ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚያደናቅፍ እንቅስቃሴ የሕዝብ ጠላትነት ተግባር ነው! (ሰማያዊ ፓርቲ)
የኢትዮጵያ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መራር መስዋዕትነት ባለፉት አራት ወራት በታየው የለውጥ ሂደት ውስጥ አገራዊ አንድነት እና መግባባት እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በአንፃራዊነት ተከብረዋል፡፡ የተጀመረው አበረታች ለውጥም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን ያሳተፈ እና ባለቤት ያደረገ ጭምር ነው፡፡ ከዚህም አንፃር ሰማያዊ ፓርቲ በአገራችን የታየው የለውጥ ጅማሮ በይበልጥ ማደግ እና ከዚህም በላይ እመርታ ማሳየት እንዳለበት ያምናል፡፡
ሆኖም ይህን ሊበረታታ የሚገባውን የለውጥ ጅማሮ ከመደገፍ እና ታሪካዊና አገራዊ አደራ ለመወጣት ከመትጋት ይልቅ ለዕኩይ ተግባር የሚፈጥኑ፤ በመንግስት ስልጣን እና ኃላፊነት ላይ ያሉ በአገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ከፍላተ ሃገሮች አልፎ አልፎ የብጥብጥና የሁከት ድርጊቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ በዜጎቻችን ላይ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማድረስ ህገወጥ ድርጊቶች እንዲስፋፋ ቀስቃሽ በመሆን ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የጥፋት ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይ ባለፉት ሦስት ቀናት በሱማሌ ክፍለ-ሃገር በጂግጂጋ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ፤ብጥብጡንም ተከትሎ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በተዛመተው ሁከት ምክንያት የደረሰው ጉዳት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በአስቸኳይ ሊገታ የሚገባው ድርጊት ነው፡፡ ድርጊቱም በማንአለብኝነት የተፈጠረ የጭካኔ ተግባር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በዜጎች ላይ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአለም አቀፍ ደረጃ እየታወቀ ምንም አይነት እርምጃ በአጥፊዎች ላይ አለመወሰዱ ለተጨማሪ ጥፋት ዳርጎናል የሚል እምነት አለን፡፡ አሁንም ማንነትን መሰረት ያደረገው ጥቃት አብያተ ክርስቲያናትን ጭምር በማቃጠል ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት እየተቀጠፈ ይገኛል፣ ንብረት በጠራራ ፀሐይ ይዘረፋል፣ እንዲሁም ይወድማል፤ እንደዚህ አይነት ወንጀሎች እና አስነዋሪ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት የክፍለ-ሃገሩ አስተዳዳር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አልቻለም፤ ይልቁንም በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት መጠንና ዓይነቱን ጨምሮ ወደ ሌላው አካባቢ እንዲዛመትና ሐይማኖታዊ ቅርፅ እንዲይዝ በር እየከፈተ ይገኛል፡፡ ይህ ማንነትን መሰረት ያደረገው ጥቃት እና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ወደ ኋላ የመመልስ እንቅስቃሴ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡
በተለይ የሱማሌ ክፍለ-ሃገር ሕዝብ የመንግስት ሥልጣን መጦሪያቸው ያደረጉና ለግል ጥቅማቸው አገር የሚያፈርሱና ህዝብ የሚያጫርሱ ባለስልጣናት መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት ሰማያዊ ፓርቲ ስለሚያምን ህዝቡ አምባገነን ገዢዎቹን ከጫንቃው አሽቀንጥሮ እንዲያወርዳቸው እና የአገራዊ ለውጡ አካል እንዲሆኑ ፓርቲው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በአካባቢው ከሚኖሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች ጋር በወንድማማችነት እና በእኩልነት መንፈስ ቀድሞ የነበረውን ፍቅር፣ አንድነት እና ሠላም በማጠናከር፣ የተበደሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እና ተቋማትን በማህበራዊ ትስስር በመርዳት እና የወደቀውን በማቅናት በሕዝቡ ላይ የፖለቲካ ሸፍጥ መፈፀም ለሚሹ አካላት የማያዳግም ምላሹን በመስጠት አንድነቱን ማጠናከር አለበት፡፡
የፌደራል መንግስት የሕዝብ ሰላም እና ደህንነት አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ መጠበቅ ዋነኛ ሃላፊነቱ ነው፤ ሆኖም ግን በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚፈጠረውን ሁከትና ብጥብጡን በዝምታና በቸልተኝነት በማየት፣ እንዲሁም በአካባቢው ለሚፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መጠየቅ ያለበት አካል ባለመጠየቁ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመውሰዱ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡
አሁንም ቢሆን ዘግይቶ በተወሰደው እርምጃ ምንም እንኳዋን በአካባቢው መጠነኛ መረጋጋት ቢፈጠርም በዘላቂነት ተገቢውን እና ሕጋዊ ውሳኔዎችን በመውስድ የሕዝብን ፍላጎትና ምርጫ መሠረት ያደረገ ማስተካከያ በአስቸኳይ ሊወሰድ እንደሚገባ ሰማያዊ ፓርቲ አጥብቆ ይጠይቃል ፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ በድሬዳዋ ከተማ ገንደ-ገራዳ በተባለው አካባቢ በተከሰቱ ግጭቶች የዜጎች ሕይወት ማለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአካባቢው ከዚህ የከፋ ችግር እንዳይገጥም መንግስት በአስቸኳይ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ተገቢውን ኃላፊቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለደረሰው የዜጎች ሞት፣መፈናቀልና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እና ዝርፊያ ምክንያት የሆኑ የመንግስት ሹመኞች ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል ፤ለሰሩትም ወንጀል መጠየቅ አለባቸው ፡፡ በልዩ ልዩ ሰበቦች የሚከሰተው የሰላም መደፍረስ እና እሱን ተከትሎ ለዜጎች አሳዛኝ ሞት መበራከትና መቁሰል እንዲሁም ከባድ መፈናቀል በአገራችን በመድረሱ ሰማያዊ ፓርቲ በእጅጉ የሚያሳስበው ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከሰሞኑ በአገራችን በጂግጂጋ እና በድሬዳዋ ገንደ-ገራዳ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢ በተቀሰቀሱ ግጭቶች ለሞቱ ዜጎች ነብስ ይማር በማለት፣ ሰማያዊ ፓርቲ ለሟች ቤተሰቦች ፣ዘመዶችና ወዳጆች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል ፡፡
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ በልጆቿ ትኑር !
ነሀሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም
No comments