Latest

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥቅም ለአሁኗና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ - ክፍል ~ ፫ (ከፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ )

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥቅም ለአሁኗና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ

በመጀመሪያ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያኒዝም መሠረት አድርጎ ሲፀነስ ሐገሪቷ ልዩ ቦታ እንደ ተሰጣት ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢትዮጵያ መንፈሳዊ ምግብ ለዓለም የሰጠች መሆኑ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም። ዛሬ ቁሳቁሳዊ እርዳታ ከሚሰጡት እንደ አሜሪካ ካሉ ሀገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ መንፈሳዊ የነፃነት ምግብ ለዓለም የሰጠች ታለቅ ሐገር መሆኗ ጥርጥር የለውም።

እንግዲህ ኢትዮጵያን ሊጎዷትና ሊገድሏት ያሰቡ ሐገሮች ግለሰቦች እንዲሁም ቡድኖች ማወቅ የሚገቧቸው ነገሮች ቢከሷትም በታሪኳ ቢፈርዱም ብትሞትም ዘላለም የምትኖር ሐገር ናት። ሁላችንም ቢሆን ይህችን ሀገር እንዲህ ያለ የተጨቆነውን ዓለም በሙሉ ያከበረውን መንፈሳዊ ስጦታ ያበረከተች ሐገር አሳልፈው የሰጡንን አባቶቻችንና እናቶቻችንን ማክበር እንጂ በውጭ ሐገር ፕሮፖጋንዳና በማናውቀው ሥልጣኔ ባልገባንና ባልተረዳነው ተውጠን ይህችን ሐገር መናቅ ትልቅ ስሕትተ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያኒዝም የተመሠረተው በክርስትና ሃይማኖት ላይ የነጭ ቄሶች ዘረኝነትን በማስፋፋት የእግዚአብሔርን መልክ በነጭ ቅልፅ በመግለፅ ሌሎችን በማግለልና መጠቀሚያ ብቻ በማድረግ እንደማይቻል በመቃወም ነበር። የእስልምና ሃይማኖትን በኢትዮጵያኒዝም አመለካከት ስናየው ተቃውሞ በተነሳበት ጊዜና ምዕመናኑ ስደት ባጋጠማቸው ወቅት የኢትዮጵያ ድጋፍ ትልቅ ልዩነት እንዳመጣ ታሪክ ይመሰክራል።

ኢትዮጵያ ለሙስሊሞች ያደረገችው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ይገልፃል። ከእኛ ምን ይጠበቃል? በመጀመሪያ ይህንን ታሪክና ፍልስፍና ማወቅ ይገባናል። ይህንን ታሪክና ፍልስፍናን መሰረት አድርገን ዘመናዊነትን ለመገንባት ዝግጁ መሆን ያሰፈልጋል።

ከውጭ የተለያዩ ሀሳቦችን እየኮረጅን ሐገራችን የፈጠረችውን ፍልስፍና ማንቋሸሽና ታሪኳን መወንጀል አላግባብ መፍረድ አይገባም። መጠየቅ ያለብን የራሳችን ሐገር ምን ፈጠረች፣ ለምን በዓለም ዙሪያ ያሉ ሐገሮች እንደዚህ ተማሩባት አከበሯት ብለን በትሕትና ሐገራችንን አክብረን ያለባትን የተወሳሰቡ ችግሮችን አጥንተን ተወያይተን ተባብረን አንድ መንገድ ፈጥረን በሐገሪቷ ባህል መሰረት ካላንዳች ኩረጃ ታላቋን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን።

መደምደሚያ ሃሳብ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ለአዲስ ብሔራዊ ውይይት አሁን አዲስ የብሔራዊ ውይይት ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። ስለ ሐገራችን ነባራዊ ሁኔታ በሰለጠነ አስተሳሰብ መወያየትና ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል። ለውጥ መጣ በተባለበት ዘመን ማለትም ባለፉት ዓርባ አመታት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ነበር ማለት ያስቸግራል። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ይህ የብሔራዊ ውይይት መድረክ መፈጠር አለበት።

