Latest

ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ማለት የትግራይን ህዝብ ማሳነስ ነው – ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ

ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ

የህወኃት አንጋፋ ታጋይና የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ትንተና በስፋት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ 


በአሁኑ ወቅትም አገራዊ ለውጡን በመደገፍ፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ ተስፋና ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳይ፤ በለውጡ ዙሪያ፣ በትግራይ በሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና በቀጣዩ ጉባኤ የሚጠበቀውን የህወኃት ሪፎርም በተመለከተ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

አዲስ አድማስ – ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ በሀገሪቱ የመጡ ፖለቲካዊ ለውጦችን እንዴት ይገመግሟቸዋል?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ - ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በነበረው ቀውስ፣ ሃገሪቱ ወዴት ነው የምትሄደው የሚል ትልቅ ስጋት ነበር፡፡ በኋላ ግን ብዙ ሰው ባልጠበቀው ሁኔታ፣ ዶ/ር አቢይ ከኢህአዴግ ውስጥ በመውጣት ስጋቱ እልባት ማግኘት ችሏል። 

በወቅቱ በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረው ደመና ወዴት እንደሚያመራ ግልፅ ስላልነበረ፣ ዶ/ር ዐቢይ መምጣቱና የስልጣን ሽግግሩም በሰላማዊ መንገድ መከናወኑ ነው ተስፋ የሰጠን፡፡ ከዚያ ቀደም እንግዲህ የኢህአዴግ አስተዳደር፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን በኃይልና በአስተዳደራዊ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ነበር የሚሞክረው፡፡ 

በዚህ መንገድ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥቦ፣ የሰዎችን መብት ገፍፎ፣ ዲሞክራሲዊ መብቶችን አፍኖ፣ ህገ መንግሥቱን ሳይከተል ሲሰራ የቆየ የመንግስት አስተዳደር ዘይቤ መቀየሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡

አሁን ያለንበት ሁኔታም ለኔ አንድ የሽግግር ወቅት ነው፡፡ ድሮ ኢህአዴግ ሲከተለው ከነበረው የአስተዳደር ዘይቤ ወደ ሌላ የአስተዳደር ዘይቤ እየተሸጋገርን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አዲሱ የአስተዳደር ዘይቤ ግን በደንብ መልኩን አውጥቶ የገለጠ አይመስለኝም፡፡ ገና ራሱን በመግለጽ ሂደት ላይ ያለ ነው፡፡ 

ያላለቀለት በሽግግር ላይ ያለ የአስተዳደር ዘይቤ ደግሞ ከስጋቶች ነፃ አይሆንም። ሽግግሩን በደንብ ከተጠቀምንበት ደግሞ መልካም እድሎች ይኖሩታል፡፡

አዲስ አድማስ – የለውጥ ሂደቱ ስጋቶችና መልካም ዕድሎች ምንድን ናቸው?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ - ስጋቶቹ፤ አንደኛ በርካታ በውጭ ሃገር መሰረታቸውን አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ውስጥ በገፍ ገብተዋል። በእርግጥ የኢትዮጵያ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሃገር ውስጥ እንዲሆን መደረጉ ጠቃሚ ነው። 

በሌላ በኩል፤ በኢህአዴግ ድርጅቶች መካከል ያለው አለመግባባትም ስጋት ነው። በሀገር ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ኃይሎች እየተጠናከሩ ከሄዱ፣ እስከ 2012 ምርጫ ድረስ አዳዲስ የፖለቲካ አሰላለፎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች የአሰላለፍ ለውጥ ይኖራል የሚል ግምት አለኝ፡፡ 

ይሄ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ለውጥ በአንድ በኩል ዲሞክራሲውን ተቋማዊ ሊያደርገው ይችላል። በደንብ የታሰበባቸው ሁለትና ሦስት ጠንካራ አማራጭ ሃሳቦች ወደ ህዝቡ ቀርበው፣ በነፃ ምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ ስልጣን የሚይዝበት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ጠንከር ብለው ወደ ፓርላማ የሚገቡበት፤ ፓርላማው የኢትዮጵያን እውነተኛ የፖለቲካ ገፅታ የሚያንፀባርቅበት፤ የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ የበሰሉ ሃሳቦች ውይይት የሚካሄድባቸውና በዚያ ውይይት መሰረት ህዝብን ያሳመኑ ውሳኔዎች የሚደረጉበት ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

