Latest

ጀርመን የሚኖረው ዳንሰኛ አንዷለም "የአዲስ አበባ ጠረን ናፍቆኛል" ይላል። ከኢትዮጵያ ውጪ የምትኖሩ ስሜቱን ትጋራላችሁ? ቢቢሲ

ጀርመን የሚኖረው ዳንሰኛ አንዷለም

ስሜ አንዱዓለም ከበደ ይባላል ብዙ ሰዎች በቅጽል ስሜ 'ሞንዶ' በሚለው ያውቁኛል። አሁን የምኖርባትን ከተማ ሉድቪግስሃፍን በምትባለው የጀርመን ከተማ ነው። አዲስ ለሆነ ሰው የምኖርባታ ከተማ ስም ለማስታውስም ሆነ ለመጥራት ተንሸ ከበድ ትላለች።

በግል ምክንያት ወደ ጀርመን ከመጣሁ በኋላ ጥገኝነት ጠይቄ ነው እዚሁ ነዋሪ ልሆን ችያለው። ወደዚህ ከመጣሁ ዓመት ሊሞላኝ ነው።

ጀርመን ሃገር አንድ ሰው ጥገኝነት በሚጠይቅበት ወቅት ሁኔታዎች ከተመቻቹ በኋላ ጥገኝነት ጠያቂው በመረጠው ከተማ እንዲኖር ይደረጋል። እኔም በዚህ ከተማ እንድኖር ተደርጊያለሁ።

ለእኔ ጀርመንን ከኢትዮጵያ ማነፃፀር በጣም ይከብደኛል ምክንያቱም ሁለቱን ሃገራት የሚያመሳስሏቸውን ነገሮች ማግኘት ያቅተኛል። ጀርመን በጣም ፀጥ ያለች ሃገር ናት። በተለይ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር ሽብርቅርቅ ያለ ሃገር አይደለም፣ ዝም ያለ ነው።

የአየር ሁኔታው ግን በጣም የተለየ ነው። ብርዱም ሆነ ሙቀቱ ሁልጊዜ ጽንፍ ነው። ወይ በጣም ይበርዳል ወይ በጣም ይሞቃል። ስለዚህ ለእኔ አዲስ አበባ ትሻለኛለች ከጽዳቷ በቀር።

በተረፈ ግን የሕዝብ ማመላለሻ አማሮጮቹ በተለይ ለእኔ፣ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ እዚህ በጣም አመቺ ነው። ከዚያ የበለጠ ግን ብዙ የሚመሳሰሉም ሆነ የሚላያዩ ነገሮችን አላይም።

ከኢትዮጵያ ከወጣሁ ወዲህ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ ቢሾፍቱ የሚባል አውቶቡስ አለ ተብያለሁ። እንደውም በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ አያቸዋለሁ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እሱን የሚመስል ባስ እዚህ ሉድቪግስሃፍን አለ።

የዚህ ሃገር አውቶቡሶች ደግሞ ለየት ያሉ ናቸው። ሹፌሮቹ አካል ጉደተኛ ሰዎች፣ አዛውንቶችና ሕፃናት ወደ አውቶብሱ ሳይቸገሩ በቀላሉ እንዲገቡ የአውቶብሱን በር ዝቅ ያደርጉላቸዋል።

አዲስ አበባ በጣም ትናፍቀኛለች። አንድ ሃገር ጠረን አለው። የሃገሬ ጠረን በጣም ይናፍቀኛል።

ሰኳር ስላለብኝ ብዙ ጊዜ የምመገባቸውን ምግቦች በጣም እጠነቀቃለሁ፣ 'ጠየም' ያሉ ነገሮችን ነው እየመረጥኩ የምመገበው።

ብዙውን ጊዜ ፓስታ፣ሩዝ እና ኩስኩስ መመገብ እመርጣለሁ።

ወደ ከተማ ለተለያዩ ጉዳዮች በወጣሁ ቁጥር 'ኬባብ' ወይም 'ዶነር' የሚባለውን ምግብ በምላት ያስደስተኛል። ዶነር የበሰለ ስጋ ቂጣ በሚመስል ወፈር ያለ ዳቦ ውስጥ ሆኖ የሚቀርብ ምግብ ነው። እንደውም የፊታችን ቅዳሜ ወጣ ስለምል እናንተንም እጋብዛችኋለሁ።

