Latest

የቦንብ ጥቃቱ ዓላማ ምን ነበር? ጠ/ሚኒስትሩን መግደል ወይስ ሕዝብን በጅምላ መፍጀት? ከስዩም ተሾመ




“ዳኛ የሚያየው ‘Law, Intention and Action’ ነው” ይለኝ ነበር ታዬ ደንደኣ። በእርግጥ ከታዬ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ መታሰር ትምህርት ቤት እንደመግባት ነው፡፡ እናም ከእሱ ጋር ማዕከላዊ እስር ቤት በነበረኝ ቆይታ ከተማርኳቸው ነገሮች ውስጥ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ ፍርድ የሚሰጠው የተላለፈው ሕግ፣ ወንጀሉን የፈፀመበት ዓለማ እና በወንጀል ድርጊቱ በነበረው ተሳትፎ መሆኑን ነው። ከዚህ አንፃር የኮ/ል ቢኒያም ተወልደ ክስ እንዴት መታየት እንዳለበት የተወሰነ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ።

በእርግጥ ግለሰቡ በመስቀል አደባባይ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥሮ መታሰሩ ይታወቃል። ሆኖም ግን፣ በዚህ የወንጀል ተግባር የነበረው ሚና ገና በምርመራ ሂደት ላይ ነው። ስለዚህ ጉዳዩ በምርመራ እስከሚጣራ ድረስ ስለፈፀመው የወንጀል ድርጊት (Action) እና ስለሚከሰስበት የህግ አንቀፅ (Law) በግልፅ መናገር ያስቸግራል። ሆኖም ግን፣ ይህን የወንጀል ተግባር ከማቀድ ጀምሮ በቦንብ ፍንዳታው ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ሃሳብና ፍላጎት (Intention) ምን እንደነበረ መገመት ይቻላል።

በመስቀል አደባባይ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ ተከትሎ የብዙዎቻችን ግምት የነበረው ጥቃቱ በጠ/ሚ አብይ አህመድ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራ እንደሆነ ነው። ነገር ግን፣ ዶ/ር አብይ እና አቶ ጌታቸው አሰፋ አብረው በተቀመጡበት መድረክ ላይ እነ ኮ/ል ቢኒያም ጠ/ሚኒስትሩን በቦንብ ለመግደል ይሞክራሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ለዶ/ር አብይ የተወረወረ ቦንብ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ እና አቶ ጌታቸው አሰፋን ባይገድል ሊያቆስል ይችላል። ኮ/ል ቢኒያም ዶ/ር አርከበ ላይ ቢጨክኑ እንኳን በነፍስ አባታቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ የሚጨክኑ አይመስልኝም።

የቦንብ ጥቃቱ ዶ/ር አብይን ለመግደል ካልሆነ ለምን ተፈፀመ ታዲያ? ጥቃቱ የተፈፀመው ጠ/ሚኒስትሩን ወይም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን ለመግደል ሳይሆን በቦታው የተገኘውን ሕዝብ ለመፍጀት ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ላይ የእጅ ቦንብ የመወርወሩ ፋይዳ ሰው በድንጋቴ ራሱን ለማዳን ሲሯሯጥ እርስ-በእርስ ተፋፍኖና ተጨፈላልቆ እንዲሞት ለማድረግ ነው። በዚህ መልኩ የሚሞተው የሰው ብዛት በቦንብ ከሚገደለው በብዙ እጥፍ ይበልጣል።

ስለዚህ የቦንብ ጥቃቱ አላማ ጠ/ሚኒስትሩን በቀጥታ ከመግደል ይልቅ ሕዝቡ በድንጋጤ እርስ-በእርስ ሲገፋፈፋ በሚፈጠረው የሰው ናዳ በብዙዎች ላይ የሞትና አካል ጉዳት አደጋ ለማድረስ ታቅዶ ነው። እርግጥ ነው በጥቃቱ ምክንያት የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ ወደ ከ160 በላይ ቆስለዋል። ሆኖም ግን፣ ጥቃቱ በታቀደው መሰረት በከናወን ኖሮ በመቶዎች ምንአልባትም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞትና አካል ጉዳት ሊዳረጉ ይችል ነበር።