ይህ መልካም ዕድል ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል የዲሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት በደንብ ከተጠናከሩ፣ ለምሳሌ የምርጫ ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ከተዋቀረ፣ ነፃና ተአማኒነት ላለው ምርጫ ሰፊ ዝግጅት ከተደረገ፣ ፓርቲዎች አማራጫቸውን በበሰለ መንገድ ለህዝብ ማቅረብ ከቻሉ፣ ሚዲያዎች ነፃና ገለልተኛ ከሆኑ፣ የሀገራችን የዲሞክራሲ ስርአት ጠንካራ እየሆነ፣ ስር እየሰደደ፣ ህብረተሰቡም የተለያዩ የሃገር ግንባታ አማራጮች እየቀረቡለት፣ በቀረቡለት ሃሳቦች ላይ እየተወያየ ነፃ ምርጫ የሚያካሂድበትና የሃገራችን የፖለቲካ ሽግግር በአስተማማኝ መንገድ መሰረት የሚይዝበት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ የሚመስል የፀጥታ ስጋት አለ፡፡ የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ይገደላሉ፣ በየአካባቢው የታጠቀ ኃይል ህዝቡ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥርበት ሁኔታ እየታየ ነው።  

ይሄ የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ካልዋለ፣ ሀገር ውስጥ ህግና ስርአት ካልነገሰ፣ የፖለቲካ ተቃውሞና ወንጀል በግልፅ ካልተለየ ለቀጣይ ጉዞው ትልቅ ስጋትና አደጋ ነው፡፡ የፖለቲካ አስተሳሰብን በሰላማዊ መንገድ መግለፅ መብት ነው፤ በተቃራኒው ታጥቆ እየተንቀሳቀሱ ሰውን ማሸበር ደግሞ ወንጀል ነው፡፡ 

ስለዚህ መንግስት በፖለቲካው ተቃውሞና በወንጀል መሃል ግልፅ መስመር አስምሮ፣ እርምጃ መውሰድ አለበት። በሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱት ምህዳሩ የበለጠ እንዲሰፋላቸው ማድረግ፣ በአንፃሩ በታጠቀ ኃይል ተፅዕኖ ሰው ማሸበር ለሚፈልጉት ደግሞ በጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ መከላከል ካልቻለ፣ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እየሄዱ፣ ሀገሪቱን ለበለጠ አደጋ ሊያጋልጧት ይችላሉ፡፡ 

እዚህ ላይ ጠንከር ያለና ህዝብንም ያሳተፈ፣ የመንግስት ውሳኔና እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ መልካም ዕድል የተፈጠረውን ያህል፣ ትልቅ አደጋም ሊያጋጥመን ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡

አዲስ አድማስ – አገሪቱ በአብዛኛው ተቀባይነትን ባገኘ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚፈጠሩት ግጭቶች ምንጫቸው ምንድን ነው ይላሉ?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - እንግዲህ በህዝቡ ውስጥ ቀደም ሲል የተከማቹ ብሶቶች አሉ፡፡ አሁን ትንሽ ከፈት ሲደረግ ብሶቱ በሙሉ ይገነፍላል፡፡ በዚህ መንገድ መውጣቱም የሚጠበቅ ነበር፡፡ ትልቁ ጉዳይ ጉዳቱን መቀነስ እንጂ ሂደቱን ማስቀረት አይቻልም ነበር። 

የማዕከላዊ መንግሥቱ ደግሞ ሁኔታውን ተረድቶ ብሶቱን ከማባባስና ሂደቱን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ከመግፋት ይልቅ ሁኔታውን ማርገብ ይገባው ነበር። አንዳንድ በጅምላ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ብሶትን እየተጠቀሙ፣ በሌላው አካል ላይ ያልሆነ ቁርሾ እየፈጠሩ ያለ ይመስለኛል። በአሁኑ ወቅት ህዝብ ብሶቱን እየገለፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጉዳቱን የሚያመጣው የብሶት አገላለፁ ነው፡፡

በሌላ በኩል፤ ቀደም ሲል በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ተሰርቶ ነበር፡፡ የበደሉ፣ የብሶቱ ሁሉ ምንጭ፣ እሱ ነው ተብሎ፣ ውስጥ ለውስጥ በርካታ የፕሮፓጋንዳ ስራ ተሰርቷል። በአንፃሩ፤ ይሄን ፕሮፓጋንዳ የመመከት ስራ አልተሰራም፡፡  

ቀደም ሲል የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣንን ይቆጣጠራል ተብሎ የነበረው ኃይል ከቦታው ሲወጣ፣ ለዘመናት የነበሩ ጥላቻዎች ፊት ለፊት እየወጡ ነው ያሉት። ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የጥላቻ ፖለቲካ ደግሞ ለወደፊት በሃገራችን ውስጥ ልንፈጥር የምናስበውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም የሚበርዝ ነው፡፡ 

