Latest

አብይ ምናችን ነው?

አብይ

ለመነሻ
ሀ፦ “አሁንም…ኢትዮጵያ አንድ አብዮት ያስፈልጋታል። ልጆቿን የማይበላ አብዮት! ራሱን የማይውጥ አብዮት! ሳይንቲፊክ ሪቮሉሽን። በሳይንስና ቴክኒዮሎጂ የታገዘ አብዮት። ለውጥን የሚጠላ ኢትዮጵያዊ የለም። ለውጡ ሆዳቸውን ከሚያጎልባቸው ጥቂቶች በቀር።” ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ በዴርቶጋዳ መፅሀፍ ላይ በ2001 ዓ/ም እንደፃፈው ወይም በራዕዩ እንዳስቀመጠው። 

እነሆ በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜው ላይ ይገኝ የነበረው ወጣቱ ባለራዕይ ደራሲ እንደታየው ሳይንሳዊው አብዮት፤ ልጆቹን የማይበላው አብዮት፤ ራሱን ውጦ የማያሳብጥና የማይፈነዳ አብዮት፤ በሳይንስና ቴክኒዮሎጂ ላይ የታገዘ/የሚታገዘው አብዮት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ/ም የኢትዮጵያን መንበር ከህወሃት መዳፍ በይፋ ፈልቅቆ በወሰደው ሌላኛው ወጣት/ጎልማሳ ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ በርግጠኝነት ተጀምሯል ማለት እንችል ይሆን? አብይ የአዲሱ ዘመን አብዮታችን መሪ? ኢትዮጵያን እንደ መረግ ተጭኖ እንደ መዥገር ስሩን ሰዶ ያሰቃያትን የኢህአዴግን ካንሰር ቀዶ ቆራጭ ሰርጀን? የኢትዮጵያን ትንሳኤ አብሳሪ የወጣቱ ትውልድ ምልክት?

ለ፦ “እኔን የአእምሮ በሽተኛ እንዳትሉኝ። በጣም ጤነኛ ነኝ። የማደርጋትን ነገር እያንዳንዷን አውቃታለሁኝ። እዚህ አካባቢ ያለ የካቢኔ ባለሥልጣን እኔን በሽተኛ ልትሉኝ ትችላላችሁ። ግና የዳውሮ ብሄረሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠበቅለት ራሴን እሰዋለሁ። ነፃነቴን ስጡኝ ወይንም ሞቴን” በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን ዋቃ ከተማ መምህር የነበረው የ34 ዓመቱ ወጣት የኔስው ገብሬ ታህሳስ መጀመሪያ 2004 ዓ/ም ለፍትህና ለመልካም አስተዳደር ሰሚ ያጣውን የዳውሮ ወጣትና ህዝብ ትግል በመሥዋዕትነት ለመታደግ ራሱን በቤንዚን ሲያቃጥል የተናገረው።

‘የዳውሮ ህዝብ በመምህሩ ሞት በጣም ሀዘን ላይ ነው ያለው። ሙዚቃ ቤት ሁሉ ዝግ ነው። እንኳን ለማልቀስ ከንፈር በሀዘን ለመምጠጥ ሀዘን የተሰማው ሁሉ ተወግሮ ወደ እስር ቤት ይገባል። እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ይሁን። የእናንተ (ጋዜጠኞች) ወደኛ ደውሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የሠማይ አምላክ ደውሎ ይጠይቀን። በጣም ያሳዝናል። የኛ ኑሮ ከፍተኛ ፀፀት ሆኖብናል” የዳውሮ ነዋሪ የተናገሩት። የወቅቱ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር /ህወሃት/ መሪና የኢህአዴግ ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ 300 ወታደሮችን ወደ ስፍራው በአፋጣኝ በማዝመት የመምህሩ ዜና እና የህዝብ ተቃውሞ እንዲታፈን አድርጓል።