ኢትዮጵያ የት ነው ያለችው፣ ወደ የት ነው ምትሔደው? ያለችበት ጎዳና ትክክል ነው ወይስ አይደለም በሚሉ ሀሳቦች ላይ በጋራ በመወያየት ስምምነት ላይ በመድረስ በኢትዮጵያኒዝም በመጠቀም አሁን ሐገራችን ካለችበት ውስብስብ ችግር መውጣት እንችላለን። ባጠቃላይ ከእንግዲህ ወዲህ ለውይይት የሚጠቅሙን ኢትዮጵያ በንፅህናዋ የተበጀውን ፣ በመንፈሳዊ ኃይል የተመራውን የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ተጠቅመን ትልቅ እንደ ነበረች እንደ ገና ትልቅ ለማድረግ ተሳስበን ተደማምጠን በታላቅ ትሕትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንገንባት። ሁሉ ነገር ከሃገራችን ስለ ተፈጠረ ለሌሎች ምሳሌ ስለ ሆንን ሃገራችን ወደ ፊት እንድትሄድ ጠንክረን እንሥራ።

ከእርስዎ አመራር ምን ይጠበቃል?
ሌሎች ሃገራት በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ተጠቅመው ነጻ የወጡና ሃገራቸውን ወደ ተሻለ መንገድ የመሩት በእኛ ኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ እና የደረሱብንን የተለያዩ ተግዳሮቶች ተቋቁመን በነፃነት መኖር በመቻላችን ነው። አሁን ሃገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በዘር፤ በኃይማኖት እና በጎሳ ተከፋፍሎ ሕዝቡን በቋንቋ እና በክልል አዋቅሮ በመግዛት፤ ከኢትዮጵያዊነት በፊት ለጎሳ ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በሥራ ምክንያት ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስና ሥራ እንዳይሠራ አድርጓል።

ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በክልል መንግሥት አደረጃጀት የተመሠረተ ስለሆነ ሕዝቡ ከሃገሩ ይልቅ ቅድሚያ ለብሔሩ እና ለክልሉ እንዲሰጥ አድርጎታል። ይህ የክልል አደረጃጀት እስካልተስተካከለ ድረስ አሁን ሃገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግር ውስጥ መውጣት አትችልም።

ሃገራችን ከገባችበት ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግር ልትወጣ የምትችለው የክልል አወቃቀር ተስተካክሎ ዜጋው ከቦታ ወደ ቦታ በነፃነት የመዘዋወር፤ የመሥራት፣ የመማርና የመኖር መብቱ ተጠብቆ ሊያስኬድ የሚቻለው ለኢትዮጵያዊነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሕገ መንግሥት ሲኖር እንደሆነ እሙን ነውና ሕገ መንግሥቱ መሻሻያ ቢደረግበትና ቢስተካከል ለሃገራችን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል።

ሃገራችን ኢትዮጵያ ለውጪው ዓለም በተለይም ለተጨቆኑ ሕዝቦች ራሷ ተቸግራ እና የደም ዋጋ በመገበር የሰጠችው መንፈሳዊ ፀጋ ቀላል የሚባል አይደለም፣ ከራሷ አልፋ ለተጨቆኑ ሕዝቦች ሁሉ ምሳሌ እና አርዓያ የሆነች ሕገራችንን ችግሮቿን እና እንከኖቿን እኛ ልጆቿ በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ በመነጋገር በመደማመጥና በመከባበር ልንፈታና አሁን ካለችበት ወደ ተሻለች ኢትዮጵያ ልናሸጋግራት ይገባል።

የሃገራችን የትኛውም ዓይነት ችግር መፈታት ያለበት በራሷ ልጆች መሆን አለበት! በፖለቲካ አመለካከት እና አመከንዮ ባንግባባም እንኳ ለሃገራችን እና ለሕዝቧ ቅድሚያ በመስጠት ወደ መፍትሔ መንገድ መምጣት እንችላለን። እርስዎ የጀመሩት ኢትዮጵያዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአራቱ አቅጣጫ አስተጋብቷል! ሕዝቡም ሲናፍቀው የነበረ ዓቢይ ጉዳይ ነውና ተቀባይነትዎ ጨምሯል! ይጨምራልም።

