የዶክተር ዐቢይ ሕዝባዊ መሠረትን የካደው መጽሐፍ! (ደረጀ በላይነህ)
ሰሞኑን እጄ የገባው የሚካኤል ሽፈራው መጽሐፍ ርዕሱ ትኩረት ሳቢ፣ ምሥሉም አጠራጣሪ ነበር፡፡ “የማስጠንቀቂያ ደወል” ከሚለው ርዕስ ሥር፣ ሌሎች ኃይለ ቃል መሰል ሀሳቦች ተንጠልጥለዋል፡፡
“በመደመር ፍልስፍና ወዴት እያመራን ነው?” “ዐቢይና ጎርባቼቭ”፣ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ህውሓት” በሚል ተደርድረዋል። ይህንን የሚያይ አንባቢ ወዲያው የሚጠብቀው በጥራዙ ውስጥ፣ የዶክተር ዐቢይ የለውጥ ሂደትና የሕወሓት ምላሽ፣ ከዚህ ጋር በንፅፅር ደግሞ የሚካኤል ጎርባቾቭ “ፔራይስትሮካ” ምንነትና ውጤቱን ማየትና መተንተን ነው፡፡
በተለይም ደራሲውንና ሥራዎቹን ለሚያውቅ ሰው አንዳች የተለየ አተያይ፣ አሊያም ጠብሰቅ ባለ አመክንዮ የተሞላ ሃሳብ ይጠብቃል፡፡ ምክንያቱም ሚካኤል ሺፈራው የኪነ ሕንፃ ባለሙያ ይሁን እንጂ በሀገራችን ስነጽሑፍ ጥሩ አበርክቶት ያለውና አራት ያህል መጻሕፍትን ለንባብ ያበቃ ነው፡፡ ያም ብቻ አይደለም፣ ንግግሮቹ በማስረጃ የተሞሉ፣ ሀሳቡም የበሰለ ነው፡፡
ጉዳዬ የመጽሐፉ ጉዳይ ስለሆነ ወደ ጥራዙ መግባት ግድ ቢለኝም፣ ሚካኤል እንደ ሰውም ማንንም የማያስቀይም፣ ቀናነት የሚታይበት፣ ተቃውመው ለሚከራከሩትም ከቁጣ ለዘብ ያለ ውይይት ማድረግ የሚችል፣ በጥቅሉ ስልጡን አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እማኝ የሚሆኑኝ ገጠመኞች አሉኝ።
ሀሳቡን ተቃውሜ አይቼዋለሁ፡፡ “ለምን ተቃወምክ” ብሎ የመቀየር ምልክት እንኳ አላሳየኝም፡፡ ይሁንና የማንግባባቸው የምርጫ መንገዶች አሉን፡፡
ወደ መጽሐፉ ስመለስ፤ የመጽሐፉ የመግቢያና ጥቂት የመዝጊያ ገፆች ካልሆኑ በስተቀር ሌላው በቀጥታ ከርዕሱ ጋር በጥብቅ የሚገናኝ አይደለም። በእኔ አተያይና ምርመራ፤ የመጽሐፉ የተወሰኑ ምዕራፎች የተፃፉት ከዛሬ አራትና አምስት ዓመታት በፊት ነው።
ከዚያ ባሻገር እጅግ ብዙው ክፍል ስለ ቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረትና ስለመበታተንዋ የሚያትት ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ የኛን ሀገር ታሪክና የትግል ስልት ከሶቪየት ጋር ለማጣቀስ ሞክሯል፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ባብዛኛው የሶቪየት ሕብረት ታሪክ ነው ማለት ይቻላል።
ማንም መጻሕፍትን በጥንቃቄ የማንበብ ልምድ ያለው ሰው፤ የመጽሐፉ የውስጥ ብልቶች የተከፋፈሉ፤ ልዩነትና የአንድ ያለመሆን ችግራቸው ማጤን ይችላል፡፡ ምናልባትም የተፃፉበት ጊዜና መንፈስ ሹክ የሚለን ነገር፣ የመጽሐፉ አዲስ ሃሳቦች (ወቅታዊ ሃሳቦች) ከሃምሳ ገፅ ያልዘለሉ መሆናቸውን ነው፡፡
ይህንን ለምን እንዲህ እንዳደረገና እንደተጠቀመበት ከመገመት ያለፈ ድምዳሜ መስጠት ለስህተት ሊዳርግ ስለሚችል መናገር ያስፈልጋል ብዬ አላምንም፤ ይሁንና ዳር ዳር ላይ የለጠፋቸው መግቢያና መውጫዎች አልፎ አልፎ መሀል ላይ ያሉትንም ሃሳቦች ስላጠቀሱ የዳሰሳዬ ትኩረት ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡
