Latest

ታጋይ አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ (ከፕ/ር መስፍን ወልደማርያም)

ታጋይ አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ (ከፕ/ር መስፍን ወልደማርያም)

ብርሃኑ ነጋን መጀመሪያ የተዋወቅሁት በኒው ዮርክ ከተማ ነበር ። እንደሚታወቀው በኒው ዮርክ ሁሉም ነገር በጣም ፈጣን ነው ፤ ብርሃኑም ደምበኛው የኒው ዮርክ ሰው ሆኖብኝ ነበር ።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኃላ የበለጠ ለመተዋወቅ ቻልን ። በጣም እየተቀራረብን መጣን ። በብርሃኑ ላይ ሁለት በኢትዮጵያውያን መሃከል ውድ የሆኑ ጠባዮችን አግኝቼበታለሁ ፤ አንዱ በሚያምንበት ነገር ላይ ሥራ ተጠይቆ ሰበብ አይፈልግም።

ለምሳሌ ኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባሄ) በተለያዩ ርዕሶች ላይ ንግግር የሚያደርግ ሰው ለማግኘት በጣም ይቸገራል ፤ ብርሃኑ ሲጠየቅ ሁልጊዜም ፈቃደኛ በመሆኑ ለኢሰመጉ ንግግር ለማድረግ እንኳን በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች ይሄድ ነበር ።

ብርሃኑ ይሄንን የሚያደርገው ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ጊዜ ኖሮት አይመስለኝም ፤ ሕዝብን ለማስተማር የሚደረገው ጥረት በጣም አስፈላጊ መሆኑን በማመን ነበር ። በዚህም ምክንያት ስለመብት አስተማራችሁ ተብለን በማዕከላዊ ለአንድ ወር ታስረናል ።
.
ሁለተኛው የብርሃኑ ብርቅ የሆነ ጠባይ ሥራ በጭራሽ የማይደክመውና ደከመኝ የማይል መሆኑ ነው ። እስካሁን ድረስ እንዳየሁት እንዲያውም ሥራው በከበደ መጠን ብርሃኑ ኃይል እየጨመረ ይሄዳል ። ከሥራ ጋር የተያያዘ ግሩም ጠባይ ሌሎችንም ሰዎች ለማሰራት መቻሉ ነው ።

ሥራ ከሌለ ብርሃኑ ሥራን ይፈጥራል ። ለሥራ ኃላፊነትን በገዛ እጁ ለመውሰድ ወደኋላ አይልም ። ማዕከላዊ በነበርንበት ጊዜ ራሱን የፅዳት ሹም አድርጎ መፀዳጃዎቹንና ክፍሎቹን ፣ መተላለፊያዎቹንም በጣም ንፁህ አድርጎ ይዞ ነበር ።

አንድ ሌላ በቅርቡ ስለ ብርሃኑ የተረዳሁት ነገር አለመግባባት ባለበት ሁኔታ ሰዎችን ለማቀራረብና ለማግባባት ቁርጥ የሆነ አቋም ይወስዳል ፤ እንዲያውም እልህ ውስጥ ይገባል ።

አንድ ጉዳይ ላይ ሌላ ሰው የበለጠ የሚያውቅ ከመሰለው መጠየቅ በጭራሽ አይፈራም ፤ የተለያየ ዕውቀት ፤ የተለያየ ችሎታ ፣ የተለያየ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ማማከርና ሀሳቡንም በሚያገኘው ለማሻሻልና ለማጠናከር የሚሞክር ሰው ነው ። የራሱን ሀሳብ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዘኛ ለማስረዳት ከፍ ያለ ችሎታ አለው።

ያዝልቅለት ።
.
ምንጭ: መዝናኛ 1ኛ ዓመት ቁጥር 001 ፣ ገፅ 11
©ፕ/ር መስፍን ወ/ ማርያም ፤ ነሐሴ 1997

No comments