ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች የተሰጠ መግለጫ
በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር!
በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት የዓመታቷን መፈራረቅ ለዓለም በማብሰር የምትታወቀው ኢትዮጵያ ሃገራችን የሁለተኛውን ሚሌንየም 11ኛ ዓመት ከእስከ ዛሬው ክስተት ሁሉ በገዘፈና በላቀ ድባብ ልታከብር ዝግጅቶቿን በማቀላጠፍ ላይ ትገኛለች፡፡
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚነት ሲስተዋል የነበረው አለመረጋጋት፣ ህዝባዊ ቅሬታና ያልተመለሱ አያሌ ጥያቄዎችን በጥንቃቄ ለይቶ ለመመለስና ሠላም ለማስፈን መንግስት የወሰደው ተከታታይ የለውጥ እርምጃ እና የጠንካራ ህዝባዊ ተሳትፎ ድምር ውጤት አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአዲስ መንፈስ ለመገንባት ጽኑ መሠረት እየሆናት ባለበት አዲስ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
በይቅርታ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር መርህ የአንዲት ሉአላዊት ሃገር ህዝቦች በልዩነት ውስጥ ደምቆና ፈክቶ በሚወጣ ማንነት የጥላቻና የመለያየት ግንቦችን በማፈራረስ ጽኑ የአንድነት ድልድዮችን በየአካባቢው በመገንባት ወደ ፊት በመገስገስ ላይ ነን፡፡
ለእነዚህ አፈጻጻሞች በእማኝነት ከሚነሱት ጥቂት ማሳያዎች መካካል የጠበበውን የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳር ለመለወጥ በተሠሩት ሥራዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ታራሚዎች በይቅርታ ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸውና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል፤ ለዓመታት በትጥቅ ትግልና በተለያዩ መንገዶች በውጪ ሆነው በሃገራቸው ጉዳይ ፈቅደውና ነጻ ሆነው እንዲሳተፉ በይቅርታ ጥሪው ተስማምተው ሠላማዊ ትግል ለማካሄድ ዕለት በዕለት ወደ ሃገራቸው አየገቡ ይገኛሉ፤ ሁሉም የሚዲያ አውታሮች ነፃ የዘገባ አቅማቸውን መጠቀም የቻሉ ሲሆን ህብረተሰቡም ካለአንዳች ስጋትና መሸማቀቅ ነፃ ሃሰቡን እየገለፀ ይገኛል፡፡
በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ውስጥ የነበሩ ዓይነተ ብዙ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ፣ የማረሚያ ቤት አመራሮችም ከሃላፊነታቸው ለቀው በአዲሱ የለውጥ ሃይል እንዲተኩ ተደርጓል፡፡
በዲፕሎማሲው ረገድ ከቅርብ የጎረቤት ሃገር እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ካሉት ሀገራት ጋር የተደገረው ግንኙነት የላቀ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን ከኤርትራ መንግስት ጋር የተካሔደው ስምምነት ደግሞ ራሱን የቻለ ታሪካዊ ምዕራፍ የተከፈተበት ተግባር ነው፡፡
በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለይም በአሜሪካ ልዩ ልዩ ግዛት ከሚገኙት ጋር በተካሄደው ውይይት መሠረታዊው የልዩነትና የተቃውሞ ምዕራፍ ተዘግቶ አዲስ በሆነ የአንድነትና የሃገር ፍቅር ስሜት በገንዘብ፣ በእውቀትና በልዩ ልዩ የሙያ አቅም አገራቸውን ለመርዳት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡ የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በማቋቋምም ለሃገራቸው ልማት የድርሻቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ይህ ብቻም አይደለም በተለያዩ ምክንያቶች ለሁለት ተለያይተው የነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አባቶች በአስደናቂ ሁኔታ በመታረቅ ከስደት አገር ተመልሰው የፍቅር ጉዞአቸውን በአንድ አቅጣጫና ዓላማ አጣምረዋል፡፡
በእስልምና ሃይማኖት ረገድም በተመሳሳይ በሁለት ተለይተው የነበሩ ወገኖች በፍቅር ተስማምተው አንድነታቸውን አድሰዋል፡፡
በኢኮኖሚውም ረገድ ከወራት በፊት በከፍተኛ ጉድለት ውስጥ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ጉድለት እንዲስተካከል በተሠራው አበረታች ሥራ ከሃገር ውስጥና ከውጪ ደጋፊ አካላት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ይህ ማለት ግን እስከ አሁን በተሠሩት ሥራዎች የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ ላይ መገኘታችንን የሚያመላክት አብሪ ምልክት ነው እንጂ ገና ከፈተናና ከልዩ ልዩ መሰናክሎች ወጥተናል ማለት አይደለም፡፡
በመሆኑም መንግስትም እንደ መንግስት ህዝብም እንደ ህዝብ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለው ሁሉ በይቅርታ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር መንፈስ የልዩነትና የጥላቻ ወይም የመነቃቀፍ አላስፈላጊ አዝማሚያዎችን አምርሮ በመከላከልና ወደ ኋላ በመጣል በአዲሱ ዓመት በአዲሱ የለውጥ ጎዳና ወደ ፊት እንዲገሰግስ የሚያነሳሳው መርሃግብር አካል እንዲሆን ጥሪ ቀርቦልናል፡፡
በነባሩ የሃገራችን ወግና ልማድ አዲስ ዓመት የአዲስ ተስፋ ምኞት ማንፀባረቂያ የብሩህ ህይወት የምሥራች ማብሰሪያ፣ ሜዳ ሸንተረሩ የአደይ አበባ መፍኪያና መድመቂያ እንደመሆኑ እንደ ሃገር እነዚህን አኩሪ እሴቶች በሃገራዊ ለውጡ መንፈስ በመቃኘትና በማጉላት አዲሱን ዓመት “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር!” በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ መርሃ ግብር ከፌዴራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች በድምቅት ይከበራል፡፡
በፍቅር ስንደመር ጥላቻ ይከስማል፤ በይቅርታ ስንሻገር ቂምና ቁርሾ በነበር ይተረታል፡፡ ይህን ጊዜም በብዝሃነት ልዩነት ውስጥ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ደምቆ ይታያል!
No comments