Latest

እንደዚህ ብንነጋርስ? (ጠገናው ጎሹ)

እንደዚህ ብንነጋርስ?

በተከታታይነትና በረጅሙ ከወጡና እየወጡ ካሉ መጣጥፎች አንዱና ባሳለፍነው ሳምንት ለንባብ በቅቶ ያነበብኩት ክፍል “… ያገኘነውን ታላቅ ስጦታ እንዳናጣ አይናችንን ከፍተን መጠበቅ አለብን!” ይላል። እንዲሁ ከሰማዬ ሰማያት በተአምር የተሰጠን ስጦታ (gift) ነው ወይስ በግለሰቦች (በመሪዎች) የተበረከተልን ስጦታ?  


ከኢህአዴግ ማህፀን ለህዝብ ሲል የተወለደልን ሥጦታ ነው ወይንስ ለዓመታት በተከፈለ እጅግ ግዙፍና መሪር የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ መስዋትነት የተገኘ ስጦታ ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የመጣጥፍ ርእሰ ጉዳይ የተሸከመው ሃሳብ ቀላል አይደለም።

የዚህን መጣጥፍ አቅራቢዎች በግል (in person) ባላውቃቸውም በኢትዮጵያ ዕውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ዕውን ይሆን ዘንድ በየሙያቸው ያደረጉትንና አሁንም እያደረጉ ያሉትን ያላሳለሰ ጥረት (አስተዋፅኦ) በጥሞና ከሚከታተሉና የአገራቸው (የኢትዮጵያ) ጉዳይ ከሚያሳስባቸው የአገሬ ልጆች መካከል አንዱ ነኝ ።

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በኢትዮጵያ እውነትኛና ዘላቂ ነፃነት ፣ የህግ የበላይነትና የጋራ ብልፅግና እውን እንዲሆን በሙያ ክህሎታቸው ተጠቅመው ያደረጉትንና አሁንም እያደረጉ ያሉትን ጥረት (አስተዋፅኦ) ከሚከታተሉና ተገቢ አድናቆት ካላቸው ወገኖቼ መካከል አንዱ ነኝ ።  


ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በባእድ ቋንቋ ተፅፈውና ወደ ወንዜኛ ቋንቋም ተመልሰው (ተተርጉመው) በተከታታይነት እስከአሁን ለአንባቢያን የበቁ እጅግ ረጃጅም ፅሁፎቻቸውን ከሚከታተሉ ወገኖች መካከልም አንዱ ነኝ ።

የታማኝ በየነን ከኪነጥበብ (ከመድረክ ሙያ) ጋር የሰብአዊ መብት መከበር አራማጅነትን ደርቦ በተዋጣለት አኳኋን የመወጣቱን ችሎታና ብቃት በአድናቆትና አክብሮት ከሚመለከቱት ወገኖቼ መካከልም አንዱ ነኝ ።  


 ቀደም ሲል ስለ ለውጥ እንቅስቃሴው ያለውን ምልከታና ተስፋ በተለያዩ አጋጣሚዎችና የመገናኛ ዘዴዎች ሲገልፅ እና በቅርቡ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ወቅት በተለይም በኮንቬንሽን ማእከል የሆነውን ሁሉ በአካል ተገኝቼ ባይሆንም የዘመኑ የመገናኛ ቴክኖሎጅ ምስጋና ይግባውና በጥሞና ከተከታተሉት ብዙ ወገኖቼ መካካልም አንዱ ነኘ ።

አስቀድሜ ይህን ለማለት የወደድኩት የሂሳዊ አስተያየቴ (critical comment) መነሻና መዳረሻ እንዲያው በደምሳሳው (blindly and irrationally) አለመሆኑን ለማስገንዘብ እንጅ የፕሮፌሰር አለማየሁንም ሆነ የክቲቪስት/አርቲስት ታማኝን ጥረትና በጎ አስተዋፅኦ በቅን ልቦና እና በሚዛናዊ ህሊና የሚከታተል ሁሉ አይገነዘበውም ከሚል መነሻ አይደለም ። 


በሌላ አባባል የዚህ ፅሁፌ ዓላማ በአወንታዊነት በሚታወቅ (በሚታይ) ነገር ውስጥ ልንተቸው የሚገባን ጉዳይ ሲኖርበግልፅና በቀጥታ መነጋገር ተገቢ ወይም ትክክል በመሆኑ በዚሁ መሠረት ሂሳዊ አስተያየቴን ለመግለፅ እንጅ የሚታወቅን የግለሰቦች ወይም የቡድኖች ማንነትና አስተዋፅኦ መልሶ መላልሶ በመንገር አንባቢን ለማሰልቸት አይደለም ።

ወደ ዝርዝር የርእሰ ጉዳዬ አስተያየት ከማለፌ በፊት እራሴን እንደሚከተለው ግልፅ ላድርግ ።

  • ሃሳብን (አስተሳሰብን) እንጅ የግል ሰብእናን እስከአልተዳፈርኩ ድረስ አስተያየቴ አካፋን አካፋ (call it as it is) እስከ ማለት ይሄዳል ። 

ይህ እምነቴ ደግሞ ለሁሉም የሚገባውን አክብሮት ከመስጠትና ጉድለቶችን (ድክመቶቸን) ከሚከሰቱበት ጊዜና ሁኔታ አንፃር ለማየት ከመሞከር አልፎ የሥራ አይነትንና ደረጃን ፣ የትምህርት ደረጃን ፣የዕድሜና የተሞክሮ ባለፀጋነትን ፣ የአለማዊውም ሆነ የሃይማኖታዊ ሥልጣንን ፣ ወዳጅ መሆንን ወይም አለመሆንን ፣ በህዝብ ታዋቂነትን ፣ ወዘተ መመዘኛ አያደርግም ።

ለዘመናት ከአገዛዝ ወደ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ካላቻልንባቸውና አሁንም ከዚህ አዙሪት ለመውጣት በተስፋና በሥጋት ,መካከል እንድንገኝ ካደረጉን ምክንያቶች አንዱ እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የሆኑ የአገር (የህዝብ) ጉዳዮችን በእንዲህ ዓይነት መመዘኛዎች ተፅዕኖ ሥር የማዋላችን የፖለቲካ ባህል ፣ አስተሳሰብና ልማድ ስለመሆኑ የሚያጠያይቀን አይመስለኝም። እናም እንዲህ አይነት ልፍስፍስና የማይጠቅሙ (clumsy and unproductive) መመዘኛዎችን አልጠቀምም ።
  • አንባቢያን አስተያየቴን እኔ ባየሁበት መንገድና ሁኔታ ያዩታል የሚል የደንቆሮ አመለካከትም ጨርሶ የለኝም ።

