Latest

''በሐረሯ ሕጻን ጫልቱ ሞት የተጠረጠረው ግለሰብ እስካሁን ክስ አልተመሠረተበትም'' - ቢቢሲ

''በሐረሯ ሕጻን ጫልቱ ሞት የተጠረጠረው ግለሰብ እስካሁን ክስ አልተመሠረተበትም'' - ቢቢሲ

በ14 ዓመቷ ጫልቱ አብዲ ላይ አሰቃቂ ጥቃት አድርሷል የተባለው ግለሰብ እስከዛሬ ክስ እንዳልተመሠረተበት ጉዳዩን የሚከታተሉት ጠበቃ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ከበደ ግልጽ ባልሆኑ ምክንያቶች ግለሰቡ ላይ ክስ ሳይመሠረት አራት ወራት መውሰዱንም ጠቁመዋል።

ፖሊስ ማስረጃ ሰብስቦ ለአቃቢ ሕግ ሲያስተላልፍ መደበኛ ፍርድ ቤት ፋይል እንደሚከፈት የሚናገሩት ጠበቃዋ እስካሁን ግን በተጠርጣሪው ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት ክስ አልተመሠረተም።

ክሱ ለምን እንደዘገየ የተጠየቁት ጠበቃዋ ጉዳዩን የያዙት የክልሉ ፖሊስ መርማሪዎች የሐኪም ማስረጃ ሐረር ድረስ ወስደው ለማስተርጎም በሚል አላስፈላጊ ጊዜ እንደወሰዱ አስረድተዋል።

ክስ ለመመሥረት በሚጠበቅበት ጊዜም ሐረር ድረስ ይዘውት የሄዱትን የሐኪም ማስረጃ «የትርጉም ስህተት አለው» በሚል በድጋሚ አዲስ አበባ ተመልሰው «ተጨማሪ ማስረጃ ፈልገን ነው የመጣነው» በሚል ክስ እንዳዘገዩም ነግረውናል።

የሆስፒታል ማስረጃ በእንግሊዝኛ እንደሚጻፍ፣ የፍርድ ቤት የሥራ ቋንቋ ደግሞ አማርኛ በመሆኑ ማስረጃው መተርጎሙ አስፈላጊ እንደሆነ ካብራሩ በኋላ፣ የሐኪም ማስረጃን ለማስተርጎም አዲስ አበባ በብዙ መልኩ ከክልል የተሻለ እንደሆነ የታወቀ ቢኾንም፤ ፖሊስ ማስረጃውን ክልል ድረስ ይዞ መሄድ ለምን እንዳስፈለገው ለጠበቃ ኤልሳቤጥ ግልጽ አልሆነላቸውም።

የሐኪም ማስረጃን ከወሰዱ በኋላ አራት ሆነው በድጋሚ ተመልሰው መምጣታቸውንና ማስረጃውን ይዘው የካቲት 12 ሆስፒታል መሄዳቸውን ጠቅሰዋል። ለአራት ወራት ክስ ላለመሥረት ምክንያታቸውም ይኸው ነው ብለዋል።

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓቱ መሠረት አንድ ፖሊስ ከ21 ቀን በላይ ጊዜ ቀጠሮ ማቆየት አይችልም የሚሉት ጠበቃዋ፤ ፖሊስ ማስረጃ አልተሟላልኝም ካለ ሦስት ጊዜ ሰባት ሰባት ቀናት ማራዘም እንደሚችል ጠቅሰዋል። ነገር ግን እስከ አራት ወራት ክስ ሳይመሰረት ማለፉ እንዳስገረማቸው አብራርተዋል።

''ባለፉት ወራት ሟች ቃል ትሰጣለች፥ ፖሊስ ተመላልሶ ይመጣል። ለምን ክስ መመሥር እንዳልፈለጉ ግልጸ አይደለም።''

የሆስፒታሉ ማስረጃ ምን እንደሚያሳይ የተጠየቁት ጠበቃዋ የሞቷ መንስኤ ምን እንደሆነ ያስረዳል ብለዋል።

"18 በመቶ ሰውነቷ በቃጠሎ ተጎድቷል። ይህም ከጡቷ ሥር እስከ ጉልበቷ ይደርሳል። ቃጠሎው ወደ ጀርበዋም ዘልቋል።" ይላሉ።

ጠበቃ ኤልሳቤት ጨምረው እንደተናገሩት መጀመሪያ ተጠርጣሪና ተባባሪዎቹ ልጅቷን እንዳስፈራሯትና በኋላ ላይ ግን በፖሊስ ስትጠበቅበት ከነበረ ክፍል ውስጥ ላገኘቻቸው ሰዎች የደረሰባትን መናገሯን ጠቅሰው፤ ለኔም መደፈሯን ነግራኛለች ብለዋል።

ሟችን በሆስፒታል ሳለች ብልቷ አካባቢ ከጥቅም ውጭ ሆና እንደነበረና በመደፈር ስንጥቅ ስለደረሰባት ምናልባትም ያንን ለመሸፈን ሲባል ቃጠሎ እንደደረሰባት የሚገምቱም አልጠፉም። ጠበቃዋም ተመሳሳይ ግምት አላቸው።

''ምንም ሳትሆን የተቃጠለች ቢሆን ኖሮ እንዳለ ሁሉም ነጭ ይሆን ነበር። ከማህጸኗ እስከ ፊንጢጣዋ ድረስ ስንጥቅ አለው። እዛጋ ደም አለው። ለነርሱ [ለሐኪሞች] ትንገራቸው አትንገራቸው፥ ወይም ደግሞ በምርመራ ሂደት ይድረሱበት አይድረሱበት አላውቅኩም። ግን ለኔ የሆነችውን ነግራኛለች።'' ብለዋል።

