት አልነበረብንም፤ ማለቴ እኛን የሚመለከት አይደለም፡፡ እንደው እንዲህ አሰለጠንን፣ እንዲህ አደረግን ለማለትና ከህገ መንግስትና ከህግ የበላይነት ውጭ የሚያሰለጥኑት ነገር ስለሌለ እንጂ ያንን ስልጠና ለእኛ መስጠት አልነበረባቸውም፡፡ እኔ ይሄንንም አልቀበልም ነበር፡፡  

ምንድነው የምላቸው፤ የሰውን ልጅ በግድ በጉልበት ይዞ አካላዊና ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ይቻል ይሆናል፣ እንዴት አዕምሮውን እናሰለጥናለን ትላላችሁ፣ ያውም ይሄን ያህል የኖረ ሰው፣ በዚያ ላይ ያለ ፍላጎቱ እንዴት ይሆናል? ለመሆኑ ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ታውቁታላችሁ ወይ?--- እላቸው ነበር፡፡ እነሱ ደግሞ ከላይ ታዘን፣ ይህን ለማስተማር ነው የመጣነው፣ ለጥያቄያችሁ መልስ የለንም ይሉናል፡፡  

አንድ ሰው እኔን ሊያስተምር ሲመጣ፣ ማንን ነው የማስተምረው፣ አቅሙ ምን ያህል ነው ማለትና እኔን ማወቅ አለበት፡፡ ህይወት አጭር ነው፤ ትምህርት ሰፊ ነው፤ እኔ 1ኛ ክፍልን 12 ዓመት መማር የለብኝም፤ በአንድ አመት ጨርሼ ወደ ቀጣዩ ትምህርት ማለፍ አለብኝ፡፡ ይህቺ አገርም እኔም መማርና መለወጥ ካለብን፣ በማይረባ ነገር ጊዜ ገንዘብና ጉልበት መባከን የለበትም፡፡ 

ይሄን እላለሁ እጠይቃለሁ፣ እሟገታለሁ። የሚገባቸው ፖሊሶች ሀሳቤን ይረዳሉ፣ ያልገባቸው ደግሞ አንተ ምንድነው እዚህም እዛም የምትናከሰው ይላሉ፡፡ ከዚህ ያለፈ ግን የተለየ ጫናም ድብደባም ስድም ደርሶብኝ አያውቅም፡፡

ገና ስትወሰዱ በምን ጥፋት ተከሰሳችሁ?

ምንም ዓይነት ክስ አልነበረም፡፡ የብዙዎች ፍርሃትም በምን እንከሰስ ይሆን የሚለው ነበር፡፡ እንደውም ወደ ጦላይ የተጋዘው ሰው አንዱ የተነጠቀው መብት ይሄ ነበር፡፡ ከሳሹንም በምን እንደተከሰስም አያውቅም ነበር፡፡ ልንለለቅ ሶስት ወይም አራት ቀን ሲቀረን፣ መርማሪዎች መጥተው የክስ ቻርጅ አቀረቡ። በሶስት ወንጀል ክስ አለባችሁ አሉን፡፡

ምን ምን ነበሩ ሶስቱ ክሶች?

አንዱ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት የሚያንፀባርቀውን፣ አርማ ያለውን ባንዲራ ትታችሁ አርማ የሌለውን ይዛችኋል ይላል፡፡ ይሄ ማንንም የሚያስቅ ነው፡፡ ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለበት ነበር፣ አገር ምድሩ አርማ የሌለው ባንዲራ በየአካባቢው፣ በየሰላማዊ ሰልፉ፣ በየአደባባዩ ሲጠቀም የነበረው፡፡  

ሁለተኛው ህዝባዊና መንግስታዊ ተቋማትን በኃይል በማፍረስና በማውደም እንዲሁም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እሰጥ አገባ በመፍጠርና ሁከት በመቀስቀስ ይላል። ይሄ ለእኔ ድራማ ነው፡፡ መጀመሪያ ክስ ይመጣብናል ብለን ያሰብነው ከሺሻ ቤት ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ የጦላይ ወሬ ሲነሳ በሺሻ ቤት እንዳልሆነ ገባን፡፡ ከመካከላችን ነፍሰ ገዳይ፣ አስገድዶ ደፋሪም --- የለም፡፡ ፍርድ ቤት ሳንቀርብ ከህግ አግባብ ውጭ ነው የቆየነው፡፡

ቤተሰብ ይጠይቃችሁ ነበር? በስልክ በፌስቡክ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ትገናኙ ነበር? ቴሌቪዥንስ ማየት ይፈቀዳል?