እነሆ በመጋቢት 24 2010 ዓ/ም ከኢህአዴግ ማህፀን የወጣው ጠ/ሚር አብይ አህመድ እነ የኔስው ገብሬ ራሳቸውንም በማንደድና ሌሎች አእላፎችም በህወሃት መራሹ አጋዚ ጥይት በመርገፍ ባቀጣጠሉት የነፃነት ቀንዲል ‘ከፈርዖን መንደር’ የተገኘ የጨለማው ዘመን አሻጋሪያችን ነው ማለት አይቻልምን? በህወሃት የግፍ አገዛዝ መቀመቅ የገቡትን፤ የጨለማ ቤት ሰቆቃ ተሸካሚዎችን፤ የነፃነትና የፍትህ አራማጆችን ከዘመናት እስር የፈታ በእርሱ አመራር በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ዳግም የኔሰው ገብሬዎች ራሳቸውን እንዳይሰዉ የነፃነት ታጋዮችም ጨለማ ቤት እንዳይወረወሩ ከቀን ጅቦች ጋር በሚደረገው ትንቅንቅ ራሱን በመጀመሪያው ረድፍ ያቆመ ከክፉው ዘመን ሊያወጣን የሚደክም ‘ሙሴ’ያችን አይደለም ማለት እንችላለን?

ሐ፦ ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የተሰጠ “መንግስትነት እና ገዢነት ማይፍርስበት” መግለጫ ነው። “ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እስከአሁን ባደረገው ግምገማ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅታችን አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ ይገነዘባል። ሃገራችን በአሁኑ ሰዓት ለምትገኝበት አስጊ ሁኔታ ድክመቱ ያደረገው አስተዋፆ ከፍተኛ ነው። 

የድርጅታችን በየደረጃው ያለው አመራር ከሞላ ጎደል የዚሁ ድክመት ተጋሪ ቢሆንም ስራ አስፈፃሚው የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት መሆኑንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ የእርስ በርስ ንትርክ ላይ እንደሚያተኩር መግባባት ላይ ተደርሷል።” ኢትዮጵያን የሚመራው ይሄን የጻፈ የከረፋ ተቋም ነው። “አቅም የሌላቸውን በጭካኔ እና ጅምላ ገድያለሁ” ብሎ ኃላፊነት የሚወስድ መረን ገዢ። #መንግስት ሲኖረኝ ቀስቅሱኝ – ይህንን የፃፈው ስደተኛው ጎልማሳ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ነው። 

ኢህአዴግ ጥልቅ ግምገማ አድርጌያለሁ ብሎ ታህሳስ 2010 ዓ/ም ላይ ያወጣውን ማላገጫ መግለጫ ተመልክቶ አንጀቱ እየነደደ ፅፎት አደረ። “መንግሥት ሲኖረኝ ቀስቅሱኝ” ብሎ በፃፈ በአስራ አራተኛው ቀን አንጀቱ ያረረው የነፃነትና የዴሞክራሲ አርበኛው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ በአርባ ዓመቱ ገደማ በስደት ህይወቱ አለፈች። ኢብራሂም “መንግሥት ሲኖረኝ ቀስቅሱኝ” ብሎ እስከወዲያኛው ባንቀላፋ ከሶስት ወር በሁዋላ ደግሞ ሌላኛው የዕድሜ አቻው የኢህአዴጉ አብይ አህመድ ኢትዮጵያዊነትን እየዘመረና የሁዋለኞቹን እያወደሰ የኢትዮጵያን መንበር ከህወሃት ፈልቅቆ ወሰደ። 

ማማው ላይ ቆሞም ኢትዮጵያን ክፍ አድርጎ አከበረ፤ አነሳትም። “ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን” ሲል ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ብሥራት፤ ለቀን ጅቦቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ መርዶ ተናገረ። እነሆም ኢትዮጵያ በ27 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥትና የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ የሆነ አገኘች ማለት እንችል ይሆን?

መ፦ “እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ያዩ ዘንድ ወደዱ፤ አላዩም። እናንተ የምትሰሙትን ብዙዎች ይሰሙ ዘንድ ወደዱ፤ አልሰሙም። የእናንተ ያዩ አይኖችና የሰሙ ጆሮዎች የተመሰገኑ ናቸው።” የመፅሀፍ ቅዱስ አስተምህሮ። አእላፍ ኢትዮጵያውያን ለሃያ ሰባት ዓመት በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የተንሰራፋውን ዘረኛውን፤ ከፋፋዩን፤ ዘራፊውን፤ ዘር አጥፊውን፤ ዘር አምካኙንና ጅምላ ገዳዩን የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር /ህወሃት/ ዘመነ አገዛዝ ሲፋለሙ መስዋዕት ሆነዋል፤ በሀገር ውስጥም በስደትም። አእላፍ ኢትዮጵያውያን የአካልና የህሊና ቁስለኞች ሆነዋል፤ በሀገር ቤትም በስደትም። 