አንደኛውን ወገን ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ጠባሳም ጥለው የሚያልፉ ናቸው፡፡ በእርግጥ በዚህ ተስፋ የሚቆርጥ ህዝብ ይኖራል ብዬ አላምንም፤ ነገር ግን ተፅዕኖ አላቸው። ከላይ ያለው አመራር፣ ይህ አካሄድ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ እያወቀ ካልሄደ፤ ህዝቡም ይሄ ነገር ፈር መያዝ አለበት ካላለ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም። 

በህግ መጠየቅ ያለበት አካል ካለ፣ መጠየቅ አለበት። አጥፊዎች ከትግራይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ውስጥ አሉ፤ አጥፊዎቹ ወግ ባለው መንገድ ተጠይቀው፣ ለፍትህ ቢቀርቡ ይሻላል፡፡ አለበለዚያ በአጠቃላይ ይቅር እንባባል የሚል ስሜት ይዞ፣ በተቃራኒው የጥላቻ መንገዱን ወደ አንድ አካባቢ በመግፋት፣ ይቅርታም ሰላምም አይመጣም፡፡  

ስለዚህ ማዕከላዊ መንግስቱ፤ በህግ የሚጠየቁ አጥፊዎች ካሉ በወጉ በህግ መጠየቅ እንጂ ጥላቻን ወደ አንድ አካባቢ የሚያሰራጭ አካሄድ ማቆም አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የመንጋ ፖለቲካ ረገብ ማለት አለበት፡፡ ብዙ ጉዳቶች እያደረሰ ነው፡፡

አዲስ አድማስ – አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን የለውጥ ስሜትና ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - መጀመሪያ ይሄ ለውጥ ሲመጣ እኔ እስከማውቀው ድረስ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ፣ ”እንኳንም ይሄ ለውጥ መጣልን” የሚል ቀና አመለካከት ነበረው፡፡ “እኛ ለሀገር አንድነትና ነፃነት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለን ብዙም ያገኘነው ጥቅም የለም፣ በትግሉ ምክንያት የደረሰብንን ጠባሳ እስካሁን ተሸክመነው ነው ያለነው፣ አሁን ጥሩ ቀን መጥቶልናል” በሚል በትልቅ ተስፋ ነበር የደገፈው።  

የትግራይ ህዝብ፤ የተወሰኑ ከውስጡ የወጡ ሰዎች ስልጣን በመያዛቸው አልተጠቀመም፡፡ ህዝቡም ዘንድ ያለው ስሜት ይሄ ነው፡፡ አሁን ለውጡ ሲመጣ፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል የምንጠቀምበት ጊዜ መጥቷል የሚል ትልቅ ተስፋ ይዞ፣ ለውጡን በሙሉ ልቡ ሲደግፍ ነበር፡፡ በኋላ ግን በጅምላ የሚፈርጀውና ትግራይ ላይ ያነጣጠረው እንቅስቃሴ ሲመጣ፣ ህዝቡ ለውጡን በስጋትና በጥርጣሬ ለማየት ተገድዷል፡፡ 

ለስብሰባ በተመላለስኩበት ጊዜ ህዝቡ ዘንድ ያየሁት ስሜት ይህ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ የሀገሪቱ ሁኔታ ወዴት ነው እየሄደ ያለው የሚል ጥያቄ አለው ህዝቡ፡፡ በየሄድንበት እየተሸማቀቅን ልንኖር ነው ወይ? በሀገራችን ተዘዋውረን ሃብት አፍርተን፣ እንደ ማንም ሰው መብታችን ተጠብቆ በስርአት መኖር ልንከለከል ነው ወይ? የሚል ስጋት አለው፡፡ 
ለዚህ ስጋት ደግሞ ዋናው ምክንያት በየአካባቢው የትግራይ ህዝብ ዒላማ እየተደረገ፣ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት የመንጋ ፖለቲካ ነው። ሁለተኛው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚደረገው ግንኙነት ህዝቡን ያሳተፈ፣ የትግራይ ህዝብ በሚፈልገው ፍጥነትና አካሄድ የሄደ ስላልመሰለው ሰላሙ መፈጠሩን እየወደደውና እያደነቀ፣ አካሄዱን ግን በስጋት ነው የተመለከተው። እኛን የሚያገልል፣ ባዕድ የሚያደርግ ግንኙነት ሊመጣ ነው ወይ? የሚል ስጋት ህዝቡ ውስጥ እንዳለ፣ በየስብሰባ መድረኮቹና ከህዝብ ጋር በነበረኝ ግንኙነት መረዳት ችያለሁ፡፡

