አቶ ኦባንግ ለምን በይፋ አምባሳደራችን አይሆንም?
አሁን ኢትዮጵያ ልትጓዝበት እየተጠረገ ያለው መንገድ ከቀደሙት ሁሉ የተለየ ይመስላል። አዲሱ መንገድ ጥላቻን በመስበር የኢትዮጵያን ህዝብ ያለ ልዩነት በፍቅር ተጋምዶ እንዲጓዝበት ታስቦ የሚዘጋጅ ነው። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት የሩቁን ትተን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተኬደበት የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የቂም፣ የመለያየት፣ የጎጠኝነት ድምሩ አጠቃላይ አገራዊ አደጋ በማስከተሉ ነው። ይህ እውነት ሊካድ በማይችል መልኩ የታየ በመሆኑ አዲሱን ጥርጊያ ማበጀት ብቸኛው አማራጭ ሆኗል።
እያደር እየከረረና እየፋመ የመጣው የዘረኛነት በሽታ፣ ስርዓቱ የቆመበትን የጎጥ አስተሳሰብ ለማስጠበቅ የሚከተለው መንገድ የፈጠረው ጥላቻ፣ በስርዓቱ ውስጥ በስልትና በዕቅድ የተፈጠረው ሃብት የማጋበስ በሽታ፣ የፍትህ ዝቅጠት፣ የርትዕ መጓደል፣ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች መሞት፣ ድህነት፣ ችጋር፣ ጠኔ፣ ረሃብ፣ የጥቂቶች መበልጸግ፣ የሌብነት መንሰራፋት፣ ሥራ አጥነት፣ በየቀዬው ቦታ ለይቶ የሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ተግባርና ግድያ አንድ ላይ ተዳምሮ የቀሰቀሰው ህዝባዊ ማዕበል ፍሬ አፍርቶ አገሪቱ በለውጥ ጎዳና እንድትራመድ አድርጓታል። ይህ የለውጥ ጉዞ ገና ለጋ ቢሆንም ያልተለመዱና ያልተገመቱ ለውጦች ተመዝግበውታል።
አብዛኞች እንደሚሉት፣ ከራሱ ከስርዓቱ የወጡ የለውጡ ፍሬዎች በመሪ ደረጃ ደጋግመው እንደነገሩን አዲሱ ጥርጊያ መንገድ “የፍቅር” ተጓዦችን በማስቀደም የሚጸና ነው። ይህ የፍቅርና “የመደመር” አዲስ እሳቤ አገሪቱን ከዳር እስከዳር ያነቃነቀ፣ በውጪ አገር ያሉትንና በፍረጃ ሲገፉ የኖሩትን ዜጎች ሳይቀር የሞተ ተስፋቸውን ህይወት የዘራበት ሆኗል። ለዚህም ማረጋገጫው በአደባባይ ባለሥልጣናትን ሲረገሙበትና ክብራቸው ሲቆሽሽበት በነበሩት ጎዳናዎች ላይ የታየው የድጋፍ ስሜቶች ናቸው። በድፍን አውሮጳ፣ አሜሪካ እንዲሁም አገር ቤት።
ለውጡ ይፋ ከሆነ በኋላ “መሪያችን” ለመባል አፍታ ያልቆዩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እየሰበኩ ያሉትና እሳቸውን ከሚመስሉ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የኮሰሰችውን ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው ሲያሳዩን በደስታ ታመናል። ጮቤ ረግጠናል። ሰክረናል። ማመን እስከሚያቅተን ዓይናችንን ለዘመናት በምንጠየፈው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ላይ ለመሰካት ተገደናል። ያለ ምንም ማጋነን የምንሰማውና የምናከብረው አክባሪ መሪ በማግኝታችን በርካታ ርሰናል። ግን ስጋትም አለብን።
