Latest

የባለዳንቴሏ የክር ጫማዎች - ቢቢሲ

የባለዳንቴሏ የክር ጫማዎች

ዘወትር ማልዳ እየተነሳች የሊስትሮ ዕቃዋን ሸክፋ ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ ትሄድና "ጫማ ልጥረግሎት? ይወልወል? ወይስ ቀለም ላድርግሎት? " እያለች አልፎ ሂያጁን ትጣራለች።

በለስ ቀንቷት ሰው ካገኘች እሰየው በትጋትና በቅልጥፍና ጫማ ትሰፋለች፣ ትጠርጋለች፣ በቀለም ታስውባለች።

የሊስትሮ ገበያው ተቀዛቅዞ እጆቿ ስራ ሲፈቱ ደግሞ ኪሮሽና ክር እያስማማች ዳንቴል ትሰራለች። ይህ ራሷን በስራ ለመለወጥ ዘወትር የምታትረው መሰረት ፈጠነ የአራት ዓመታት እውነታ ነው።

ምንጊዜም ቢሆን ነገ የተሻለ ቀን እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች፤ ትናንት ያስተማራትም ይህንኑ ነው።

"ድንጋይ ከምረን ከላይ ሸራ አድርገን ነበር የምንኖረው"
መሰረት በ 2004 ዓ. ም. ነበር ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ አምርታ በቤት ሰራተኛነት የተቀጠረቸው። ቀኑን በስራ እየደከመች ማታ ደግሞ የገጠማትን ፈተና እየታገለች ለሶስት ወራት ቆየች።

"ሁለት ጎረምሶች ያስቸግሩኝ ነበር፤ እኔ የምተኛበት የማዕድ ቤት በር አልነበረውም፤ እነሱ ደግሞ ሳሎን እያደሩ ያስቸግሩኝ ነበር። አንድ ቀን ስራ ስላልነበረ ቤት ውስጥ በር ቆልፈውብኝ ሊታገሉኝ ሞከሩ፤ ጩኸቴ በቤቱ ሲያስተጋባ ተድናግጠው ተዉኝ።"

መሰረት በጊዜው በአካባቢው ሰው በመኖሩ ከጥቃቱ ብትተርፍም አንድ ትልቅ ውሳኔ ላይ ደረሰች።

"ምርር ስላለኝ በቃ ካሁን በኋላ የመኪና አደጋም ቢደርስብኝ፤ ምንም ቢሆን ሰው ቤት አልገባም ብዬ ወጣሁ።"

ለሃገሩ ባዳ የነበረቸው መሰረት ማደሪያ ስላልነበራት ከዚያን ቀን ጀምሮ መዋያዋ ማደሪያዋም ጎዳና ሆነ።

የእለት ጉርሷን በተገኘው ትርፍራፊ እየሞላች ስታጣም አንጀቷን እያጠፈች ማደር ጀመረች። ቆየት ብሎ ደግሞ እዛው በጎዳና ከተዋወቀችው ወጣት ጋር በመጣመር እንደ አቅሟ ጎጆ ቀለሰች።

"ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲው አምስተኛ በር አካባቢ ድንጋይ ከምረን ከላይ ሸራ አድርገን ነበር የምንኖረው፤ አንዳንድ ቀን ፖሊሶች ያባርሩናል፤ ዝናብ ሲሆን ድንገት ይመጡብናል፤ በተለይም ስብሰባ ካለ በጣም ያስቸግር ነበር"

መሰረት ከኑሮ ጋር የያዙት ግብ ግብ እስከመቼ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ ራሷን ትጠይቅ እንደነበረ ትናገራለች።

