ደርሼ መጣሁ፡፡ (አንዷለም ቡቄቶ ገዳ)
ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ከእምባ ጋር እየታገልን ወገኖቻችንን ጠየቅን፡፡ ከቤሮ ከሶራምባ ወዘተ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጲያውያን ህጻናት ፡ሴቶች፡ አዛውንት፡ ጎልማሶች… በገዛ አገራቸው ቀደም ብሎ "መጤ" አሁን ደግሞ "ተፈናቃይ" ተብለው ግራ ግብት ብሏቸው አይናቸውን ክርትት ክርትት ሲያደርጉ ሳይ ገና ከጅምሩ ሆዴ ቡጭ ቡጭ ሲል ይታወቀኛል፡፡
ከንፈሬን በቁጭት እንደነከስኩ ከጓደኞቼ ጋር ይዘን የሄድነውን ውሃ ለአስተባባሪ ወጣቶች ሰጥተን የምናደርግው አጥተን ግራ ገብቶን ቆመን ሳለን ያሬድ ሹመቴን ከሩቅ አየሁት ፡፡ከወዲያ ወዲህ ይዋከባል፡፡ገና ሰላምታ ተሳጣጥተን ስለጉዳዩ በደንብ የሚያስረዳኝ ሰው ፈልግልኝ እያልኩት ሳለ ሁሉም ሰው ጩኀቱን አቀለጠው"….ኡ ኡኡኡ… በናታችሁ ያዙት …ወይኔ ወይኔ .."….እየተጯጯኹ ወደ አራተኛ ፎቅ ያንጋጥጣሉ..(በነገራችን ላይ ተፈናቃዮቹ የሚገኙት በፊሊጶስ የመ/ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ነው)፡፡
የአንዷ ተፈናቃይ እናት ህጻን ልጅ (በግምት 3 አመት የሚሆነው) ከአራተኛ ፎቅ ባልኮኒ ላይ በብረቱ መሃል ሾልኮ ወጥቶ ሊፈጠፈጥ በጉዞ ላይ ነው፡፡ ከስር ሊሾ ንጣፍ ነው የሚጠብቀው…እንዲህ አይነት በተለይ የህጻን ልጅ ሰቆቃ ማየት ስለማልችል ጭንቅላቴን በእጄ ይዤ መሬት ቁጭ አልኩ …ያሬዶ ከመቅጽበት ወደ ፎቁ ስር ሮጠ›…
በህይወቱ ፎቅ ላይ ወጥቶ የማያውቀው የገጠር ህጻን ልጅ ከስር ሆነው "ተው ተው እዛው ሁን "ወደ ሚሉት ሰዎች እጁን ዘርግቶ በአንድ እጁ ብቻ ብረቱን ይዞ እግሩን ወደ አየር ላይ ሲዘረጋ …..ከተቐመጥኩበት በአንድ አይኔ ወደላይ ሳጮልቅ ከኋላው ከየት ሮጦ አራተኛ ፎቅ እንደደረሰ ያልገባኝ ሰው የህጻኑን ልብስ ጭምድድ አድርጎ መለሰው፡፡….በትእይንቱ ምክንያት እስከአሁን ሰውነቴ በአግባቡ አልተረጋጋም፡፡
እኔ በድንጋጤ አፌን ከፍቼ ስለ ህጻኑ ሳስብ…ያሬድና ጓደኞቹ ወዲያዉኑ ወደማስተባበር ስራቸው ተመለሱ፡፡ስለጉዳዩ ያውቃል ያለውን አንድ ወጣት አገኘልኝ …የተለያየ ጥያቄዎችን ጠየኩት …..ብቻ ልጁ በደንብ አያውቅም ."…..በቃ ቤት ሲቃጠል ሳይ ግዜ ሮጬ ወደ ዚህ መጣሁ….ይልቁንስ እኛን ሰውዬ ጠይቃቸው "አለኝና ጥቁር በጥቁር ወደ ለበሱ አዛውንት መራኝ፡፡
ወዲያው ሽማግሌውን በስልኬ እየቀዳሁ ቃለመጠይቁን ሳደርግ ወጣቶቹም ከበቡኝ እና እየተሻሙ መረጃ ይሰጡኝ ጀመር፡፡መረጃውን በጥልቅ ስሜት የሚሰጡኝ ሰው ለእነሱ ምንም ላደረግላቸው የማልችል ሰው ተራ ብሎገር መሆኔን ሳስበው ልቤ ደማ፡፡….ጠየኩ ጠየኩ….የተፈጠረውን ነገር ሲያወሩ ስሰማ …አይኔም ብቻም ሳይሆን ልቤም አነባ….
