Latest

የንግዱ ማኅበረሰብ ሕገወጥ ተግባራት መቆም እንዳለባቸው አሳሰበ - ዳዊት ታዬ

የንግዱ ማኅበረሰብ ሕገወጥ ተግባራት መቆም እንዳለባቸው አሳሰበ

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ሕገወጥ ተግባራትን መንግሥት ማስቆም እንዳለበት የንግዱ ማኅበረሰብ ማሳሰቢያ አቀረበ፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ያለ ሥጋት ሥራውን ማከናወን የሚችለው ሕገወጥ ተግባራት ሲቆሙ እንደሆነም ጥያቄ ቀርቧል፡፡

የሥጋት ጥያቄው የቀረበው ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት የንግድ ምክር ቤቱ ቀደምት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ውብሸት ኃይሉ (ኢንጂነር)፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየታየ ያሉ ሕገወጥ ተግባራት እጅግ አሳዛኝ እንደሆኑ በመግለጽ፣ ሁኔታው የንግድ ማኅበረሰቡን ሥጋት ላይ መጣሉን አስታውቀዋል፡፡

የትም ይሁን የት አሁን በንግዱ ማኅበረሰቡ ላይ የተጋረጠ አደጋ እንዳለ ያመለከቱት አቶ ውብሸት፣ ‹‹አደጋው ሁላቸንንም ሥጋት እንዲገባን አድርጎናልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያቀርበው ጥያቄ ግን ሕግና ሥርዓት ይከበር ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ይምጣ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ልማት ይከተላል፤›› ሲሉ መንግሥት የጉዳዩን አሳሳቢነት መረዳት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

‹‹አውቃለሁ ሽግግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በሽግግር ወቅት ብዙ ውጣ ውረዶች ይኖራሉ፡፡ ብዙ ያልተጠበቁ ክስተቶች ሊያገጥሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ልንቆጣጠረው እንችላለን፡፡ ዝም ስንል ግን የሚጠፋው የሰው ሕይወትና እየወደመ ያለው ልማት ያሳምማል፤›› በማለት ድርጊቱ በንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ ፈጥሯል ያሉትን ስሜት አንፀባርቀዋል፡፡

በአንድ ሰው ከልጅነት እስከ እውቀት የለፋበት ንብረት በሥርዓተ አልበኝነት እንዳልነበር ሲሆን መንግሥት አለ? ሕግና ሥርዓት አለ?፡፡ በማለት ጥያቄ አንስተው፣ ‹‹ይህ ያሳዝናል፣ ስለዚህ ለንግዱ ማኅበረሰብ ሕግና ሥርዓት ይከበር፣ ሰላምና መረጋጋት ይስፈን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ይህንንም ሐሳብ በንግድ ምክር ቤቱ ስም ለመንግሥት እንዲደርስላቸው የጠየቁት አቶ ውብሸት፣ መረጋጋት ጠፍቶ ሥርዓተ አልበኝነት ከቀጠለ ለልማት አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራታቸውን የገለጹ አንድ ባለሀብት ደግሞ፣ ኢንቨስትመንታቸው ባለበት አካባቢ የሚታዩ አለመረጋጋት በሥራቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እሳቸውም እንደ አቶ ውብሸት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በኢንቨስትመንትና በአጠቃላይ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ስለሚፈጥሩ፣ የመንግሥት ዋስትና እያስፈለገ ነው ብለዋል፡፡ 


በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ኢንቨስትመንታቸው ወዳለበት ቦታ በመሄድ ሥራቸውን በቅርብ መከታተል እንዳለባቸው የገለጹት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ባለሀብት፣ መንግሥት ድርጊቱን በዝምታ መመልከት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ 

ሰላምና መረጋጋት በመጥፋቱ ምክንያት የሠራተኞቻቸው ዋስትናም እንደሚያሠጋቸው አስረድተዋል፡፡ ኢንቨስትመንታቸውን ለማስቀጠል መንግሥት ጥበቃና ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

No comments