Latest

ዛሬ ከአራት አመት በኋላ ~ መስቀሉ አየለ




የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል የሚለው አነጋገር ቀደም ባለው ዘመን የተለመደ ዘይቤ ነበር። ውርደትን አጎንብሶ እንደ ኒሻን ለተቀበለና ሃሞቱን ለሸና ሰው ሁነኛ ገላጭ ቢሆን ነው። ሙሴም ቢሆን "ሰውን በእዳ ብትይዘው ያለ ሰባት አመት አትግዛው። 

በዚህ ግዜ ውስጥ ግን እዳውን መመመለስ ከተሳነው ምን ባለ እዳ ቢሆን ሰው ክቡር የአምላክ ፍጥረት ነውና በነጻ ልቀቀው፤ ያም ሆኖ ሂድ ስትለው እምቢ ካለ ደግሞ እድሜ ልኩን ግዛው" ይላል። ሙሉ የሆነ ነጻ ፈቃድ ይዞ የተፈጠረ የሰው ልጅ ነጻነትን አቃሎ ባርነትን ገንዘብ ቢያደርግ በውርደት ኖሮ በውርደት እንዲሞት በራሱ ላይ ፈርዷል ለማለት ነው።

ባርነት ክፉ መርገምት ነው። ብትማር ባትማር፣ ንጉስ ብትሆን ገበሬ ብትሆን፣ የባርነት ስነ ልቦና ካለህ ባሪያ ነህ። ዙፋን ላይ ተቀምጦ በባርነት ስነ ልቦና ስለኖረ ሰው ምሳሌ ለመፈለግ በዚህ ዘመን ከኃይለማርያም ደሳለኝ የተሻለ ሰው ከገሃዱም ሆነ ከድርሰቱ አለም ለምልክት ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።

ሰውየው አንድ ቀን በንጉሱ ዙፋን ላይ መቀመጡን ሳያምን ድፍን አምስት አመት ሙሉ በትግርኛ እያሰበ ባማርኛ ሲሳደብ፣አብዮታዊ ዲሞክራሲና ወንጌል፣ ክርስቶስና መለስ ተጣርሰውበት ፣ የጌታውን "ራእይ" በሉት ቅዠት አንድ እርምጃ ሳያራምድ ኖሮ አውራ ጎዳና ተክሃይማኖት አካባቢ የጣለውን አሮጌ የካርታሜ በርሚል ያህል ላይን ሳይቆረቁር ከስሩ እንደበሰበሰ የደረቀ ቁልቋል ያለ ኮሽታ ወረደ።

ይኽ ሰው እንደ ጌታው በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ የዘለፋ ቃል ካስተላለፈባቸው ቀናት አንዱ ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ መያዝ የተናገረው አረፍተ ነገር የሚረሳ አልነበረም። "አንዳርጋቸው የኢሳያስ አፈወርቄ ትሮጃን ሆርስ ነው" ነበር ያለው። 

ዛሬ ዘመን ተገልብጦ ኃይለ ማርያም ከቤተመንግስት ወርዶ በመናኛ ሰው ደረጃ አንዳርጋቸው ጽጌ ደግሞ ከምድር ውስጥ ገሃነም ወጥቶ ነገር ግን ከፍ ባላ ግርማ ሁለቱም አስመራ ላይ በተመሳሳይ ሰዓት የደረሱበትን ኩነት ከገሃዱ ዓለም ቀርቶ እንደ ልቦለድ ማሰብ አይቻልም።

No comments