ይህ አሰቃቂ ክስተት እንዳይፈጠር ያደረገው ብቸኛ ነገር የመድረክ መሪው ግሩም ጫላ ንግግር እና ቦንቡ የፈነዳበት ቅፅበት መገጣጠም ነው። መድረክ መሪው ጠ/ሚኒስትሩ ዝግጅቱን አጠናቅቀው ከመሄዳቸው በፊት አንድ ዝግጅት እንደቀረ ከተናገረ በኋላ ልክ “ይህ ኢትዮጵያዊያን የሚኮሩበት ቀን ነው!” እንዳለ ቦንቡ ፈነዳ።

በዚህ ግዜ አብዛኛው ሰው ያሰበው ርቺት የተተኮሰ እንጂ ቦንብ የፈነዳ አልመሰለውም። ሌላው ቀርቶ ቦንቡ ከፈነዳበት 57 ሜትር ርቀት ላይ ሆኜ ለእኔ ራሱ ርችት መስሎኝ ነበር። ቆሜ ስመለከት ነው ቦንብ መሆኑን የተረዳሁት። ከመድረኩ ራቅ ብሎ የሚገኘው ሕዝብ በሙሉ ርችት መስሎታል።

የቦንብ ፍንዳታ እንደሆነ የተመለከቱት ግን በምን አይነት አሰቃቂ ሆኔታ ላይ እንደነበሩ ተመልክቼያለሁ። ወደ ግዮን ሆቴል ከገባሁ በኋላ ሰዎች በድንጋጤ ከገደል ላይ እየዘለሉ ወንዝ ውስጥ ሲወድቁ፣ ድንጋይ ላይ ሲፈጠፈጡ፣ በውሃና ጭቃ ተጨማልቀው ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሮጡ ተመልክቼያለሁ። 

ይህ እንግዲህ የቦንብ ፍንዳታ መድረሱን ያወቁት ናቸው። እነዚህ መስቀል አደባባይ ከወጣው ህዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይ እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። ያ ሁሉ ሕዝብ በተመሳሳይ መልኩ በድንጋጤ መሮጥና መሸሽ ቢጀምር የስንት ሰዎች ሕይወት እንደሚቀጠፍ፣ ስንቶች አካል ጉዳት እንደሚደርስባቸው ሳስብ በጣም ይሰቀጥጠኛል።

ከዚህ አንፃር ጥቃት የፈፀሙት ወገኖች ዓላማቸው ጠ/ሚኒስትሩን እና ጥቂት ሰዎችን ለመግደልና ለማቁሰል ሳይሆን መስቀል አደባባይ የወጣውን ሕዝብ በጅምላ ለመፍጀት ነበር። በቦንብ ፍንዳታው የደረሰው ጉዳት ሊደርስ ይችል ከነበረው አንፃር ሲታይ በጣም ትንሽ ሊባል የሚችል ነው። የእነ ኮ/ል ቢንያም እቅድ የሁለት ንፁሃን ዜጎችን ሕይወት መቅጠፍ ሳይሆን በመቶና ሺህ የሚቆጠሩ ንፁሃንን ለመግደልና ለማቁሰል ነው።
 

ስለዚህ የቦንብ ጥቃቱን ሃሳብና ፍላጎት (Intention) ፍፁም ሰይጣናዊ የሆነ እርኩስ መንፈስ ነው። ይህን እንኳን ለሀገር ልጅ ለጠላትም የማይታሰብ እኩይ ተግባር ነው። ፍርድ ሂደቱም ይህን እኩይ ዓላማና ፍላጎት ከግንዛቤ ያስገባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

No comments