Latest

በገደሉን ቁጥር ሰልፍ ልንወጣ አንችልም! አይገባንም! መፍትሄም አይደለም! (ጌታቸው ሽፈራው)

ጌታቸው ሽፈራው

ድሮ ቢሮ ቁጭ ብለው የመንግስት ተቋማትን ኃላፊ ሆነው ሲገድሉ የነበሩት መካከል አንዳንዶቹ ከቢሮ ወጥተዋል። ድሮ የሚወቀሱት በተቋም ደረጃ ነበር። ዛሬ የሚወቀስ መስርያ ቤት የላቸውም። የለየላቸው ሽፍቶች ሆነዋል።  ሽፍትነት የሙሉ ጊዜ ስራቸው ሆኗል።

ድሮም ግዴለሽ ነበሩ። ከድሮ የባሰ ግን ተጠያቂነት ርቋቸዋል።  አሁን የለየለት ውንብድና መግባታቸው ብቻ አይደለም።  ድሮ ለመግደልም የሚያስወስኗቸው ነገሮች ነበሩ። ምን አልባትም የሚገጥሟቸው አንዳንድ መሰናክሎች ነበሩ። አሁን ውንብድናው ብሷል። በግንፍልተኝነት ተነስተው መገድል፣ መረበሽ ይችላሉ።

ሰልፍ ለእነሱ ምቹ ነው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርፈው ሰልፍ ለማስረበሽ፣ ሰልፍ ላይ ያልሆኑ መልዕክቶች እንዲተላለፍ የሚያደርጉ፣ የሕዝብ ተቋም የሚያቃጥሉ ለመግዛት ለእነሱ ቀላል ነው። በበጎ ፈቃደኝነት፣ በሀዘንና ስሜት ከሚወጣው ሰልፈኛ በላይ ተከፋይ፣ ሁሉንም ነገር አገናዝቦ የሚሰለፍ ሰው አላቸው።

ሰልፍን ወደ ትርምስ መቀየር ለእነሱ ስራ ነው። የሙሉ ቀን ስራ፣ በበጎ ፈቃደኝነት ሰልፍ መውጣት ለሕዝብ የሙሉ ጊዜ ስራ አይደለም! ሕዝብ ለሞተ አዝኖ በስሜት ሲወጣ እነሱ ተረጋግተው ትርምስ ስለመፍጠር ያስባሉ።

ወቅቱ ፈታኝ ነው። ምቹ ሁኔታ ከተሰጣቸው የምትታየውን ጭላንጭል ለማዳፈን፣ የሕዝብ ትግል ለማጠልሸት ወደ ኋላ አይሉም። ይህን መከላከል የሚችለው ሕዝብ ነው። ግርግር ለሌባ እንደሚመቸው ሁሉ፣ የወቅቱ ሰልፍም ለገዥዎች ሁከት መፍጠሪያ ምቹ ይሆንላቸዋል።

ገና ይገድላሉ፣ አሁን ስራቸው ግድያ ሆኗል። ከተቋማዊ ሽፍትነት ወደ ግል ሽፍትነት ገብተዋል። ተቋማዊ ውንበድና ከሚፈፅሙበት ጊዜ በባሰ ግድ የለሽ ሆነዋል።

 ሰው እየሞተም ለቅሶን፣ መልካም ነገር ቢፈጠርም ደስታን እምቅ የምናደርግበት ፈታኝ ጊዜ ላይ ነን። መከራ የበዛበትን ሕዝብ ለቅሶውን በቅጥ እንዲያደርግ መጠየቅ ፈታኝ ነው። ደስታ የራቀውን ሕዝብ ትንሽ መልካም ነገር ሲያገኝ "ደስታው በልክ ይሁን" ማለት ፈታኝ ነው።

ግን ከዚህ የባሰ ላለመጎዳት፣ ከዚህ የባሰ ለቀን ጅቦች ሰለባ ላለመሆን መጣር አለብን። ለጊዜው ለጅቦቹ የሚመቹ መድረኮችን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ተቋም ያጣ ሕዝብ፣  ተቋም ያልተገነባለት ሕዝብ፣ ድሃ ሕዝብ  በሀዘን ብዛት ንብረቱና ሕይወቱ ላይ አደጋ እንዳይደርስ መከላከል  አለበት። ለቀን ጅቦች የሚመቹ፣ የቀን ጅቦች የሚጠቀሙበትን ቀዳዳ ሁሉ መድፈን ያስፈጋል። ብዙ ሰልፍ ተደርጓል። ግድያ ግን በሰልፍ ብቻ ሊቆም አይችልም። ከሰልፍ በላይ ማሰብ አለብን።

ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ በኋላም መግደል ይቀጥላሉ። በገደሉ ቁጥር ሰልፍ እየወጣን አንዘልቀውም።  ግድያውን ለማቆም ማሰብ  ያስፈልጋል።

ግድያን በሰልፍ፣ ንብረት በማቃጠል ልናስቆመው አንችልም። የኢፈርትም ሆነ ሌላ ንብረት ከኢትዮጵያ የተዘረፈ እንጅ ከየትም የመጣ አይደለም። ዘራፊዎቹ ለሕዝብ መመለስ እንዳለባቸው መጠየቅ እንጅ ማቃጠል መፍትሄ አይሆንም። በተለይ በዚህ ፈታኝ ወቅት እነሱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፉትን ንብረት ሲቃጠልም ደስታቸው ነው። ለውጡ ወደ ሁከት አመራ ብለው መክሰሻ ያገኛሉ።

ንብረት ማቃጠልም ሆነ ሁከት መፍጠር የገዥዎቹ አላማ ነው። ለዚህ አላማ፣ ለጅቦቹ አላማ ተባባሪ መሆን የለብንም።

አሁን ፈታኝ ጊዜ ነው፣ በሀዘንም ቢሆን ተረጋግተን የምናስብበት ፈታኝ ጊዜ ነው!

No comments