አእላፍ ኢትዮጵያውያን እንደወጡ ደብዛቸው ጠፍቷል። የቅዱስ መፅሀፉ ጥቅስ የተነገረው በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ዳግም የሰፈነውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለማምጣት መሥዋዕት ሆነው ‘ለማብያዊውን’ (ለማ አብይ) ኢትዮጵያዊውን መንፈስ ሳያዩና ሳይሰሙ እኛን ግን በዘመናችን ያላየነውን ለማየት ያልሰማነውን ለመስማት ለዚህ ላደረሱን የለውጥና የፍትህ ሠማዕታት ማስታወሻ ይሆን እንዴ የተነገረውና የተፃፈው?

አንድ
አብይ የመሰዋዕትነታችን ውጤት፤ የድምፅ አልባዎች ድምፅ፤ የሰቆቃችን ምላሽ፤ የማንነታችን ነፀብራቅ፤ የትንሣዔያችን መሪ? እኒህ ቀጣዮቹ መጠሪያ ስም ቢኖራቸውም የሚያውቋቸው ቤተሰቦቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ብቻ ናቸው። መድረክ ይዘው እየተዘባነኑ ኮት ገልብጠው የተደመሩ አልያም የተደመሩትን ለመቀነስ የሚያሴሩ የቀን ጅቦች ወይም የጅቦች ጓደኞች ተኩላዎቹን አይደሉም። 

እነሱ ገዳዮችና ሌቦች ዘረኞችና ዘራፊዎች ሲደመሩ ያማቸዋል። እነሱ ቀን እያዩ የሚገለባበጡ መድረክ የሚያጣብቡ አፈ ቅቤ ልበ ጩቤዎች አይደሉም። እነሱ የትምህርት ደረጃቸውን እየዘረዘሩ አይኮፈሱም፤ ባልዋሉበት መቀመጫ አይጠይቁም። እነሱ ዝና ፈላጊ አልያም በነፈሰው የሚነፍሱ አከርካሪ አልባ ሰንበሌጥ አይደሉም። እነሱ ሥልጣን አይፈልጉም፤ የሚሰራላቸውን እንጂ የሚገዛቸውን ግን በሥልጣን አያኖሩም። እነሱ አድፋጭም ጀብደኛም አይደሉም። 

እነሱ የዛሬዋ ‘ለማብያዊ’ ዘመን ዕውን ሆና ለማየትና ለመደመር ህይወታቸውን ሙሉ የፈጉ፤ የጠወለጉ ያላቸውን ሁሉ ለዘመናት የገበሩ ናቸው። እነሱ ሲወዱ ፍቅራቸውን ሲጠሉም መጠየፋቸውን መግለጫ የራሳቸው መለያ የሆነ መንገድ አላቸው። እነሱ በደምና በሰቆቃ በፀሎትና በዱዓ ያገኙትን መሪ አብይን ለመታደግ የተወረወረን ቦንብ በደረታቸው ለመመለስ በእጃቸውም ለመመከት ለሰከንድ ያላመነቱ የማያመነቱ ህይወታቸውን ለለውጡና ለመሪያቸው በመስመር ላይ ያቆሙና የሚያቆሙ እንጂ። 

ተገደው ሳይሆን ወደውና ተነሽጠው ዘብ የቆሙ እንጂ። አጎብድደው ሳይሆን የፍርሃት ቆፈንን በለውጥ ወላፈን አምክነው የተመሙ እንጂ። እልፍ ወአእላፍ ናቸው። ሚሊዮን ወሚሊዮናት። እነሱ እንደ መሪያቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። መነሻቸውም መድረሻቸውም ኢትዮጵያ! እነሱ የወል መጠሪያ አላቸው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ!እንዲህ ይላሉ ባደባባይ ሲናገሩ፤-