ባለቤቷ በዱቤ የወሰደው የሊስትሮ ሳጥን የተስፋ ጭላንጭል ይዞላት ቢመጣ ብላ አንድ ቀን እሱ በሌለበት የራሷን እርምጃ ወሰደቸ።

"ድንገት ተነስቼ 'ጫም ይጠረግ? ጫም ይጠረግ?'ብዬ መጮህ ጀመርኩኝ፤ ሊስትሮ እሰራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ግን ራሴን አሳመንኩኝ፤ ያኔ የጫማ ማሰሪያ መፍታትም ሆነ ማሰር አልችልም ነበር፤ የመጀመሪያው ሰው ሲቀመጥልኝ ካልሲውን ቀለም አስነክቼበት ተናዶብኝ ነበር።"

መሰረት የሊስትሮ ስራውን እንዲህ ጀምራው ለሁለት ወራት ከሰራች በኋላ ኑሮ ሲፈትናት በመሃል ወደ ባለቤቷ ሃገር ወላይታ ብትሄድም አሁንም ተመልሳ የሊስትሮ ስራዋን በፒያሳ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ ቀጠለች።

መሠረት ልጇን ታቅፋ
መሠረት ልጇን ታቅፋ
"የስድስት ቀን ጨቅላ ይዤ ወደ ስራ ተመልሻለሁ"
ፈተና ከእሷ ብዙም አልራቀምና መሰረት የሶስት ወር ጽንስ መያዟን አወቀች። ስምንት ወር እስኪሆናት ድረስ አጎንብሳ ጫማ መጥረጓን አላቆመችም ነበር።

"ወልጄም ከስድስተኛ ቀን ጀምሮ እዛው ተመልሼ ሰርቻለሁ። ያው በስድስት ቀን ስወጣ እንግዲህ ጨቅላዋ አትታዘልም ገና ደም ናት፤ ስለዚህ ትንሽዬ ነገር አንጥፌ አጠገቤ አስተኛትና ከዛ በጥላ እከልላታለሁ፤ እንዲያውም በአጋጣሚ ድምጽ ስታሰማ ሰዎች ይደነግጡ ነበር።"

ለሶስት ወራት ገደማ በዚህ ሁኔታ ከሰራች በኋላ ክረምት ሲገባ ህጻኗን ብርድ ይመታብሻል የሚል ተግሳጽ ቢያይልባት ተመልሳ ልጇን ይዛ ወደ ገጠር ገባች።

ጥቂት ቆይታ ስትመለስም ልጇን እዚያው አጠገቧ እያደረገች በየአካባቢው እየዞረች ስትሰራ ቆይታ ሲቪል ሰርቪስ አካባቢ እንደወትሮው ሁሉ ገበያው በተቀዛቀዘበት ጊዜ ዳንቴሉን ስትሰራ የተመለከተቻት አንዲት ሴት ያቀረበችላት ጥያቄ ለዛሬው ፈጠራዋ መንገድ ቀየሰላት።

"ዳንቴል ከቻልሽ እኔ አሰራሻለሁ ብላኝ ለወር አካባቢ እኔ ቤት ውስጥ እየሰራሁኝ የዳንቴል ስራውን እያጋመስኩላት እርሷ ደግሞ እያጠናቀቀችው ጫማ ሲሆን አየሁ። ግን ለወር አካባቢ ሰርቼ በህመም ምክንያት አቋረጥኩት።"

መሠረት የምትሠራቸውን ምርቶች ስታሳይ
መሠረት የምትሠራቸውን ምርቶች ስታሳይ
ያለአንዳች ማሽን የምትሰራው የዳንቴል ጫማ
መሰረት በጊዜ ሂደት እሷ ዳንቴል ከመሰራት የዘለለ ሚና ባልነበራት ስራ የጎደለውን እውቀት ለመሙላት መፍጨርጨር ጀመረች።

እስከ ሶስተኛ ክፍል ብቻ የዘለቀችበት ትምህርት ለዚህ ምንም እንደማይጠቅማት ብታውቅም ተስፋ አልቆረጠችም።

"መጀመሪያ በሰው እግር እየለካሁኝ ይሄ ተጠቅጥቆ ጫማ መሆን ይችላል እንዴ? እያልኩኝ በወንድ ጫማ መሞከር ጀመርኩኝ፤ የሚሆን አልመሰለኝም ነበር፤ ግን በመጨረሻ ተሳካልኝ። ከዛ የሴት ጫማ እያልኩኝ፣ ነጠላ ጫማ እያልኩኝ የወንድ ሸበጥ እያልኩኝ ቀጠልኩ።"