ለዘመናት የዘለቅንበትና አሁንም የለውጥ ፍላጎታችንና ተግባራዊ እርምጃችን እንዳይገናኙ በማድረግ በብርቱ እየተፈታተነን ያለው ይኸው “የኔ የሆነ አስተሳሰብ (አመለካከት) ሁሉ ትክክል ነው” የሚለው በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረና ጋግርታም የፖለቲካ አስተሳሰባችን መሆኑ አንድና ሁለት የለውም ።

እናም ይህን አስተያየቴን ከሚያነቡ አንባብያን መካከል (ምናልባትም ብዙዎቹ) “እንዴት በፕሮፌሰር አለማየሁና በታማኝ ላይ” በሚል እስከ ውግዘትና እርግማን የሚሄድ ምላሽ አይሞከርም የሚል የቂልነትና የግብዝነት እሳቤ የለኝም። 


እንኳን አሁን ወደ እውነተኛው ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ገና በቅጡ ወይም በአስተማማኝ ዳዴ ወይም ወፌ ቆመች ባላልንበት ሁኔታ ይቅርና ተሳክቶልን ብንሸጋገርም በዚህ ረገድ የሚኖርብን የቤት ሥራ በስፋቱም ሆነ በጥልቀቱ በእጅጉ ከባድ መሆኑን ማነኛውም የአገሩ (የወገኑ) ጉዳይ የሚያሳስበው የአገሬ ሰው የሚገነዘበውን ያህል እገነዘባለሁና “እንዴት ለለውጥ ሐዋርያው አመራርና ቡድን ጠንካራና ሙሉ ድጋፋቸውን የሰጡና የሚሰጡ ታዋቂ ሰዎች ሃሳብ ይተቻል?” የሚል ተቃውሞ ቢሰነዘር ከቶውንም አይገርመኝም ።  

ይህ አይነቱ አስተሳሰባችን (አመለካከታችን) በሁለንተናችን የዓለም ጭራዎችና በምፅዋት አዳሪዎች ካደረጉን እጅግ ከባደ የፖለቲካ ፈተናዎቻችን አንዱ መሆኑን ግን በሚገባ እረዳለሁ።
  • እንዴትና ወዴት እየሄድን ነው ? 
  • የለውጥ እንቅስቃሴውስ በጥናትና እና በእቅድ የሚመራ ነው ወይስ በፖለቲካ ትኩሳት ዘመቻ ? 
  • ለመሆኑ ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር የሚመጣጠን የሥልጣን ተዋረድና ክፍፍል እንዲኖር እያገዝን ነው ወይስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና የለውጥ አራማጅ በምንላቸው ዙሪያ ወደ አምልኮ (cult) የሚጠጋ የፖለቲካ ሰብእና እየፈጠርን ነው?  
  • ምን ያህል ተሳክቶልን ምን ያህል ወደቅን ?
  • የሥራዎቻችን መለኪያዎቸስ ምን ያህል ከፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም ማጀቢያነት ነፃ ናቸው ? 
  • ስህተትንና ውድቀትን ለማረምስ ምን ያህል ዝግጁዎችና ቀልጣፎች ነን? 
  • ቁልሉንና እጅግ አስቸጋሪ የቤት ሥራችንን እንደነገሩ እያድበሰበስን በሌላ በኩል ግን ያስገኘናትን አወንታዊ ውጤት እያገዘፍን ወይም እያጋነን ድርሰት መሰል ሪፖርት ወይም መግለጫ ማዥጎድጎዳችንስ የት ያደርሰናል?  
  • የስኬት ወይም የውድቅት መለኪያዎቻችን ምን ያህል ከፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም ማጀቢያነት ነፃ ናቸው ? 
  • ገና ትርጉም ባለው ተግባር የተፈተነ ነፃነትና አቅም ያላቸው ተቋማት በሌሉበትስ ዛሬን በተገቢው መንገድ ተረድቶና ገምግሞ ለተሻለ ነገና ከነገ ወዲያ ማስተላለፍ እንዴት ይቻላል ? ወዘተ 

ብለን ሳንጠይቅ በፖለቲከኞች ዙሪያ እየተኮለኮልን ሆያ ሆዬ እና ጎሮ ወሸባዬ የማለቱን ልማድ በቅጡ ለማድረግና የተሻለ ሥራ ሠርተን ለመገኘት ረጅምና አስቸጋሪ መንገድ መጓዝ እንደሚኖርብን ስለምገነዘብ “እገሌንና እነገሌን ለቀቅ” የሚል ከድንቁርና ወይም ከግብዝነት የሚመነጭ ማስጠንቀቂያ ቢጤ ቢሰነዘርም ጨርሶ አይደንቀኝም።  

 እጅግ ግዙፍነት ፣ ውስብስብነትና ጥልቅ ያለው ፈታኝ ጉዳይ የመሆኑ ጉዳይ ግን እንደማነኛውም የአገሩና የወገኑ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የአገሬ ልጅ ያሳስበኛል ።

የማንወደውን (የማንፈልገውን) ሃሳብና ድርጊት ያራምዳሉ የምንላቸውን አካላት (ፖለቲከኞች) ቢቻል በሃሳብ ማሸነፍና ወደ እሚበጀው ነገር ለመመለስ ፣ ካልሆነ ግን ትውልድ አስተማሪ በሆነ ህግና ፍትህ አማካኝነት ድል ለማድረግ እልህ አስጨራሽ ትግል (ጥረት) ከማድረግ ይልቅ በጅምላ ውግዘትና በእደመስስሃለሁ/እደመስስሻለሁ ፉከራ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይቻላል ከሚል አስተሳሰብ ገና ያለመውጣታችን አንደኛው ምክንያት ከፖለቲካ ባህላችን ወደ ኋላ መቅረት አንፃር ሲታይ የሚገርም አይሆንም ። ከዚህ ለመውጣት የምናደርገው ጥረት ደካማነት ግን በእጅጉ የሚያሳስብ መሆኑን ተቀብለንና አምነን ልፍስፍስ ምክንያት (ሰበብ) ሳንደረድር የመረባረቡ አስፈላነት ጊዜ የማይሰጠው የቤት ሥራችን ሙሆኑን በሚገባ መገንዘብ የኖርብናል ብየ አምናለሁ ።

እንዴት ከዚህ ክፉ አዙሪት እንውጣ? የሚለው ግን በእጅጉ ያሳስባል ወይም ያስጨንቃል ። ምክንያቱም ይህ አይነቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ አዙሪት አብዝተን የምንደሰኩርለትን በይቅርታና በብሔራዊ እርቅ ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመሸጋገር ራዕይ እውን ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው አፍራሽ ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ነውና ።


