Latest

በፅኑ ታመናል!! እሸቱ ታደሰ

በፅኑ ታመናል!! እሸቱ ታደሰ

በዚህ ዓለም ጥድፊያ እጅጉን ታመናል። ፀንተን መቆም ተስኖናል። ግብዝነታችን መጠን የለውም፣ ዘመናችንን በምልልስና በመዋተት ሞልተነዋል ምን እንደምንፈልግ እንኳን አናውቅም።

በዚህም ምክንያት ፍለጋችን አላለቀም። በአፍላ እንጀምራለን፣ በወረት እንተወዋለን፤ ያወቅነውን እንረሳለን ያላወቅነውን ለማወቅ እንጥራለን፤ የያዝነውን እንረግጣለን፣ የረገጥነውን እንይዛለን።

ምኞታችን ልክ የለውም፣ አምሮታችን ብዙ ነው። ያማረንን ስናገኝ ወዲያው እንሰላቻለን። ተው የተባልነውን እንሽራለን፣ የተከለከልነውን እንደፍራለን፤ የተፈቀደልንን ችላ እንላለን። ሁሉን ማወቅ እንፈልጋለን በአንዱም ግን አንጠቀምም።

ሁሉ አለን ግን ባዷችንን ነን ። ሃይማኖት እንጂ እምነት የለንም። አባቶቻችን ጥበብን ሃ…ለ ብለው ለማስተማር ቢምክሩ መንደር ውስጥ በቃረምናት እውቀት ተመክተን በመሰልቸት ፕ...ፖ ብለን ቀድመን እንዘጋባቸዋለን።

የግል ታሪካችን ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተልከፈከፈ የተማሪ ኮፋዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል። ተምረን እውቀት ስናገኝ፣ ሰርተን ሃብት ስናፈራ ከላይ የሆንበትን ሃገር ለቀን ሰፋ ወዳለው እንሂድ ብለን እንደገና ከታች እንጀምራለን።

በመጨረሻም ከጀመርንበት እንገኛለን። ቸኩለን እንወስናለን ወዲያው እንፀፀታለን። ከታሪክ ፍቅርንና ልማትን ሳይሆን ጥላቻንና ጥፋትን ለይተን እንቆፍራለን። ከዚያም የከበረ ማዕድን ቆፍረን እንዳወጣን ሁሉ በኩራት ደረታችንን ነፍተን ሳንመርጥ ሁሉን በአደባባይ እንዘራዋለን።

ለግልፅነት ና ለነፃነት እያለን በምናደርገው ሽኩቻ እርቃን ወደመሆን ወርደናል። በዚህም የተነሳ ሃገር ለመቀበል የሚያስችል ስብዕናን አልገነባንም። ለዚህም እንደምክንያት የምናቀርበው "አባቶቻችን በኛና በእነርሱ መሃል የመገናኛ ድልድይ ስላልሰሩ ነው" የሚል ነው።

ግን በፍፁም አይደለም፤ አባቶች የመገናኛውን ድልድይ ስላልሰሩትና ስለራቁን ሳይሆን ስለማናየው ወይም ማየት ስለማንፈልግ አለበለዚያም እንደልቦለድ ገፀባህሪይ የራሳችንን ያሸበረቀ ምናብ ፈጥረን እውኑን ሳይሆን ምናባችንን መያዝ ፈልገን ስለምናጣው ነው።

አባቶች ደግሞ እኛ እናያቸው ዘንድ አላሸበረቁም ማሸብረቅም አይፈልጉም። የኛ አባቶች አባቶቻቸውን ያምናሉ፣ በነርሱም ደስተኞች ናቸው። የተነገራቸውን ሰምተው ቃል ኪዳኖቻቸውን ጠብቀው ይኖራሉ።

ለዚህም ማሳያ ፅላተ ሙሴ አክሱም ፂዮን እንዳለ ሲነግሯቸው መጋረጃ ገልጠው፣ ሳጥን ከፍተው እንይ አላሉም። ጌታ የተሰቀለበት ግማደ መስቀሉ ክፋይ ግሽን ማርያም አለ ሲሏቸው ቆፍረን አውጥተን እንመልከት አላሉም።

አባቶቻቸውን አምነው፣ ሃገራቸው የበረከት ምድር መሆኗን ተረድተው፣ የጌታቸውን የፀጋ ስጦታ ተቀብለው በእምነት ይኖራሉ። ምንም የላቸውም ግን ሁሉ የእነርሱ ነው። ድሆች ቢባሉም ባለጠጎች ናቸው። የተራቆቱ ቢመስሉም የፀጋ ልብስ አላቸው። ሃዘንተኞች ቢመስሉም ደስተኞች ናቸው።

ስለኢትዮጵያ መባረክ ቅድስት ሃገር መሆኗን ቅዱስ ቅርሳናት በእጃቸው መሆኑን አለም እንዲያረጋግጥላቸው አይፈልጉም። የሌላቸውን አለን ያልተሰጣቸውን ተቀበልን ብለው የሚ ኮፈሱ ግብዞች አይደሉም።

እኛ ደግሞ ፍለጋችን የማያልቀው የዚህ ትውልድ አካሎች ነን። የምንፈልገውን ብናገኝም አናምንም። የምንፈልገው እራሱ ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለን? እንላለን። እራሳችንና የራሳችንን እውነት የምናረጋግጠው በምዕራቡ ዓለም መለኪያ ብቻ ነውና።

መምሰል መሆን አይደለም፤ መሆንም መምሰልን መምሰል የለበትም፡፡ ለመሟላት እንደግ፤ የጎደለውን ለመሙላት እንትጋ፤ የሚጠቅመውን እንመልከት፤ የሚበጀውን እንመስርት።

No comments