“27ቱ ዓመት የግፍ ነበር። አሁን ሶስት ወራችን ነው ከተወለድን። ይሄንን መንገድ (በእጃቸው እያሳዩ) አጎንብሼ እንዲህ ብዬ (እያጎነበሱ) አቀርቅሬ ከሰው በታች ሆኜ ነበር የምሄደው። አሁን ሰው ሆኛለሁ። ቀጥ ብዬ እሄዳለሁ። ይሄንን ነው ያመጣልን አብይ። ዕድሜውን ያርዝመው። ከክፉ ነገር ይጠብቀው።” ከአዛውንቱ ጀርባ አንድ ወጣት ልሙጡን (ምልክት አልባውን) የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ያውለበልብ ነበር። ሌላ አዛውንት ሠልፈኛ ከሌላ ወገን ደግሞ ይህን አሉ፤-

“ከዚህ በፊት የነበረው የዘረኝነት፤ የጎጠኝነት እኛን እየበታተነን የገዛንን ሥርዐት አውግዘን ዛሬ ዶ/ር አብይን ደግፈን የርሱን ሥርዐት የርሱን ራዕይ ለማሳካት ከጎኑ ለመቆም መጥተናል። ኢትዮጵያን ሠላም ያድርግ። ሠላምም ትሆናለች። ኢትዮጵያ ትደመራለች። መሪ ነበረች፤ መሪ ትሆናለች አሁንም።” በዙሪያቸው የተሰበሰበው ወጣት ወአረጋዊ በጭብጨባ ደገፋቸው። አንዲት እናት ሠልፈኛ ከሌላ የሠልፍ ትዕይንት መንደር ደግሞ ይህን ተናገረች፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ተለያይተን ቆይተናል። ተከፋፍለን ቆይተናል። አብይ አንድ ስላደረገን በጣም ደስታ ተሰምቶኝ እዚህ ከወገኖቻችን ጋር አንድ ላይ የኛን ድምፅ የኛን አንድነት ለማሰማት ነው።” በደቡብ ኢትዮጵያ የተመመውን ሠልፍ አዘጋጅ የሚመስል ሠልፈኛ ወጣት ደግሞ ቀጣዩን ተናገረ፤-

“በሶስት ወር ውስጥ ሰርተው የህዝብ ፍቅር በማግኘታቸው ምክንያት እኛም በያለንበት ድጋፋችንን ለማሳየት ነው። ከዚህ በሁዋላ ይበቃናል። ነፃነት እንፈልጋለን። ጫና ይበቃናል። ዘረፋ ይበቃናል። መገረፍ ይበቃናል። መገደል ይበቃናል ብለን ስሜታችንን ለመግለፅ ነው በዚህ ሠላማዊ ሠልፍ ላይ የተገኘነው። ሠላማዊ ሠልፉን ለማደናቀፍ ብዙ ጫና ያደረጉብን ሠዎች አሉ። ይህ ሠላማዊ ሠልፍ በግድ የተደረገ ነው።” ወጣቱን ሲሰሙት የነበሩ በዙሪያው ያሉ ሠልፈኞች ሁሉ በጭብጨባ አቀለጡት። ከልካዮቹ ወይም ጫናውን ፈጣሪዎቹ ጅቦቹ ወይም የጅቦቹ ሸሪኮች ይሆናሉ ብለን ጠርጥረናል፤ ከታዳሚዎቹ ደስታ አንፃር።

“ዶ/ር አብይ ማለት ለኛ የለውጥ አባት ነው። የለውጥ ሃዋርያ ነው። አብይ ማለት ለኛ ከምንም በላይ የምንወደው ሠው ነው። እኒህን የቀን ጅቦች ከእኛ ላይ አስወግዶ ሠላምን መልካም አስተዳደርን ዴሞክራሲን ያሰፈነልን ደግ መንግሥት በመሆኑ ልንደግፈው ነው በዋናነት ዛሬ ሠልፍ የወጣነው። (በዙሪያቸው ያሉት የጋለ ጭብጨባ ቸሩዋቸው) እስከዛሬ ድረስ 27 ዓመት ከኤርትራ ጋር ተነጣጥለን ስንኖር ዛሬ ይሄንን አንድነትና ሠላም ምንም ድንበር የለሽ እንደመር በማለት የሚያስተዳድረን መንግሥት ስላገኘን ከኤርትራም ጋር አንድ ሆነናል። ከእንግዲህ የሚለየን የለም” አሉ ንቃተ ህሊናቸው በእድሜና በተሞክሮ የዳበረ የሚመስሉ ሸበቶ ሠልፈኛ።