ለዚህም ነው በዚህ ረገድ የሚጠብቀን የቤት ሥራ እጅግ ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ የሚሆነው ። ከትኩረቶችና ጥንቃቄዎች መካከል አነዱና ከቅን ህሊና በስተቀር ብዙም ዋጋ የማያስከፍለው በስሜታዊነት የፖለቲካ ትኩሳት በጅምላ (በደምሳሳው) የመደገፍ ወይም የመቃወም አስቀያሚ ልማድን ቢቻል በማስወገድ ፧ ካልሆነ ግን ቢያንስ በመቆጣጠር ለለውጥ እንቅሳቃሴው ስኬታማነት የበኩልን አስተዋፅኦ ማድረግ ነው።

ለዚህ ነው “እንደ ፕሮፌሰር አለማየሁና አክቲቪስት /አርቲስት ታማኝ የመሳሰሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የለውጥ አራማጅ ቡድኑ እውቅ ደጋፊዎችንና ድጋፍ አስተባባሪዎችን ለቀቅ”የሚለው አስተሳሰብ (አመለካከት) ልፍስፍስና የማይጠቅም (clumsy and unproductive) የሚሆነው ።

ሐ) በሌላ በኩል ግን ይህ አስተያቴ ቢያንስ እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ከባድ በሆነው ወቅታዊ የአገራችን ሁለንተናዊ ፈተና አፈታት ላይ ያተኮረ ሥራ ለመሥራትና የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግራ ወይም ከቀኝ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አቅጣጫ የሚነሱ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን እንደ አመጣጣቸው ለማስተናገድና ለህዝብ (ለአገር) የሚበጅ አቅጣጫ አስይዞ ተፈላጊውንና ዘላቂውን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ለማድረግ ከሚደረግ የጋራ ጥረት አንፃር ይጠቅማል የሚል እምንት አለኝ ።

በሌላ አገላለፅ ይህን ታሪካዊ ሊሰኝ የሚችል አጋጣሚ በመደማመጥ ፣ በተገቢው ትእግሥትና መከባበር ፣ ልጠይቅህ/ልጠይቅሽ ወይም እንጠያየቅ በመባባል ፣ ከአፍንጫ ሥር አልፎ በሚሄድና ነገን የተሻለ ለማድረግ በሚያስችል አስተሳሰብ ፣ በከፍተኛ ትእግስትና ጥበባዊ የፖለቲካ ሰብእና ፣ ከቁጥጥር ውጭ ባልሆነና በጤናማ ስሜታዊነት ፣ መሬት ላይ ለመርገጥ በሚያስችል ተስፈኝነት ፣ የትም አታመልጥም/ አታመልጭም በሚል የግብዝነትና የብሽሽቅ ፖቲካዊ አስተሳሰብና ቁመና ሳይሆን 


ደካማና ክፉ ሃሳብን በጠንካራና በጎ ሃሳብ በማሸነፍ ፣ በሃሳብ ሲሸነፍ/ስትሸነፍ ዱላ የሚያነሳውን/የምታነሳዋን በህግ የበላይነት በማሸነፍ ፣ የምንደግፈውን “በጅምላ (በደምሳሳው) እንደግፈው” እና የምንቃወመውን ደግሞ “በጅምላ እንደምስሰው” ከሚል በእጅጉ ጋግርታምና አጥፊ የፖለቲካ አስተሳሰብ በራቀ አካሄድ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ጊዜውን ካልተሻማን ነገራችን ሁሉ ታጥቦ ጭቃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም የከፋ እንደማይሆን ምንም አሳማኝ ምክንያት የለንም ።

በጎውንም ሆነ ክፉውን ወይም የምንደግፈውንም ሆነ የምንቃወመውን እንደየባህሪው ፣ እንደየልማቱና ጥፋቱ ደረጃ እና በለውጥ ሂደት ላይ እንደሚያስከትለው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ የተፅዕኖ ክብደትና ቅለት በሚዛናዊነትና በምክንያታዊነት ከማስተናገድ ይልቅ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ እየተለጠጥን የመተሻሸት (የመላላስ) ወይም የመላተም (የመጠፋፋት ) የፖለቲካ ታሪካችንን ፣ ባህላችንንና አስተሳሰባችንን የእያንዳዳችንን የህሊና ነፃነት በሚያረጋግጥ የትግል ወኔ መታገል ይኖርብናል ። ይህን ሳናደርግ የፍቅርና የሰላም ትርጉምና ጠቀሜታ አዲስ የቋንቋ ግኝትእስኪመስል ድረስ በምናዥጎደጉደው ቃለ ነቢብ (rhetoric/theory) ከጊዚያዊ ደስታ መሰልስሜት (amusement and excitement ) በላይ ብዙ እርቀት አይወስደንም ።

በጥልቅ ሂደት ( reformism) ላይ ያለው የኢህአዴግ ፖለቲከኞች (መሪዎች) መሬት ላይ ያለውን ግዙፍና ውስብስብ የቤት ሥራቸውን የሚገልፁበት ቋንቋ የፖለቲካ ቁመናቸውን እንዳይጎረብጠው ወይም እንዳያንገጫግጨው በእጅጉ እየተጠነቀቁ ፣ በሌላ በኩል ግን አስመዘገብነው ወይም አከናወነው የሚሉትን ሁሉ ይገልፅላቸው ዘንድ እጅግ ከፍተኛውን የማነፃፀሪያ ቋንቋ (superlative ) እያዥጎደጎዱ ከመከራውና ከውርደቱ የዘመን ርዝመት ፣ ስፋትና ጥልቀት የተነሳ በጎ ነገር በሰማና ባየ ቁጥር “ተአምር ተሠራ” የሚለውን የዋህ የአገሬ ህዝብ “ባልበላና ባልጠጣም ረካሁ ፣ ባለብስም ሞቀኝ ፣ ባይደላኝም አማረብኝ ፣ ሰላሜን የነሳኝ ሁሉ ተሸነፈና ሰላሜን እስከወዲያኛው (ለዘለቄታው) አገኘሁ” ብሎ እራሱን እንዲያሳምን (እንዲያታልል) ይጋብዙታል ።

ለዚህ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “እድሜ ለተአምረኛው ዶ/ር አብይ አህመድ፥ ከእንግዴህ የተቃውሞ ፖለቲካ ፖለቲከኛ ሁሉ ደህና ሰንብች” የሚል አንድምታ ያለው ዝንባሌና አስተሳሰብ መስማት እጅግ የተለመደ እየሆነ የመጣው ። የመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የመሆንና ያለመሆን እጅግ ከባዱ ፈተና የሚመነጨውም ከእንዲህ አይነት ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን ከተሳነው ልማድና የአስተሳሰብ ድህነት ነው።

