Latest

ስለ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጥቂቱ - ቢቢሲ

ስለ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጥቂቱ - ቢቢሲ

1997 ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ ሃገር አቀፍ ምርጫ ቅንጅት ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲን ወክለው የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው መመረጥ ችለዋል ነበር። ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ለእሥር ተዳረጉ፤ ለጥቆም ስደት።

የአርበኞች ግንቦት 7 ፓርቲ ዋና ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከ11 ዓመታት የስደት ሕይወት በኋላ ጵጉሜ 4/2010 ወደሃገራቸው ተመልሰዋል።

ለመሆኑ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ማን ናቸው?
ከአዲስ አበባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ እትብታቸው የተቀበረው ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያገኙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው።

በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ የወቅቱን ወታደራዊ አገዛዝ (ደርግ) በፅኑ በመቃወምም ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) በግልፅ ነቅፈዋል በሚል ክስ ለወራት ከታሠሩ በኋላ ወደ ሱዳን አመሩ፤ እዚያም ለሁለት ዓመት ያክል ቆይተው የጥገኝት ጥያቄያቸውን ወደ ተቀበለችው አሜሪካ አመሩ።

እዚያም 'ከስቴት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒው ዮርክ' በኢኮኖሚክስ ትምህርት ድግሪ አገኙ፤ 'ኒው ስኩል ፎር ሶሻል ሪሰርች' ከተሰኘው ተቋም ደግሞ የዶክትሬት ድግሪያቸውን በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ማግኘት ቻሉ።

ከዚያ ቀጥሎ ባክኔል ዩኒቨርሲተን በመቀላቀል ኢኮኖሚክስ ትምህርት ለሶስት ዓመታት አስተማሩ።


ወደ ሃገር ቤት
በ1986 ዓ.ም. ብርሃኑ (ፕ/ር) ባለቤታቸው ዶ/ር ናርዶስ ምናሴ፣ ኖህ ብርሃኑ እና እያሱ ብርሃኑ የተሰኙ ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ሃገር ቤት የተመለሱት።

የንግዱን ዓለም በመቀላቀልም የማዳበሪያ ፍብሪካ አቋቁመው መሥራት ያዙ፤ ጎን ለጎን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማራቸውን ተያያዙት።

ፕ/ር ብርሃኑ ሲነሱ ሁሌም አብሯቸው ከሚጠቀሱ ክስተቶች መካከል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማሕበር አንዱ ነው።

በእርሳቸው መሪነት የተቋቋመውን ይህን ማህበር ከ1988 - 92 ድረስ በፕሬዚዳንትነት መርተውታል።

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥም በአማካሪነት ይሠሩ ነበር፤ ፕ/ር ብርሃኑ።


መጋቢት 30፤ 1993 ዓ.ም. ፕ/ር ብርሃኑ እና ፕ/ር መሥፍን ወልደማርያም በብሐራዊ ሎተሪ አዳራሽ የትምህርት ዓለም ነፃነትን በተመለከተ አንድ ቀን የፈጀ ውይይት አካሄዱ።

በቀጣዩ ቀን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባነሱት ግርግር ተናጠች፤ ምሁራኑም ለዚህ ግርግር መነሾ ናቹ በሚል ለእሥር ተዳረጉ፤ ከቀናት በኋላም ተፈቱ።
ምርጫ 1997
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ በጉልህ ተፅፎ ባለፈው ምርጫ 97 ላይ ከፍተኛ ተሣትፎ የነበራቸው ፕ/ር ብርሃኑ ፓርቲያቸው ቅንጅት ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ወክለው ቅስቀሳ መካሄድ ተያያዙ።

ከወቅቱ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋርም ፊት ለፊት ክርክር አካሄዱ፤ ከ138 የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መቀመጫዎች 137 በማግኘት ፓርቲያቸው መዲናዋን መቆጣጠር ቻለ።

ፕ/ር ብርሃኑም አዲስ አበባን በከንቲባነት እንዲያስተዳድሩ በፓርቲያቸው ተመረጡ፤ ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ምክትል ከንቲባ፤ አሰፋ ሃብተወልድ ደግሞ አፈ ጉባዔ በመሆን ተሾሙ።

ነገር ግን ምርጫውን ተከትሎ የተነሳው ግርግር ፕ/ር ብርሃኑ ለእሥር እንዲዳረጉ ምክንያት ሆነ።

ፕሮፌሰሩ ብቻ ሳይሆኑ የፓርቲ አጋሮቻቸው፤ በርካታ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችም ለአሥር እንዲዳረጉ ሆነ።

ፕ/ር ብርሃኑ 'የነፃነት ጎህ ሲቀድ' የተሰኘውን መፅሐፋቸውን የፃፉት ቃሊቲ ሳሉ ነበር፤ መፅሐፉ በኡጋንዳ ከተማ ካምፓላ 1998 ላይ ሊታተም ችሏል።
ድህረ ቃሊቲ
ፕ/ር ብርሃኑ ለ21 ወራት ያክል እሥር ላይ ከቆዩ በኋላ 1999 ላይ ወደ አሜሪካ በመመለስ በክኔል ዩኒቨርሲቲ ማስተማራቸውን ቀጠሉ።

አሜሪካ ሳሉም ግንቦት 7 የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋማቸውን፤ ፓርቲው በተገኘው አማራጭ ሁላ ሥርዓቱን በመቋቋም ለውጥ ለማምጣት እንደሚጥርም ይፋ አደረጉ።

ሚያዝያ 16፤ 2001 ዓ.ም.፤ ኢህአዴግ ግንቦት 7 መፈንቅለ መንግሥተ ሊያካሂድ ቢሞክርም አክሽፊያለሁ ሲል አስታወቀ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም 35 ሰዎች ለእስር ተዳረጉ።

በዚያው ዓመት የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሌሉበት የሞት ብይን ወሰነባቸው፤ ከእርሳቸው ጋር ሌሎች 4 ግለሰቦች በሌሉበት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ሲሆን 33 ግለሰቦች ደግሞ የዕድሜ ልክ እሥራት ሰለባ ሆኑ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ 2007 ላይ ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከበክኔል ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ።

በተመሳሳይ ዓመት ወርሃ ሐምሌ ላይ ፕሮፌሰሩ ወደ ኤርትራ በማቅናት መሬት ላይ ያሉ የፓርቲው 'የናፃነት ታጋዮችን' በይፋ መቀላቀላቸውን አስታወቁ።

በፈረንጆቹ 2016 መባቻ ላይ ግን የፓርቲውን ደጋፊዎች ለማበረታታትና የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ወደ አሜሪካ መመለሳቸውን አሳወቁ።

የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፓርቲ ግንቦት 7 በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ትጥቅ በመፍታት ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ እንዳሰበ ያሳወቀው በቅርቡ ነበር።

ግዜው ደርሶም ፕሮፌሰሩን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከዓመታት የውጭ ሃገራት ቆይታ በኋላ ጳጉሜ 4/2010 ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል።

No comments