ምክንያቱም ደራሲው ቁልጭ ብሎ በሚታይ መልኩ ኢሕአዴግን (ሕወሓትን) ቅዱስ የማድረግ ያፈጠጠ ፍቅር ስለሚታይበት፣ ይህንን ቅድስና ለሕዝብ ለማሳየት መሞከሩን፣ ስንፍና እንደሚመስል ማሳሰብም እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ አሁን ያልተለወጠው ኢህአዴግ፤ ብዙ ዘግናኝና የግፍ ሥራዎች በመገናኛ ብዙኃን አደባባይ ላይ ተሰጥተው ሕዝብ ካያቸው በኋላ ለገፀ ንባብ ማብቃቱ፣ አቶ ሚካኤልን ባይተዋርና የሕዝቡን ሕመም የዘነጋ ያስመስለዋል።
ያም ብቻ አይደለም፣ አንዳንድ ቦታ ላይ የሰጣቸው አስተያየቶችና ያስቀመጣቸው ሃሳቦች ዐይኑን ጨፍኖ፣ ለአንድ ወገን መዝሙር እየዘመረና እያሸበሸበ እንደሆነ ያሳብቅበታል፡፡ “የዶክተር ዐቢይ ህዝባዊ መሰረት” ከሚለው ንዑስ ርዕስ ብንነሳ፣ ሀሳቡ ከራሱ ሀሳብ ጋር ሳይቀር የሚጣረስ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
“ይህ ዶክተር ዐቢይን በሰፊው የሚደግፍ ወገን እንደሚከተለው ሊቀመጥ የሚችል ይመስለኛል፡፡
- ራሱን ከዚህ ወይም ከዚያ ብሔር ለመመደብ የሚቸገር፣ ባብዛኛው በከተሞችና በዋና ከተማችን የሚኖረው፣ በብሔር አቀፍ ፖለቲካው ተገልሎ የኖረውና ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ብዙ ግፍና በደል በብሔራዊ ነፃነት ስም ሲፈጸም ሲያስተውልና ሲሸከም የኖረው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
- በተለይም በአማራ ክልል የሚኖሩ፣ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአማራነታችን ብቻ ላለፈው ዘመን በደል ሁሉ ተጠያቂ ሆነን፣ በብሄር ብሄረሰቦች እንድንጠላ እንድንወገዝ ተደርገን ስንኮነን፤ ስንበደልና ስንጠቃ ኖረናል የሚለው፣ ብሔር አቀፍ ፌደራሊዝም ወደ ስልጣን ከመጣበት ከ1983 ወዲህ የተፈጠረ አክራሪ አማራ ብሔርተኝነት አራማጆች ወገን ነው፡፡ … (ዝርዝሩን ትቼዋለሁ)
- ሌላው የዶክተር ዐቢይ ደጋፊ ኃይል ዳያስፖራው ሲሆን ይህ ክፍል ባመዛኙ የብሄር ብሄረሰቦች ፖለቲካ አገራችንን ከፋፍሎ፣ ያንድ ብሔር የበላይነትን አንግሶ ኖሯል፡፡ የሚል አመለካከት ያለው ነው፡፡”
ወደ ዝርዝሩ ሳንገባ በደራሲው ዐይን፣ የዶክተር ዐቢይ ደጋፊዎች እነዚህ ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሀሳብ ምን ያህል ከእውነት እንደተራራቀ ለማወቅ ብዙ ርቀት መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
ለመሆኑ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከ3 ሚሊዮን የበለጠ ህዝብ የተገኘበት አልነበረምን? …
ታዲያ ይህ ሁሉ ከዚያ ወይም ከዚህ ብሔር መመደብ የተቸገረ ሕዝብ ነው ወይስ ከአማራ ክልል ተጭኖ የመጣ? አሊያስ ከአሜሪካ የበረረ ዳያስፖራ? አቶ ሚካኤል፤ በሀዋሳ ከተማ ከዶክተር ዐቢይ አቀባበል ለማድረግ ገና በሌሊቱ ወጥቶ አደባባዩን የሞላው የደቡብ ሕዝብንስ ጉዳይ የት አስቀምጠውት ይሆን?