በአገር ውስጥ በህጋዊ ( በገዥው ቡድን) ፈቃድ ህልውናቸውን አስጠብቀው የቆዩት ፣ ቀደም ሲል ከለውጥ አራማጁ አመራር ቡራኬ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የገቡት እና በአንፃራዊ እይታ በሁለንተናዊ ትግል ላይ የቆዩና በቅርቡ ለመግባት ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ተቀዋሚ የፖለቲካ አካላት ከሚገጥሟቸው ከባድ ፈተናዎች አንዱ “ከእንግዴህ ድነቴንም ሆነ ሞቴን ከዶ/ር አብይ አህመድ ( በንስሃ ታጥቦ ከዳነው ኢህአዴግ) ጋር ያድርገው” የሚለው እራስ ከራስነት ዝቅ የሚያደርግ (self-defeating and self- dehumanizing) ፖለቲካዊና ሥነ-ልቦናዊ ድህነት ነው ።

መልካም እድሎች ከሌላው ጊዜ እጅግ በተሻለ መጠንና አይነት ደረጃ ላይ ቢገኙም እጅግ ዘርፈ ብዙነት ፣ ስፋት እና ጥልቅ ባላቸው ፈታኝ ሁኔታዎች በተበተቡበት ሁኔታ ውስጥ ባለንበት በዚህ ወቅት ወደ ፍፁምነት የተጠጋ የውዳሴና የአሜን ፖለቲካ በተለይ ተማርኩና ተመራመርኩ በሚለው የህብረተሰብ ክፍል ያለማሳለስ ሲስተጋባ በምን አገባኝነት ወይም መስሎ በመኖር ሰብዕና ማለፍ ቢያንስ ለሞራል (ለህሊና) የሚመቸ ነገር አይደለም ። 


አዎ ! የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ለውጥ በተከሰተ ቁጥር በነፃነት ፣ በምክንያታዊነት ፣ በሚዛናዊነት ፣ ከትናንት ተነስቶ ዛሬንነና ከዛሬ ተነስቶ ነገን ማየት በሚያስችል ፣ እና ለትውልድ በሚተርፍ የእውቀትና የሞራል ልእልና ላይ መቆም እያቃተው ፖለቲከኞች በየአደባባዩና በየስብሰባ አዳራሹ ሰብስበው ይበቃቸውን ያህል “ከአስተማሩት” በኋላ “ከፈለግህ ጥያቄ ጠይቀን” ሲሉት ጨርሶ ምሁርነትን በማይመጥን አኳኋን ከላይ ከታች ሲረግጥ ስብሰባው ያልቅና ለመሆኑ ለውጥን እውነተኛ ለውጥ ሊያደርግ የሚችል ቁም ነገር አገኘህበት ወይ ? ሲባል ፖለቲከኞች የነገሩትን መልሶ ይናገራል ወይም ይፅፋል ። ከዘመናት የመከራና የውርደት ቆይታ በኋላም በእንዲህ አይነት እጅግ በዘቀጠ ሁኔታ ውስጥ ራስን ማግኘት በእጅጉ ሊያሳፍረንና በጊዜ ልናስተካክለው ይገባል ።

እንደሰው ሰው ሆነን ፧ እንደዜጋ መብት አስከብረን እና እንደባለሙያ ኮርተንና አኩርተን የምንኖርበት ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን መሆን ካለበበት ትክክለኛው አካሄድ ይኸው ብቻ ነው ።

ይህን ለምን እንደምል ማሳያ የሚሆኑ ነጥቦችን እንደሚከተለው ላቅርባቸው ።


እንደእኔ ግንዛቤና አረዳድ በፕሮፌሰር አለማየሁ ረጃጅምና ተከታታይ ፀሁፎች ውስጥ አጠቃላይ መልካም ዝንባሌን (good intention) ካልሆነ በስተቀር ከላይ ለማሳየት ከሞከርኳቸው ሂሳዊ አካሄዶችና ትንታኔዎች አንፃር ለውጡንም ሆነ የለውጥ አራማጅ መሪዎችን የማገዝ አቅማቸው የተዋጣላቸው አይደሉም ።


አንብበን ከጨረስን በኋላ የተረዳነው ዋና ሃሳብ (መልእክት) ምን እንደሆነ እራሳችን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ “ውዳሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና መርገመ የለውጥ አደናቃፊ ሃይሎች “ የሚል ነው ። ይህ አይነቱ አቀራረብና አካሄድ ለረጅም ጊዜ በእጅጉ ከገዘፈው ፣ ሥር ከሰደደው ፣ ከተወሳሰበውና በተለይ ደግሞ ላለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት በዘር አጥንት ቆጠራና በመንደር ማንነት ከተመረዘው አደገኛ የፖለቲካ ሥርዓት ለመላቀቅ የሚደረገውን እጅግ ውስብስብና እልህ አስጨራሽ ትግል ጨርሶ የሚመጥን አይደለም ።

ፖለቲከኞችን ወደ እንከን የለሽነት በሚያስጠጋ የውዳሴ ድርሰት ማንቆለጳጰስ ለትክክለኛና ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚደረግን እልህ አስጨራሽ ትግል ይጎዳል እንጅ አይጠቅምም ።ይህ አይነቱ አስተሳሰብና አካሄድ በከፍተኛ ጥንቃቄ ፣በጥበብ ፣ በአርቆ አሳቢነት ፣ በእልህ አስጨራሽ ትዕግሥት ፣ በጋራ መግባባት/ምክክር ፣ በተሟላ ተሳትፎ እና በህግ (በፍትህ) የበላይነት ላይ ተመሥርቶ የሽግግር ሂደትን ወደ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ግንባታ በሚፈለገው መጠን ፣ ይዘትና የጊዜ ማዕቀፍ እውን ማድረግ አያስችልም ።


በዚህ ተስፋና ሥጋት በተቀላቀሉበት የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ ከእንደ እኔ አይነቱ ፊደል ከመቁጠር ካልዘለለው ጀምሮ በሊቀ ልሂቅነትና በተሞክሮ በልፅጊያለሁ እስከሚለው የማህበረሰብ ክፍል ድረስ “ጎሽ መማርና ማወቅ እንዲህ ነው እንጅ!” በሚያሰኝ አኳኋን ከአሮጌውና ከክፉው ሥርዓት ወደ አዲሱና በጎው ሥርዓት የሚያሸጋግር የአስተሳሰብና የድርጊት እመርታ (breakthrough) አይታይበትም ። እንደ አለመታደል ሆኖ ሳይሆን በራስ ቅጥ ያጣ ድክመት (ውድቀት) ምክንያት ሰብሮ ለመውጣት ያልተቻለ አዙሪት ማለት ይኸው ነው ። 


