Latest

ትግራይ – የኢትዮጵያ ሰሜን ኮርያ (ነፃነት ዘለቀ)

ትግራይ – የኢትዮጵያ ሰሜን ኮርያ

በአንድ “ፌዴራል” ሥርዓት ሥር በሚተዳደሩ ክልሎች መካከል ትግራይን እንደፈሳች ዝንጀሮ ተገልላ በባዕድነት እንድትኖር እያደረጉ ያሉ አኩራፊዎች አንድ ካልተባሉ ማለትም ሽማግሌ ተገኝቶ ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ ካልተደረገ አካሄዳችን ግንጥል ጌጥ እንደሆነ መቀጠሉ ነው፡፡  


የትግራይ ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ መደሰትም ሆነ መሰቃየት እንደማይገባው የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ እንደሀገር ሁላችንም የጋራ የሆነ የአሁንና መፃዒ ዕድል ያለን አንድ ሕዝብ ነንና በነዚህ ጥቂት “ጥቅማችንና ሥልጣናችን፣ የበላይነታችንና አዛዥ-ናዛዥነታችን ተነካብን” ባሉ ወገኖች ምክንያት የአንድ ክፍለ ሀገር ሲሶ የሚሆን ሕዝብ መቸገር የለበትም፡፡

“ሲሶ” ያልኩበት ምክንያት ለብልኆች ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በትግራይ ውስጥ ከሚኖረው ትግራዋይ ይልቅ በቀሪው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖረው ትግራዋይ የሚበልጥ መሆኑን በእግረ መንገድ ለመጠቆም ነው እንዲህ ማለቴ፡፡

ይህ አዲሱ የሕዝብ አሰፋፈር እውነት ስለመሆኑ ጥናት የማያሻው ታላቁ የዘመናችን ሰው-ሠራሽ ክስተት ነው፡፡ የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ልጓም ለመቆጣጠር ከተፈለገ ደግሞ ወያኔው ያደረገው የዘረኝነት አካሄድ አማራጭ የሌለው የራስን ጥቅምና ፍላጎት የማስከበሪያ መንገድ ነው፡፡

ከዚህ ነባራዊ የነገሮች አካሄድ ተነስተን አንድ ሃቅ መናገር እንችላለን፡፡ እሱም ተጋሩ በሙሉ ኃይላቸው በመላዋ ኢትዮጵያ ተሰራጭተውና ሀብት ንብረት አፍርተው የሚኖሩ መሆናቸው ለወያኔዎች ነባር የግንጠላ ዕቅድ እውን መሆን የሚያስቸግር መሆኑ ነው፡፡ 

ያላሰቡት ሁሉ ሆኖ ያልጠበቁት በመድረሱ ምክንያት ወያኔዎች ሳይጨነቁ አልቀሩም፡፡ ሕዝብና ህንፃ ከተከዜ ወዲህ፣ የግንጠላ ሃሳብና “የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፓፕሊክ” ምሥረታ ቅዠት ከተከዜ ወዲያ ሆኖባቸው የተቸገሩ ይመስላሉ፡፡ 

አዲስ አበባ መቀሌ እስክትመሰል ድረስ፣ መቀሌ በሰው ድርቅ ምች ተመትታ ከፎቅና ከመንገድ ውጪ ባድማ እስክትሆን ድረስ፣ የፌዴራልም ሆነ የአንዳንድ ክልሎች የመንግሥት መ/ቤቶች ካለ ትግሬ መቅጠር የሚያስቀጣቸው እስኪመስሉ ድረስ በተጋሩ ተሞልተው ባሉበት ሁኔታ ትግራይን መገንጠል ለነሱም ፍቺ-አልባ ዕንቆቅልሽ ሆኖባቸው ሳይቸገሩ አልቀሩም፡፡  

በጥቅሉ ትግራይን መገንጠል አስቸግሯቸው እንዲህ በኩርፊያ መሰል ፖለቲካ እየተናጡ በሚያሳዝን ሁኔታ ሊገኙ ችለዋል፡፡

ትግራይ ውስጥ የነዶ/ር ዐቢይን ምስል መኪና ላይም ይሁን ግድግዳ ላይ መለጠፍ እንደሚያስቀጣ ይነገራል – ነውረኞች ናቸው፡፡ በሀገራችን የመጣውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከማውገዝና ከመቃወም በስተቀር መደገፍ ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ብሃፂሩ ትግራይ የኢትዮጵያ ሰሜን ኮርያ ሆናለች፡፡  

