Latest

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ! ከጌታቸው ሽፈራው (ሐምሌ 30/2010 ዓ.ም)

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

አባታችን አስር አለቃ ጌትነት ምስክር በደቡብ ጎንደር እስቴ ወረዳ ልዩ ሰሙ ቆማ ፋሲለደስ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ተለወዶ ያደገ ሲሆን በውትድርና ሙያ ሐገሩን አገልግሏል።

አባታችን በውትድርና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከማገልገሉም ባሻገር ሁመራን ጨምሮ በአብዛኛው የደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ደግሞ በከተማ አስተዳደርነት ለረጅም ጊዜ አገልግሏል። በዚሁ ስራ ላይ በእሰቴ ወረዳ በማገልገል ላይ እያለ 1983 የመንግሥት ለውጥ ሲሆን አባታችን የኢሰፓ አባል ነበርክ ተብሎ ከአንድ አመት በላይ ታስሯል። 

ከአንድ አመት በላይ ከተሰረ በኋላ ምንም አይነት ወንጀል እንደሌለበት እና ባገለገለበት ቦታ ሁሉ በሰው በጣም ተወዳጅ መሆኑን ሲረጋገጥ በነፃ ከእስር ተፈትቷል። ነገር ግን አባታችብ በነፃ ቢለቀቅም ከዛ በኋላም ልክ እንደበፊቱ መቀጠል አልቻለም። ወደ ስራ መመለስ እና እኛን ልጆቹን በሰላም ማሳደግ አልቻለም። 

አዲስ አበባ ድረስ ሄዶ ሲያመለክት ከጠቅላይ ሚንስትሩ "ነፃ ነው ወደ ስራ ይመለስ!" የሚል ደብዳቤ የተሰጠው ቢሆንም ደብዳቤውን ይዞ በተመለሰ ማግስት ባልታወቁ ታጣቂወች ታፍኖ ተወስዷል።

ከዛ ቀን ጀምሮ አባታችን ለመፈለግ እናታችን ያልፈለገችበት እስር ቤት የለም። ግን ምንምነገር ልታገኝ አልቻለችም። አባታችን መኖር መሞቱን ሳናውቅ ለ 24 አመት በትልቅ ሰቀቀን እና ጭንቀት ውስጥ ኖረናል።

አሁን ግን በወቅቱ በተፈጠረው የነፃነት አጋጣሚ ለዘመናት ውስጣችን አፈነነው የነበረውን ጭንቀት ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ልናጋራ እንፈልጋለን።

የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትር!
አባታችን በህዝብ ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅ እና ሰው አክባሪ እንደነበር በተለያዩ አጋጣሚ ያገለገለው ህዝብ ምስክር ነው። በዚህ ስአት አባታችን የደረሰበትን ማወቅ አንድ በተስፋ ማጣት እና በፍትህ እምነት ማጣት እየተሰቃየ ያለውን ቤተሰብ ማትረፍ ነው! ለአመታት ያጣውን ሰላም መመለሰም የእርስዎና የኢትዮጵያ ሕዝብን እገዛ እንፈልጋለን። 

በመሆኑም በግፍ ታፍኖ ለ24 አመት የት እንደደረሰ ያላወቅነውን አባታችን ሁኔታ እንዲያጣራልንና ተፈትቶ ለዘመናት ሲናፍቀውና ሲጨነቅለት ወደነበረው ቤተሰቡ እንዲቀላቀል በትህንትና እንጠይቃለን! የኢትዮጵያ ሕዝብም በግፍ ታፍኖ የጠፋው አባታችን ፍትህ እንዲያገኝ ከጎናችን በመሆን ጩኸት እንዲያሰማልን በአክብሮት እንጠይቃለን!

እናታችን:-  ወ/ሮ ፀሀይ ዘውዱ
ልጆቹ:-
  1. አለኝታ ጌትነት
  2. አንዳርጋቸው ጌትነት
  3. ቃልኪዳን ጌትነት
  4. ትዕግስት ጌትነት
  5. ፍትሕአለው ጌትነት
  6. ማህደር ጌትነት
  7. ማቲዎስ ጌትነት

No comments