ይህ የህበረተሰብ ክፍል ሚዛናዊና ገንቢ በሆነ ሂሳዊ ምልከታ ፣ ትንታኔና በድርጅታዊ ሃይል በተሳስረ ቁመና የለውጥ እንቅስቃሴውን ከማገዝ ይልቅ የለውጥ አራማጅ ፖለቲከኞችን ” በተአምር የተገኙ ተአምር ሠሪዎች “ በሚል እያሞካሼ ህዝብን ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን ፖለቲከኞችንም ያሳስታል (ያዘናጋል) ። የምንነጋገረው በፈታኝ ሁኔታዎች ከተወጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ (የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ) አንፃር ከሆነ እውነታው ይኸው ነው።

በዚህ ሰሞን አንጋፋው ምሁር ፕሮፌስር መስፍን ወ/ማርያም በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በአፅንኦትና በአግራሞት ከተናገሯቸው ነጥቦች መካከል ሁለቱ ሀ) በዚህ ስብሰባ ላይ እርሳቸው ተጋብዘው መገኘታቸው ኢትዮጵያ የደረሰችበትን መልካም ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ እንዳሳያቸው ለ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ለማ መገርሳ “ከሰማይ የተሰጡን” ስለመሆናቸውና ደግፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሚሉ መሆናቸውን በጥሞና ታዝቤያለሁ።

እንዲህ አይነት እራስን የሁሉም ጥሩ ነገር ማመሳከሪያ የሚያደርግ የግብዝነት አስተሳሰብ (arrogance) እና ፖለቲከኞች “ከሰማየ ሰማየት የተላኩልህ ናቸው” የሚል የፖለቲካ ትርክት ለትክክለኛው የምሁርነት ባህሪና እሴትም ሆነ የዚህ ዘመን ትውልድ ለሚያስፈልገው ግንዛቤና እውቀት ጨርሶ አይመጥንም ። 


በእልህ አስጨራሽ ተጋድሎና በከፍተኛ መስዋዕትነት ላይ የፈጣሪ ድጋፍ ታክሎበት ወደ ኋላ የማይመለሰውን የለውጥ ማዕበል ለራሳቸውም ሆነ ለአገር የሚበጅ መሆኑን ተገንዝበው ወደ መሪነት የመጡትን ፖለቲከኞች ከጠንካራና ገንቢ ሂሳዊ አስተያየት ጋር እንደግፍ ማለት ተገቢ ነው ።  

የምንደግፋቸውም በጥልቅ ተሃድሶ (reform) ስም መሻገሪያዎችም ሆነ አሻጋሪዎች እኛው ነንና እየመጣቸሁ ተደመሩ እንዲሉን ሳይሆን እንደዜጋ ፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ፣ እንደ የሲቭል ድርጅት ፧ እንደሙያ ማህበር ፣ ወዘተ ባለድርሻ የሆነንና የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚልን አካል ሁሉ በእኩልነትና በነፃነት ከሂደት እስከ ውጤት ያሳተፈ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ መሆኑን በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ አስረግጦ የማይናገርን (የማያስገነዝብን ) ምሁር የምሁረነትን እውቀት (intellect) እውነተኛ ትርጉምንና እሴትነትን ወይም ዓላማን ከምር እንዲመረምር በግልፅና በቀጥታ መንገር ያስፈልጋል ። ለዚህ ደግሞ አገራችን አሁን ከምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በላይ ሊነግረን የሚችል መሪር ሃቅ የለም ።

የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት የሚባል ጨርሶ የማይታወቅባትን እንደኛ አይነት አገር በተፈላጊው መጠን ፣ ጥራትና የጊዜ ማእቀፍ ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሸጋገር ካለብን ለፖለቲካ ማባዣ ሲባል ያልሆነውን ሆነና ያልሆነውን ሆንን ብሎ ከማጋነን ቅዠት (illusion) ለመውጣት ብርቱ ትግል ማድረግ ይኖርብናል ።

የድጋፍ አሰጣጣችንና የተቃውሞ አቀራረባችን እጅግ ኋላ ቀር በሆነው የረጅም ዘመን የፖለቲካ ታሪካችን እና በተለይ ደግሞ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በዘለቀው የህወሃት/ኢህአዴግ እጅግ የከፋና የከረፋ አገዛዝ ምክንያት በእጅጉ የተስፋፋውን ፣ የተወሳሰበውንና ሥር የሰደደውን የአገራችን ሁለንተናዊ ቀውስ በተዋጣለት አኳኋን ለመፍታት የሚያስችል ጥራት ፣ ፅናትና ጉልበት የለውም ።  


 በአንድ በኩል የምንደግፋቸውን አካላት (ፖለቲከኞች) በውዳሴ ፖለቲካ ማወደስ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምንቃወማቸውን አካላት ደምሳሳ በሆነ መርገመ ፖለቲካ መራገም ወንዝ የሚያሻግር የፖለቲካ ፋይዳ አይደለም ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ወቅት የታዘብነው አይነት ጨርሶ ከልክ ያለፈ የስሜታዊነት ትዕይንት ለምናካሂደው እጅግ ከባድና ውስብስብ የለውጥ እንቅስቃሴ አይመጥንምና ሊታረም ይገባል።


ከዘመናት የመከራና የውርደት ቀንበር ለመላቀቅ ገና በተስፋና በከባድ ሥጋት መካከል የምትገኝ የገሃዱ ዓለም ኢትዮጵያ መሪ (ፖለቲከኛ) ሳይሆን ከሞት የተነሳው ክርስቶስ የተዘጋው በር ሳይከፍት በመሃላቸው ሆኖ “ሰላም ለእናንተ ይሁን !” ብሎ የተከሰተልን በሚመስል አኳኋን አቅላችን (አመዛዛኝ ህሊናችን) እስከመሳት የደረስንበት የአደባባይ (የአዳራሽ) እና የመድረክ ትዕይንት አሁን ላለንበት እጅግ ፈታኝ ሁለንተናዊ እውነታ ጨርሶ የሚመጥን አይደለምና በቅንነትና በሰለጠነ የፖለቲካ ሰብእና ተቀብለን ከዛሬ ጀምሮ እንማርበት ።

የለውጥ አራማጅ መሪዎችን በሚመጥናቸው ልክ ማበረታታትና ማክበር በጣም ትክክል ነው ። “ለሩብ ምዕተ ዓመት ስትረግጡትና ስታስረግጡት የነበረው የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ቆጭቷችሁ የህዝብን ትግል ስለተቀላቀላችሁና የምትችሉትን በማድረግ ላይ በመሆናችሁ ተገቢው ድጋፍና ከበሬታ ይገባችኋል “ ማለት ተገቢ ነው ። ከዚህ አልፎ ግን በእግራቸው ሥር መነጠፍና የምትሉትንና ያዘዛችሁንን ሁሉ በፍፁምነት አሜን ተቀብለን እንፈፅማለንና እናስፈፅማለን ብሎ መማልና መገዘት የራስ የሆነን ኩራትና በራስ የመተማመን ፅናትን ሳናወቀው ( unintentionally ወይም በሌላ የራሳችን ፍላጎት (ulterriour motive) ምክንያት ዝቅ ማድረግ ነውና በድፍረት ልናረመው ይገባል።  