ይህ ለውጥ ለምን ቅር እንዳሰኛቸው ማስረዳት የማይችሉ ክፍሎች በየዕለቱ በሚገምዱት የተንኮል ድር መሪያችን በሰላም ውሎ ማደሩን ለመስማት የምንታትር ዜጎች ጥቂት አይደለንም። ይህ ስጋት የብዙሃኑ አገር ወዳድ ቢሆንም ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት የለውጥ አራማጅ እንጂ የለውጥ ሃሳብ ስለማይሞት በዚህ እየተጽናናን እየነጋ መሽቶ ዛሬ ላይ ደርሰናል። አውሬ ተደርገው የተሳሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስም አገር ቤት ገብተው ሰላም ሲያውጁና ይህ ለውጥ እንዲቀለበስ እንደማይፈቅዱ ሲነገሩን ለመስማት ታድለናል።
አሁን የተጀመረው አዲሱ የ“መደመር” እሳቤ ለሁሉም ዜጎች ክፍት እስከሆነ ደረስ በቀናነታቸው፣ በኢትዮጵያዊነታቸው፣ በፍቅር አቀንቃኝነታቸው፣ በርካታ የተሰባበሩ ድልድዮችን መጠገን የሚያውቁበትን፣ ለሰው ልጆች መብት እገሌ ከገሌ ሳይሉ የሚታገሉትን፣ ቂምና የዘር ፖለቲካን አጥብቀው የሚኮንኑና ለዚህ ተግባራቸው ድፍን የወገኖቻቸውን ምስክርነት ያለ አንዳች ህጸጽ ማግኘት የሚችሉ ወገኖችን መጠቆም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት በመሆኑ አቶ ኦባንግ ሜቶን የአዲሱ ጥርጊያ መንገድ መሃንዲስ ከሆኑትና እንዲሆኑ ከታሰቡት መካከል አንዱ እንዲሆኑ ለመጠቆም ወደድኩ።
እኔ የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አገርቤት ከሚነገረው ባላነሰ ከሚከወንበት የምስራቁ ጠረፍ የአሜሪካ ግዛት የምገኝ ነኝ። የአገሬንም ፖለቲካና የሕዝቤን ጉዳይ በቅርበት ለበርካታ ዓመታት ስከታተል የኖርኩ ነኝ። በሁሉም መስክ ለአገራቸው በቅንነት የሚታገሉትን ወገኖቼን በሙሉ አከብራቸዋለሁ። ለሚከፍሉትም ታላቅ መስዋዕትነት አክብሮት እሰጣለሁ። በአሁኑ ወቅት ከዚህ ጽሁፍ ጋር በተያያዘ ማንነቴን ለመግለጽ አልፈለኩም።
በብዕር ስምና የኢሜል አድራሻ መጻፍ እችል ነበር። ያንንም ማድረግ አልፈለኩም። ስለዚህ ይህንን ጽሁፌን ኢትዮጵያን ለመጥቀም በቅንነት የተጻፈ አድርጋችሁ በመውሰድ አስተያየት ካላችሁ ከዚህ ጽሁፍ ሥር ጻፉልኝ። ወደ ጽሁፌ ሃሳብ ልመለስና አቶ ኦባንግ ሜቶን ለምን ለዚህ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት እንዲሾሙ እንደፈለግሁ ላብራራ። (ለአጻጻፍ እንዲመች በሚል አቶ ኦባንግን አንተ ማለቴ ይታወቅልኝ)።
ኦባንግ ሜቶ
ከአራት መቶ በላይ የአኙዋክ ወንድሞቹ በጅምላ በተጨፈጨፉ ማግስት ከዘርና ቂመኛ አካሄድ በማፈንገጥ “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ አይሆንም፤ ከጎሰኝነት በፊት ሰብአዊነት” በሚሉት መርሆቹ ከሌሎች ጋር በመሆን የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በማቋቋምና በመምራት ከባልደረቦቹ ጋር ስለ ፍቅር ሲዘምር የኖረ፣ ጥላቻን ሲቃወምና ዘረኝነትን ሲጸየፍና ባደባባይ ሲዋጋ የቆየ፣ ሌብነትን አጥብቆ የሚጠላ፣ በዳያስፖራ ወገኖቹ የሚደመጥና በፍቅር የሚከበር፣ ኢትዮጵያን በመወከል በከፍተኛ መድረኮች ሲታገል የቆየና አሁንም በዚሁ የትግል መስመር የጸና ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነው።
