ሥልጣን ፍቅር እውቀት - በሌሊሳ ግርማ
ይሄንን ፅሁፍ ልፅፍ ሐሳቤን እየሰበሰብኩ ሳለሁ፣ አንድ ተስፋ የሚስቆርጥ / አሳዛኝ ዜና ሰማሁኝ፡፡ ፅሁፉን ትቼ በሰማሁት ዜና አቅጣጫ መጓዝ ነበረብኝ፡፡ ግን ተቆጣጠርኩት፡፡ ፅሁፉን ፅፌ ስጨርስ ወደ አሳዛኙ፣ ዜና እመለሳለሁኝ፡፡ ፈፅሞ ከቁጥጥር ውጭ የሚያወጣኝ አይነት ባይሆን ነው የተቆጣጠርኩት፡፡ አሁን ወደ ቅድመ ሃሳቤ ልመለስ፡፡
ልትቆጣጠረው ትችላለህ ወይ? ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ልብ በሉልኝ፤ ይኼ ጥያቄ ከዚህ ቀደም “ዋና” ካልኳቸውም በላይ ነው፡፡ ሀይል አለህ? ሃይለኛ ከመሆን በበለጠ ልትቆጣጠረው መቻልህ ነው የሃይልህ ምንጭ፡፡ ሃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ትችላለህ፡፡ ያመነጨኸውን ሃይል ልትቆጣጠረው ካልቻልክ ምን ዋጋ አለው?... እቺ በየቤቱ ግድግዳ ላይ ያለች የመብራት ማብሪያና ማጥፊያ ጉጥ፣ መቆጣጠሪያ ናት፡፡ ኮረንቲ ወደ አንፖሉ እንዲፈስ ወይንም እንዳይደርስ መከላከልት ችላለች፡፡ ግን የመብራት እስዊቿን ምርጫ የሚያደርገው የሚያበራና የሚያጠፋ ሰው ነው፡፡
መቆጣጠር አለመቻል ነው ቀውስ፡፡ እብድ ራሱን መቆጣጠር አለመቻሉ ነው ...የእብደቱ ምክኒያት፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ ሰውነታችንን ማስተማርና መቆጣጠርን ነው በአንድ ላይ የምንለማመደው፡፡ በመቆጣጠር ውስጥ ምርጫ ማድረግንም ያካትታል፡፡ መብራቱን ለማብራትና ላለማብራት መወሰን የሚችል ሰው ነው፤ መቆጣጠሪያውን የሚጠቀመው፡፡ እውቀት አለህ? እውቀት ጥሩ ነው፡፡ ልትቆጣጠረው ካልቻልክ ግን ዋጋ የለውም፡፡ እምነት አለህ? የምታምንበትን ነገር ማግኘት ሸጋ ነው፡፡ ግን ልትቆጣጠረው ትችላለህ? ወይንስ እምነትህ ይቆጣጠርሃል? እምነትህ ላይ ስልጣን አለህ ወይንስ እምነትህ ባንተ ላይ ሰልጣን አለው? ወይንስ እምነትህ ሌሎችን የመቆጣጠሪያ ስልጣን ይሰጥሀል?
ማንም ግለሰብ የራሱን ምርጫ የማድረግ ምርጫ አለው። ይኼ ፈፅሞ አይካድም፡፡ ግን የግለሰቡ ውሳኔ በመንግስት ውሳኔና ምርጫ ስር ነው፡፡ ግለሰብ ራሴን መቆጣጠር እችላለሁ ቢልም፤ መንግስት ግን ይቆጣጠረዋል፡፡ ግለሰቡ ተቆጣጣሪውን “ይመራኛል” ወይንም “ይነዳኛል” ብሎ የመውደድ ወይንም የመጥላት ምርጫ አለው፡፡ በምርጫው ተጠቅሞ፣ ነጂን በነጂ ወይንም ነጂን በመሪ ይለውጣል፡፡ ስለዚህ የመቆጣጠሪያው ቅደም ተከተል፣ ከላይ ወደ ታች ብቻ ሳይሆን ከታች ወደ ላይም ሊሰራ ይችላል፡፡
እስፒኖዛ እንደኔ እምነት፤ ራሱን መቆጣጠር የሚችል ፈላስፋ ነው፡፡ ምክኒያታዊ አማኝ ነው፡፡ ሁለቱንም ግን በጥሩ ልጓም ተቆጣጥሯቸዋል፡፡ እንደ እስፒኖዛ ፈጣሪ ማለት፦ ሁሉን የሚቆጣጠር ግን የሚቆጣጠረው ነገር መልሶ የማይቆጣጠረው ማለት ነው ይላል፡፡ ሁሉንም የሚገዛ፣ በማንም ግፊት ግን የማይገዛ ማንነት ካለ… የፈጣሪ ነው፡፡
“That he has supreme right and dominion over all things, and that he does nothing under compulsion, but by his absolute fiat and grace. All things are bound to obey him, he is not bound to obey any.” ( Defenition of faith )
“That he has supreme right and dominion over all things, and that he does nothing under compulsion, but by his absolute fiat and grace. All things are bound to obey him, he is not bound to obey any.” ( Defenition of faith )
እኛ ግን ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ መቆጣጠር የምንችለውንና የማንችለውን መጠየቅ አለብን፡፡
ቁጣህን መቆጣጠር ትችላለህ? ... ደስታህንስ? ድንገት “ተቅማጥ” ቢያጣድፍህ ቤትህ ደርሰህ ሱሪህን እስክትፈታ ያህል በሰውነትህ ውስጥ የተቀሰቀሰውን አመፅ ተቆጣጥረህ ማቆየት ትችላለህ? ራስህን መግዛት ትችላለህ? ከማን ነው ግን የምትገዛው? ከተፈጥሮ?