አሁን የተጀመረውን ኢትዮጵያዊነት መነቃቃት ወደ ተሻለ እና ከፍ ወደሚል ደረጃ ለማድረስ እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እና አሁን ካለንበት የብሔር እና የሃይማኖት ችግር ወጥተን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ተከብሮ የሚኖርበትን ዕድል ለመፍጠር ሁላችንም በጋራ የምንሠራበት ዕድል መፈጠር ይኖርበታል።

አሁን ከሚታየው ተስፋ እና ጅማሮ በመነሳት ሃገራችን ወደ ቀድሞ ክብር እና ዝናዋ የምትመለስበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። በእርስዎ አመራር የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባሮች እንዲከናወኑ በትሕትና እናመለክታለን፤

1ኛ/ የኢትዮጵያኒዝም መንፈስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ፤ እንዲዘረጋና እንዲዳብር ማድረግ፤

2ኛ/ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሙሉ መሻሻል እንዲያስገኝ መለወጥ ከሚገባቸው ብዙ ጉዳዮች አንዳንዶቹን እንጠቁማለን፤

የክልል አስተዳደር ኢጣልያኖች ኢትዮጵውያንን መግዛት የሚቻለው በመከፋፈል ነው በማለት የዘረጉት አስቀያሚ ሥልት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከዚህ መላቀቅ አለባት። በዘር፤ በኃይማኖት፤ በቋንቋ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከፋፈል እንደ ሀጢአት የሚቆጠር በመሆኑ ሐገራችን በክፍለ፟ ሐገር እንድትደራጅ ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሃገራችንን ረጅም ታሪክ፤ ጥበብና ዕውቀት በሚያጎላ መንፈስ እንዲስፋፋ ይሁን። በተለይ ሰንደቅ ዓላማው ኣረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት ብቻ የሚታይበት ሆኖ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር ሊለዋወጥ አይገባም። በአፍሪቃ አፍሪቃውያን የፈጠሩት ፊደል ግዕዝ ብቻ ነው።

ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ፊደል መጠቀም ሲገባን በሌሎች ባእድ ቋንቋዎች ፊደሎች ለምሳሌ በላቲን መጠቀም ተገቢ አይደለም። ከኢትዮጵያ አካባቢ እንደዚሁም የመላ አፍሪቃ አንድነት በጣም አስፈላጊ ነው። በእዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ልዩ ሚና እንዳላት መገንዘብ ያስፈልጋል።

ይኸውም በዓለም ሕዝብ ከ1829 እስከ 1929 ድረስ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጊዜ የነበረ መሆኑ በዓለም ተሰራጭቷል። በኢትዮጵያ ስም ሁለት ማኒፌስቶዎች (መመሪያዎች) በ1829 ዓ.ም. በአሜሪካ፤ በ1896 በደቡብ አፍሪቃ፤ ከአድዋ ጦርነት ድል በኋላ ተሰራጭተዋል።

አፍሪቃ በሙሉ በኢትዮጵያ ስም የሚታወቅበት ጊዜም እንደ ነበረ ማስተዋል ይገባል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ያከናወነችውን አሁንም እንድትቀጥልበት ያስፈልጋል። ይህም ታሪካዊ መሠረታችን ነው። ከእዚህ ቀደም የነበረው የእርስ በርስ መፈራረጅ፤ የመለያየትና ችግር ሲያጋጥም ወደ ጦርነት ከማዘንበልና በውጭ ሃገሮች መሣሪያ ከመጠቀም፤ ወደ መወያየት፤ መግባባትና መመካከር ባሕል መለወጥ ይጠቅማል።

የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያውያን መፍትሔ ማስወገድ ይገባል። በውጭ እጅ ላይ መተማመን መክፋፈል ያስከትላል። የመንግሥቱ አወቃቀር ግልጥነት፤ የወስጥ ቁጥጥር፤ ውጤታማነት የሚያሰፍን ሊሆን ይገባዋል። የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣኖችም ሊመደቡ የሚገባው በተገቢ መስፈርት ብቁነታቸው ብቻ ሳይሆን ተደጋጋሚ ሥልጠናም እየተከናወነላቸው በቂ ቅልጥፍናና ከሙስና የተላቀቀ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ማድረግ ያስፈልጋል። የበላይ አመራሩ የጊዜ ገደብ ይወሰን።