በጣም በሚገርም ሁኔታ የኦሮሚያን ሕዝቦች በተለይ ወጣቶችን በዶክተር ዐቢይ ተቀባይነት ለመገንጠል ያሰበበት መንገድ ደስ አላለኝም፡፡ ይሁንና ይህ አባባሉ በየቱም ወገን፣ በማንም ቢገመገም ተዐማኒነት የሌለውና ምናልባትም እንደ ነፍሱ የሚወደው የህወሓት /ኢህአዴግ ፍቅር ማየት የከለከለው ያስመስልበታል፡፡
አቶ ሚካኤል ገፅ 25 እና 26 ላይ የዶክተር ዐቢይን ደጋፊዎች ለማሳነስ ሲሞክር እንይ እንጂ በራሱ ብዕር፣ በራሱ ቃል፣ ስለ ህዝባዊ ተቀባይነታቸው የጻፈው ማሥረጃ አለ፡፡ “የማስጠንቀቂያ ደወል” ገፅ 9 ሁለተኛው አንቀፅ ላይ፤
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እየወሰዱዋቸው ባሉ እርምጃዎች አገር ከጫፍ እስከ ጫፍ በተስፋና በማይመጠን ደስታ እየተቀጣጠለች ባለችበት በዚህ ወቅት …
ይላል፡፡ ልብ በሉልኝ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ባለበት በዚሁ አንደበት ነው የዶክተር ዐቢይን ደጋፊዎች ቁጥር ለማሳነስ የተጣጣረው፡፡ እንግዲህ መጽሐፉ ውስጥ እጅግ ካስገረሙኝ ነገሮች አንዱ ይህ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የለውጡን መንገድና ተስፋ ለማጣጣል የሚደረግ ሙከራ ይመስላል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ጥቂት ገፆች ከተሰጡትና ከሶቭየት ሕብረት ታሪክ በተረፉት ገፆች ላይ ያሉትን ሀሳቦችን ጨምቀን ስናጠላቸው፣ ወደ አንድ ማጠቃለያ ያደርሱናል፡፡ ያ ማጠቃለያ ደግሞ “ኢሕአዴግ” የታደሰውን ሳይሆን በበረሀ ተወልዶ ከተማ ውስጥ እንደ ልቡ የኖረውን፣ የኢትዮጵያን የዘመናት ጥያቄ መልስ ሰጪና ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ አድርገው በማሽሞንሞን፣ ቅጥሩ እንዳይደፈር ጉበኛ ሆኖ ለመቆም የሚያደርጉትን ወገንተኝነት ያሳያል፡፡
ለምሳሌ ደራሲው ወገንተኛ መሆናቸውን ገፅ 15 ላይ “የህወሓትና የኢህአዴግ አመራሮች ብሔር አቀፉን ፌደራላዊ ስርዐት የተከተሉት ሆን ብለው አገራቸውን ከፋፍለው ለማባላትና ለመግዛት ሲሉ ነው የሚለው አስተሳሰብ፣ ፍትሃዊነት የጎደለው አመለካከት ይመስለኛል፡፡” በሚለው ሀሳባቸው መመዘን ይቻላል፡፡
ለመሆኑ ለዚህ የከፋፍሎ መግዛት መርህና አስተሳሰብ ከአቶ ሚካኤል ይልቅ ሕዝቡ ምስክር ይሆን ዘንድ አይችልም? በቃልና በጽሑፍ የተረጩት መርዞችስ በቀላሉ ሊካዱ ይችላሉ? ታዲያ አቶ ሚካኤል ያንን ሁሉ “እሳትና ጭድ” የማድረግ ዘመቻ እንዴት ዘነጉት? የበደል መታሰቢያ ሀውልት ያስገነባውስ ለፍቅር ይሆን?
ፀሐፊው አልፎ አልፎ ለውጡን ደጋፊ የሚመስሉ ጥቂት ዐረፍተ ነገሮች ጣል ከማድረግ ባለፈ፣ በአብዛኛው የሚያንፀባርቁትና የሚያተኩሩት የለውጡን ህፀፆች በማጉላት ላይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢትዮ - ኤርትራ የእርቅና የሰላም ሀሳቦች ዙሪያ፣ በብሔር ብሔረሰቦች መብት አጠራጣሪነት፣ በትግራይ ተወላጆች ስጋትና ሌሎች ችግሮችን አሳማኝ ባልሆነ መረጃና “ይመስለኛል፣ እገምታለሁ” በሚል ማሰሪያ እየሸበቡ፣ የለውጡን ተስፋ በማሳነስ አደጋውን ለማግዘፍ ሞክረዋል፡፡
በተለይም የኢሕአዴግን የኢትዮጵያን ህዝብ የዘመናት ጥያቄዎች መላሽነት ለማግዘፍ ሲሉ የኢሕአፓን፣ የኢሕዲንን እና የብአዴንን የትግል አቅጣጫዎች ወደ ታች ደፍቀዋል፡፡
ኢሕአፓ ብሔራዊ ፓርቲ በመሆኑ፣ የብሔረሰቦችን ጥያቄ መመለስ ያልቻለና በብሔራዊ አንድነት የተወሰነ በመሆኑ፣ የብሔር ችግሮችን መፍታት ባለመቻል በሶሻሊስታዊው መስመር፣ ኢትዮጵያዊነትን የሙጢኝ ማለቱን፣ በሌላ በኩል ግን የሕወሓት ታጋዮች በብሔር ተደራጅተው፣ ህዝባቸውን በማቀፋቸው ውጤማ እንደሆኑ ለመስበክ ጥረዋል፡፡