በፍፁም! ቤተሰብ መጥቶ ሳያየን ተመልሷል፤ ስልክም ኢንተርኔትም -- አልነበረም፡፡ ቴሌቪዥንም አይተን አናውቅም፡፡ ምንም ዓይነት መረጃ ከማንም ጋር ተለዋውጠን አናውቅም፡፡

ታዲያ ከምን ተነስታችሁ ነው “ስለ እኛ በፌስ ቡክና በተለያዩ መንገዶች የሚነገረው እኛን አይወክልም” የሚል የአቋም መግለጫ አውጥታችሁ በቴሌቪዥን የተላለፈው?

ይሄን ስንሰማ አብረን ነው የሳቅነው፡፡ እኔ በበኩሌ እዚህች አዲስ አበባ እስክደርስ ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ ከጦላይ መጥተን አዲስ አበባ ስንደርስ አንዳንድ ፖሊሶች ስልክ ለቤተሰብ እንድንደውል ተባብረውናል፡፡ 

የአቋም መግለጫው በጣም ያስቃል፤ በፌስ ቡክ የሚወራው እኛን አይወክልም ብቻ አይደለም፣ የተከሰስንባቸው ቀደም ብዬ የነገርኩሽ ጉዳዮች አሉ አይደለ መንግስት አልተሳሳተም፣ መታደስ ያለባቸውን ልጆች ነው የያዘው፣ በትክክል አድሷል፣ ተፀፅተን ህብረተሰቡን ለመካስ ነው የመጣነው ምናምን ይላል …. ይሄ እስካሁን በጣም በጣም ያስቀኛል፡፡

ይሄን ነገር ስትሰማ አልተቃወምክም?

ሲነበብ ሳይሆን ገና ሲፃፍ ጀምሮ ነው የተቃወምኩት። እኔ አወያይ ነበርኩኝ፡፡ የሄድነው ከ1270 በላይ ነን፡፡ በሶስት ሻምበል ተከፍለናል፡፡ አንድ ሻምበል 320 ገደማ ታራሚዎችን ይይዛል፡፡ የዚያ ሻምበል አወያይ ነበርኩኝ፡፡ ስለምናገር እኔን መረጡኝ፡፡

አንድ ቀን አስተምረውን ሲጨርሱ ጥያቄ ካላችሁ ሲሉ እጄን አወጣሁና፣ እኔ እዚህ ቦታ ላይ እንደ ሰብሰዊ ፍጡር ከተቆጠርኩ መብቴን ጠብቁ፤ ስትፈልጉ የምታነሱኝ ስትፈልጉ የምትጥሉኝ አይነት ድንጋይ አድርጋችሁ ካሰባችሁኝ ተሳስታችኋል፡፡ ከአገርና ከመንግስት አለመረጋጋት አንፃር፣ እስከሆነች ቀን እጠብቃችኋለሁ፡፡ 

ከዚያ አልፋችሁ ያለ ጥፋቴ እዚህ የምታስቀምጡኝና ጊዜዬን የምታባክኑ ከሆነ፣ በግሌ ማንንም ሳልወክል እርምጃ እወስዳለሁ፤ ቢያንስ ያለ ጥፋቴ ልታስቀምጡኝ እንደማትችሉ ለማሳየት ራሴን አጠፋለሁ፡፡ ምን እንዳጠፋሁ ማን እንደከሰሰኝ፣ ለምን እንደተከሰስኩ የማወቅ መብት አለኝ፡፡ 

የአገሪቱን ህግ አክብሬ የትኛውም ቦታ የመኖር መብት አለኝ ስላቸው፤ ይሄው ግቢው ውስጥ ከዚህ እስከዚህ እንድትንቀሳቀሱ ፈቀድንላችሁ ይሉኛል፤ አንተ ማን ስለሆንክ ነው የምትፈቅድልኝ? እንኳን እዚህ በየትኛውም አለም ተዘዋውሬ እንድኖር ነው የተፈጠርኩት፤ ይህን የማታውቁና የማታከብሩ ከሆነ ራሴን በማጥፋት መብቴን አሳያለሁ እንጂ ለወራት እዚህ አልታሽም አልኳቸው፡፡  

ከዚህ ንግግር በኋላ ስብሰባዎች ተደረጉ፤ ስልጠና መቼ እንደምንጀምር ተነገረን፡፡ እዛ ሻምበል ውስጥ ታውቄ ነው አወያይ የሆንኩት፡፡ ጠዋት ጠዋት እንማራለን፤ከሰዓት እኔና ሄኖክ የሚባል ልጅ አወያይተን ያንን ስልጠና ምን ያህል ተረድተውታል፣ ምን ያህሉ ተቃውመውታል የሚለውን እናቀርባለን፡፡ 