3ኛ/ ኢትዮጵያ ካለችበት ቀውጢ ጊዜ ተላቅቃ አስተማማኝ ወደ ሆነ ጎዳና እንድትገባ ሁሉም ማለት የፖለቲካ፤ የማሕበረ ሰብዓዊ፤ የመንፈሳዊ፤ ወዘተ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የሽግግር ሒደት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ።

የእርስዎንም የአስተዳደር ዘመን እስክ መጨረሻው ለሃገር የሚበጅ ውጤታማ እንዲሆን እንመኛለን። ኣገርን በጎሳ መከፋፈል ኢትዮጵያን ሰማንያ ቦታ መከፋፈል ነው። በኢትዮጵያዊነቱ ተከባብሮ መኖር የማይችል ሕዝብ በየቤተሰቡ መንግሥት ፈጥሮ መኖር ኣይችልም። ለኣፍሪቃውያን መከታና ኣለኝታ ሆኖ የቆየው ኢትዮጵያዊነት ኣፍሪቃ ኣንድ ኣገር ሆና መብቷ በዓለም ደረጃ እስኪመለስ ከመንደርና ጎሳ ኣስተሳሰብ መላቀቅ ይገባናል።

ከታላቅ አክብሮት ጋር!
እግዚአብሔር ሃገራችንን ይባርክ!!

  • ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ 
  • ፕሮፌሰር ሲሳይ አሰፋ 
  • ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግስቱ 
  • ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ 
  • ዶ/ር ኣበራ ሞላ 
  • ዶ/ር ወርቁ አበራ 
  • ዶ/ር ጌታቸው ተመስገን
  • ዶ/ር አበባ ደግፌ 
  • ዶ/ር እጀቡሽ አርጋው 
  • ወ/ሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታ 
  • የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ 
  • አቶ ምንተስኖት መንገሻ 
  • አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው 
  • አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሄር 
  • አቶ ኪዳኔ አለማየሁ 
  • አቶ እርቅርማሪያም ደረስ 
  • አቶ ተፈራወርቅ አሰፋ
  • አቶ ይልማ ዘሪሁን 
  • አቶ ይርጋለም ጎበዜ 
  • አቶ ከድር ሰይድ 
  • አቶ መሸሻ ካሳ 
  • አቶ ኤሊያስ ማሞ 
  • አቶ ብርሃኑ ገመቹ 
  • ወ/ሮ አስቴር ኃይሌ 
  • አቶ በቀለ ተገኝ 
  • አቶ አብርሃም ቀጀላ 
  • አቶ ግርማ ካሳ 
ዋቢ
  1. Ethiopianism, http://www.druglibrary.net/olsen/RASTAFARI/campbell.html 
  2. ETHIOPIANISM IN PAN-AFRICAN PERSPECTIVE, 1880-1920, https://www.upjournals.co.za/index.php/SHE/article/view/85 
  3. Abyssinian Baptist Church, New York City (1808- ) http://www.blackpast.org/aah/abyssinian-baptist-church-1808 
  4. Ethiopianism in African Christianity, https://repository.up.ac.za/bitstream/handle/2263/21579/011_Chapter10_p258- 277.pdf?sequence=12 
  5. Ethiopianism and African Nationalism in South Africa before 1937, https://www.persee.fr/doc/cea_0008-0055_1986_num_26_104_1689 
  6. Ethiopianism, http://www.blackpast.org/gah/ethiopianism 
  7. Ethiopianism and the Independent Church Movement, http://www.worldhistory.biz/sundries/47078-ethiopianism-and-the-independent-churchmovement.html 
  8. Ethiopianism, https://www.britannica.com/topic/Ethiopianism 
  9. Ethiopianism a symbol of resistance to injustice, http://www.aau.edu.et/blog/ethiopianism-a-symbol-of-resistance-to-injustice-thabo-mbeki/ 
  10. John Dube, http://www.anc.org.za/content/john-dube
  11. Ethiopian Muslims History, http://www.selamta.net/ethiopian%20muslims%20history.htm 
  12. http://www.ethiomedia.com/1000dir/oromigna-be-amara-kilil-be-geez-fiddelendiset.pdf 
  13. http://www.ethiomedia.com/1000dir/open-letter-to-president-lemma-megersa.pdf8

No comments