“…ኢሕአፓ ራሱን የሚያውቀው እንደ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ድርጅት ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን አርሶ አደሮችና “ላብ አደሮች” እወክላለሁ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ያመራሩ ስብጥርም ከአማራና ከትግራይ ከሌሎችም ያገራችን ክልሎች በወጡ ወጣቶች የተዋቀረ ሲሆን ሁሉም በብሔራዊ ማንነታቸው ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታቸውና በግራ ዘመም የፖለቲካ አመለካከታቸው የተቧደኑ ነበሩ፡፡
ምናልባት ሚካኤል፤ ጌታቸው ማሩ የጉራጌ ቡድን፣ ተስፋዬ ደበሳይና ብርሃነመስቀል ረዳ፣ የትግራይ፣ እነ ክፍሉ ታደሰና ሌሎቹም በራሳቸው ጎጥ እንዲደራጁ ለመምከር ሳይፈልግ አልረቀም፡፡
መጽሐፉ ሕወሓት ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪነት ወደ ኢትዮጵያዊ ነፃ አውጭነት የመጣው ከማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ቀርፎ የወሰዳትን የአንድነት መንፈስ፣ ይዞ ከተነሳው የብሔር ጥያቄ ጋር በማዋደድ ነው በማለት ፀበል ይረጨናል፡፡
ሌላው በሚካኤል ብዕር ውስጥ የወቀሳ በትር የወረደበት ኢሕዴን፣ በኋላም ብአዴን የተባለው ድርጅት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወቀሳው ዋንኛውንና በአደባባይ የምናውቀውን የድርጅቱን ደቃቃነት ምክንያት ሸፍኖ፣ ከኢሕአፓና ከሌሎች ሀገራዊ ፓርቲዎች የተዛመተበት በሽታ ለማስመሰል ሲሞክር ይስተዋላል፡፡
ለመሆኑ ኢሕዴን ከሕወሓት ጋር ተጣምሮ የትጥቅ ትግል ሲጀምር በብሔር ብሔረሰቦች መብት ተስማምቶና ተዋውሎ መሆኑን በበርካታ ድርሳናት አንብበን እንደነበር እንዴት ይዘነጋል?
ይሁንና ደራሲው በገፅ 224 ላይ የሚነግረን ነገር ከእውነት ጋር ይጋጫል፡፡ ኢሕዴን ከሕወሓት ጋር ስለመቀላቀሉ እንዲህ ይላል፡- “በመጨረሻ ኢሕአፓ በከተማው የሽምቅ ውጊያም ሆነ በገጠሩ የትጥቅ ትግል ተሸንፎ የመጨረሻ ርጋፊው ሲቀር አሁንም የሕወሓት የኃይል ሚዛን አይሎ አዲሱ የኢህአፓ ልጅ ኢህዴን በሁሉም መስክ በተዳከመበት ምእራፍ ላይ ሆኖ የትግራይን ህዝብ የነፃነት ትግል ተቀብሎ ከህወሓት ጋር ግንባር መሰረተ፡፡
ይህ ሀሳብ ብቻውን ኢሕዲን ከሕወሓት ጋር በግንባር ትብብር የመሰረተበትን መንገድ እየነገረን፣ ቀጥሎ ባለው አንቀጽ ደግሞ ከዚህ ጋር የሚጣረስ ሀሳብ ያስነብበናል፡፡
“ስለዚህ ኢህዲን ወይም የኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ተብሎ ባዲስ መልክ ትግል ጀመረ፡፡ በዚህ ማንነቱ ከ1973 እስከ 1983 የአማራውን ክልል ገበሬ እያንቀሳቀሰ ሲታገል ሌሎች ደርሶብናል ስለሚሉት ብሔራዊ ጭቆና እያስተነተኑ ሲቀሰቅሱ ኢህዲን የሚያነሳው በሌሎች ላይ ስለደረሰ ብሔራዊ ጭቆና እንጂ የየራሱን ማንነት አስመልክቶ ሊቃኘው የቻለ ፖለቲካዊ አመለካከት ወይም አይዲዮሎጂ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡
” ደራሲው ይህንን ሲሉ ኢሕዴን ውስጥ የነበሩ ታጋዮች ሁሉ አማሮች ናቸው፤ ግን ለአማራነታቸው መታገል አልፈለጉም፡፡ እያሉን ነው፡፡ ግን ኢሕዴን የአማራ ታጋዮችን ብቻ ያቀፈ ፓርቲ ነበር? … ሰበቦቹስ እነዚህ ብቻ ናቸው?
(ይቀጥላል)
No comments