Latest

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የውጪ ሃገራት ዜጎች ንብረት ተዘረፈ

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያዊያንን

ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በምትገኘው ሶዌቶ በምትባል ትንሽዬ ከተማ ኢትዮጵያዊያን እና ሶማሊያዊያን ነጋዴዎች ላይ ባነጣጠረ ዝርፊያ የሶስት ሰዎች ህይወት አልፏል።

በአካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደሰማነው ከሆነ ሟቾቹ የሶማሊያ፣ የደቡብ አፍሪካ እና የፓኪስታን ዜጎች ናቸው።

ይሁን እንጂ የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከሟቾቹ መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው ብሏል።

የሶዌቶ ፖሊስ ሪፖርት እንደሚያሳየው የውጪ ሃገራት ነጋዴዎች ላይ በተሰነዘረው ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት አልፏል።

የጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪ የሆነው ኢትዮጲያዊው ሞሐመድ ኑር ''የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ትሸጣላችሁ በሚል ያጠቁናል እንጂ 'የውጪ ሃገር ዜጋ እኛን ሥራ ያሳጣሉ' የሚል አቋም አላቸው'' ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሞሐመድ እንደሚለው ከሆነ ፖሊስ የውጪ ሃገር ነጋዴዎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የለፈባቸውን ምርቶች ለገብያ እንደማያቀርቡ አረጋግጧል።

ምንም እንኳን ጊዜው ያለፈበት እና ደረጃውን ያልጠበቅ ምርት ነው የምትሸጡት ቢሉም መልሰው ይህንኑ ንብረት ነው የሚዘርፉት ሲል ሞሐመድ ይናገራል።

በ'ዋትስአፕ የመገናኛ አውታር የአካባቢው ሰዎች ሶማሊያዊ ተከራዮችን ከቤታቸው እንዲያስወጡ ካልሆነ ግን ጥቃቱ ለእነሱም እንደሚተርፍ ቀነ ገደብ የተቀመጠለት የዛቻ መልዕክት እንደተሰራጨም ተነግሯል።

''ከመዘረፍ ባሻገር የተደበደቡ ጓደኞች አሉኝ፤ እንዲሁም የታሰሩ አሉ'' ሲል ሞሐመድ ይናገራል።

''የአካባቢው ማህብረሰብ ለኛ መልካም ያልሆነ አመለካከት ነው ያለው። እንደ ሰው እንኳን አይቆጥሩንም'' በማለት የውጪ ሃገራት ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ያስረዳል።

ሌለው ነዋሪነቱን በደቡብ አፍሪካዋ ራንድፎንቴን ያደረገው ኢትዮጵያዊ ኢብራሂም በድሩ ከዝርፊያው ጋር በተያያዘ ከተገደሉት ሶስት ግለሰቦች መካከል አንዱ የ15 ዓመት ደቡብ አፍሪካዊ ሲሆን ሁለቱ የሶማሊያ እና የፓኪስታን ዜጎች ናቸው ብሎናል።

የዋትስ አፕ መልእክቱ የተላለፈው ለመላው ደቡብ አፍሪካውያን ቢሆንም ምላሽ ለመስጠት የቀደሙት የሶዌቶ ነዋሪዎች ነበሩ ሲል ሁኔታውን ያስረዳል።

ግርግሩ ሲጀመርም ሱቃቸው ከተዘረፈባቸው ግለሰቦች መካከል አንድ የሶማሊያ ዜጋ ንብረቱን ለመከላከል የጦር መሳሪያ በመጠቀም አንድ የ15 ዓመት ደቡብ አፍሪካዊ መግደሉንና ከዚያም በኋላ ነገሮች እንደተባባሱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ግርግሩና ዝርፊያው በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ቀጥሏል ወይ? ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ ኢብራሂም ሲመልስ ''ለጊዜው ችግሩ ያለው በሶዌቶ ብቻ ቢሆንም፤ በሌሎች ከተሞች የሚኖሩ የሌላ ሃገራት ዜጎች ግን በፍርሃት ንብረታቸውን እያሸሹ ነው'' ይላል።

ነገር ግን ሌላ ዘረፋ ለማካሄድ በዋትስ አፕ ዘመቻ እንደተጀመረና እስከ መስከረም ስምነት ድረስ የሚቆይ የደቦ ጥቃት እየታሰበ እንደሆነ መስማቱን ኢብራሂም ይናገራል።

ፖሊስ እስከ አሁን ድረስ 27 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውያለው ያለ ሲሆን ጥቃቶቹንም አውግዟል።

ንብረቱን እንደ ተዘረፈ የሚናገረው አንድ ሶማሊያዊ ነጋዴም ''ከአሁን በኋላ እንዴት አድርጌ የንግድ ሥራዬን እንደምቀጥል አላውቅም'' ይላል።

ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመጣ ስምንት ዓመታት እንዳስቆጠረ እና በእነዚህ ዓመታት ሶስት ጊዜ መዘረፉን ይሁን እንጂ የትኛውም የሃገሪቱ የመንግሥት አካል እንዳላነጋገረው በምሬት ያስረዳል።

ሌላኛው ያነጋገርነው አህመድ ዳንኤል ደግሞ የሚኖረው ሜሴር በሚባል አካባቢ ሲሆን፤ የሚሰራው ግን ''ዋይት ሲቲ'' ሶዌቶ ውስጥ ነው።

እሱ እንደሚለው በደቡብ አፍሪካ እንደዚህ አይነት ዝርፊያዎች የተለመዱ ናቸው። ''የአካባቢው ተወላጆች ማንኛውም አይነት ጥያቄ ሲኖራቸው መጀመሪያ የሚመጡት የሌላ ሃገር ተወላጆች ወደሚሰሩበት የንግድ ቦታ ነው'' ይላል።

''ጥያቄው የውሃ ሊሆን ይችላል፤ ጥያቄው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ጥያቄውን ለመንግሥት አቅርበው የኛን ሱቆች ዘርፈው ነው የሚሄዱት'' ሲል በምሬት ለቢቢሲ ተናግሯል።

''አሁንም ቢሆን ያቀረቡት ጥያቄ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች እየሸጡ ነው የሚል ቢሆንም፤ አንደኛ ምንም ማስረጃ የላቸውም ሁለተኛ ደግሞ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት ከሆነ ለምን ዘርፈው ይበሉታል?'' በማለት ይጠይቃል።

የዋትስ አፕ መልእክቱን እንደሰማም ከሱቁ አንዳንድ እቃዎችን ለማሸሽ እንደሞከረና የተረፈውን ግን በአካባቢው ሰዎች እንዲሁም ፖሊሶች እርዳታ ማዳን እንደቻለ ነግሮናል።

በሶዌቶ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ሶማሊያዊያን፣ ዚምባብዌያዊያን እና ፓኪስታንያዊያን ሱቆችን ከፍተው ይሰራሉ።

በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሶዌቶና አካባቢዋ በሚገኙ የኢትዮጵያውያን ዜጎች ንብረትና ሀብት ላይ ጥቃት መድረሱን መስማቱን እና ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ በፌስቡክ ገጹ ላይ አሳታውቋል።


ኤምባሲው ጨምሮም ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና እርዳት የሚሹ ከሆነ ወደ ኤምባሲው ስልክ መደወል እንደሚችሉ ገልጿል።

No comments