ትግራይ የአፍሪካ ቀንድ አልባንያ ሆናለች፡፡ የአሁኗ ሰሜን ኮርያና የቀድሞዋ አልባንያ የሕዝቦቹ እስትንፋስ በመንግሥቶቻቸው የርቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ አማካይነት ሲፈቀድ የሚለቀቅ ሳይፈቀድ የሚታገድ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በትግራይም በተመሳሳይ ሁኔታ ሕወሓትን ከመደገፍ ውጪ ምንም ዓይነት ሌላ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ዕግድ ነው – ይህን ሕወሓታዊ ቀኖና መተላለፍ በእሳት እንደመጫወት ነው፡፡

የማይቀጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል፡፡ ወያኔም የለመደው ፈላጭ ቆራጭነት ስለቀረበት፣ አንዱን አሽከር ሌላውን ገረድ አድርጎ እንዳሻው እንደከብት መንዳትና አሽቆጥቁጦ መግዛት ስላልተቻለው፣ የጠላውን የሕዝብ ክፍል እንደፈለገው እያኮላሸና እየገረፈ ቀጥቅጦ መግዛት ስላልሆነለት፣ አንዱን ጎሣ ከሌላው እያጋጨ ዕድሜውን ማርዘሙ ስላልተሳካለት … በ“ለምን ተደፈርኩ!” የጀብደኝነት ስሜት ተውጦ አንድን ሕዝብም በመያዣነት ይዞ ትግራይ ውስጥ መሽጓል፡፡ መጨረሻው ያጓጓል፡፡ የሚገርም የነገሮች ሂደት፡፡

ትግራይ ቴሌቪዥን ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ከወጣ ሰነበተ፡፡ በመሀል አገር የሚከናወኑ አወንታዊ ነገሮች በዚህ ቲቪ አይዘገቡም፡፡ የኢትዮጵያውያን የደስታ ምንጭ ለትግራይ ክልል የሀዘን መንስኤ የሆኑ ያህል በኢትዮጵያ የሚደረጉ አበረታች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በዚህ ጣቢያ እንደስጋት ስለሚቆጠሩ ይመስላል በዜና ሆነ በሀተታ መልክ አይቀርቡም፡፡ ወያኔዎች ትግራይን ወዴት እየወሰዷት እንደሆነ በአግራሞት እየተከታተልኩ ነኝ – በበኩለይ፡፡ ሀፍረት ብሎ ነገር መቼም አልፈጠረባቸውም፡፡

የሚገርመው ሌላው ነገር “ እኛ ሕወሓቶች ኢትዮጵያን እየቀጠቀጥንና እየጨፈጨፍን ካልገዛናት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም” ብለው መማማላቸው ነው፡፡ ምን ዓይነት ድፍን ቅል እንደሆኑ ሳስበው ሁሌም ይደንቀኛል፡፡ ነገን የማያስቡ ድንጋይ ራሶች ናቸው፡፡

ይህችን ማስታወሻ እየጻፍኩ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ስለአቶ በረከት የሰጡትን ገለጻ በሠይፉ ፋንታሁን የሬዲዮ ዝግጅት ከዩቲዩብ እያዳመጥኩ ነው፡፡ ጠንካራ ጎኑን በተመለከተ አቶ ንጉሡ ይናገራሉ፡፡ እኔ ግን የበረከት እጅግ ብዙ ጠንጋራ ጎን እንጂ ሚዛን ደፍቶ በአደባባይ ሊጠቀስ የሚችል ጠንካራ ጎን ብሎ ነገር የለውም እላለሁ፡፡  

አማራን ለማጥፋት ተብሎ በአማራ ስም ተመልምሎ ላለፉት 30 ዓመታት ሀገር ያጠፋ ሰው መጽሐፍ አነበበ አላነበበ፣ የሚሰጣቸው ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ማራኪና አሳማኝ ሆኑ አልሆኑ፣ ሥልጠና አሰጣጡ ውብ ሆነ አልሆነ… አንዴ ለጥፋት የተፈጠረ ዲያብሎስ መልካም ነገር ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በዕውቀት እኮ ሰይጣንም ከተራው የመላእክት ሠራዊት የተሻለ ነበር፡፡

ለማንኛውም ብአዴን ወደ ቀናይቱ መንገድ መግባትና አማራንና ኢትዮጵያን ከተደገሰላቸው ሕወሓታዊ ጥፋት መታደግ ከፈለገ ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ ነው፡፡ እነበረከትን ለማጽዳት ደግሞ ከሰማይ በታች ያሉ ምክንያቶች ሁሉ በብአዴን እጅ ውስጥ ናቸው፡፡ 

በመጀመሪያ ደረጃ የወያኔ ፖለቲካ መሠረቱ ዘር በመሆኑ እነበረከት በአማራ ስም የአማራን ሥልጣን መያዝ ይቅርና በአማራው መሬት ለመኖር ራሱ ከብአዴን ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል – አስቂኙና አስገራሚው ድራማ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፡፡  