በአንድ አውራ ጎዳና ላይ ከሠልፈኞቹ መኻል ጡሩንባ የሚነፉ አዛውንት ደግሞ ጡሩንባቸውን ቱቱቱቱቱቱ…አድርገው “ጅቦች ተቀበሩ፤ ጅብ የበላችሁ ዳናችሁ” እያሉ ለመደመር ተጓዙ፤ አንድ አስገራሚ መልዕክት ደግሞ እንዲህ ይላል፤ ‘በፀሎት የመጣ በቦንብ አይሞትም!’ ለሁሉም ጊዜ አለው ማለት ይሄ ዘመን ይሆን እንዴ?

ሁለት፤ ‘አብይ መንፈስ’
እናቶች እንዲህ ይላሉ። “እሱ ከሰው ሳይሆን ከፈጣሪ የተሰጠን ነው። ቀንም ሆነ ማታ ቲቪ ላይ ሲታይ መጣ ይሉኝና አየዋለሁ። ልጆቼን ፎቶውን ስልኬ ላይ አድርጉልኝ ብዬ እመለከተው ነበር። ግን ሌባ ስልኬን ሰረቀብኝ። እንደ ልጄ እንደ ዘመድ ነው የምደሰትበት። በሀገር ደረጃ ያለው ለውጥ አስደስቶናል። ሆኖም ታች ወርዶ ነገሮችን ማስተካከል አለበት።” ሌላኛዋ እናት ደግሞ እንዲህ አሉ፤-

“ሴቶች የሚሉት በጣም ቆንጆ ነው። ሴቶች ብርታት እንዲኖራቸው ያደርጋል። የሥራው አገባብ በጣም ቆንጆ ነው። በተለይ በሙስናው ላይ በርታ በሉልኝ። እንደጀመረው ጨርስ በሉት። ደስ የሚለው ነገር መደመር ነው። ኢትዮጵያ አንድ ናት ብሎ መደመርን ማምጣቱ ደስ ይላል። ፈጣሪ ዕድሜውን ያርዝምለት ወደ አዘቅት እንዳያሰምጧቸው ፈጣሪ ከጠላት ይጠብቅልን።” ሌላኛዋ እናት በበኩላቸው ይህን ተናገሩ፤-

“ዶ/ር አብይ በጣም ደስ የሚል ጠ/ሚር፤ በሰው ልብ ውስጥ ያለውን የሚናገር፤ የሰውን ልጅ ችግር የሚረዳ፤ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ ወጣት መሆኑ። ከወጣቶች ጋር እየተጓዘ ነው። ለእናትና ለሀገር ያለው ክብር ደስ ይላል።” አንዲት ሌላ እናት ደግሞ ይህን አሉ፤- “እኔ በጣም ደስ አለኝ። ደስታውን አልችለውም። ይኸው (ደረታቸው ላይ ያለውን የአብይን ፎቶ በመዳፋቸው እየያዙ) በልቤ አስቀመጥኩት። አላህ ያቆይልኝ። አላህ ያሰንብትልኝ”

ሶስት፤- አብይ የፈጣሪ ስጦታ፤ ልጃችን፤ ወንድማችን፤ አባታችን፤ መሪያችን?
ጠ/ሚር አብይ አህመድ ለእናቶችና ለአባቶች በአንድ ድምፅ ልጃቸው ሆኗል። ያፈቅሩታል እንደ ልጆቻቸው። ይሳሱለታል፤ ይፀልዩለታል፤ መንገዱ ሁሉ ቀና እንዲሆንለት ምኞታቸው ነው። ከደንቃራ፤ ከክፉ ጠላት፤ ከሚያደባ ወዳጅ ፈጣሪ ይጠብቀው ዘንድ አጥብቀው ይፀልዩለታል። አብይን በሰው ችሮታ ብቻ ያገኙት ሳይሆን በፆም በፀሎት የተገኘ ከፈጣሪ የተመረጠም ነው ብለው ያምናሉ። 