ሟች ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ወላጆቿ አቅም ስላልነበራቸው የካቲት 12 ሆስፒታል የሚያሳክምላችው እንዳልነበረ ያወሱት ጠበቃዋ፤ በኋላ ላይ በፌስቡክ በተሰበሰበ እርዳታ 32ሺ ብር መገኘቱንና ልጅቱ በሱ መታከም መጀመሯን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ወ/ሮ ሜሮን አራጋው ጫልቱ ጥቃቱ ከተፈፀመባት በኋላ ያለምንም እርዳታ በተደፈረችበት ቤት ውስጥ ለ15 ቀናት እንድትቆይ መደረጉን ለቢቢሲ ገልፀዋል። የታዳጊዋ ቃጠሎም ሦስተኛ ደረጃ ማለትም አጥንት ዘልቆ የሚገባ እንደነበርም አመልክተዋል።

ቢቢሲ የሟችን እናትና አባት ለማግኘት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ስልክ ስለሌላቸው ማግኘት አዳጋች ሆኗል።
"በክልሉ ልዩ ኃይል ጥበቃ ይደረግላት ነበር"

የ14 ዓመት ታዳጊዋ ጫልቱ አብዲ በአሰሪዋ ተገዳ ከተደፈረች በኋላ ምንነቱ ያልታወቀ ፈሳሽ ተደፍቶባታል ተብሏል። በዚህም ታዳጊዋ ከጉልበትዋ እስከ እምብርቷ ድረስ ከፍተኛ የመቃጠል ጉዳት እንደደረሰባት ተገልጿል።

ከምሥራቅ ሐረርጌ በደኖ ከሚባል ቦታ ወደ ሐረር የመጣችው ታዳጊ፤ በተጠርጣሪው ቤት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ነበር የምትሰራው።

ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ኤልሳቤጥ እንደሚሉት ታዳጊዋ ከመደፈሯ በተጨማሪ በሰውነቷ ላይ የተደፋባት ፈሳሽ ያደረሰባት ጉዳት እያለ ምንም ዓይነት ሕክምና ሳታገኝ በቤት ውስጥ እንድትቆይ ተደርጋለች። ''ሕመሙ እየባሰባት ሲመጣና ሕይወቷ አስጊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ወደ ሐረር ምሥራቅ አርበኞች ሆስፒታል በድብቅ ተወስዳለች።''

በሆስፒታሉ ውስጥም ማንም ሰው እንዳያያት ባዶ ክፍል ውስጥ እንድትተኛና ሌሎች ሰዎች ወደ ክፍሉ እንዳይገቡ በክልሉ ልዩ ኃይል ጥበቃ ይደረግባት እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ''የሚከታተላት ነርስም ቢሆን ከውጪ ነው የተቀጠረው'' በማለት የጉዳዩን ውስብስብነት ያመለክታሉ።

ሁኔታው ጥርጣሬ የጫረባቸው የሆስፒታሉ ሠራተኞችና ሌሎች አስታማሚዎች ወደ ክፍሉ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉም በወታደሮቹ ይከለከሉና ይባረሩ እንደነበረ ነግረውናል ይላሉ ጠበቃ ኤልሳቤጥ። በመጨረሻ ተሳክቶላቸው መግባት የቻሉ ሰዎች አስር ታካሚዎችን በሚያስተናግድ ክፍል ውስጥ ለምን ብቻዋን እንደተኛች ሲጠይቋት፤ የደረሰባትን ነገር እንዳስረዳች ጠበቃዋ ያመለክታሉ።

ጥቃቱን ያደረሰባት ግለሰብ ባለትዳር ሲሆን፤ የተጠርጣሪው ባለቤትም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውላ ከአንድ ቀን በኋላ መፈታቷን ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ነግረውናል።
"ሐረር ካልተቀበረች ብለው መቃብር ቆፍረው ነበር"

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና የጫልቱን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ አንድ ግለሰብ ጉዳዩን ለመሸፋፈን የተጠርጣሪው ቤተ ዘመድና በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር እጃቸውን ያስገቡ እንደነበር ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሕክምናውን አስመልክቶ በቴሌቨዥን እሷን የተመለከቱ መርሐግብሮች እንዳይተላለፉ ጫና መደረጉን፣ ከዚያም ባሻገር ቃሏን እንድትቀይር የሚያደርጉ ተጽእኖዎችም ነበሩ ተብሏል።

ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ከእናቷ አንደበት ሰማሁ ብለው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደግሞ ጫልቱን ሐረር ሕክምና ላይ ሳለች መሣሪያ የያዙ ፖሊሶች ናቸው ሲጠብቋት የነበረው። "ይህም ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲቀር ሙከራ ይደረግ እንደነበር ያሳያል" ብለዋል።

እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የፍርድ ሒደቱ ምን ያህል ነጻ ሊሆን ይችላል በሚል የተጠየቁት ወይዘሮ ሜሮን ፍርድ ሂደቱ ሐረር ክልል ላይ ቢታይ መጨረሻ ላይ የሚሰጠው ፍትህ ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አቤት ማለታቸውን ገልጸው "የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቢ ሕግም ምላሽ ሰጥቶናል።" ብለዋል።

በገንዘብ የማባበል ሙከራን ጨምሮ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች የተለያየ የማዋከብ ሥራ ሲሠሩ ነበር ያሉት እኚህ ግለሰብ፤ ቀብሯ በተወለደችበት ቀዬ እንዳይፈጸም ይልቁንም ሐረር ከተማ ካልተቀበረች ብለው መቃብር ቆፍረውም እንደነበርም ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት ግለሰብ ገልፀዋል።

No comments