Latest

በኮምቦልቻ ከተማ በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ ችግር ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ - ቢቢሲ

በኮምቦልቻ ከተማ በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ ችግር ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ትናንት በኮምቦልቻ ቀበሌ 6 "ተቅዋ መስጂድ" መጠነኛ የቀኖና የአስተምህሮ ልዩነት ባላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ ግጭት 33 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደረሰባቸው።

በወቅቱ ጉዳት ያደረሱ 10 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ያለለት ዘገየ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የተጎዱት በመስጂዱ መድረሳ ውስጥ ቁርአን ይቀሩ የነበሩ ተማሪዎች ሲሆኑ ከነዚህ መካከልም አስራ አንዱ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተልከዋል።

ቀሪዎቹ 22ቱ በኮምቦልቻ ከተማ በሚገኙ ሁለት ጤና ጣቢያዎች ሕክምና አግኝተው ወደየቤታቸው መመለሳቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

የፖሊስ ኃላፊው ጨምረው እንደሚናገሩት ይህ መስጂድ በ2004 በተካሄደው የእስልምና ምክር ቤት ምርጫ በመጅሊሱ ሥር እንዲተዳደር የተወሰነ ቢሆንም አሁን ግን 'መስጂዱን እኛ ነን የሠራነው፤ ይመለስልን፤ የሃይማኖት አባቶቹም ይመለሱ' የሚሉ ወገኖች መጥተዋል።

ይህ የመጅሊስ ውሳኔ ያስኮረፋቸው አማኞች ወደ መስጊዱ መምጣት አቁመው የነበረ ቢኾንም በዚህ ዓመት ግን እነዚህ ወገኖች በረመዳን የጾም ወቅት ወደ መስጂዱ ገብተው መስገድ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።

ኃላፊው እንደሚሉት ችግሩን ለረጅም ጊዜ በከተማው አስተዳደር፣ በፀጥታ አካላትም በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ውጤት አላስገኘም።

በአማኞቹ መካከል አለመግባባት በመኖሩ የፖሊስ አባላት ለአንድ ወር ከአስር ቀን ሰላም ሲያስከብሩ እንደቆዩና ከዚህ በኋላ ግን ለሕይወታችን ያሰጋናል በሚል ተመልሰው ማመልከቻ በመጻፍ ለቅቀው እንደወጡ ይናገራሉ።

ሰሞኑን በድጋሚ ለከተማው አስተዳደር ጥያቄያቸውን ማንሳታቸውን የሚያስታውሱት ኃላፊው ፖሊስ እና የከተማው አስተዳደር በእርቅ ለመፍታት ከተመረጡ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን እየሠራ እያለ ይህ ግጭት ተፈጥሯል ይላሉ።

በፖሊስ ኃላፊው ሐሳብ የሚስማሙት እና ለቢቢሲ ምስክርነታቸውን የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች የሱፍ መሃመድና መሃመድ አሊ በመስጂዱ ይማሩ የነበሩት ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ እንደነበሩ ይናገራሉ።

መስጂዱ ለአካባቢው ሙስሊም ማኅበረሰብ ምንም ዓይነት አገልግሎት እየሰጠ አልነበረም የሚሉት እነዚህ ግለሰቦች መስጂዱን የሠራነው እኛ ነን በማለት የባለቤትነት ጥያቄ ያነሳሉ።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ኪሮስም መስጂዱ ከዚህ በፊት የባለቤትነት ጥያቄ ይነሳበት እንደነበር ይናገራሉ።

"መንግሥት ማንኛውም መስጂድ በመጅሊስ ሥር እንዲተዳደርና ሕዝበ ሙስሊሙ በጋራ እንዲጠቀምበት በወጣው መመሪያ መሠረት ሁሉም አማኝ በመስጂዱ ይጠቀሙ ነበር" በማለት ያስታውሳሉ።

ነገር ግን በትናንትናው ዕለት ጠዋት 2፡00 ሰዓት አካባቢ አዳጊዎች ቁርአን እየቀሩ ባለበት ሰዓት መስጂዱ "ለኛ ይገባል" በሚሉ ወገኖች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተናግረዋል።

በመስጂዱ ከ14 -18 ዓመት ድረስ ያሉ አዳጊዎች እንደሚገኙበት የተናገሩት አቶ ሳሙዔል ጥቃት ያደረሱት ወገኖች በእጃቸው ዱላ፣ ፌሮ እና መዶሻ ይዘው እንደነበር መስክረዋል።

ጤና ጣቢያ በሕክምና ላይ የሚገኙትን አማኞች እንዳናገሯቸው የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል ቁርአን እየቀሩ ባሉበት ሁኔታ አጥሩን ገነጣጥለው ገብተው እንደደበደቧቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ወረዳ የእስልምና ጉዳዮች ተጠሪ የሆኑት ሼህ ሰዒድ አሊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሐሙስ በፊት መስጂዱ ይገባናል በሚሉትና በመጅሊሱ መካከል የከተማው ከንቲባ በተገኙበት ውይይት ማድረጋቸውንና ሽማግሌዎች ተመርጠው ውይይት አድርገው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሐሙስ ማለዳ ከኮሚቴዎች ጋር ለመወያየት ተቀጣጥረው ሳለ መስጂዱን እናፀዳለን በሚል ሕዝበ ሙስሊሙን በነቂስ ቀስቅሰው እንደመጡ ይናገራሉ።

"ስብሰባው የተጠራው ኻሊድ መስጂድ ነው፤ እዛ አይደለም" ቢባሉ እምቢ በማለት ችግር መፈጠሩን ይናገራሉ።

መጅሊሱ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል ብሎ የሚያስበውን ምን እንደሆነ የተጠየቁት ሼህ ሰዒድ አሊ ከፌደራል የእስልምና ጉዳዮች እና የኡላማ ምክር ቤት ውሳኔ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ያስረዳሉ።

ይህንን ሐሳብ 'መስጂዱ ይገባናል' ላሉ ወገኖች አቅርበው የነበሩ ቢሆንም "ተበደልን፤ ልጆቻችን ቁርአን እየቀሩ አይደለም፣ ኢማሞቻችን ገብተው ያሰግዱ፤ የራሳችን ሰዎች እንሰይም'' የሚለው ጥያቄ ገፍቶ በመምጣቱ ችግሩ መፈጠሩን ያስረዳሉ።

"እኛ ግን 'በመመሪያ የተሾሙ ሰዎች አሉ እርሱን መሻር አንችልም' ብንልም እነርሱ ስለቸኮሉ ይህ ጥፋት ደረሰ" ብለዋል።

ከተማችን አሁን ስጋት ውስጥ ናት የሚሉት ሼህ ሰዒድ አሊ በፌደራል ያሉ አካላት መፍትሄ ይስጡን ሲሉ ተማፅኗቸውን ያቀርባሉ።

መስጂዱን እስካሁን እያስተዳደርን የነበረው መጅሊሱ እንደነበር ሼክ ሰዒድ አሊ አስታውሰው አሁን ከግጭቱ በኋላ ግን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየጠበቁት እንደሚገኙም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

No comments