ለፖለቲከኞችም የተሳሳተ መልእክት ያስተላልፋልና በጊዜ እርምት ሊደረግበት ይገባል። “የአሁኑ መሪዎች (ፖለቲከኞች) ከፈጣሪ የተላኩ በመሆናቸው እንዲህ አይነት የፖለቲካ ሰብእና (ባህሪ) የላቸውምና አያሳስብም” የምንል ከሆነ ደግሞ የምንኖረው በገሃዱ ፖለቲካ ዓለም ሳይሆን በምናባዊው ወይም በቅዥቱ የፖለቲካ ዓለም ነውና ራሱን የቻለ ከባድ የአስተሳሰብ ለውጥ ትግል ይጠይቃል ።

ፕሮፌሰር አለማየሁ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ትርጉም ያለው ሂሳዊ አስተያየት በማይንፀባረቅባቸው ረጃጅምና ተከታታይ ፅሁፎቻቸው ከማወደስ አልፈው ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ምትክ ስለማይገኝለት የተቀዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችንና የሲቭል ማህበራትን ከሂደት እስከ ውጤት የመሳተፍና የማሳተፍ አስፈላጊነት እንኳን ትርጉም ባለው መንገድ ሊተነትኑ በቅጡም አያነሱትም ።  

ለጠቅላይ ሚኒስትሩም “ጠቅልላችሁ ግቡና ተደመሩ” ከሚል የጅምላ ጥሪ ያለፈ በዚህ ረገድ ምን ዓይነት ስትራቴጅና እቅድ እንዳላቸው ሂሳዊ ጥያቄ ለማንሳት አልፈለጉም ወይም አልደፈሩም ። ለዚህ ነው እንዲህ አይነት በእጅጉ የተንጋደደ (የተንሻፈፈ) የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ከየትኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ይምጣ ተጠየቅና እንጠያየቅ መባል ያለበት ።

ለመሆኑ የለውጡን እንቅስቃሴ በመሪነት የተቀላቀሉት ፖለቲከኞች የህዝብ እምቢተኝነቱ በተለመደ የማስተንፈሻ ስልትና የማኮላሻ የሃይል እርምጃ የሚገታ ስለመሆኑ እርግጠኞች ቢሆኑ ኖሮ ግፍና መከራ ይብቃ ብለው ወደፊት ይመጡ ነበር ብሎ ለማመን የሚያስችል ተጨባጭ መረጃ አለን እንዴ? አነሳሳቸውስ በስፋትና በጥልቀት የታሰበበት ፣ የተጠና ፣ የታቀደ እና ከብሶት ከሚነሳ የጅላ ተቃውሞ አልፎ ትርጉም ባለው እና ከጎሳና ከመንደር ባለፈ ድርጅታዊ መረብ የታገዘ ነበር ብሎ ለማሳመን የሚያስችል ግልፅ ወይም የሚጨበጥ ማሳመኛ አለን እንዴ ?

የለውጡ እንቅስቃሴ ከመነሻው በዚህ አይነት እጅግ መሠረታዊ ሁኔታዎች የታጀበ (የታገዘ) ቢሆን ኖሮ ባየነውና አሁንም እያየነው ባለነው መንግሥት የሚባል አካል የለም ወይ በሚያሰኝ ሥርዓተ አልበኝነት ባልተሸማቀቅን ነበር።


በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሆነውና እየሆነ ያለው ከእኛ አልፎ የዓለም የአደባባይ ሚስጥር ስለሆን ብዙ ማለት አያስፈልገኝም ። በእጅጎ የሚገርመው ደግሞ ምሁሮቻችን ከዚህ ክፉ አዙሪት መውጣት የሚያስችል ሂሳዊ ትንታኔና የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ከማተኮር ይልቅ አሰልች የሆነና የተለመደ የፀረ-ለውጥ ሃይሎች ሰበብ (execuse) በመደርደር መሪዎችን እንከን የለሽ እያሉ የማሞካሸት ፖለቲካ ውስጥ የመጠመዳቸው አባዜ ነው።

ሌላውና በፖለቲካ አስተሳሰባችን ወደ ታች መውረዳችን የሚያሳየው ስለአስቸጋሪውና ውስብስቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስንነጋገር ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከመንሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጥንካሬና ድክመት አንፃር ሳይሆን ዶ/ር አብይ አህመድ፧ ለማ መገርሳ ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ደመቀ መኮንን ፣ ወዘተ ማለቱን ልማድ ስለአደረግነው ህዝቡ እንዚህን ፖለቲከኞች “ሲሆን በአይኔ ካላየኋቸው ቢያንስ ግን ድምፃቸውን ካልሰማሁ ሰማይ እንደባርኔጣ ይደፋብኛል” የሚል ፖለቲከኞችን የማምለክ አደገኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ግንባታ ፀር የሆነ አስተሳሰብ ሰለባ እያደረግነው እንደሆነ በግልፅ የሚሰማና የሚታይ እውነታ የመሆኑ ጉዳይ ነው ።  


ይህ እጅግ የተሳሳተና አደገኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ በአግባቡና በወቅቱ መታረም ካለበት ትክክለኛው የመፍትሄ ሃሳብ መሪዎች “በሁሉም ሥራ እና ቦታ እኔ/እኛ ከሌለሁበት/ከሌለንበት” ከሚል የግብዝነት ፖለቲካ ወጥተው ተገቢውን ሥልጣንና ተግባር ለተገቢው ባለሥልጣንና አካል (ተቋም) የማከፋፈሉን ፖለቲካ ባይወዱትም እንዲላመዱት መምከርና እንደአስፈላጊነቱም መሞገትን ግድ ይላል ።

አንድ ወይም ጥቂት ፖለቲካኞችን የማምለክ ፖለቲካ ድንቁርናን ጨርሶ ማስቀረት ባይቻልም በቅጡ ማድረግ የሚቻለው የየግል የሥልጣን ፍላጎትን (excessive egoን) ተቆጣጥሮ ከሥር ወይም ከጎን የሚገኙ የሥራ ባልደረቦቸና ባለሙያች በማነኛውም አስፈላጊ ጊዜና ሁኔታ ከፍተኛውን የሥልጣን ቦታ በሃላፊነትና በተጠያቂነት ተክተው እንዲሠሩ በሚያስችል ሁኔታ በማብቃትና ዝግጁ በማድረግ ነው ።ይህን ግን በዚህ ባሳለፍናቸው የለውጥ ሂደት ወራት ለማየትና ለመመስከር አልቻልንም ።