ይህ ተጨባጭ ስጋት ነው፣ መሪዎች የፈጠሩት ስጋት አይደለም፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝብ በድንበር ይገናኛል፣ ለዘመናት አብሮ ኖሯል፣ በሚገባ ይተዋወቃል፣ ተዋልዷል፣ ተዛምዷል፤ በጦርነቱ ወቅትም በጋራ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ከዚህ አንፃር የተጀመረው ግንኙነት እኛን ሊያገልል የሚችል ነው የሚል ከፍተኛ ስጋት አለው፡፡
ይሄ ተጨባጭ የሆነ የህዝብ ስጋት ነው፡፡ 

ግንኙነቱም ምን እንደሆነ አላወቅንም፤ ከጀርባ ያለውን ጉዳይ አላወቅንም፣ ግልፅነት የለውም በሚል ነው ስጋቱ በዚህ መጠን የተፈጠረው። ይሄን ስጋት ማወቅና እንዴት እንቅረፈው ብሎ መንግሥት ማሰብ አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ ህዝቡ ውስጥ ቁጣ ተፈጥሯል፡፡ ቁጣው ምንድን ነው? ከተባለ፣ መሪዎች አጥፍተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከትግራይ የወጡ መሪዎችን ጥፋት መነሻ በማድረግ፣ የህዝቡን መስዋዕትነት ማራከስ፣ እንደ እላፊ ተጠቃሚ መቆጠር ህዝቡ ውስጥ ቁጣ እየፈጠረ ነው፡፡ 

የዲሞክራሲ እጦትና የመልካም አስተዳደር ችግር ከየትኛውም የሀገሪቱ ክልል በትግራይ የባሰ ሆኖ ሳለ፣ እላፊ የስርአቱ ተጠቃሚ ተደርገን በጅምላ መፈረጃችንና የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ መሆናችን ተገቢ አይደለም ከሚል የመነጨ ቁጣ ህዝቡ ውስጥ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ለውለታችን ምላሽ ይሄ ነው ወይ የሚል ቁጣ አለ፡፡ ስለዚህ መሃል ሃገር ያሉ ፖለቲከኞች ይሄን ተገንዝበው፣ ለሃገር አንድነትና ለወደፊት ሰላም የሚጠቅም ነገር ቢያደርጉ መልካም ይመስለኛል፡፡

አዲስ አድማስ – ለውጡን የማይደግፉ አንዳንድ ወገኖች በየቦታ በህዝቡ ውስጥ ስጋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህ ረገድ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ሊነግሩን ይችላሉ?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - ከላይ የገለፅኩት ስጋትና ቁጣ እንዳለ ሆኖ፣ አሁን በተፈጠረው ለውጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው፣ ስልጣናቸውን ያጡ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሲያስቡት የነበረው የፖለቲካ አካሄዳቸው በድንገት የተቀየረባቸው ኃይሎች አሉ፡፡ 

እነዚህ ኃይሎች፤ የህዝቡን ስጋትና ቁጣ እነሱ ለሚፈልጉት አላማ ያውሉታል፡፡ በተደራጀ መንገድ ያባብሱታል። ህዝቡ ለውጡ መምጣቱ ጥሩ ነው ሲል ቆይቶ፣ “እንዴ! ይሄ ነገር ሁላችንንም ሊያጠፋን ነው እንዴ? ያጠፉትን መሪዎች ከህዝቡ የማይለይ ነው እንዴ?” የሚል ስጋት እየተፈጠረበት ነው፡፡ 

ከላይ የጠቀስኳቸው ሃይሎች ደግሞ ይሄን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ “ይሄውልህ ያልንህ አደጋ ሊፈጠር ነው፣ ትግራይን አደጋ ውስጥ ሊከቱ ነው” በማለት ቤንዚን ያርከፈክፋሉ። “ኢትዮጵያ እያልን አንድነቱን ለማጠናከር እንጥራለን እንጂ በዚህች ሃገር ውስጥ እኛ አንፈለግም፤ እንደ አጥፊ ኃይል እንታያለን፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ አንድነት የምትለው ነገር ላንተ አይጠቅምም” የሚል የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ተጀምሯል። ግማሹ ፕሮፓጋንዳ ራስን ከጥፋት ለመከላከል የሚደረግ ነው፡፡

አዲስ አድማስ – “ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው” የሚለው አባባል ብዙ ጊዜ ሲያወዛግብ ይታያል። እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? ህወኃት እና ለውጡስ ምንና ምን ናቸው?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - በህወሓት እና በትግራይ ህዝብ መሃከል ያለውን ቁርኝት በአግባቡ አለማየት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ሊያድበሰብሰው ይችላል። እርግጥ የህወሓት መሪዎች፤ ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ይላሉ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፤ የትግራይን ህዝብ ማሳነስ ነው።  