ኦባንግ የመርህ (የፕሪንስፕል) ሰው ነው። የሰላማዊ ትግል ዋጋቢስ ነው በሚባልባቸው ፈታኝ ጊዜያትም ሆነ የጽሁፍ (የግልጽ ደብዳቤ) ፖለቲካ ሳይሆን ወያኔን በሚገባው ቋንቋ ማናገር ይገባል በሚባልባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ከአቋሙ ንቅንቅ ሳይልና የሌሎችን የትግል መስመር ሳይነቅፍና ሳያንቋሽሽ ያመነበትን የራሱን መንገድ ያለመወላወል በጽናት የጠበቀ ብርቱ ታጋይ ነው።
ኦባንግ ስብዕናው ድንቅ ነው፤ የማንኛውም ሰው ማንነት የሚጀምረው ከሰውነቱ ነው ይላል፤ ይህንንም ሲያስረዳ “ስንወለድ ዘር፣ ቋንቋ፣ ጎሳ፣ ወዘተ ሳንሆን ሰው ሆነን ነው የተወለድነው” ይላል። ከሰውነቱ ቀጥሎ ማንነቱን የሚገልጸው በኢትዮጵያዊነቱ ነው።
ኦባንግ ሜቶና አገሩ
ኦባንግ አገሩን የሚወድውና የሚያከብረው በተግባር ነው። አገሩን የሚያገናኛት ከሕዝቧ ጋር ነው። ሁሉም ነገር ኢትዮጵያ ከምትባለው አገር የሚጀምር መሆኑን በይፋ የሚያስተምር፣ ለጥላቻ ከቶውንም ቦታ የሌለው፣ በአገሩ የማይደራደር፣ ከበቀል የጸዳና ዘረኝነትን አጥብቆ የሚጠየፍ በዚያም በተግባሩ አገራቸውን ለሚወዱ ሁሉ ኩራት የሆነ ሰው ነው።
አገሩን በተግባር ስለሚወድና ከህዝቧ ጋር ስለሚያገናኝ ለኦባንግ የአንድ ኢትዮጵያዊን ጉዳት የኢትዮጵያ ጉዳት አድርጎ ነው የሚወስደው። ለዚህም ነው ባለፉት በርካታ ዓመታት ኦባንግን ሥራ ስንከታተል ለነበርን ሁሉ በስደትና በተለያየ ችግር ለሚንገላቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ሲሟገትላቸው የኖረው።
ለኦባንግ ኢትዮጵያ የምታምር የአበባ ቦታ ነች (ይህ የራሱ አገላለጽ ነው)። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም አንድ ውብ አበባ ነው። በዚህ የአበባ ቦታ የማያምር አበባ የለም፤ ሁሉም የተለያየ ቀለምና ውበት አለው። ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ነን ነው ኦባንግ የሚለው። ሁላችንም እናምራለን፤ ሁላችንም ውብ ነን። ይህንን ሲናገርም ሆነ ሲጽፍ ኦባንግን ሰምቼዋለሁ፤ አንብቤዋለሁ። ከእርሱ ቀጥሎ አገሬን በዚህ መልኩ ውብ አድርጎ ሲጠሩ የሰማሁት ዶ/ር አብይና አቶ ለማ ናቸው።
ኦባንግ ሜቶና ዳያስፖራ
በመላው ዓለም የሚገኙ ወገኖቹን በክፉ ቀን የሚታደግ፣ የወገኖቹ ሁሉ ጠበቃ የሆነ፣ በሄደበት አገር ሁሉ በር የማይዘጋበት፣ ሥራውን እንዴት መሥራት እንደሚችል የሚያውቅ፤ በኦፊሴል ሳይሾም የወገኖቹ ሁሉ አምባሳደር ሆኖ በሄደበት ሁሉ የተሳካ ሥራ ያከናወነ፣ በዚህም ተግባሩ በዓለም ላይ በሚገኙ ዳያስፖራዎች ላይ ዓለምአቀፋዊ ተጽዕኖ የፈጠረ፣ የሚደመጥ፣ የሚታመን፣ የሚከበርና የሚወደድ የኢትዮጵያ ልጅ ነው ብል ማጋነን አይሆንም። በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል ቀድሞ በማምከን ከበርካታ ዜጎች ልቡና የማይወጣ ተግባራት ያከናወነ ስለመሆኑ በቂ ዋቢ የሚቀርብለት ጀርባው የጸዳ ወገናችን ነው።