እጅግ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ምሁሮቻችን ጨምሮ በወቅቱ ጉዳይ ላይ ሃሳብ አለኝ የሚለው አብዛኛው የገሬ ሰው በዚህ ረገድ ካለበት ድክመት ለመውጣት የሚያግዝ የመፍትሄ ሃሳብ ማመንጨትና ማበርከት አለተቻለውም ። ለዚህ ነው ምሁሮቻችን ጨምሮ አብዛኞቻችን የዋሁ የአገሬ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከስብሰባ አዳራሽ፣ ከአደባባይ ውሎ እና ከሚዲያ እይታ በታጡ ቁጥር “ሰማይ ተደፋብኝ” ሲል አብረን “እኛም ተደፍቶብናል። የፀረ-ለውጥ ሃይሎች ተጠርጣሪዎቻችን ናቸው” የሚል እጅግ የዘቀጠ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ የምንሆነው ።

የፕሮፌሰር አለማየሁ በርካታና ረጃጅም መጣጥፎችና አሁን ከሰሞኑ ደግሞ የአርቲስት/አክቲቪስት ታማኝ ስም ታክሎባቸው የሚወጡ ፅሁፎች ውስብስቡንና አስቸጋሪውን የፖለቲካ ፈተናችን ለመወጣት የሚጠብቀንን ሃላፊነት ጥብብና ሚዛናዊነት በተሞላበት አኳኋን እንድንወጣ የሚያግዙን ሳይሆኑ “ከተአምረኞቹ የለውጥ አራማጅ መሪዎች ጋር ተደመሩ ወይም ለመደመር ተሽቀዳደሙ” የሚል አዋጅ የሚነግሩ ናቸው ።  


እጅግ አብዛኛው ( majority) የአገሬ ምሁር “የእለት እንጀራየን አታሳጡኝ እንጅ የማላወቀውን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቴን ደስ ካላችሁ አክብሩልኝ ካልሆነም ምንም አይደለም” በሚል አይነት ማንነት በተሸበበት አገር የፕሮፌሰር አለማየሁና መሰል ምሁራን የማያሳልስ ጥረት ብርቅየ ቢሆን አያስገርምም ። ተገቢው እውቅና እና አድናቆት ግን ይገባቸዋል ።

የህዝብን የአልገዛም ባይነት ተጋድሎ በተለመደው የአገዛዝ መንገድ መግታት እንደማይቻል ተገንዝበውና ተያይዞ ከመጥፋት ወደ ህዝብ መቀላቀል ይሻላል ብለው የወሰኑ የአሁኑ መሪዎችን ጨምሮ ሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የህወሃት የትሮይ ፈረሶች ሆነው ለሩብ ምዕተ ዓመት በመዝለቃቸው ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ከቶ ሊሸሹ ባይችሉም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ህወሃት መሆኑ እውነት ነው ። 


የእርግማን ፥ የስድብ/የዛቻ ፥ የጥሎ ማለፍ አና የልጆች ጨዋታ የሚመስል የፖለቲካ ብሽሽቅ ግን አስከፊው የፖለቲካ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የምናደርገውን ጥረት ይጎዳል እንጅ አይጠቅምም ።እንዲያውም ወደ መጣንበት ብቻ ሳይሆን ወደ ባሰ አዙሪት ይዞን ይወርዳል። 

ጅቡ መጣብህ/መጣብሽ ፧ ለማያውቅሽ ታጠኝ ፣ እዚያና እዚሀ የመሸጉ አሸባሪዎችና ፀረ -ለውጥ ሃይሎች ፣ አገር በታኞች ፧ ጭራቆች፣ ወዘተ የሚል የጅምላ ስምና ስድብ በመለጣጠፍ የፖለቲካ ጨዋታ ግዙፍና ጥልቅ የሆነውን የአገር ጉዳይ መፍታት ከቶ የሚቻል አይሆንም ።

ህግና ህገ መንግሥት ተጣሰ የሚል ስሞታ ወይም ተቃውሞ ከህወሃት መሪዎቸም ይሁን ፀረ-ለውጥ ከምንላቸው ቢመጣ እንኳ በአግባቡ አዳምጦና ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “እናንተ ለብዙ ዓመታት የጨፈለቃችሁትን አሁንስ ብንጨፈልቀው ምን አገባችሁ ?”የሚል መከራከሪያ ጨርሶ ስሜት አለመስጠት ብቻ ሳይሆን ወደ እነሱ ደደብ የፖለቲካ አስተሳሰብ መጠጋትም ነው ።  


የአገሬ ምሁራን ይህን አይነት አስተሳሰብ ትክክለኛ አቅጣጫና መልክ ማስያዝ የሚጠበቅባቸው ሆኖ ሳለ እንዲያውም የጨዋታው አካል ሲሆኑ በምንም አይነት ምክንያት “አሜን!” ሊባልላቸው አይገባም ።

ለህገ መንግሥት ተጣሰ ባዮች መሰጠት ያለበት ምላሽ “እናንተ ስትረግጡትና ስታስረግጡት ዓመታት ያስቆጠረውን ህግና ህገ መንግሥት የሚያስከብር ሥርዓት ለመመሥረት በሚደረግ ሂደት ውስጥ በሚያጋጥም ፈታኝ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር እንደእናንተ ለፖለቲካ መሣሪያነት ለመጠቀም ያለንበት ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሁኔታ አይፈቅድም እና አስፈላጊውን እርምት እንወስዳለን” የሚል መሆኑ ቀርቶ “የምታወሩት እናንተ ስለደፈጠጣችሁትና ስለአስደፈጠጣችሁት ህግና ህገ መንግሥት ከሆነ እንክትክትና ስብርብር ይበል “ የሚል ከሆነ በምንና እንዴት ከእነሱ እንደምንሻል ስሜት የሚሰጥ መከራከሪያ ጨርሶ የለንም ።


የሚያስከፍለው የዋጋ ክብደትና ቅለት ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ እንኳን እንደኛ በሁለነተናዊ ድህነት ውስጥ በሚገኝ ህብረተሰብ ውስጥ በተሻለ ደረጃ ላይ በሚገኝ ህብረተሰብ ውስጥ የሚደረግ የለውጥ እንቅስቃሴም ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙት የማይጠበቅ አይደለም ። 


ይህ ግን አጠቃላይ እውነት (general truth) እንጅ ግልፅና አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን በወቅቱና በአግባቡ ባለመወጣት ለሚደርሰው አስከፊ ጥፋት (ውድቀት) ሁሉ የሰበብ ( execuse) ማጣቀሻ (refrence) በጭራሽ አይደለም። ሊሆንም አይገባም።

