Latest

ከቻይና- አፍሪካ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት ጀርባ ምን አለ? ቢቢሲ

ከቻይና- አፍሪካ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት ጀርባ ምን አለ?

"ቻይና ለአፍሪካ የቅርብ ወዳጅና ታማኝ ጓደኛ ነች" ብለዋል ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ትናንት በተከፈተው የአህጉሪቱና የአገራቸው የጋራ ጉባኤ መክፈቻ ላይ።

"አፍሪካን እንወዳለን፤ እንደግፋለን" ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ ምቾት የሚሰጡ ቃላትን አስተጋብተዋል። ለመሆኑ ከቻይና የአፍሪካ ወዳጅነት ጀርባ ምን አለ?

አቶ ሀይለመለኮት ተከስተብርሃን የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ባለሞያ ናቸው። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡት የቻይና አፍሪካ ወዳጅነት በገበያና በጥሬ ዕቃ የሚመራ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ነው።

"የቻይና ሕዝብ ከ1 ቢሊዮን በላይ ነው። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ሕዝባቸው ወጣት ነው። በዕድገት ላይ ናቸው። ትልቅ ሸማች እየተፈጠረ ነው። ይህ እውነታ የቻይናን ሞልቶ የሚፈስ ምርት ላያጓጓ አይችልም።" ይላሉ።

ሁለተኛው የሚያቀርቡት ምክንያት የርካሽ ጥሬ ዕቃ ረሀብ ነው። ቻይና ተስፋፊ ፋብሪካዎቿ በጥሬ ዕቃ የከበረችውን አህጉር እንዲያማትሩ ያስገድዳቸዋል። "በርካሽ የሚያገኙትን ጥሬ ዕቃ እሴት ጨምረው ለራሳችንም ለተቀረው ዓለምም ያደርሱታል።"

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ፖል ካጋሜ ለሺ ጂንፒንግ የእስከዛሬው ድጋፍ ሞቅ ያለ ምስጋናን ካቀረቡ በኋላ ቻይና "እኩል ተጠቃሚነትን መሠረት የምታደርግ ወዳጃችን ናት" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ተመሳሳይ ምስጋናን አቅርበዋል።

በዚህ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ብቻ የምጣኔ ሐብት ቀውስ ውስጥ ገብታ የቆየችው ዚምባብዌን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች የቤጂንግን ደጅ ጠንተዋል። ለመሆኑ የአፍሪካ መሪዎች ለምን ቀድመው ወደ ቻይና ያማትራሉ?

አቶ ኃይለመለኮት ለዚህም ሁለት አበይት ምክንያቶችን ያቀርባሉ።

አንዱ ቻይና የምትሰጠው ብድር በቅድመ ሁኔታዎች የተጀቦነ አለመሆኑ ሲሆን ይህ ለብዙ ከዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ለተኳረፉ የአፍሪካ መሪዎች ምቾትን የሚሰጥ ነው ይላሉ።

ሌላው ደግሞ …የቻይና የተፍታታ ብድር ለመስጠት አለማቅማማቷ ነው። የብድር እፎይታዋና የወለድ ምጣኔዋ ከምዕራቡ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር ሻል ያለ ነው።

የኢትዮጵያ እና ቻይና «ወዳጅነት»
ከ80 በላይ የሚሆኑ ጥናቶችን በአፍሪካ-ቻይና ግኝኙነት ላይ ያጠኑት ጌዲዮን ገሞራ ጃለታ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት ጥንተ-መሰረት እንዳለው ያስረዳሉ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአውሮፓውያኑ በ1995 ወደ ቤጂንግ ማቅናታቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቻይናን እንደ ፈጣን እድገት አብነት ማየቷ እንደጨመረ የሚያነሱት አጥኚው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማግዘፍ የፈለገችበት ምክንያት ኢትዮጵያ ካላት ዲፕሎማቲክ እና የገበያ ጠቀሜታ አንፃር እንደሆነ ያብራራሉ።

ምሁሩ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ መናገሻ መሆኗ እንዲሁም ያላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ጋር ተያያይዞ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለየ መንገድ እንደምታየው ነው።

