አርቲስት ታማኝ በየነና አለምፀሃይ ወዳጆ ከ25 ዓመት በኋላ አገር ቤት ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ይጠብቃቸዋል
“በኢትዮጵያ ማንነት አቀንቃኝነቱ” የሚታወቀው አርቲስት ታማኝ በየነ፤ ነሐሴ 26 ከሁለት አስርት አመታት በላይ ከኖረባት አሜሪካ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለስ የታወቀ ሲሆን አርቲስቱን በመቀበልም የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከአርቲስቶችና ከታዋቂ ፖለቲካኞች የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡
ለአርቲስቱ ነሐሴ 26 ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ከሚደረግለት አቀባበል በተጨማሪ ነሐሴ 27 ሚሊንየም አዳራሽ ልዩ የአቀባበል ስነ ስርአት ይደረግለታል ተብሏል፡፡
በቅርቡ ከምትኖርበት አሜሪካ ከአዲስ አድማስ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ባደረገችበት ወቅት “ሃገሬ ህዝቡ፣ ቲያትር የሠራሁበት መድረክ ናፍቆኛል፤ በቅርቡ ወደ ሃገሬ እመለሳለሁ” ያለችው ተወዳጅዋ አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆ ማክሰኞ ነሐሴ 22 ቀን ከ25 አመት በኋላ አዲስ አበባ እንደምትገባ ታውቋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፤ አርቲስት ታማኝ በየነና አለምፀሃይ ወዳጆን እንዲሁም በክልሉ የህዝብ ድምፅ በመሆን በአክቲቪስትነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጋዜጠኛና ፖለቲከኞችን በአዲሱ አመት ዋዜማ በክብር ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ አስታውቋል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩ ምቹ ስላልነበረ ከሃገር ወጥተው የቆዩት ጋዜጠኛ አበበ በለው፣ ሙሉቀን ተስፋው፣ የ “ልሳነ አማራ” እና የሌሎች ገፆች ጦማሪያን ወደ ሃገር ቤት ከሚመለሱት መሃከል እንደሚገኙበት የጠቀሡት የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ በቆይታቸውም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ከህዝብ ጋር ውይይት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን ሃገራዊ የለውጥ ንቅናቄ ተከትሎ፣ ወደ ሃገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ ከቀረበላቸው የተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሠቦች መካከል አብዛኞቹ ወደሃገር ቤት መመለሳቸውን መንግስት የገለፀ ሲሆን በመጪው አዲስ አመትም በርካቶች ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት ይመለሣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አለማየሁ አንበሴ
No comments