Latest

ለአ.ብ.ን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች (አቤኔዘር ቢ. ይስሃቅ)



ለአ.ብ.ን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች

"ለአማራ ሕዝብ ይጠቅማል" ባላችሁት መንገድ ተደራጅታችሁ በመንቀሳቀስ ላይ ናችሁ። ያለፈውንና አሁን ያለውን ነገር መሰረት አድርጌ የወደፊቱን ሁኔታ ስገምት ሀገሪቱ ውስጥ ለመጪዎቹ 15 ወይም 20 ዓመታት የብሔር ፖለቲካ በቀጣይነት ይኖራል ብዬ እገምታለው።

በዚህ ምክንያትና አሁን ላይ "ልትታገልሉት" ከምታስቡት ሕዝብ አንጻር መደራጀታችሁ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነው።

ከምንም ነገር በላይ ግን የእናንተ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጠንክሮ መውጣት ገና ፖለቲካን "ሀ" ብሎ ሲጀምር በየሚዲያውና በየቦታው የአማራ ሕዝብ ላይ አንደበቱን በስድብ የሚከፍተው ሁሉ ንግግሩን ገታ አድርጎ ለመደራደርና ለመወያየት ይዘጋጃል። ከዚያም አልፎ የሀይል ሚዛኑን ያስጠብቃል።

የያዛችሁትን ዓላማና አጀንዳ ከግቡ ለማድረስ ግን የምትሄዱበትን መንገድ፣ አቀራረብ ወዘተ መገምገምና በተቻለ መጠን ምንም ሥህተት ላለመፈፀም መሞከር ይጠበቅባችኋል።

ተራ አታካራ ከሚፈጥሩ ለድጅታችሁም ሆነ ለምትታገሉለት ሕዝብ ምንም የማይጠቅም ነገር ከመናገርና ከመጻፍ ተቆጠቡ። በአንድነት ጎራ ውስጥ ይሁን በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ በግልጽ ፀረ-አማራ አመለካከትና አቋም ያላቸው ግለሰቦች አሉ።

በእናንተ አሳበው በውስጣቸው ያለውን ጥላቻ ለመዘርገፍ ሰበብ የሚፈልጉና "አማራ ማለት ይሄ ነው" ብለው የተሳሳተ ምስልና መልዕክት ለማስተላፈ የሚፈልጉ አሉ። ስለዚህ በምንም መልኩ መንገድ አትክፈቱላቸው።

የአጀንዳ ቅደም ተከተል ኖሯችሁ ስራችሁን ስሩ። በየአቅጣቸው ለሚነሳው ተቃውሞና ስድብ መልስ መስጠቱን ትታችሁ የአማራ ሕዝብ ከፊቱ ያለውን ተግዳሮት መወጣት በሚችልበት ጉዳይ ላይ ማንቃታችሁን፣ ማደራጀታችሁን. . . ቀጥሉ።

በምንም አይነት መልኩ የትህነግንና የኦነግን አይነት አካሄድ እንዳትከተሉ። ይሄ ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ለሚኖረው የአማራ ሕዝብ አደጋ ያመጣበታል። ነገሮችን በማስተዋልና በጥንቃቄ አድርጉ።

በአማራ ክልል ውስጥ ከእናንተ ውጪ በዋናነት "በአማራ ሕዝብ ሥም" የተደራጀ ቡድን ያለው ብአዴን ነው። ይሄ በራሱ ለእናንተ አደረጃጀትና በፍጥነት መስፋፋት ጠቃሚ ነውና ትኩረታችሁን አጀንዳችሁ ላይ አድርጋችሁ አጋጣሚውን በደንብ ተጠቀሙበት።

የእናንተ መብት እንዲከበር የምትፈልጉትን ያህል የሌሎችም እንዲከበር ታገሉ። በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል ውስጥ በማንኛውም ግለሰብና የብሔር አባል ላይ ጥቃት ሲፈጸም ከማንም ቀድማችሁ ድርጊቱን አውግዙ። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደተከሰተው ወጣቶች በስሜት ተነሳስተው ፍርድን በራሳቸው እንዳይፈጽሙ አጥብቃችሁ ስሩ።

በአካባቢው ያለው ወጣት እናንተን ይሰማልና በምታካሂዱት ሕዝባዊ ስብሰባ ወቅት ይሄንን መልዕክት አበክራችሁ አስተላልፉ።

ራሳችሁን በጠራ አጀንዳ፣ በሰው ሀይል፣ በሚዲያ. . . በደንብ አጠናክራችሁና አደራጅታችሁ ስትንቀሳቀሱ ከ1983 ዓም ጀምሮ አማራውን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ ወዘተ ሲገፉ የነበሩ ሀይሎች፣ 


አሁን ደግሞ ዶር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ "ጊዜው የእኛ ነው" ብለው ተመሳሳይ ነገር ለመድገም እየተንደረደሩ ያሉ ሀይሎች፣ በአንድነት ጎራ ውስጥ ሆነው በአማራ ሕዝብ ጉዳት የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ የሚፈልጉ ወገኖች ቦት መስጠትና ማድመጥ ይጀምራሉ።

ይሄ ሁሉ ነገር ሊሆን የሚችለው ግን እናንተ ስሜታዊ ከሆኑና ምንም ጥቅም ከሌላቸው ነገሮች እርቃችሁ ስራችሁ ላይ ብቻ አተኩራችሁ ስትንቀሳቀሱ ነው።

No comments