በረከት በአማራ ስም ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን መሆን ይቅርና በተራ አባልነትም የመመዝገብ መብት የለውም – ውልደት፣ ዕድገት፣ ሥነ ልቦና ምናምን ሌላ ነገር ነው፤ “እባብ የወጣበትን ጉድጓድ አይስትም” እያለ የሚተርት ሕዝብ የበረከትን “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ”ን እስስታዊ ተፈጥሮ ለመገንዘብ የሚቸገር አይመስለኝም፡፡  

ይህ ሃቅ በራሱ ወንጀለኞቹን በረከትንና ቢጤዎቹን ከአማራ ክልል በአንድ ጀምበር የሚያስወጣ ወያኔያዊ የዘር መሥፈርት ነው፡፡ ስለዚህ ሌላ ሰበብ ሳያስፈልግ ብአዴን እነዚህን የሕወሓት ትክል መዥገሮችና የአማራ ጠላቶች በዚህ ምክንያት ብቻ መንጥሮ አማራውን በአንድ ቀን አዳር ከተጫነበት የወያኔ ቀምበር ነፃ ማውጣት ይችላል፡፡  

ሌላ ምክንያት መደርደርም ሆነ እነበረከትን እያንቆለጳጰሱ መለማመጥ አያሻም፡፡ ለወያኔ ቅንጣት የማንሰራሪያ ዕድል መስጠት ብልጭ ያለችውን የነፃነት ጮራ እንደማጥፋት ነውና ከእንግዲህ ሁሉም ይወቅበት፡፡ ወያኔዎችን መለማጥ ራሱ መቆም አለበት፡፡ በማን እንደሚብስ ግምቴን መናገር እችላለሁ፡፡ 

የሠሩት ግፍና በደል የፈጠረው ሰማያዊ ጥቀርሻ ማን ላይ እንደሚራገፍ ለማንም የታሪክንና የፈጣሪን ሞራ አንባቢ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም በነሱ ብሶ ወደፍቅርና ሰላም ማዕድ ለመምጣት የሚግደረደሩና የሚያፈገፍጉ ከሆነ ዕዳው የነሱና እነሱ እንወክለዋለን ለሚሉ ወገኖች ነው፡፡ የኛን ዕዳ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ከነወለዱ አሳምረን ከፍለን ጨርሰናልና ከእንግዲህ የሚያሳስበን ብዙም የለም፡፡

ከደርግ አገዛዝ ነፃ ስላወጣነው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ውለታ ሊከፍለን ይገባል” የሚለው ብጥለው ገለበጠኝ ዓይነት አባባልም በእንግሊዝኛው አገላለጽ “adding an insult to injury” እንደሚሉት ወዝ የሌለው የበለጠ አቁሳይ መራራ ቀልድ ነው፡፡

የሚያዋጣው ብቸኛ መንገድ የሕወሓት ንስሃ መግባትና ከኢትዮጵያና ሕዝቧ ጋር በአፋጣኝ መታረቅ ነው – ይህም ከተቻለ ነው እንጂ የወያኔ ክፋት ከዕርቅና ከይቅርታ በላይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ሁሉ ዶንኪሾታዊ መፈራገጥ ለበለጠ መላላጥ የሚዳርግና በዱሮ በሬ ለማረስ የመዳዳትን ሙከራ የሚያሳይ ከንቱነት ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ወጣት አምርሯል፡፡ እነዐቢይ ወደ መድረክ ባይመጡ ኖሮ ወያኔን እገባበት ገብቶ በጥቂት ቀናት ውስጥ ድራሹን ያጠፋው ነበር፡፡ ተዘርፎ የተከማቸ የጦር መሣሪያ ቀን ሲያዘነብል ከማማሰያም አይሻልም፤ ተዘርፎ የተከማቸ ሀብትና ገንዘብ ቀን ሲከዳ ብል እንደበላው ጨርቅ ብትክትኩ ይወጣል፤ ለክፉ ቀን ያሉት የሕዝብ ደጀን ጊዜ ሲከዳ እንደጉም ይበንና ከአጠገብ ይጠፋል፡፡  

ቀንን አለማወቅ ሞኝነት ነው፤ የትንቢትን ፍጻሜ አለማጤን ጅልነት ነው፤ በፋሲካ እንደተቀጠረች ገረድ ሁልጌዜ ፋሲካን ማሰብ ከየዋህነት ያለፈ ቂልነት ነው፡፡ የነሂትለርንና ሙሶሊኒን ፍጻሜ አለማስታወስ ድንቁርና ነው፡፡….

“የምታደርገውን ንገረኝ – መጨረሻህን እነግርሃለሁ” የሚል አባባል ይኖር ይሆን?

No comments