ህወሓትን የፈጠረው የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ ህወሓት አይደለም የትግራይን ህዝብ የፈጠረው። የትግራይ ህዝብ ከፈለገ ህወሓትን ያጎለብታል፤ ካስፈለገው ደግሞ ይገድለዋል፡፡ ትግራይ ውስጥ ልጆቹን ቤተሰቡን በህወሓት በኩል ትግል ውስጥ ያላስገባ የለም፡፡ ስለዚህ ህወሓት ሲያደርገው የነበረው ትግልና በህዝቡ መሃከል፣ በደምና በአጥንት የተሳሰረ ግንኙነት አለ። ይሄ ግንኙነት የፈጠረው ስነ አዕምሯዊ ጫናም አለ፡፡ ከዚህ ጫና ራስን በአንዴ ማላቀቅ ቀላል አይደለም፡፡

በሌላ በኩል፤ ከማንኛውም ህዝብ በላይ እኮ የዚህን ሥርአት ጭቆና መታገል የጀመረው የትግራይ ወጣት ነው፡፡ በሶሻል ሚዲያ ሥርአቱ እንዲስተካከል ሲጮህ የነበረው የትግራይ ወጣት ነው፡፡ ግን ደግሞ በህወሓት ስር ሆኖ ነው ይሄን ለውጥ ማምጣት የፈለገው። ምክንያቱም ድርጅቱ፣ ቤተሰቦቹ በስሩ ተሰልፈው የተሰዉበት ስለሆነ፣ ድርጅቱን ማሻሻል ይቀላል የሚል እምነት ነበረው።  

ነገር ግን ወጣቱ በዚህ ትግል መጓዝ የቻለው ጥቂት እርምጃ ብቻ ነው፤ አፈናው ጠንካራ ነበር፡፡ በ2007 እና 2008 አካባቢ ትግራይ ውስጥ ተቃውሞ ይደረግ ነበር፤ ነገር ግን በዚያው ልክ አፈናው ጠንካራ ነበር፡፡ አሁንም እየተደረገ ባለው ትግል፣ ወጣቱ ህወሓትን ሪፎርም አድርጎ የለውጡ አካል ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ 

ለውጡን የማይፈልጉ፣ ጥፋታቸውን በድርጅቱ ውስጥ ደብቀው ዋስትና አግኝተው ማለፍ የሚፈልጉ መሪዎች ደግሞ የወጣቱን ስጋትና ቁጣ ያባብሱታል፡፡ ለምሳሌ ጣና በለስ ለስራ የሄዱ ንፁሃን የትግራይ ልጆች፣ በትግሬነታቸው ብቻ መንግስትና ሃገር ባለበት፣ በጠራራ ፀሐይ አድኑን እያሉ ተቀጥቅጠው ሲገደሉ ስሜት ይነካል፡፡  

ጥርጣሬና ቁጣ ይፈጥራል፡፡ ይሄ ደግሞ ከለውጡ በተፃራሪ ቆመው ስጋት ለሚዘሩት ጥሩ ማስረጃ፣ ማረጋገጫ ይሆናቸዋል። አሁን እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡

ሶማሌ ውስጥ የተደረገው ነገር ትግራይ ውስጥ ሊመጣ እንደሚችል ወጣቱ ይነገረዋል፤ በዚህም ይሰጋል። የትግራይ ህዝብ በትግሉና በመስዋዕትነቱ ያገኘውን መብት ማንም ሰው መጥቶ እንዲድጠው አይፈልግም። ከውስጡ የወጡት አጥፊ ኃይሎችንም ቢሆን ራሱ ሊቀጣቸው ይፈልጋል እንጂ በሌላ ኃይል ተድጠው፣ አንተ የትም አትደርስም የሚል መልዕክት እንዲተላለፍለት አይፈልግም፡፡  

“ጥፋት ያጠፉ ካሉ በህገ መንግሥቱ መሰረት ይስተካከል እንጂ ኃይል ያለው ሁሉ በዘፈቀደ ከህግ ውጪ፣ እኛን ወደ ጎን ትቶ ለውጥ አመጣለሁ የሚል ከሆነ፣ የኛን ክብርና ማንነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” የሚል ነገር ይፈጠራል፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ ነው የሚል ስሜት በቀላሉ እየተፈጠረ ነው፡፡ 

በግልፅ ለመናገር እኔም ብሆን ቀደም ብሎ የመጣውን ለውጥ እያደነቅሁ፣ ነገር ግን ኋላ ላይ በሚታየው ነገር፣ ወዴት ነው እየሄድን ያለነው? ህግና ስርአትን እያከበርን ነው? ህዝብ እርስ በርሱ የሚጋጭበት ሁኔታ ሊመጣ ነው ወይ? የሚሉ ስጋቶች አድሮብኛል። ይሄን ሽግግር መልካም እድሎችን በሚያሰፋ መንገድ እየተራመድነው ነው ወይ? የሚል ስጋት እኔም አለኝ፡፡

