Latest

የአጼ ምኒልክ አስገራሚ ውልደት

አጼ ምኒልክ

ዛሬ ነሐሴ 12 የዐፄ ምኒልክ የልደት ቀን ነው፡፡ ታላቁ ደራሲ መንግሥቱ ለማ አባቱን አለቃ ለማን ስለታሪክ እየጠየቀ ከ80 በላይ በሆነ የቴፕ ካሴት ቀድቶ፤ ከዚያም እንደወረደ ጽፎት በታተመው መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ መጽሐፍ ላይ የእምዬ ምኒልክን አወላለድ (ልደት) አለቃ ለማ እንዲህ አጣፍጠው ይተርኩታል፡፡  


ታሪኩ እንዳይበዛ በከፊል ነው ያቀረብኩት፤ ቀጥሎ ካስቀመጥኩት ትረካቸው በፊት አለቃ ለማ ስለ ምኒልክ እናት ልደትና ቤተሰብ የተረኩት ነበር፤ እኒህ የምኒልክ እናት አለቃ ምላት ቤት “በግርድና” ከገባች በኋላ ያለውን መሳጭ የሽማግሌ ትረካ በወቅቱ የአካባቢ ዘየ ከድምጽ የተወሰደ ስለሆነ ቃላቶቹን ልብ ይሏል … 
መልካም ንባብ!

“…እንግዲህ የምኒልክ እናት ባባቷ መቄት ናት፡፡

መጣችና ኻለቃ ምላት ቤት ግርድና ገባች፡፡ ያንኮበር ሚካኤል አለቃ ናቸው፤ አለቃ ምላት በዚህ አገር ክቡር ናቸው እንደ ጳጳስ፡፡ ልጅ እግር ናት፣ ማለዳ ግብ ውኃ ጠጥተዋል ከጓደኞቿ ጋራ

‘ዛሬ እንዲያው ሲጫዎትብኝ አደረ ቅዠት፡፡’

‘ምንድነው?’

‘ኧረ እንዲያው ምኑን አውቀዋለሁ? – ከብልቴ ጠሐይ ወጣች’ አለች፡፡ እነዚያ ገረዶች ሣቅ! ሃይ! ሃይ! ሣቅ፡፡ እየተሳሳቁ እቤት ገቡ፡፡ ጠሐይ ከብልቴ ወጣች አለች ሲሉ የቤቱ ምስሌኔ ሰማ፡፡ ኻለቃ ምላት ዘንድ ገባ፤

‘ኧረ ጌታዬ ይች ዕንግዳ ገረዳችን ጉድ አመጣች!’

‘ምን አረገች – ምን አረገች?’

‘ጠሐይ ከብልቴ ወጣች አለች፡፡ አሁን አሽከሮቻችን ሁሉ ይሳሳቃሉ’ ብሏቸዋል፡፡

‘እህ! ታዲያ ይች ከኛ ዘንድ ምን አላት? ኸላይኛው ቤት ውጪ በሏት፡፡’ አሉ፡፡

አንኮበር ቤተ መንግሥቱ ኸላይ ነው፤ ጉባ ነው ቤተ መንግሥት ያለበት፡፡ (አንኮ ኦሮሞይቱ ባላባት ናት፤ የሷ ከተማ ነው አንኮበር፡፡ እሷን ወግተው አስለቅቀው የሣህለ ሥላሴ አያታቸው ገቡ፡፡)

ተመለሰ ሄደና ‘ኧረ ጌታኮ መልካም ተርጎሙላት’

‘ምናሉ?’

‘ኸላይኛው ቤት ውጪ በሏት ፤ ከኛ ምናላት?’ ብለው አሉ፡፡ ጓደኞቿ ሁሉ ሰምተዋል ፤ ተሳሳቁ፡፡

ውሀ እሚቀዱት ከቤተ መንግሥቱ ጋር ካንድ ነው እታች ከሚካኤል ግርጌ ነው፡፡ ይችም ዕንግዳዋ ወንዝ ወረደች አንድ ቀን፡፡ እነዚያ የቤተ መንግሥቱ ሥራ ቤቶች የማያውቋት ናቸውና፤

‘ይችም የናንተ ናት?’

‘አዎ’

‘የየት አገር ናት?’

