Latest

ህወሃት ሁለት ግንባሮችን ከፍቶ በሰፊው እየሰራበት ነው (መሳይ መኮንን)

ህወሃት ሁለት ግንባሮችን ከፍቶ በሰፊው እየሰራበት ነው

ህወሀት ከቤተመንግስት ተባሮ መቀሌ ከመሸገ ወዲህ ሁለት ግንባሮችን ከፍቶ በሰፊው እየሰራበት ነው። አንደኛው ግንባር የቀድሞውን መዋቅር በመጠቀም ከፍተኛ ገንዘብ ውጪ አድርጎ በየአከባቢው አለመረጋጋትን መፍጠር ነው። ሁለተኛ ደግሞ በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች የተዛቡ፡ ሀሰተኛና ህዝብን ሰላም የሚነሱ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ወደ 100ሺህ የሚጠጉ አካውንቶችን በዘመቻ ከፍቶ መረበሽ ነው። 


በቅርቡ መቀሌ የመከሩት የህወሀት ”ምሁራን” ላይ አንዱ የፌስ ቡክ አዛማቻቸው ቃል በቃል ያለውም ይሀው ነው። ” በ100ሺዎች ሆነን መረጃው ላይ መዋጋት አለብን” ያለው ልጅ አሁን አሜሪካ መጥቶ ምን እያደረገ እንዳለ ግልጽ ነው። በይፋ ኤታ ማዦር ሹሙ ጄነራል ሳዐረ መኮንን ለዶ/ር አብይ እንዳይታዘዙ አደገኛ መልዕክት እያሰተላለፈ ነው።

አዎን! ህወሀት በሁለቱም ግንባሮች እረፍት አጥቶ በመስራት ላይ ነው። የምንዋጋው ሁለቱንም ግንባሮች መሆን አለበት። ሁለቱ ግንባሮች ተደጋጋፊ ናቸው። አንደኛው ለአንደኛው እንደፍግ፡ ማዳበሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

ህወሀት የሚከተለው የቀውስ አመራር ነበር። ህዝብ ከህዝብ ጋር ካልተጋጨ በስልጣን የመቆየት እድል እንደሌለው ስለሚያምን የአመራር ስልቱን ማጋጨት ላይ አተኩሯል። ባይዘልቅበትም ለተወሰኑ ዓመታት ዕድሜን አግኝቷል። አሁን ያለው አመራር በተቃራኒው የቆመ ነው። ከግጭት ይልቅ ሰላምን የሚመርጥ አስተዳደር ነው። 

ህወሀት የማወከ ስትራቴጂ ነድፎ፡ በግልጽ ጦርነት እያወጀ እንኳን የሚታገስ አመራር ነው ቤተመንግስት ያለው። በእርግጥ ትዕግስት ድንበር አለው። ሀገርን ወደ ለየለት ቀውስ ለመክተት ሁለት ግንባሮችን የከፈተ አጥፊ ቡድንን መታገሱ እስከመቼ ሊዘልቅ ይችል ይሆን? እነአብይ የመረጡት መንገድ ህወሀትን ከጥፋት ጉዞው ያስቆመዋልን?

ጠ/ሚር አብይ ህወሀትን እያፈራረሱት መሆኑ ግልጽ ነው። በጥበብና በድፍረት በፌደራል መንግስቱ ያሉትን የህወሀትን መዋቅሮች በማወላለቅ በአጭር ጊዜ ከመንግስትነት ወደተራ ሽፍታ ቡድን እንዲቀየር ማድረጋቸው አስደማሚ ነው። 

በዚህ ፍጥነት ህወሀት ተሰባብሮ ከነጥቁር ታሪኩ ወደ መፈጠሪያ ዋሻው ደደቢት እንዲጠጋ የተደረገበት ድምጽ አልባው መፈንቅለ መንግስት በሆሊውድ መንደር ቢሆን ጥሩ ፊልም የሚወጣው ታሪክ ነው። ህወሀት ከእንግዲህ ወደ አራት ኪሎ ቤተመንግስት የሚመመለስበት አንድም እድል የለውም። በምርጫ አይችልም።  

ለምርጫ የሚያበቃ ተፈጥሮአዊ ባህሪ የለውም። ሌላው መንገዱ ሃይል ነው። ሞትን የማይፈራው ትውልድ በእነዶ/ር አብይ እየተመራ ህወሀት በሀይል ልሞክር ቢል ትርፉ እስከወዲያኛው መጥፋት ነው። አጉል አሟሟት ነው። ቢሞክሯት ጥሩ ነበር።

ህወሀት ለጊዜው ያለው ምርጫ መረበሽ ነው። ማወክ ነው። የስነልቦና ጦርነት ማወጅ ነው። በዝርፊያ በተከማቸ ገንዘብ በየአቅጣጫው ብጥብጥ መፍጠር ነው። ለዚህም ሁለት ግንባሮችን በይፋ ከፍቷል። ሁለቱ ግንባሮች ጊዜያዊ ሰላም መደፍረስን እያስከተሉ ነው። ለሰላም፡ እርቅና እድገት የሚውለውን ጊዜና ገንዘብ መብላት ጀምረዋል።  