አዲስ አድማስ – የህወሓትን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - በአሁኑ ወቅት በህወሓት በራሱ ውስጥ የኃይሎች ፍትጊያ አለ፡፡ በአንድ በኩል አነስተኛ ቢሆንም ሪፎርም የሚፈልግ አካል አለ፡፡ አሁን የመጣው ለውጥ መልካም አጋጣሚ ነው፣ ለኛ ይጠቅመናል የሚል አለ። ህዝቡን አደራጅተን መብቱን አስጠብቀን፣ ተግባራዊ የሆነ ጥሩ ስርአት መንግሥቱ እንዲኖረው አድርገን፣ የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት አለብን የሚል ወገን አለ። 

የፖለቲካ ችግሮች እኮ ትግራይ ላይ ይብሳሉ። ፓርቲና መንግስት ያልተለየበት ስርዓት ነው ያለው፡፡ የትግራይ ሥራ አስፈፃሚ፡- ፓርላማውን፣ ህግ አስፈፃሚውን፣ ኮሚሽኖችን በሙሉ ነው የሚቆጣጠረው፡፡ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው የሁሉም ነገር ጌታ፡፡ ይሄ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈጥረው መከራ፣ የፍትህ መጓደል በጣም ከባድ ነው። ከዚህ አንፃር ሪፎርሙ ለትግራይ ህዝብ ከማንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ ይሄን ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ቢሆኑም በህወሓት ውስጥ አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደነበረው እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ አሉ፡፡ እንደነበረው ቀጥሎ፣ እነሱ ኃላፊ ሆነው ሁሉም ነገር ተድበስብሶ እንዲቀር የሚፈልጉ አሉ። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በመሃል ሀገር የሚደረገው ፀረ-ትግራይ እንቅስቃሴ፣ በነበረው ይቀጥል የሚሉትን ኃይሎች የሚያጠናክርና ድጋፍ የሚያስገኝላቸው ነው የሚሆነው፤ ግን በግልፅ በህወሓት ውስጥ ሁለት ኃይሎች ፍትጊያ እያደረጉ ነው፡፡ 

ሰው ማወቅ ያለበት አሁን የትግሉ ሁኔታ ጫፍ ደርሷል። ኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ አደርጋለሁ ብሏል። ህወሓትም ጉባኤውን ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው። በዚህ ጉባኤ ዲሞክራሲ እንዲሰፋ፣ ፓርቲና መንግስት እንዲለያይ፣ መንግስት ደግሞ “ቼክ ኤንድ ባላንስ” በውስጡ እንዲኖረው፣ የህዝቡን መብት የሚያስጠብቁ ነፃ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣ የፍትህ ስርዓት ትግራይ ውስጥ እንዲነግስ የሚያደርግ ጉባኤ ነው የሚያስፈልገው፡፡  

ውሳኔውን ደግሞ ተግባራዊ የሚያደርጉ ወጣትና አዳዲስ አመራሮች ያስፈልጉናል የሚል ነው የህዝቡ ስሜትና ፍላጎት። ትግራይ ውስጥ የፓርላማ አባል የሚሆነው፣ ወይ የሚሊሻ አባል የነበረ ወይ ታጋይ የነበረ ነው፡፡ ሰው ለአስተዋፅኦው ውለታ የሚከፈልበት እድል ማግኛ ሆኖ ነው የቆየው። ሃሳብ የሚያመነጭ አልነበረም። 

ስራ አስፈፃሚውን እያወደሰ የሚኖር ነው፡፡ የክልሉ ፓርላማ አባላት የሚሆኑ ሰዎች በኔትወርክ ተሳስረው ነው የሚመጡት። ትግራይ የመልካም አስተዳደር ችግር የነገሰባት ነች። ሰው ለውጡን የሚፈልገው ዶ/ር ዐቢይን ከመደገፍ ብቻ ሳይሆን ለውጡ የግድ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ 

እናም ለውጥ ለማምጣት የሚጥሩትን ነው የሚደግፈው፡፡ በስብሰባ ለመካፈል ወደ ትግራይ ስመለስ፣ የተተበተበው ኔትወርክ ካልፈረሰ፣ የትግራይን ህዝብ እንደ ምርኮ ይዞ ሊጠቀም የሚፈልገው ኃይል ከጨዋታው ካልወጠ፣ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለሃገርም አደጋ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