‘ኧረ ይቺማ ጉድ ያላት ናት! ከብልቴ ጠሐይ ወጣች ብላ እልም አይታ፣ ጌታ ቢሰሙ ኸላይኛው ቤት ውጪ ብለው አሏት’ ተባለ – ትርጓሜ፡፡

አለቃ ምላትን መላው ሸዋ ይጠብቃቸዋል አነጋገራቸውን፡፡ እኒያ ሥራ ቤቶች ሰሙና ወጡ፤

‘ኧረ አለቃ ምላት ቤት አንዲት ገረድ ገብታለች! …’

‘እንዲህ ብላ አለመች አሉ …’

‘ኸላይኛው ቤት ውጪ ብለው ተረጎሙ አሉ …’ የሣህለ ሥላሴ ባለቤት የነኃይለ መለኮት የነሰይፉ እናት፤ ‘ጥሩልኝ ያቺን ልጅ!፡፡’ ተጠራች፤ መጣች፡፡ ‘አገርሽ የት ነው?’

‘መንዝ’

‘ኸኔ ጋር አትቀመጭም ልጄ?’

‘ምን ከፋኝ’

‘ተቀመጪ፡፡ በሉ ጥጥ አምጡላት – የጅ ሥራ ታግባ፡፡’ ዛዲያ የሸዋ ሴት ለእጅ ሥራ የጥጥ ነገር እንዲያ ነው፤ ደስ አሰኝቷል፡፡ ምንጣፉን ልብሱን እሳቸው ካሉበት ተኚ ብለው ሰጧት፡፡

ሰይፉን ነው እሚወዱ ሴቲቱ፡፡ (ሣህለ ሥላሴ ኃይለ መለኮትን ይወዳሉ፣ ትልቁን፡፡) ያ ጠሐይ ከሰይፉ እንዲወለድላቸው፤ እንዲህ ያለች ልጅ ይዤልሃለሁ – እንዲህ ያለች እንዲህ ያለች – ብለውታል ለሰይፉ፡፡

ሰነበተች፡፡ ማታ እልክልሃለሁ ብለውታል፡፡ እንግዴህ ከሣህለ ሥላሴ ቤት ግብር ይበላሉ ልጆቹ ኻባታቸው ቤት፡፡ በልተው መጥተው፤ ሽንጥም ታናሽም ቢሆን ደሞ ይጨመርና ጠጁ ይሆንና መሶቡ ወጡ መጥቶ – የልጆች ቤት አለ – በላይ ኃይለ መለኮት ይቀመጣል፤ ቀጥሎ ሰይፉ ነው፤ በወዲያ በኩል ዳርጌ፤ ደሞ ኃይሉ ነበሩ የይፋት – እነዚያ ይቀመጣሉ፡፡ ባለሟሎች ይቀመጣሉ፡፡ የቀረው ይቆማል፡፡ እንደገና ግብር ይገባል፤ ቅልጥ ይላል፡፡

ለሰይፉ የሚወዳት ሌላ ሴት አለችው፡፡ እናቱ ያቺን ሴት ለሰይፉ ውሰዱና ስጡ – ሄዳችሁ ኸሰይፉ ምኝታ አስቀምጧት አሉና፣ ላኩለትና፤ መጥታ ተቀምጣለች፡፡ ሰማ፡፡

‘ወንድሜ እምትመጣ ሴት አለችብህ?’ አለ ኃይለ መለኮትን፡፡

‘የለችብኝም፡፡’

‘እሜቴ አንዲት ሴት መርተውብኛል፡፡ የኔ እገሊት ትመጣለች፤ አሁን ተመልሳ ሁለተኛ አላገኛት፤ እባክህ አንተ ውሰድልኝ፡፡’

‘እኔ ምን ቸገረኝ!’ – ኃይለ መለኮት፡፡

ወጣችና፣ ኸዚያው፡፡ በበነጋውም መጣች፣ ኸዚያው፡፡ ምኒልክ ተጸነሰ፡፡

ከሰይፉ ጸነሰችልኝ ብለው ደስ ብሏቸው ሳለ እናትዮዋ፤ ‘ከኃይለ መለኮት እኮ ነው የጸነሰችው!’ አሏቸው ሥራ ቤቶቹ፡፡

‘እንደምን?’

‘ሰይፉ አይሆንም ብሎ፡፡’

‘ጥራት!’ አሉ፡፡ ‘አንቺ ከማነው ያረገዝሽው? ምነው? እኔ የሰደድኩሽ ከሰይፉ አይደለም ወይ?’

‘እሱማ ሌላ አለችብኝ ብሎ ለኃይለ መለኮት ሰጠኝ፡፡’

በእግር ብረት ታሠረች፡፡

ኋላ እኛ አማችዬው የሣህለ ሥላሴን ሴት ልጅ ያገቡ ሰሙ፡፡ ‘ምነው እመቤቴ! ምነው በሴት ልጅ እንዴት ይጫወታሉ?’

‘እ! ወንድማማቾቹን ልታጋድል – ከኃይለ መለኮት አረገዝኩ ትላለች!’

