Latest

ከዲያስፖራው ትረስት ፈንድ ጋር የጥምር ዜግነት (Dual Citizenship) ጉዳይ ቢታሰብበት (ዶ/ር ዘካሪያ ሙላቱ)


ለረጂም ጊዜ በተለያዩ አካላት ሲወራ የነበረው የኢትዮጵያዉያን አለም አቀፍ የመረዳጃ ፋዉንዴሽን፣ በቅርቡ አቶ ግርማ ካሳ በተባሉ ፀሃፊ እንደገና ከተወሳ በሁዋላ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ሲናገሩት በመስማቴ ደስ ብሎኝ ነበር።

በትናንትናው እለትም ይሄን ሀሳብ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለማሸጋገር የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የተባለ የባንክ አካዉንት መከፈቱን የጠቅላይ ሚኒስተሩ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። ይሄ ሀሳብ ሊበረታታ የሚገባው ሲሆን፣ በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ለሀገራቸዉ ግንባታ ከመሳተፍ ወደ ሁዋላ እንደማይሉ ጥርጥር የለኝም።

ይሁን እንጂ ከዚህ ሀሳብ ጋር ተያይዘው ሊነሱ የሚገባቸዉ አንዳንድ አስፈላጊ ጉዳዮች አሉ። በእኔ አመለካከት ከነዚህ ጉዳዮች አንደኛው የጥምር ዜግነት (Dual Citizenship) መብት ነው። በአጭሩ ለማብራራት ጥምር ዜግነት ማለት አንድ ሰው የሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሀገሮች ዜጋ የመሆን መብት ነዉ። ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት በነበረው የኢትዮጵያ አገዛዝ ጥምር ዜግነት ተከልክሎ የቆየ ሲሆን፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በተሰደደበት ሀገር ዜጋ የመሆን አጋጣሚ ካገኘ፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርቱን እንዲመልስ፣ እንዲሁም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መብቶቹን አንዲያጣ ይገደድ ነበር።

የጥምር ዜግነት ጉዳይ ብዙ ሀገሮችን የሚመለከት እና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ሀሳብ ነው። በተለይ እኛ የምንኖርባት አሜሪካ የብዙ ስደተኞች ሀገር እንደመሆኗ መጠን ጥምር ዜግነት የብዙ ሀገራት ዜጎችን ይመለከታል። በአሜሪካ ህግ መሰረት ጥምር ዜግነት አይከለከልም። ይህም ማለት ማንኛዉም ሰው የትዉልድ ሀገሩን ዜግነት እንደያዘ አሜሪካዊ መሆን ይችላል። በአሜሪካዊነቱም ሁሉም የዜግነት መብቶቹ (መምረጥ መመረጥን ጨምሮ) ይከበሩለታል።

ብዙ ሀገራትም ጥምር ዜጎች፣ በተለይም ለትዉልድ ሀገራቸው፣ ሊያበረክቱት የሚችሉትን አስተዋጽኦ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ይህንኑ ይፈቅዳሉ። የአለማችን ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሀገራትን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ ከአለም ሀገራት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጥምር ዜግነት መብትን ይፈቅዳሉ። ከነዚህም መካከል ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል እንዲሁም ሜክሲኮ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በቁጥር ብዛት ከፍተኛ ስደተኞችን ወደ አሜሪካ ከሚልኩ 20 ትላልቅ ሀገራት ዉስጥ 18ቱ ማለትም 90% የሚሆኑት ጥምር ዜግነትን ይፈቅዳሉ።

ለዚህ ከፍተኛ የሆነ የጥምር ዜግነት ተቀባይነት ዋናው ምክንያት ደግሞ በተለይ ታዳጊ ሀገራት የዉጭ ሀገር ዜግነት የያዙ ዜጎቻቸዉን እንደ ሀገር የካዱ ባይተዋሮች ከማየት ይልቅ እንደ ሩቅ ያሉ ሀብቶች ለማየት በመወሰናቸው ነው። አፍሪካ ዉስጥ ብንመለከት እንኵዋ ግብጽ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጀሪያን ጨምሮ ብዙ ሀገራት ይህንን አስተያየት ተቀብለዉ ጥምር ዜግነትን ይፈቅዳሉ።

እርግጥ ነው፣ የዲሞክራሲ ባህልን ባዳበረ ሀገር ዉስጥ የሚኖርን፣ ጥሩ የገቢ ምንጭ ኖሮት የሚፈልገዉን የፖለቲካ ፓርቲ መደገፍ የሚችል እና ከባድ ጥያቄወችን ሊጠይቅ የሚችልን ዲያስፖራ፣ የኢትዮጵያ ዜግነት ፈቅዶ በዲሞክራሲ ስርአት ዉስጥ ማሳተፍ ለኢህአዴግ ሲያስፈራው የኖረ ጉዳይ ነው።

ይሁን እንጂ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር እያስተላለፉት ካለው መልእክት እና ጥሪ አንጻር በዉጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም ሀገሪቱ ወደ እዉነተኛ ዲሞክራሲ በምታደርገዉ ጉዞ ዉስጥ ሊጠቃለሉ ይገባል። በተለይም የዲያስፖራው ነዋሪዎች በሀገራቸው ግንባታ በሀሳብ እና በገንዘብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በተጠየቁበት ጊዜ፣ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው የጥምር ዜግነት ጉዳይ ፊት እና መሀል መቀመጥ አለበት።

ሀገራት ጥምር ዜግነትን ሲፈቅዱ ያለምክንያት አይደለም። በተለይም ዲሞክራሲያዊ ለሆኑ ሀገራት ጥምር ዜግነት ብዙ ጥቅም ያስገኛል። በዉጭ የሚኖሩ ዜጎች የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸዉ በሀገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ እና እንዲያግዙ ማበረታታቱ የመጀመሪያው ጥቅም ነው። በተጨማሪም የታክስ ስርአቱን በማስተካከል በዉጭ ያሉ ዜጎች ለሀገራቸው ግንባታ በቀጥታ እንዲሳተፉ ማድረግ ይቻላል።

ከዚሁም ጋር በተያያዘ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገራቸው ወጥተዉ ጥሩ የሆነ የትምህርት እና የስራ እድል ያጋጠማቸው ኢትዮጵያዉያን፣ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ህዝብን ለማገልገል እንዲችሉ፣ በዲሞክራሲው የመምረጥ መመረጥ ስርአት ዉስጥ በመሳተፍም የኖሩበትን የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል ወደ ሀገራቸው ይዘው እንዲመለሱ መንገዱን ያመቻቻል።

ከነዚህ ምክንያቶች በመነሳት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ በአሜሪካ በሚያደርጉት ጉዞ ወቅት የጥምር ዜግነት ጉዳይ እንደሚነሳ እና፣ ከዲያስፖራው ትረስት ፈንድ ጋር ተያይዞ በሚደረገው ዉይይትም እንደ አንድ ነጥብ ሆኖ እንደሚቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ።

ዶ/ር ዘካሪያ ሙላቱ (drzekaria@gmail.com)

No comments