ትምህርቱ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ አንድ ጀምረሽ እስከ መጨረሻው፣ ከዚያ ስለ ሰብአዊ መብት ነው የምንማር የነበረው፡፡ በእነሱ ቤት ህገ መንግስት፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብት የማናውቅ መሃይሞች ተደርገን ነበር የምንታየው፡፡ ይሄ እንዳልሆነ እንዲገባቸው እንነግራቸው ነበር፡፡ ዝምታ በብዙ ነገር ይጎዳል፡፡ 

ለምሳሌ ምርጫ ሲመጣ በቀበሌ በክ/ከተማ የእኔ ድምፅ ተቆጠረ አልተቆጠረ ብለን ዝም ስንል ነው ያልመረጥናቸው ተሹመው መከራ የሚያበሉን፤ ቢያንስ የእኔ ድምፅ ለምደግፈው ለአንድ እጩ ቢሰጥ የማልፈልገው ሰው እንዳይመረጥ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ዝምታ እንደሚጎዳ ስለማውቅ፣ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ሀሳቤን እገልፅ ነበር፡፡

በጦላይ ቆይታህ ምን የተማርከው ነገር አለ?

እንግዲህ ትምህርት ሂደት ነው እንጂ አንድ ቦታ የሚቆም አይደለም፡፡ ከዚህ ቆይታዬ አልተማርኩም ማለት ተፈጥሮን መካድ ነው፡፡ በጦላይ ቆይታዬ ያለ ፍላጎት አንድ ቦታ መታገት ምን ማለት እንደሆነ፣ያንንም እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ፡፡ ብዙ ጓደኞች ከፖሊሶችም ከታሳሪዎችም በኩል አፍርቻለሁ፡፡ 

ብዙ ሰዎች አውቀውኛል፡፡ የሚመለከታቸው ለሚመስሉ አካላት ሀሳቤን አንፀባርቄያለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝብና መንግስት ማን እንደሆኑ በደንብ አውቄያለሁ። ከሚዲያ የምትሰሚው ነገር ሁሉ ሃቅ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የመንግስትም የግልም የምትያቸው ሚዲያዎች ውሸታሞች ናቸው፡፡

ከምን ተነስተህ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስከው?

ለምን እንደዛ እንዳልኩ ልንገርሽ፡፡ ብዙ ሰው እኔ የመንግስት ተቃዋሚ እንደሆንኩ ነው የሚያስበው። እኔ ግን ትክክለኛ ያልሆነ ሀሳብ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ ለምሳሌ አፍንጫሽ አያምርም ብዬ፣ አይንሽ ቆንጆ ነው ብል ምንድነው ችግሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰው ከጠላ ጠላ ነው፣ ከወደደም በጭፍን ነው የሚወደው፡፡ 

እኔ ይሄን ዓይነት የመንጋ አስተሳሰብ አልቀበልም፡፡ አሁን ጦላይ እያለን ዶ/ር ዐቢይን ላለመኮነንና ላለመጥላት ምን ይላሉ መሰለሽ … “ዶ/ር ዐቢይ እኛ መታሰራችንን አያውቅም፤ ቢያውቅ ያስለቅቀን ነበር” የሚሉ የዋሆች አሉ፡፡ “በዐቢይ ጊዜ የለም ትካዜ” ሲሉ፣ እኔ ደግሞ “በጃንሆይ ጊዜ ነው እንዴ እዚህ ተክዛችሁ ያላችሁት” እላቸዋለሁ፡፡ ይሄ አስተሳሰብ የሚዲያዎች ተፅዕኖ ነው፡፡  

የመንግስት ሚዲያዎች፤ መንግስት ምንም እከን እንደሌለው አድርገው ያቀርቡልሻል፡፡ አንዳንድ የግል ሚዲያ ደግሞ ስለ መንግስት ጥላቻና ማንቋሸሽ በቀር አንዷን ጥሩ የሰራትን እንኳን ገልፀው፣ 99ኙን ስህተቱን አይነግሩሽም፡፡ ድሮ ተገነባ ተመረቀ ለምቷል ሲልሽ የከረመ የመንግስት ጋዜጠኛ፤አንድ የፈረሰ ነገር እንዳለ ሳይነግርሽ፣ ታደሱ ታድሰናል ይልሻል፡፡ 

ታዲያ ህዝቡ በጭፍን ቢወድና በጭፍን ቢጠላ እንዴት ይፈረድበታል፡፡ መሃሉን ይዞ በሀቅ ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ ሚዲያ በሌለበት ሁኔታ አስተሳሰብ እንዴት ይቀናል፡፡

አዲስ አድማስ ጋዜጣ (Nafkot Yoseph)

No comments