ከዚህ እምነት ተነስቼ፣ በክልሉ የሚደረገውን ለውጥ እደግፋለሁ። በዚህ መሃል ግን መሃል አገር የሚደረገወ ፖለቲካ፣ ለውጡን የሚደግፍና ለለውጥ ኃይሉ ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ህገ መንግስት እንደ ዋስትና ያየዋል፡፡ የህገ መንግስቱ ዋነኛ እምብርት ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብትን ማክበር ነው፡፡ ህወሓት ዋነኛውን ስልጣን ይዞ በነበረ ወቅት እነዚህን መብቶች ረግጦ ነው ሲገዛ የቆየው፡፡ 

የትግራይ ህዝብም መብቱ ተረግጦ ነው የኖረው፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበርና እንዲከበር ነው እየጠየቀ ያለው። አንቀፅ 39ን እንደ ዋስትና ነው የሚመለከተው፡፡ ይህ ሲባል በኢትዮጵያዊነት ይደራደራል ማለት አይደለም። ራሱን ከኢትዮጵያዊነት ነው የሚያስተሳስረው።  

ኢትዮጵያዊነት ከደሙና ከአጥንቱ ጋር የተዋሃደ፣ ታሪኩም ነው፡፡ የመነጠል ፍላጎት ትግራይ ውስጥ የለም፡፡ ነገር ግን አንቀፁ ዋስትና ይሰጣል፣ መብትን ለማስከበር ይረዳል ብሎ ያምናል፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ ህገ መንግስቱ ይከበር ሲል ከዚህ አንፃር ነው፡፡

አዲስ አድማስ – እርስዎ በትግራይ በሚደረጉ ተከታታይ ስብሰባዎች ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ ለውጡን እውን ለማድረግ በማገዝ ረገድ የእርስዎ ዓይነት (በመንግስትም በፓርቲም ውስጥ የሌሉበት) ሰዎች አቅምና ተጽዕኖ ምን ያህል ነው ብለው ያምናሉ?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - ድርጅቱን ለ40 ዓመት ሲመሩት የነበሩ ሰዎች አሁን ህዝቡ እንደማይፈልጋቸው ያውቃሉ፡፡ ከእንግዲህ የማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም ስራ አስፈፃሚ አባል መሆን እንደማይችሉ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ አሁን የሚደረጉትን ጥረት እነሱን የመሰሉ የእነሱን ሃሳብ በቀላሉ የሚገዙ ወጣቶችን መልምለው አስጠግተዋል፤ የመብራቱን ማንቀሳቀሻ ግን በእጃቸው ይዘው እስትንፋሱን እነሱ እየሰሙ መቆየት ነው የሚፈልጉት፡፡ 

እኛ እያደረግን ያለው ጥረት ይሄን ለማምከን ነው፡፡ በዚህ ጥረት ግን የክልሉ ሚዲያ ሃሳባችንን እንድናወጣ እድል አልሰጠንም። በቅርቡ ዶ/ር ደብረፂዮን፤ ይከፈትላችኋል ብለውናል፡፡ እሱ ከተሳካ ይሄን የሪፎርም ሃሳብ ለማስረዳት እንጥራለን። የሚዲያ እድል አለማግኘታችን፣ ሃሳባችንን ለማስተጋባት እንዳንችል አድርጎናል፡፡ 

ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቱ ጉባኤ የሚያደርግበት ጊዜ አጭር ነው፡፡ ለ3 ወር ቢራዘም ጥሩ ነበር፡፡ በእነዚህ ወራት ውስጥ ጥሩ መንቀሳቀስ እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን ጉባኤው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው የሚካሄደው፡፡ ጉባኤተኛውን ተመራርጠው ጨርሰዋል፤ ስለዚህ ጥረታችን የተገደበ ይሆናል፡፡ 

ሶስተኛው ችግር፤ እኛ በድርጅቱ መዋቅር ውስጥ የለንበትም፡፡ የመዋቅር አካሉም አይደለንም። በክልሉ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ህወሓት 7 መቶ ሺህ ገደማ አባላት አሉት፡፡ አብዛኛው መዋቅር እርስ በእርስ የተሳሰረ ነው፡፡ በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መንገድ በኔትወርክ የተሳሰረ ነው፡፡  

እንዲህ በኔትወርክ የተሳሰረና ከላይ የወረደለትን መመሪያ ብቻ እየተከተለ ከሚሄድ አካል ጋር ነው እየተጋፈጥን ያለነው፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ ለውጡ እውን እንዲሆን ይሄ ኔትወርክ መፈራረስ አለበት፡፡ በዚህ መሃል ግን ተስፋ የሚሰጥ ነገር ደግሞ አለ። በተለይ ወጣቱና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን “በቃን! ለውጥ እንሻለን” እያሉ ነው፡፡ 

