Latest

"እናቶችና ሀገር አንድ ናቸው" አርበኛ ጎቤ መልኬ (ዜናው ዘለቀ ባየህ እንደፃፈው)


ጊዜው ረዥም ነው። መሰረተ ልማት ባልተስፋፋበት ሰዓት እናቶች ሚወልዱት በባህል አዋላጅ ነው። ከእነሱ አቅም በላይ ካልሆነ ህክምና አይወሰዱም ነበር። 


አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ እኔ እና ዋዋ እሱ ከእርሻ ቦታው አድሮ ወደመኖሪያ ቤቱ ሳንጃ ለመሄድ እኔም ለግል ስራ ወደዛው ለማቅናት በተዘጋጀሁበት ሰዓት ፍልውሀ ከምትባል ትንሽየ የገጠር ከተማ ተገናኘን ከዛም ሁሌም ስንገናኝ እንደምናደርገው ጨዋታ ጀመርን። 

ወዲያውኑ መንገዳችን ወደ አንድ አቅጣጫ መሆኑ ስለታወቀ እንደሁልጊዜው "እንካ ያዝ" ተብየ የጦር መሳሪያውን ተሽከምኩ። ጥቂት እንደቆየን ታዲያ አንድ መነሻውን ሁመራ ያደረገ ሽንጣም አውቶቡስ ከተፍ ይላል።እኛም እንዲያሳፍሩን ስንጠይቃቸው እሽ ይሉናል። ወትሮ መኪናው እንዲያ ባሉ ትናንሽ ከተሞች ላይ ቆሞ አያውቅም። ተሳፍረን 6 ያህል ኪሎ ሜትር እስክንጓዝ እኛ ጨዋታችን አልተገታም። ከአውቶቡሱ የሞተር ኮፈን ላይ እሱ ተቀምጧል።

እኔ ከገንዘብ ተቀባዩ ጎን ቆሜአለሁ። ታዲያ በእኛ ጨዋታ ሰው ሁሉ ሳቁን ያቀልጠው ይዟል። በዚህ የደመቀ ጨዋታ ላይ ሳለን ከወደኋላ ወንበር አካባቢ አንዲት ሴት ትጮሀለች። ያኔ ምን ሆና ነው ይላል ዋዋ.... "ምጥ ላይ ያለች ሴት ናት የአሁኑ ጩኸቷ ግን ከእስካሁኑ ይለያል" አሉ። የኔ ሾፌሩን መኪናውን ወደዳር አድርጎ እንዲያቆም ይነግረዋል። ሾፌሩም ያቆማል።

ቦታው ጭብጭባ ይባላል። ወዲያውኑ ወደኋላ ወንበር በፍጥነት ገስግሶ ሲደርስ ሴትዮይቱ በመውለድ ላይ ነች። ይህን ያየው ዋዋ አብሯት የመጣውን የጤና ባለሞያ ሞያዊ እገዛ እንዲያደርግላት ይጠይቀዋል። ባለሞያውም ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ያላደረገ ነበር። የጥንቃቄ ማድረጊያ መሳሪያ ግላቭ አልያዝኩም። 

  ስለዚህ ለመርዳት ይከብደኛል አለው። "አንተ እንዴት ያልክ ሞያተኛ ነህ። እነኚህን ጥቃቅን ነገሮች ሳትይዝ ነው እንዴ አጅበሀት የመጣህው?" ብሎ እራሱ ሊያግዛት ሲዘጋጅ "እንዴ ዋዋ ባልታመነው ጊዜ ስለው ምን እንዳይመጣ... አለኝ በሽታ" አልኩት.."በሽታስ እንዲህ ሚሰቃይን ሰው እያዩ ዝም ብሎ መቀመጥ ተው ባክህ ቁስቋም ታውቃለች" አለና ወደስራው ገባ። 

አዋለዳትም። በስርዓትም አንድ ሴት ስትወልድ እሚከናወነውን ነገር ሁሉ በፍጥነት እና በጥንቃቄ ከወነው የሱን ትጋት ያየው የጤና ባለሞያም ሳይጠየፍ እና ምንም አይነት ግላብ ሳያደርግ እማያቃትን ሴት ደም በእጁ ሲነካው ሲያይ በራሱ አፈረ እና ወደመጨረሻ ለመቀላቀል ሞከረ።

ያኔ ዋዋ ''እናቶች እና ሀገር አንድ ናቸው። እነሱ ዘራችንን ባያስቀጥሉት ሀገር ልትኖረን ትችላለችን።" አለው። " በሞያህ ስትሰራ ብትችል ቅድመ ዝግጅት አድርግ። ሞያህ ነው እና ትጥቅህን አሟልተህ ነው መጔዝ። ይህን ባለአሟላህበት ጊዜ ግን እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥምህ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ሰጥተህ በሞያህ ሰዎችን መርዳት አለብህ" አለው።

ሁሉም ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ መንገድ ተጀመረ።እጅግ አባጣ ጎርባጣውን እና አስቸጋሪውን መንገድ እንደምንም ጨርሰን። ሳንጃ ደረስን። ያኔ "በሉ እናንተ ሂዱ ሴትዮይቱ ግን መንገዱ አድካሚ ስለሆነ ትጎዳለች ስለዚህ ከእኔ ቤት ማረፍ አለባት።" ብሎ አብረዋት የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ከመኪናው በማውረድ ወደቤቱ ወሰዳቸው።

እንደደረስንም ለባለቤቱ የማሪያም አራስ አመጣሁልሽ ብሎ ባህላዊ ክንውኖችን አስፈፅሞ የተለያዩ እንቲባዮቲክ መርፌዎችን የጤና ባለሞያዎችን እቤቱ ድረስ አስመጥቶ እርዳታ አሰጥቶ የማረሱን ስራ ለእናቱ እና ለባለቤቱ ኅላፊነቱን ሰጠ።  

ከዛም አብረዋት የነበሩትን ሰዎች "በቃ ወደስራችሁ ሂዱ። እሷ ስትጠነክር አንድ ሰው መጥቶ ይውሰዳት። እንደምታውቁት በባህላችን አንዲት ሴት ከወለደች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀን ሲመሽ እና ንጋት ላይ ፀሀይ ሳትወጣ ለንፅህና ሲባል ነው እንጅ ከአልጋ አትወርድም ይህንን ታውቃላችሁ" አላቸው።

እነሱም "ማን ትባላለህ?" አሉት፣ "ጎቬ መልኬ እባላለሁ" አላቸው። ላደረገላቸው ነገርም አመስግነው ሰውን ያህል ነገር አደራ ሰጥተውት ሄዱ። እሱም በአደራው መሰረት ክርስና እስከትነሳ እና ቤተሰብ እስኪመለሱ ተንከባክቦ በሰላም እና በሙሉ ጤንነት ለቤተሰቦቿ ያስረከበትን ጊዜ እጅግ ከማልረሳቸው የእርሱ ተግባሮች አንዱ ነው።

(ከጌታቸው ሽፈራው የፌስቡክ ገፅ ላይ የተገኘ)

No comments