እዚህ ከመጣሁ በጣም ያስደነቀኝ ነገር ሰዎች የዘመናዊ ሙዚቃ ተወዛዋዥ መኖኔን ሲያውቁ ሰዎች ያላቸው ሁናቴ ነው። እኛ ብዙ ጊዜ ለነጮች የምንሰጣቸው ግምት ትልቅ ነው ባይ ነኝ።

ይህን የምለው ደግሞ ከእራሴ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ነው ''እንዴት ልትደንስ ትችላለህ'' ወይም '' አካል ጉዳተኛ ሆነህ እንዴት ልትደንስ ቻልክ?'' ይሉኛል እንደውም አንዳንዴ የመጠራጠር ምልክት በፊታቸው ላይ አነባለሁኝ።

ያንኑ ያህል ደግሞ ግራ እስኪገባኝ ''ሥራ ለምንድነው የማትሠራው'' የሚመሳስሉ ጥያቄዎችም ይቀርቡልኛል ከእነአካቴው አካል ጉዳተኛ መሆኔን እየረሱ ይመስል። ይህ ደግሞ ጠንካራ ያደርጋል።

ከቤቴ ሆኜ በመስኮቴ በኩል የሚታዩ በጣም የሚያስደስቱኝ ዛፎች አሉ። ዛፎቹ የሚያስገርም ግርማ ሞገስ አላችው። እነሱን ማየት በጣም ያስደስተኛል።

ዛፎቹን በክረምት ወቅት በደንእበ አድርገው ይከረክሟቸዋል። በበጋ ደግሞ ከታች በምስሉ ላይ እንዳለው ውብ ያደርጓቸዋል። ከእነዚህ ዛፎች ውጪ ሌላ ብዙም የሚታይ ነገር የለኝም።

እዚህ ከመጣሁ አንስቶ የተለያዩ ነገሮችን ታዝብያለሁ። እንደውም አንዳንዴ አቅም ቢኖረኝ ማድረግ የምሻው ነገር አለ። ይህም፤ በመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ያሉ ስደኞችን የማይወዱ እና የስደተኛ ጉዳይ ደንታቸው የልሆኑ ግለሰቦችን ካሉበት ማንሳት ብችል ደስ ይለኛል።  


በስደተኛው ላይ መልካም ያልሆነ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ፣ ሰቀቀን የሚፈጥሩ ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በግል ተደራጅተው ስደተኞችን መርዳት የሕይወት ዓላማቸው ያደረጉም አሉ።

እስካሁን የሚገርመኝ ነገር አዚህ እንደመጣሁኝ ምን የት እንዳለሁ እና የት መሄድ እንዳለብኝ የማውቀው ነገር አልነበረም። አምጥተው ብቻ ነው ያስቀመጡኝ። ቋንቋውን አልችል፣ ቦታ አላውቅ ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኝ ነበር። የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ቀጠሮ ሲሰጠኝ እንኳ አድራሻው በቁጥር ነበር የተነገረኝ።

በጣም ከባድና ፈታኝ የምለው ጊዜ ያጊዜ ነበር። ሆኖም ግን አንድ ሰው ምንም አማራጭ ሳይኖረው ሲቀር መሄድና መሞከር ይጀመራል ማለት ነው።

አሁን ኢትዮጵያ በቅስበት መመለስ ብችል እራሴን በቅድስተ ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን ባገኘው እመኛለሁ።

No comments