የሰኔ 16ቱ የግድያ ሙከራም አብይን እንደ ስለት ልጅ ይበልጥ እንዲሳሱለትና እንዲጨነቁለት አድርጓቸዋል። አብይ ልጃቸው አብይ በረከታቸው አብይ መሪያቸው ሆኗል። ከእንግዲህ የአብራኮቻቸው ክፋይ ልጆቻቸው በህወሃት መራሹ አጋዚ ጥይት ይነደላሉ፤ በቀን ጅቦች ደህንነቶች ይታፈናሉ፤ በናዚስት መሰል የእስር ማከማቻና ማሰቃያዎች ታጉረው ይኮላሻሉ ይደፈራሉ ይተለተላሉ ብለው ስጋት አያድርባቸውም፤ ምክንያቱም አብይን የልጆቻቸው ጠባቂም ታላቅ ወንድማቸው ነው ብለው አምነዋልና። አብይ ወንጀለኞችንና ሌቦችን መፀየፍ ብቻ ሳይሆን የህግን የበላይነት ለማፅናትም በህግ ይቀጣቸዋል ብለው ያምናሉና። ምክንያቱም ሌቦቹ የዘረፉት የእነሱን ላብና ደም ጭምርም ነውና!

አብይ ለወጣቶች የሚያፈቅሩትና የሚያከብሩት አባት ወይም ታላቅ ወንድማቸው ሆኗል። አብይን እሳቸው ብሎ የሚጠራው ወጣት እጅግ ጥቂት ነው። አንተ ማለታቸው ግን ከአንቱም የገዘፈ አክብሮትንና ፍቅርን የተላበሰ የማቅረብና ከራስ ጋር የማዋሃድ ምልክት ነው። {ለአንቱታው ደግሞ ቦታ አለው፤ ባስፈላጊው ቦታ በአስፈላጊው ፕሮቶኮል አንቱ ሲሉት ተስተውሏልና} እንዲህ ያለ መታደልን ከትውልድ የሚያገኙ የተለየ የፍቅር ተሰጥዖ ያላቸው መሪዎች የተመረጡ ናቸው። 

አብይን በመሪነት በወንድምነት በአባትነት የሚከተሉት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍል ወጣቶች አይደሉም። ድፍን የኢትዮጵያ ወጣት የአብይ ተከታይ ነው ማለት ይቻላል። ለወጣቱ አብይ የነገ ተስፋቸውም ሆኗል። በአብይ አሻግረው ነገ ለራሳቸው ብሩህ ዘመን ይታያቸዋል። ከወታደር እስከ ዶክተር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚደረስ። ከእንግዲህ ስለተናገሩ፤ ስለተቃወሙ፤ መብት ስለጠየቁ፤ በቆመጥ የሚሰባበሩበት በቶርች የሚሽመደመዱበት በጨለማ ክፍሎች የሚጋዙበት ዘመን አብቅቷል ብለው ያምናሉ። 

ምክንያቱም አብይን አምነዋልና! ኢትዮጵያ ጥቂት ጡንቸኞችና ቃታ ተማማኞች ዘር ዘርዛሪዎችና ሀገር መዝባሪዎች ብቻ የሚያዙባት ሀገር ከእንግዲህ አትሆንም ብለው አምነዋል። ምክንያቱም አብይን መሪያችን ብለው ተቀብለውታልና። ምክንያቱም አብይ ከዘራፊዎችና ከገዳዮች ከዘረኞችና ሀገር አጥፊዎች ማህበር የማይደመርና የተለየ ነው ብለው ያምናሉና።

አብይ ፍትህና ርትዕ ያሰፍናል ብለውም ያምናሉና ሌቦችና ዘራፊዎች የመዘበሩትን የሀገርና የህዘብ ንብረት በመነጠል ወደ ሀገር ካዝና ያስመልሳል ብለው ያምናሉ። ምክንያቱም አብይ ለፍትህና ለህግ የቆመ ነውና። ገራፊዎችና በሰው ስቃይ ሲደሰቱ የኖሩ የሣትናዔል ምስሎች ከያሉበት ተለቃቅመው ከቦታቸው ይነሳሉ፤ በወንጀሎቻቸውም በህግ ፊት ይቀርባሉ ብለውም ያምናሉ። ምክንያቱም አብይ ህዝቡን ሲያሸብር የኖረው ራሱ ‘የኢህአዴግ መንግሥት’ ነው ብሎ ዛሬ በተደመረው ኢቲቪ በኩል ባደባባይ ተናግሯልና።