እናም ነቅተንና አስምረን የተከፈቱትን ግንባሮች ልንዋጋቸው ይገባል። ከምንጊዜውም በላይ ጥንቃቄ የሚፈልግ ዘመን ላይ ነን። ከስሜት ግልቢያ ወጥተን፡ በዕውቀትና በእርጋታ፡ ከአንድ ሰሞን ዘመቻ ተላቀን በራዕይና ተልዕኮ በተቀረጸ የተግባር እርምጃ ላይ እናተኩር ዘንድ የሁላችን ቅን ልቦናና ዝግጁነት የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን።

ህወሀት በአንደኛው ግንባሩ የሚችለውን እያደረገ ነው። በሶማሌ ክልል በእጅ አዙር የከፈተበትን የእርስ በእርስ ግጭት እንደተፈራው ሀገርን የሚገነጣጥል ባይሆንም ጠባሳ አሳርፎብናል። በቅማንት አከባቢ የቀበረው ፈንጂም በአግባቡ ካልተነቀለ የፈነዳ ዕለት ጥፋቱ አደገኛ ሊሆን ይችላል። በሌሎች አከባቢዎችም ተመሳሳይ የልዩነት ቦምቦችን አጥምዶ መቀሌ ላይ በመቀመጥ የሚፈነዱበትን ሰዓት እየጠበቀ ነው።  

የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይህን ግንባር ብቻውን አይመክተውም። የኢትዮጵያውያን ድጋፍና ደጀንነት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። የህወሀትን የጥፋት ተልዕኮ ማሳካትም፡ ማምከንም የሚችለው ህዝባችን ነው። እነዶ/ር አብይ በጥበብ የሚያደርጉትን የማረጋጋት ሀገራዊ ስራ ትንሽ ፍጥነት ጨምረውበት ከቀጠሉና የህዝባቸውን ድጋፍ ካገኙ የህወሀት አንደኛው ግንባር ድባቅ መመታቱ አይቀርም።

ሁለተኛው ግንባር የተዛቡና ሀሰተኛ መረጃዎችን በስፋት በማስራጨት ህዝቡ ላይ የስነልቦና ቀውስ መፍጠር ነው። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ በተባራሪ፡ አፍና ጭራ በሌላቸው ሀሰተኛ ወሬዎች ህዝባችን ምን ያህል እንደሚደናገጥ የሰሞኑን ”የአብይ የመግደል ሙከራ” ወሬ አይነተኛ ማሳያ ይሆናል። ዶ/ር አብይ ዛሬ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ”ህዝባችን ሰምቶ ከሚወስን ለምን አይመርምርም?” ዓይነት ወሳኝ ነጥብ አንስተዋል።  

ግጭቶች የሚከሰቱት እውነት ላይ ተመስርተው እንዳልሆነና በስማ በለው በሚሰራጭ ሀሰተኛ መረጃዎች መሆኑን ጠ/ሚር አብይ ጠቆም አድርገዋል። እውነት ለመናገር የሚቀርበን የምንሰማው እንጂ የምናየው አይደለም። በገሀድ ከሚታየው ይልቅ በሹክሹክታ የምንሰማው ቀልባችንን ይገዛዋል። ህወሀት ይህችን ደካማ ጎናችንን ጠንቅቆ አውቆታል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክና የቲውተር አካውንቶችን በመክፈት ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በሰፊው የተሰማራበትን ግንባር ከፍቷል።

የህወሀት የፌስ ቡክ ሰራዊት በብዛት የገባበት በተሳሳተ መረጃ የስነልቦና ሽብር የመፍጠር ጦርነት የሰሞኑ ግርግርና ብዥታን አስከትሏል። የፌስቡክ ሰራዊቱ አባላት ማለያ እየቀያየሩ፡ የብሄር ታፔላ እየያዙ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፡ አንዱን ብሄር የሚያጥላሉ፡ በሌላው ብሄር ማለያ ተከስተው የሚያነግሱ፡ ፍጹም ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ሀገርን በሀሰተኛ መርጃዎች በማጥለቅለቅ ደረቱን ለጥይት ያልሳሳውን ትውልድ በወሬ ለማንበርከክ በሰፊው ተሰማርተዋል። 

በአማራና በኦሮሞ ስም በተከፈቱት እነዚህ አካውንቶች ስር የመሸጉት የህወሀት የጥፋት ሃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል። በቀላሉ በፈጠራና አሉባልታ ወሬዎች የሚሸበር ህዝብ አግኝተዋል። ከመጀመሪያ ግንባር የበለጠ አደጋ ሊፈጥር የሚችለው ሁለተኛው ግንባር ነው። በህወሀት የስነልቦና ጦርነት እጅ ሰጥቶ መሸበርን የመሰለ ሽንፈት የለም።

No comments