በሜክሲኮ፤ በጃፓን፣ በእስራኤል በኖርዌይና በደቡብ ኮሪያና በአካል በመገኘት በማልታ፣ በሊቢያ፣ በሳውዲ አረቢያ፣ በየመን፣ ወዘተ የኢትዮጵያውያን የፈቃድ አምባሳደር በመሆን ወገኖቹን በእስር ቤት ሲንገላቱ ፈጥኖ በመድረስ ያስፈታ፣ ባሉበት ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ፣ ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይና በዓለምዓቀፍ ደንብና ሕግጋት መሠረት ተከብረው እንዲኖሩ የረዳ የኢትዮጵያ ጥቁር አልማዝ ነው። በተጠራበት ቀድሞ በመድረስ አጋር በመሆን ሳይሾም የአምባሳደርነት ሥራ የሠራ ብርቅ ዜጋችን ነው።
ኦባንግ ሜቶና ዲፕሎማሲው
ላለፉት በርካታ ዓመታት ኦባንግ በአሜሪካ የፖለቲካ ኮሪደሮች በቀላሉ በመመላለስ ከበርካታ የኮንግሬስ አባላትና ፖሊሲ አውጪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የመሠረተ ሰው ነው። የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ በአሜሪካ ኮንግሬስ ላይ ብቻ ሳይሆን በአውሮጳ ፓርላማና የተለያዩ አገራት ምስክርነት የሰጠ፣ የተሟገተ፣ ተጽዕኖ የፈጠረ ነው።
ወደፊት ዶ/ር አብይ በአሜሪካ በኩል ለማስፈጸም ለሚፈልጉት ማንኛውም ተግባር ኦባንግን አምባሳደር ማድረጋቸው በአክቲቪስትነቱ ከሚያውቁት የአሜሪካ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቀላሉ በመሥራት ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት ምንም የሚከብደው አይመስለኝም።
በፖለቲካው መስመር ብቻ ሳይሆን የመሬት ነጠቃን በተመለከተ በአገር ውስጥ የሚፈጸመውን ሸፍጥ በማጋለጥ ጉዳዩን (በራሱ አገላለጽ) የመሬት ነጠቃ ብቻ ሳይሆን የህይወት ነጠቃም መሆኑን በማስረዳት እርሱ የሚመራው ድርጅት እንደ ኦክላንድ ተቋም ካሉ ድርጅቶች ጋር በመሆን የተቀነባበረ ዘገባ በማውጣት የታገለ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የመሬት ነጠቃ በህንዱ ካሩቱሪ የሚፈጸም በመሆኑ ይህንኑ አጀንዳ በመያዝ ህንድ ድረስ በመሄድ የኢትዮጵያን መዘረፍ ለህንዳውያኑ በግምባርና በሚዲያቸው ያጋለጠ የሕዝብ አምባሳደር ነው።
ኦባንግ ሜቶና የዶ/ር አብይ ራዕይ