አሁን ባለው የአገራችን ጅሞር የለውጥ እንቅስቃሴ ሂደት ይህን አጠቃላይ እውነት (general truth) አወቀንም ሆነ ሳናውቅ የመሪዎችን ድክመት ለመከላከል (ለመሸፋፈን) በየዲስኩሮቻችንና በየፅሁፎቻችን ማጣቀሻ (reference) አድርገነዋል። 


በተለይ ተማርኩ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የዚህ አይነት የተዛባ አተረጓጎምና ግንዛቤ አካል መሆኑን ልብ የሚል የአገሬ ሰው “ምነው አገሬ በዚህ ረገድ አልሳካላት አለ?” የሚል መሪር ጥያቄ ቢጠይቅ ትክክልነቱን የምናስተባብልበት አሳማኝ ምክንያት የለንም ።

የለውጥ አራማጅ መሪዎች በዋጋ የማይተመን ኢትዮጵያዊነትንና ተከባብሮ በአንድነት የመኖርን እሴትና አስፈላጊነት ድንቅ በሆነና ከልብ በመነጨ ቋንቋ የመግለፃቸው ሁኔታ የሚያስመሰግናቸው መሆኑ የሚያጠያይቅአይደለም ። ይህን የፖለቲካና የሞራል ልዕልና አመለካከት በተቀናጀና በፕሮግራም በሚመራ አካሄድ በተለይ የስሜታዊነት ፈረስ በሚጋልበው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያተኮረና ትርጉም ያለው ሥራ አለመሥራታቸውን ግን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም። 


ምሁሮቻችንም ገንቢነትና ሚዛናዊነት ባለው ኦኳኋን ከመተቸትና ተገቢውን ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ የፖለቲካ ምሪዎችን “በማይዳሰስና በማይመረመር ተአምር የተገኛችሁ” የሚል ውዳሴ እየደረደሩ ሀዝብን ጨምሮ የማነሁለላቸው ጉዳይ ለምሁርነት እውቀት (intellect) እውነተኛ ትርጉምና ተልእኮ ፈፅሞ አይመጥንም ።  

ለዚህ ነው የአገሩ ጉዳይ የሚያሳስበው ቅን የአገሬ ሰው “አገሬ በዚህ ረገድ ገና ያልተሳካላት የመሆኑ ጉዳይ ብርቱ ትግል ይጠይቃልና ያልሰማህ ስማ!”የሚል የአገር ጥሪ ጩኸት ቢያሰማ የጩኸቱን መሪር እውነት ለማስተባበል አሳማኝ ሞራላዊና ፖለቲካዊ ምክንያት የለንም ማለት ትክክል የሚሆነው ።

የህዝብን አልገዛም ባይነት ተከትሎ የለውጡን ሂደት በመሪነት የተቀላቀሉ ፖለቲከኞች ከጎረቤት እስከ ውቅያኖስ ማዶ አገሮች ለውጡን በማስተዋወቅ ዘመቻ ከመጠዳቸው አስቀድሞ በአልገዛም ባይነት ትግል ወደ ሥልጣን ያመጣቸውን ወጣት ትውልድ ለዓመታት እራሳቸው ከመረዙት የጎሳና የመንደር ፖለቲካ መርዝ ቢያንስ ትርጉም ባለው አኳኋን ያገግም ዘንድ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመሥራታቸውን በቀጥታና በግልፅ ለመንገር የፖለቲካና የሞራል ሃላፊነትና ደፋርነት የማይሰማው ምሁር በደምሳሳው የእንደመር አዋጅ ነጋሪ መሆኑ ቢያንስ “እንዲህ ነው እንዴ የምሁርነት ትርጉምና ባህሪ?” የሚል ጥያቄ ቢያስነሳ ከቶ ሊገርመን አይገባም ።

የአገር መሪዎች ይህን ባለማድረጋቸው ምክንያት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈጠሩ እጅግ ዘግናኝና አሳፋሪ ሁኔታወችን እጅግ ልብ በሚሰብርና በሚያሸማቀቅ ሃዘን አስተናግደናል ። አዎ! ሲሆን ቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተ ደግም እጅግ ፈጥኖ በመድረስ ጉዳቱን ለመቀነስ ያለመቻል እና በተለይ ደግሞ ከጉዳቱ በኋላ በሁለንተናዊ ሰቆቃ ውስጥ ለወደቁ ንፁሃን ዜጎች ቢያንስ ለመሠረታዊ ሰብአዊ እርዳታ ፈጥኖ ለመደረስ ያለመቻል ትልቁና የማያወላደው ሃላፊነትና ተጠያቂነት የአገር መሪዎች እንጅ የሌላ አካል ሊሆን በጭራሽ አይችልም። 


እጅግ በጣም የሚያመው ጉዳይ ደግሞ ይህን አይነት ከአመራር ደካማነት (የእልልታውና የጎሮ ወሸባየው ፖለቲካም አስተዋፅኦ ሳያደርግ አይቀርም) የመጣን እጅግ አሸማቃቂና አሳፋሪ ድርጊት መሪዎቹ ከልብ በመነጨ አኳኋን አምነው ፣ ተፀፅተውና ይቅርታ ጠይቀው አስፈላጊውን እንዲያደርጉ ከመተቸት (ከመጠየቅ) ይልቅ በለውጥ ሂደት የሚያጋጥም ስለሆነ አያስደንቅም የሚለውን እራስን አዋራጅ (dehumanizning ) ሰበብ አነደበታችን እንዴት ደፍሮ (ችሎ) እንደሚናገርልን ለመረዳት እጅግ ከባድ የመሆኑ ነገር ነው ።

በከፍተኛ መስዋዕነት የተኘውና በፍፁም ሊያመልጠን አይገባም የምንለው የለውጥ ጅማሮ ግቡን መምታት ካለበት፦
በሂሳዊ አስተያየት ያልተጠረበውን (ያልተሞረደውን) እና ልኩን የሳተውን የፖለቲካ መሪዎች ውዳሴ በቅጡ ማድረግ ግድ ይለናል ።


ፀረ-ለውጥ የምንላቸውን አካላት በጅምላ ፣ ለመቆጣጠር በሚያስቸግር ስሜታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ፣ የህግንና የፍትህን መተኪያ የለሽነት ዋጋ በሚያሳጣ እና የነገውንና የነገ ወዲያውን ማየት በተሳነው የፖለቲካ አስተሳሰብና ድርጊት የማስተናገድ እልህ ሊያስከትል የሚችለውን የጋራ ጉዳት ተረድተን የተሻለውን አካሄድ መምረጥና መጠቀም ይኖርብናል ።

አስተያየቴን ስቋጭ ባለተስፋነቴን እየገለፅሁ ነው !

No comments