Latest

የሶማሌ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል – ፖሊስ


(ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት መስኮት ሰብረው ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ሲል ፖሊስ ገለጸ።

አቶ አብዲ መሐመድ ከሐምሌ 26 ቀን እስከ ሃምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ፥ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

አቶ አብዲ ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀጠሮ ችሎት በቀረቡበት ወቅት፥ ለደህንነታቸውና ለጤናቸው ሲባል የፖሊስ ቢሮ ውስጥ ታስረው መቆየታቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ይሁንና አቶ አብዲ የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና አንድ የጥበቃ አባልን ጉሮሮ በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ብሏል ፖሊስ በማብራሪያው።

አቶ አብዲ መሐመድ በበኩላቸው ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን በመጥቀስ፥ ሆን ተብሎ ስሜን ለማጥፋትና እኔን ለመምታት የተደረገ ሴራ ነው ብለዋል።

ድርጊቱን ፈጽመዋል መባሉ ውሸት መሆኑንና በእርሳቸው ላይም ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

ምቹ ባልሆነ እስር ቤት መታሰራቸውን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነ ታሳሪ የታሰሩበትን ክፍል በር ገንጥሎ በመግባት ሁለት ቀን ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሞከረና ይህም  
በደህንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል።

በአንድ አጋጣሚም አንድ እስረኛ የሽንት ቤት በር ገንጥሎ እሳቸው ላይ በመጣል ጉዳት ሊያደርስ መሞከሩንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

የታሰሩበት እስር ቤትም የማይመችና በጤናቸው ላይ እክል እንደፈጠረባቸውም ነው አቶ አብዲ የተናገሩት።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አቶ አብዲ መሐመድ ማንኛውም እስረኛ በሚቆይበት እስር ቤት እንደታሰሩ ጠቅሶ፥ በእርሳቸው ላይ ምንም አይነት ጫና አለመደረጉን ገልጿል።

በተጨማሪም ፖሊስ ከእርሳቸው ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ለግጭቱ መቀስቀስ ተጠያቂ መሆናቸውንና በዚህም ተጸጽተው ይቅርታ መጠየቃቸውንም አስረድቷል።

ፖሊስ በአብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም ምርመራውን እያካሄደ ያለው ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ በማሳሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

No comments