እነ ያሬዶ ሰውን በየፈርጁ እያሰለፉ በየክፍሉ ይመድባሉ፡፡ ስለ ድስት ይወያያሉ…..ስለእንጀራ ከእናቶች ጋር እቅድ ያወጣሉ….በዚህ ሁሉ ክፋት መሃል እንደዚህ አይነት ኢትዮጲያውያንን ማየት ደግሞ ልብን ይጠግናል፡፡…
አንደኛው አስተባባሪ አጨበጨበ…"አንዴ ስሙኝ" ..አጨበጨበ…፡፡
"አሁን ያላችሁት ት/ቤት ግቢ ውስጥ ነው….ቅድሚያ ለሴቶች ሰጥተን የቻልነውን ያህል በየክፍሉ እንድታርፉ እናደርጋለን…..ሁሉንም ደልድለን ደልድለን የሚተርፍ ካለም ሁለት ሶስትም እያደረግን በየቤታችን እናሳድራችኋለን አይዞአችሁ ወገኖቻችሁ ነን….."
ልቤ በደስታ ስንጥቅ አለ!
መጨረሻ ላይ ያነጋገርኳቸው ሰዎች ድምጽ አሁንም ጆሮዬ ላይ አለ፡፡
እኛ እኮ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡በሊስትሮነት እና በሸማ ሰሪነት የምንኖር ሰዎች ነን.!.
" ..የኔ ቤቴ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል….ግን ከኔም የባሰ አለ ጎረቤቴ አይኔ እያየ አንጀቱ ተዘርግፏል……ጭራሽ ወደ ህክምና ቦታ እንዳናደርሰው ራሱ በስፍራው የነበረው ፖሊስ አልረዳንም"
የተለያየ ልብ ሰባሪ ነገሮች ነገሩኝ፡፡ ከግቢው ስወጣ ያሬድን ቅድም ግን ምን ልታደርግ ነበር ወደ ፎቁ ስር የሮጥከው? ስለው ቀለል አድርጎ "ባይሆን ብቀልበው ብዬ ነበራ" ያለኝ አሁንም አይኔ ላይ አለ፡፡
ከግቢው ስወጣ አስተባባሪዎቹን ዞር ብዬ አየኋቸው ….እጅግ በጣም የሚያስመሰግን ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ሀገር ወዳድ ወጣቶች እባካችሁ ሂዱና አግዟቸው….ሳንቲም ያሏችሁም የምትችሉትን እንጀራም ሆነ ዳቦ ቋጥራችሁ ዛሬም ሆነ ነገ ብትሄዱላቸው የኢትዮጲያ አምላክ ብድራችሁን ይከፍላችኋል፡፡
የነገሩኝን ከስልኬ ላይ ደጋግሜ በሰማሁት ቁጥር ሰውነቴን የሆነ ነገር ውርር ያደርገኛል፡፡መስማት ብቻውን ያማል…. (የሰማሁትን በሙሉ እንደማልጽፍም ይገባችኋል).
ይሄ ሁሉ ነገር ግን የኛ የአዋቂዎቹ ደደብነት ያመጣው "ሂውማን ዲዛስተር" መሆኑን ሳስበው የበለጠ ያመኛል…
እህሀህህህ……
ሰላም አምሹ
ቸር ያሰማን
እህሀህህህ……
ሰላም አምሹ
ቸር ያሰማን
No comments