‘ታዲያ፣ እነሱ ይተዋወቃሉ አይሆንም ሲል ጊዜ ሰይፉ – ሴት ናት …’ አሉ ፣ አስለቀቁ፡፡

ሣህለ ሥላሴ ሰሙ፤ መጽነሷን ሰሙ፡፡ ምኒልክ ተወለደ፡፡ ስትወልድ ጊዜ፤ ጎረቤላ (ኻንኮበር ማዶ ጉባው ነው) ቦታ አደረጉና ድርጎ አመላላሽ አርገው ጠባቂ ሁሉን አደረጉ፤ እዚያ አስቀመጡ፡፡ ሰንብተው ‘አምጡ አሳዩኝ’ አሉ፡፡ መጣ ያ ልጅ፡፡ አዩ ‘ምን ይልህ’ ያሉ ሣህለ ሥላሴ ናቸው፡፡ ‘እንግዲህ አንተን ሸዋ ምንይልህ? ሸዋ ምን ይልህ!’ አሉ፡፡ ‘ምኒልክ’ ያለ ተማሪ ነው – ለቅኔ -በዱሮው ምኒልክ፡፡ እሳቸው ያሉ ‘ምን ይልህ’ ነው፡፡

ኋላ ሰነበቱ፣ ‘ይኸ ልጅ በመንግሥት ይበልጠኛል በዕድሜም ይበልጠኛል’ አሉ፡፡ ‘ቁመን ጥላችንን እናለካካ ተባባልነ፡፡ የኔ ጥላ እዚህ ቀረ፣ የሱ ጥላ ከዚያ ታች ወርዶ ሄደ! ዕድሜ እሱ ይበልጣል፡፡ ጫማችንን እናለካካ ተባባልንና፤ እኔ ረግጬ እርገጥ አልኩት፡፡ አልፎ ብዙ ጋት ይሆን አልፎ ሄደ የሱ እግር፡፡ ያልገዛሁትን አገር ይገዛል፡፡ ከፈረንጅ አገር ግብር ይጣልለታል፣ ከባሕር ማዶ፡፡ ልባርጉ፡፡’ አሉ ይባላል – እንደገለጠላቸው፡፡”

ታዲያ በዚህ ግርምት ውስጥ ክስተት የሆኑት እምየ ሚኒሊክ እነዚክ ገጸ በረከቶች ለኛ ጀባ ሲሉን ለመኖራችን መሰረት ሆነውን አልፈዋል።

ጀግና ሲዘከር

ታሪክ አብሮት አይሞትም

አጼ ምኒልክን በሕይወት ዘመናቸው የሰሯቸውን ድንቅ ተግባራት በደማቅ ብእርና ብራና የተከተቡ ናቸውና!

1835 ዓ.ም. -------------ወፍጮ
1882 ዓ.ም. -------------ስልክ
1886 ዓ.ም. ------------ፖስታ
1886 ዓ.ም. ------------ባህር ዛፍ
1886 ዓ.ም. ------------ገንዘብ
1886 ዓ.ም. ----------የውሃ ቧንቧ
1887 ዓ.ም. -----------ጫማ
1887 ዓ.ም. --------------ድር
1887 ዓ.ም. -------------የሙዚቃ ት/ቤት
1887 ዓ.ም. ----------የፅህፈት መኪና
1889 ዓ.ም. ----------ኤሌክትሪክ
1889 ዓ.ም. ---------------ዘመናዊ ህክምና
1889 ዓ.ም. -------------ሲኒማ
1889 ዓ.ም. --------------የሙዚቃ ሸክላ
1889 ዓ.ም. -------------ቀይ መስቀል
1890 ዓ.ም. -----------ሆስፒታል
1893 ዓ.ም. -------------ባቡር
1893 ዓ.ም. -------------ብስክሌት
1896 ዓ.ም. -------------መንገድ
1897 ዓ.ም. ---------------ፍል ውሃ
1898 ዓ.ም. ---------------ባንክ
1898 ዓ.ም. -------------ሆቴል
1898 ዓ.ም. -------------ማተሚያ
1898 ዓ.ም. --------------ላስቲክ
1899 ዓ.ም. ------------አራዊት ጥበቃ
1899 ዓ.ም. -----------የጥይት ፋብሪካ
1900 ዓ.ም. -------------ጋዜጣ
1900 ዓ.ም. ------------አውቶሞቢል
1900 ዓ.ም. -----------የሚኒስትሮች ሹመት
1901 ዓ.ም. -----------ፖሊስ ሰራዊት
1904 ዓ.ም. ---------የመድነኒት መሸጫ ሱቅ

አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ መሐንዲስ!
ክብር ለቀደሙት አባቶቻችን!

No comments