Latest

የሙላው ቤተሰቦች ጭንቀት (ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው)



የሙላው ቤተሰቦች ጭንቀት


  • "የቀበርነው ተሸፍኖ የተሰጠንን የሌላ ሰው አስከሬን ነው፣ ሙላው አልሞተም" ብለው በተስፋ እየጠበቁ ነው
  • "ተደውሎ አልሞተም፣ በእስር ላይ ይገኛል ተብለናል" ይላሉ
ሙላው ከበደ ውብነህ በ1999 ዓም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ተመርቋል። ወልቃይት አዲረመጥ ከተማ ስራ ተቀጥሮ አንደ አመት ተኩል ሰርቷል። ሆኖም የህወሓት አባል ሁን ብለውት ሲያዋክቡት "አባል መሆን አልፈልግም፣ በሙያየ ነው የማገለግለው" ይላቸዋል። 

ወከባው ሲቀጥልበት በ2001 ስራ ይለቃል። በ2002 ሁመራ ሌላ የመንግስት ስራ ይይዛል። አዲጎሹ የሚባል ቦታ የሚገኝ የገዥዎቹን ዘመድ የሙላውን ቦታ ለመስጠት ወደ አዲጎሹ ተቀየር ይሉታል። "አልፈልግም" ብሎ ብዙ ተከራክሯል። ብዙ ውጣ ውረድ ደርሶበታል። በ2004 ዓም ስራውን ለቅቆ የአባቱን እርሻውን በውክልና ይይዛል። ከ2004-2008 ዓም የአባቱን እርሻ እያስተዳደረ ቆይቷል።

በ2008 ዓም የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ ሲነሳ፣ በማንነቱ ሲጠቃ የኖረው ሙላው በእንቅስቃሴው ውስጥ ገባ። ታህሳስ 9/2009 ኮርሁመር የተባለ ቦታ ይልማ ፈረደ የሚባል ሰው የእርሻ ካምፕ እያለ ከዘውዱ ገ/ እግዚያብሔር ጋር መከላከያ በጭካኔ እንደገደላቸው ነው የሚታወቀው።

በወቅቱ የሙላውን አስከሬን ለመውሰድ እንደፈረሙ አንድ የቤተሰብ አባሉ አጫውቶኛል። የሙላው አስከሬን ወደ ሁመራ ሄዶ ወደ እናት እና አባቱ ቤት መግባት የለበትም ተባለ። አስከሬኑ እንዳይከፈት፣ አስከሬኑ ሲሄድ ጥይት እንደይተኮስ፣ እንዳይፎከር ፈርመው እንደተረከቡ ይነገራል። የሙላው አጎት የተባሉትን "እሽ" ብለው ባይፈርሙ አስከሬኑ እንደማይሰጣቸው ተነግሯቸዋል። አስከሬኑ ተጠቅልሎ ተሰጣቸው። ሳይታጠብ ተቀበረ። ቤተሰቦቹ ሙላው ይሁን አይሁን አላዩትም።

ይባስ ብሎ በቅርቡ ቁጥሩ በማይታይ ስልክ ተደውሎ "ወንድማችሁ አልሞተም። አዲስ አበባ ትንሽ ወጣ ብሎ ታስሮ ይገኛል፣ እርዱት" ብለው ይዘጉባቸዋል። የሙላው ቤተሰቦች አስከሬኑን አላዩም፣ አስከሬኑ አልታጠበም። አልቅሰው አልወጣላቸውም።

ሳይደወልላቸውም፣ "አለ"እንዳይሉ አስከሬን ወስደውላቸዋል። ሞተ ብለው እርማቸውን እንዳይወጡ ወልቃይት ነው። ገዥዎቹ የሚፈፅሙት ዘግናኝ ግድያም፣ ማጭበርበሪያም በወልቃይት የተለመደ ነው። አስከሬኑን የሙላው መሆኑን ገልጠው አላዩም። ጭራሽ ደውለው አልሞተም የሚሏቸው ሰዎች አሉ። 

በዚህ መሃል ቤተሰቡ ግራ ተጋብቷል። አንደኛው "ሞቷል እርማችንን እናውጣ" ሲል፣ ሌላኛው "አልሞተም!" ብሎ በተስፋ እየጠበቀ ነው። ሰሞኑን የቤተሰብ አባላቱን አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር። ሙላው አልሞተም ብለው ብዙ ምክንያት ያቀርባሉ። 

አንደኛው በእርሻ ካምፑ ሶስት ከዘውዱ በተጨማሪ የተገደለው የካምፑ ጠባቂ እንደነበር፣ የካምፑ ጠባቂ ደግሞ ከሩቅ ቦታ የሄደ በመሆኑ ቤተሰቦቹ በሕይወት ይኑር ይሙት ስለማያውቁ የእሱን አስከሬን "የሙላው ነው" ብለው እንደሰጧቸው ጥርጣሬውን ይገልፃል።

ጉዳዩን በቅርብ ሊያውቁ የሚችሉ ሰዎችን ስጠይቅ ግን ሙላው ተገድሏል እንደተባለ ነው የሚገልፁት። ቤተሰቦቹ ግን ይህን አያምኑም። እየደወሉ "ወንድማችሁ አልሞተም፣ በእስር ላይ ነው" የሚሉት "ሙላው አለ" ብለው በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል።

የገዥዎች ክፉነት መግደላቸው ብቻ አይደለም። ጭካኔያቸው ለከት የለውም። መሳርያ ያልያዘን ንፁህ ሰው በከባድ መሳርያ ሳይቀር ይመቱታል። አስከሬኑ አሰቃቂ ስለሚሆን ቤተሰቡ እንዳያየው ያደርጋሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለማስፈራሪያ ገበያ ላይ አስጥተው ሰውን ያስፈራሩበታል። 

የሙላው ቤተሰቦች አስከሬኑን ገልጠው ለማየት አልታደሉም። እንደወጉ አስከሬኑ አልታጠበም። በዚህ ላይ ደግሞ "አልሞተም" እያሉ ይደውሉባቸዋል። ታዲያ የሙላውን ሞት እንዴት ይመኑ? አሁንም "አልሞተም" ብለው በተስፋ እየጠበቁ ነው።

No comments