መሰረት አሁን የሙከራ ሂደትን አልፋ ክፍትና ሽፍን የወንድና የሴት ጫማዎችን፣ የአንገት ልብስ፣ ቀበቶና አልጋ ልብስ በዳንቴል ያለምንም የፋብሪካም ሆነ የማሽን እገዛ በእጆቿ ትሰራለች።

"የምሰራበት ክር በጣም ጠንካራ ነው፤ ከጅማትም ይጠነክራል፤ ጅማት እንደውም ብዙ ጊዜ እኔ ሊስትሮ እያለሁ ስታገለው ወይ ደግሞ ጫማው በጣም ደረቅ ከሆነ ስስበው የሚበጠስበት አጋጣሚ ነበር። ክር ግን ከዚያም ይጠነክራል፤ ሶሉ ትንሽ ስለሚያስቸግር ነው እንጂ አንድ ሰው እስከ አምስት ዓመት ይሄን ጫማ እንደሚያደርግ እተማመናለሁ።"

መሰረት የአንድ ንድፉ ያለቀለትን ጥንድ ጫማ የዳንቴል ሥራ በአንድ ቀን ውስጥ ታጠናቅቃለች።

የመሠረት ጫማዎች
የመሠረት ጫማዎች
ቀጣዩ ሥራዋ ደግሞ ዳንቴሉን በእግር ቅርጽ በተሰራ የጫማ መወጠሪያ አድርጎ በመርካቶ ለመቀየሪያነት የሚሸጡ ማጫሚያዎችን (ሶሎችን) በመጠቀም በማስቲሽ ማያያዝ ነው።

ጉርድ ሾላ አካባቢ ከአምስት ዓመት ልጇ ጋር ተከራይታ በምትኖርበት ጠባብ ባለ አንድ ክፍል ቤት ውስጥ አዳዲስ ዲዛይኖች እያወጣች ወደ ተግባር ትቀይራለች።

"አምስት የነጠላ ጫማ ዲዛይን አለኝ። ቀጭን ሶል ባላቸው (ፍላት) ደግሞ ለሴትም ለወንድም በሸራ መልክ ሁለት አይነት ጫማ እሰራለሁ፤ ቡትሶች፤ ቦርሳዎችና ቀበቶዎችም አሉኝ።"

መሰረት ጫማዎቹን መስራት ከጀመረች ሁለት ዓመታት ቢቆጠሩም በጣም ትልቅ ስራ ሰራሁ የምትለው ባለፈው ሰኔ በትዕዛዝ የሰራቻቸውን 14 ጫማዎች ነው።

"በቂ ትዕዛዝ አላገኝም፤ በሰፊው ለገበያ ለማቅረብም የገንዘብ አቅም የለኝም፤ በወር አንድ ወይም ሁለት ጫማ ሊመጣ ይችላል። ከዚህ በፊት ይሄ እንጀራዬ ነው ለብዙዎችም ምሳሌ እሆናለሁ በሚል ተነሳሽነት ትዕዛዝ ኖረም አልኖረም 24 ሰዓት እሰራ ነበረ፤ አሁን ግን እጅ ላለመስጠት እየታገልኩ ነው።"

መሰረት በዚህ ስሜት ውስጥም አንደበቷ አሁንም ነገን ተስፋ የሚያደርጉ ቃላትን ከመወርወር አይመለስም። "ወደፊት ነገሮች ተሳክተውልኝ ከዚህም የተሻለ ፈጠራ ፈጥሬ ሃገሬን የማስጠራበት ጊዜ እንደሚመጣ እጠብቃለሁ።"

No comments