Latest

መንግሥት ኢትዮጵያ ጦሯን ከኤርትራ ድንበር አለማንሳቷን አስታወቀ

መንግሥት ኢትዮጵያ ጦሯን ከኤርትራ ድንበር አለማንሳቷን አስታወቀ

ኢትዮጵያ ጦሯን ከኤርትራ ድንበር እያነሳች ነው ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው ሲል መንግሥት አስተባበለ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር በተለይም በሽራሮ ግንባር የሚገኘው ጦሯን ኢትዮጵያ እያነሳች እንደሆነ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው አውቶብሶችና ኦራል ወታደራዊ የጭነት ተሽከርካሪዎች ጦሩን ሲያጓጉዙ መታየታቸውን፣ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ ነበር፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ መረጃው ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

‹‹እውነት ነው ሽራሮ ግንባር ላይ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የተለመደ አሠራር ነው ሲሉ፤›› ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ላለፉት 20 ዓመታት ከነበሩበት የጥላቻ መንፈስ ተላቀው ሰላም ካወረዱ ጥቂት ወራት እየተቆጠሩ ሲሆን፣ በመካከላቸው ያለውን የጠላትነት ስሜት አጥፍተው በሰላም ለመኖር መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባለፈ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ በተለይም ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች መጠቀም የሚያስችላት ስምምነት መደረጉ አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኤርትራ ድንገተኛ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

‹‹ሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ ያሉ ወታደሮቻቸውን ለማንሳት እስካሁን የተፈራረሙት ስምምነት የለም ሲሉ፤›› አቶ ሞቱማ አክለዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች እንደገና ወዳጅነት የጀመሩት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ በሙሉ መቀበሉን ካስታወቀ በኋላ ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ ይኼንን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረ ሥራ ባለመኖሩ፣ ከድንበር ላይ ጦር የማንሳት እንቅስቃሴ ሊኖር አይችልም ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

No comments