ይሄ ፍላጎት መኖሩ ለውጡን አይቀሬ ያደርገዋል። አንድ ማረጋገጥ የምፈልገው፣ በቀጣዩ የህወኃት ጉባኤ፣ ለውጡን የማይደግፈው ቡድን ስልጣን ላይ ከወጣ ሰላም አይኖርም፡፡ ህወሓትም እንደ ድርጅት ለመቀጠል ፈተና ውስጥ ይገባል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ህዝቡ እና ህወሓት ይፋታሉ፡፡

አዲስ አድማስ – እርስዎ በህወሓት ቀጣይ ጉባኤ፣ ምን ዓይነት ሪፎርም ነው የሚጠብቁት?
ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ  - ትልቁ ነገር መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ መወሰን ነው። ለምሳሌ መንግሥትና ፓርቲ መነጠል አለበት። ይሄ መነጠል እውን እንደሚደረግ የሚተላለፍ ውሳኔ መስማት እፈልጋለሁ፡፡ በተግባርም መፈፀም አለበት። ሁለተኛ የቁጥጥር ስርአት እንዲፈጠር እፈልጋለሁ፣ ገለልተኛ የፍትህ ስርአት እንዲኖር እሻለሁ፡፡ 

እስካሁን የፍትህ ቢሮ ኃላፊው ህወሓት ይሆንና እያንዳንዱ ውሳኔ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መሰረት ወደ ታች ይወርድ ነበር፡፡ ፓርላማው ጥቅም አልባ ነው። የፍትህ አካሉ በጠቅላላ ለፓርላማው ተጠሪ መሆን ነበረበት፤ ነገር ግን ውለታ መክፈያ ፓርላማ ተይዞ የፍትህ ስርአቱ ለፓርላማ ተጠሪ ነው ቢባል ለውጥ አያመጣም፡፡  

ስለዚህ ፓርላማው ራሱ ውለታ እየተቆጠረ መጥቀሚያ ሳይሆን ሃሳብ ያለው ሰው በውድድር የሚገባበት እንዲሆን ያስፈልጋል። ፓርላማው፤ ጠንካራ ስራ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠር እናደርጋለን ብለው በይፋ መወሰን አለባቸው፡፡ ነጻና ገለልተኛ የፀረ ሙስና፣ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ኮሚሽኖች እናቋቁማለን ብለው መወሰን አለባቸው፡፡

በአጠቃላይ የትግራይ የፖለቲካ ሪፎርም አጀንዳ ነው፣ የዚህ ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳ መሆን ያለበት። የኢኮኖሚ ጉዳይ በኋላ የሚደርስ ነው የሚሆነው፡፡ የዚህ ጉባኤ ዋና አጀንዳ፤ የፖለቲካ ሪፎርም አጀንዳ ነው መሆን ያለበት፡፡ የሚመረጠው የማዕከላዊ ኮሚቴም፣ ውሳኔ ከተላለፈባቸው አጀንዳዎች ጋር የተስማማ መሆን አለበት። ይህ ከተደረገ ትግራይ ውስጥ ለውጥ ይጀመራል፡፡

ሌላው ህገ መንግስት በስርአት አልበኝነትና በጫጫታ ሳይሆን በስርአቱ እንዲታይ፤ መሻሻል ካለበትም መሰረቱን ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲን እንዲሁም የብሄር ፌደራሊዝምን ታሳቢ አድርጎ፣ በህጉ መሰረት እንዲሻሻል የሚያደርግ ውሳኔ እንዲወስኑ እጠብቃለሁ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ከወሰኑ ትግራይ ውስጥ ትልቅ ሪፎርም ይመጣል። በሃገር አቀፍ ደረጃም ለውጡ ፍሬያማ እንዲሆን ያደርጋል።

ነገር ግን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተዘጋጀው ጉባኤ፣ ይሄን ውሳኔ ይወስናል የሚል ተስፋ ብዙም የለኝም። ምክንያቱም ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች፣ ቀደም ብለው መስራት ያለባቸውን ስራ ውስጥ ሰርተዋል፡፡ 

ስብሰባው እንዲራዘምና ሰው እንዲወያይበት ይደረግ ዘንድ የመንግስት አመራሮችን ለምኛለሁ፤ ግን እስካሁን የተሰጠን መልስ ብዙም አይራዘምም የሚል ነው። በነገራችን ላይ እኔ ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጎት የለኝም፡፡ ፖለቲካው እንዲስተካከል ግን እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ ሃሳቤን መስጠት እቀጥላለሁ፡፡

ምንጭ፡ አለማየሁ አንበሴ Addis Admass

No comments