ለዓመታት በዘለቀው የህወሓት አገዛዝ ዳያስፖራው ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ “የህወሓት ጽ/ቤት” አድርጎ ነበር የሚወስደው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በዳያስፖራውና በኤምባሲው መካከል ከፍተኛ የሆነ ያለመተማመን ችግር አለ፤ አሁንም እየታየ ያለ ጉዳይ ነው። ዶ/ር አብይ ደግሞ ለዳያስፖራው ያቀረቡት ጥሪ አለ፤ ከዳያስፖራው ጋር በርካታ ሥራ ለመሥራት ማሰባቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ይህንን የእርሳቸውን ራዕይ ለማሳካት ደግሞ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለውና የሚታመን ሰው ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ኦባንግን አላምንም የሚል ዳያስፖራው ውስጥ አለ ብዬ ለማመን ይቸግረኛል።
ኦባንግ፣ ታላቅ የልማት ኃይል መሆን የሚችለውን የኢትዮጵያን ዳያስፖራ ዳር እስከዳር ማነቃነቅ የሚችል፣ በኢህአዴግና በዳያስፖራው መካከል መተማመን ባለመኖሩ ምክንያት የተገነባውን የልዩነት ግንብ ማፍረስ የሚችልና ይህንን ታላቅ ኃይል የልማት ሠራዊት አድርጎ የማስደመር አቅም ያለው ሰው መሆኑንን በግል አልጠራጠርም። በሁሉም ወገኖች ዘንድ የገነባው መልካም ግንኙነትና አመኔታ ከምንም ወገን ጣት ሊቀሰርበት የሚችል ሰው አለመሆኑን ሳስብ ኩራቴ ታላቅ ነው። ስለዚህ የዶ/ር አብይን ራዕይ በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም ከኦባንግ የተሻለ ሰው አለ ለማለት አልችልም።
ከሁሉም በላይ በጅምላ ከተጨፈጨፉት፣ በስደትና በመፈናቀል ሊጠፉ ከተቃረቡት ወገን መሆኑን በማሰብ ለአገሩ ያለውን ክብር፣ ከበቀልና ከቂም የጸዳ መሆኑ፣ ወደ አደባባይ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ፍቅርን የሚሰብክ፣ አንድነትን የሚያውጅ፣ ርህራሄ የተላበሰ፣ የጸና የእምነት ዓለት ላይ የቆመ ቅን ሰው መሆኑ ከሁሉም ልዩ ያደርገዋል።
ከዚህ በላይ ስለ ኦባንግ አምባሳደር የመሆን ብቁነት በጣም ብዙ ማለት ይቻላል። ግን በዚሁ ላብቃ። ይህንን የጻፍኩት ኦባንግን በቅርብ ከመከታተልና በድርጅቱ ድረገጽና በራሱ ፌስቡክ ላይ የሚወጡትን በማንበብ ነው። ማንም ሰው ይህን የጻፍኩትን ለማረጋገጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድረገጽን እንዲሁም የአቶ ኦባንግን ፌስቡክ ገጽ እንዲመለከት እጋብዛለሁ።
ይህንን የጻፍኩት አባንግንና ሥራውን ለዓመታት በመከታተል ራሴ የታዘብኩትን በመሰብሰብ ነው። ለአምባሳደርነትም እንዲታጭ ሃሳቤን ያቀረብኩት በአገርቤት ካለኝ መረጃ በመነሳት መሆኑ እንዲታወቅልን እፈልጋለሁ። ኦባንግ በዳያስፖራ ላለነው በመንግሥት ያልተሾመ አምባሳደራችን ሆኖ በፈቃዱ አገልግሏል። አሁን ደግሞ የመደመርን ርዕዮት እያራመድን ባለንበት ወቅት ለዳያስፖራውም፣ ለዶ/ር አብይ አስተዳደርና የተሃድሶ እርምጃ እንዲሁም እርሳቸው ከዳስፖራው ጋር ለመሥራት ላቀዱት አቶ ኦባንግ ሜቶ በሁሉም መስክ ገጣሚ ሰው ብዬ አምናለሁ። (ፎቶዎቹ ከነጽሁፎቹ በፀሐፊው የተላከ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ (http://www.goolgule.com)
No comments