የሶማሌ ክልል የቀድሞው ሰንደቅ አላማ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውል ተወሰነ - ቢቢሲ
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጠራው ልዩ ስብሰባዉ የቀድሞ የክልሉ ሰንደቅ አላማ ተመልሶ የክልሉ መለያ ሆኖ እንዲያገለግል ወሰነ።
ከዓመታት በፊት ለውጥ ተደርጎበት የነበረው በከፊል የሶማሊያ የሰንደቅ ዓላማ ሰማያዊ ቀለምና ነጭ ኮከብ ያለው ሰንደቅ ተመልሶ እንዲያገልግል ተወስኗል። ቀደም ሲል የነበረው ሰንደቅ አላማ በከፊል ቢጫ ቀለምና የግመል ምስል ይዞ ቆይቶ ነበር።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ዑመር በፌስቡክ ገጻቸው በክልሉ ሰንደቅ አላማ ላይ ለውጥ መደረጉን በተመለከተ በማህበራዊ ገፃቸው ላይ "በሶማሌነታችንና በኢትዮጵያዊነታችን መሀከል ተቃርኖ የለም" ሲሉ አስፍረዋል።
የቀድሞው ሰንደቅ አላማ ተመልሶ ሥራ ላይ መዋል መጀመሩን በተመለከተም "የሶማሌ ክልል ህዝቦች ነን፤ ከፊትም ከኋላም ቅጥያ የለም፤ የቀደመው ሰንደቅ አላማ ተመልሷል" በማለት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በገፃቸው ላይ ገልፀዋል።
የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደድር አቶ አብዲ ሙሀመድ ዑመር ከስልጣን ከተነሱ በኋላ የተተኩት አቶ ሙስጠፋ ዑመር፤ "የሶማሌነት መገለጫችንን በኩራት ስንጠብቅ ብሔራዊ ግዴታችንንም ባለመዘንጋት ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት በዛሬው ልዩ ስብሰባው አዲስ አፈ-ጉባኤ ለምክር ቤቱ የሰየመ ሲሆን ለዳኞችም ሹመት ሰጥቷል።
No comments