ድፍን ኢትዮጵያ አብይ የሠላም መልዕክተኛ ነው ብሎ ያምናል። ከኤርትራ ጋር የነበረውን የሃያ ዓመት ቁርሾ በአዚመኛው የሠላም መንፈሱ እንደ ጉም አትንኖ ሁለቱን የተለያዩ ግን አንድ የሆኑ ህዝቦች አገናኝቷልና። የዓመታት እንባና ሰቀቀንን በፈገግታና በሀሴት ቀይሮ አሳይቷልና። አሰብን በአስደናቂ ጥበብ ለኢትዮጵያ ግልጋሎት እንድትውል አድርጓልና። በእነ መለስ ዜናዊ የጥፋትና የበቀል ማነቆ ዙሪያው ገደል የሆነባትን ኢትዮጵያ ዙሪዋን የሠላምና የፍቅር ቄጤማ ነስንሶላታልና።

አብይ አስታረቂያችንም ነው ብለው ያምናሉ። እንዲህ አለ፤ “አንድም ሠው ሠላም እስካልሆነ ድረስ ሁላችንም ሠላም ልንሆን አንችልም። ስለዚህ ይቅር ተባብላችሁ ከማንም በላይ አንድነታችሁን ልታጠነክሩ ይገባል።” በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ጣልቃ የገባው የመለስ ሌጋሲ ሥርዐት የፈጠረውን ቀውስ ለማስታረቅ በቤተ መንግሥት ሁለቱን ወገኖች ጠርቶ ሲያወያይ የተናገረው ነው። 

በዚሁ አግባብና መንፈስም እንዲሁ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት በህወሃትና ህወሃታውያን ተንኮልና በቀል ለሁለት የተከፈለውን ሲኖዶስ ወደ አንድ ለማምጣት ያደረገው የሠላም ጥሪና ጥረት እነሆ ፍሬው ጎምርቷል። ቤተ ክርስቲያኗ ወደ ቀድሞዋ ሞገሷ የመመለሻ ዋዜማ ላይ ናትና። እና አብይ አህመድ የሠላምና የዕርቅ ሽማግሌያችን ነው ብሎ ያምናል ድፍን ኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያውያን አብይ የነገይቷን የበለፀገች ለዜጎቿ ሁሉ በእኩል የቆመች በምርጫ እንጂ በጠመንጃ ሥርዐት የማታምን፤ በህዝብ ይሁንታና ብልጫ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያስተዳድራት፤ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ፍትህም የሰፈነባት፤ የዜጎቿን ሁሉ ሰብዐዊ መብት ያከበረች እንጂ ያልጣሰች፤ በጎረቤቶቿ የተወደደች የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለማዋለድ የሽግግሩ ዘመንም መሪያችን ነው ብለው ያምናሉ። 

 አዎ በጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት ይህ ዕውን ይሆናል ብለን ኢትዮጵያውያን እናምናለን!! የየበኩላችንንም እንደየአቅማችንና ችሎታችን ለማገዝ ከልብና በቅንነት ከአብይና ከቲሙ ጋር ተደምረናል!! ጊዜው በመተጋገዝና በመተማመን ለውጡን ወደፊት የማራመድ እንጂ ንዑሳን አጀንዳዎችን እያንጠለጠሉ (ለምሳሌ አብይ በባውዛ እየፈለገ የሚሾማቸውን ባለሥልጣናት የዘር ግንድ በመምዝ) በዜናና በፖለቲካ ትንታኔ ሽፋን አብይንና ቲሙን ማብጠልጠሉ አንዳች ፋይዳ የሌለው ከመሆንም አልፎ ተጠቃሚዎቹ ጅቦቹና ተኩላዎቹ ብቻ ናቸው ብለን በፅኑ እናምናለንና! ሀላፊነት የተሞላው ተዓቅቦና ስክነትን የሚጠይቅ ጊዜ ላይ መሆናችንን ፀሀፍትና ፖለቲካ ‘ተንታኞች’ ሊረዱ ግድ ነው።

አብይ ሆይ፤ እንግዲህ ፅናቱንና ትዕግስቱን ማስተዋሉንና ጥበቡንም ፈጣሪ አምላክ ከዕድሜና ከጤና ጋር ባለህ ላይ ይጨምርልህ! እኛም ከጎንህ አለን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!
ሐምሌ 2010 ዓ/ም (ጁላይ 2018)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com


ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ (http://www.goolgule.com)

No comments