«።ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ የመላው አፍሪካን ዐይን(ቪዚብሊቲ) እንደሚያገኝ ስለሚያውቁ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነታቸውን ለማጠንከር ፈልገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ አላት ፤ይሄ ለቻይና ትልቅ የገበያ መዳረሻ ነው።  


ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሸጡ ያሉ ብዙ ሸቀጦች እየመጡ ያሉት ከቻይና ነው።» የሚሉት አቶ ጌዲዎን ከእነዚህ በተጨማሪ የመንገድ ስራን በመሳሰሉ ዘርፎች ያለውን የስራ ዕድል ቻይናዊያን በመልካም ማየታቸው ለሁለቱ ሀገራት ዕድገት መጠንከር እንደ ምክንያትነት ያነሳሉ።

ይሄም ቢሆን ቅሉ ግኑኝነቱ በጥንቃቄ መከወን እንዳለበት አጥኚው ይመክራሉ፤ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከቻይናዊያን ወደ ዜጎቿ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር መዋቅር እንዲኖራት፣ ተመጣጣኝ ያልሆነው የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት እንዲስተካከል፣የቻይና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ገሸሽ ያደረገ የኢኮኖሚ ስርዓትን ፍፁም ትክክል አድርጎ ከመቀበል ራስን ማቀብ እንደሚገባ ይመክራሉ።

የብሔራዊ ባንክ አዲሱን ገዢና ሌሎች ቁልፍ የካቢኔ አባሎቻቸውን አስከትለው በጊዜ ቤጂንግ የገቡት ዐብይ አህመድ፣ ከትናንት በስቲያ ዕሑድ የቻይናን ፕሬዚዳንት አግኝተው በአበይት ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዯች ላይ ተነጋግረዋል።

በውይይቱ ሺ ጂንፒንግ "የኢትዯጵያ ዕድገት ጎዳና ከቻይና ብሔራዊ ልማት ቅድመ ሁኔታ ጋር ስምምነት ነው" ብለዋል። ይህ ዲፕሎማሲያዊው ቋንቋ በትክክል ምን ማለት እንደሆነ ባይብራራም።

ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከቤጂንግ ምን ጉዳዮችን አሳክተው መመለስ ይኖርባቸዋል? አቶ ሓይለመለኮት "ቢያንስ ሦስት ጉዳዮችን ይላሉ። ቀዳሚው ግን ይላሉ አቶ ኃይለመለኮት፣ "ቀዳሚው ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው።

"በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በተከሰቱ ፖለቲካዊ ኩነቶች ላይ የተፈጠረባቸውን ጥያቄ መመለስ፣ ከኢህአዴግ ጋር የነበረው የርዕዮተ ዓለም መጣጣም እምብዛምም ማፈግፈግ እንደሌለ ለቻይናዎቹ በአገሪቱ ላይ የነበራቸውን እምነት መመለስ ይኖርባቸዋል ይላሉ አቶ ኃይለመለኮት።

ይህን ፖለቲካዊ መደላደል በስኬት ካጠናቀቁ በኋላ ግን ሁለት ተጨማሪ ሥራዎች ይጠብቅዋቸዋል ባይ ናቸው አቶ ሀይለመለኮት።

የመጀመሪያው በኢኮኖሚው ረገድ የሚከተለው ስራ ነው።

ቻይና ከፍተኛ ብድሮችን ለኢትዮጵያ ስለሰጠች፤ በዋናነት እንደ ባቡርና ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ያሉ ትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የብድሩ የመክፈያ ጊዜ ደርሷል።

በመሆኑ የመክፈያ ጊዜውን እንዲያራዝሙላቸው ይጠይቃሉ ተብሎ ነው የሚገመተው።

ሌላኛው የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብ ነው። አጠቃላይ ኢኮኖሚው በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሬን ማመንጨት አልቻለም።

አሁን እየተሄደበት ባለው አሰራር ትላልቅ የመንግስት ድርጅቶች በግሉ ዘርፍና በመንግስት ሽርክና ወይንም ለተለያዩ የሃገር ውስጥና የውጪ ድርጅቶች በሽያጭ መልክ ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፤

ቻይናም በዚህ ሂደት ውስጥ ሚና እንዲኖራት ያደርጋሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

No comments