ቁጣህን መቆጣጠር ትችላለህ? ... ደስታህንስ? ድንገት “ተቅማጥ” ቢያጣድፍህ ቤትህ ደርሰህ ሱሪህን እስክትፈታ ያህል በሰውነትህ ውስጥ የተቀሰቀሰውን አመፅ ተቆጣጥረህ ማቆየት ትችላለህ? ራስህን መግዛት ትችላለህ? ከማን ነው ግን የምትገዛው? ከተፈጥሮ?
የሰውነት አካላችን የጂኖቻችን ስጋዊ መገለጫ ( Phenotype ) ነው ይላሉ፡፡ ጂኖቻችን አካሎቻችንን ይሰራሉ፡፡ ከአካልም መሃል እንደ አእምሮና የነርቭ መዋቅርን የመሰለ ልዩ የአካል ክፍል የተቀረውን ሰውነታችንን ከላይ ሆኖ እንዲቆጣጠር ያደርጋሉ፡፡ ግን ቅድም እንደ ገለፅኩት “የፈጣሪ ፅንሰ ሃሳብ” ጂኖች (ሁሉን የሚቆጣጠሩ ማንም ግን የማይቆጣጠራቸው) ማለት አይደሉም፡፡ ጂኖች በአካል ግዛት ላይ ሰው በምድር ላይ ያለውን የተቆጣጣሪነት ስልጣን ነው ያላቸው፡፡ በአካል ግዛት ላይ ሆነውም፣ አንድ ያደረጋቸውን አካል ለመጥቀም አይደለም የሚተባበሩት፡፡ እንዲያውም አንድ ላይ የተሰባሰቡበትን አካል (ዓለም) ተጠቅመው፣ የየራሳቸውን የተናጠል ፍላጎት፣ በግለኝነት ለማሳካት የሚሞክሩ ናቸው፡፡
እርስ በራሳቸው ይፎካከራሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ይቆጣጠራል፤ ያፍናል ይጨቁናልም፡፡ አካል ደግሞ፤ በሚኖርበት የምድር ኢንቫይሮመንት የሚያሳልፈው ተሞክሮ፣ የጂኖቹን እጣፋንታ በእጅ አዙር ይወስናል፡፡ ግንኙነታቸው፤ በግለሰብና በማህበረሰብ መሃል ያለውን ወይንም በግለሰብና በመንግስት መሃል ያለውን ይመስላል፡፡ እርስ በራሳቸው አንዱ በሌላው ላይ ቁጥጥር የደርጋል፡፡ ውስብስብ ሆነው ከላይ ወደታች እና ከታች ወደ ላይ በቁጥጥር እና ምርጫ መዋቅር ተቆጣጥረዋል፡፡
የእኛን ጂን እና የኛን አካል ለጊዜው እንተወው፡፡ እንደው ለመሆኑ አምላካዊ ነፍስ ወደ ሰው አካል ቢገባ፣ ቁጥጥሩ የተሳካ ይሆናል ወይ?...
ለዚህ ጥሩ መመሰያ ሊሆን የሚችለው እየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ለእኔ፡፡ ብዙ ሰው እኔን ጨምሮ የአምላክን ማንነት ከስልጣንና ፈራጅነት ጋር እናያይዘዋለን፡፡ አባታዊ ባህሪ እናላብሰዋለን፡፡ ወደ ክርስቶስ ስንመጣ ስሱነትን፣አዛኝነትን፣ ህፃናትን ጉልበቱ ላይ አስቀምጦ የሚያጫውት ማንነትን ነው የምናገኘው፡፡ ባህሪዎቹ ከስልጣን (ያውም ከሙሉኤ ኩሉው ስልጣን) የመነጨ መሆኑ ያጠራጥረናል፡፡ ክርስቶስ ይሄንን ያህል ስልጣኑን በሰው ግዛት እብሪተኛ አካል ውስጥ አስማምቶ፣ በሰላም በምድር ላይ ያቆየበትን መንገድ “ፍቅር” በሚባል ስያሜ ይጠራዋል፡፡
ፍቅር ማለት በመሰረቱ የሁለት ነገሮች መገናኘትና መስማማት ነው፡፡ የሁለት ተቃራኒ ነገሮች - የትልቅ እና ትንሽ፣ የበዳይ እና ተበዳይ፣ የወንድ እና የሴት፣ የፈጣሪ እና የሰው መገናኘት እና ርቀታቸውን አቀራርቦ ማስማማት ነው ትርጉሙ፡፡ (ለኔ፡፡)
ፍቅር ማለት በመሰረቱ የሁለት ነገሮች መገናኘትና መስማማት ነው፡፡ የሁለት ተቃራኒ ነገሮች - የትልቅ እና ትንሽ፣ የበዳይ እና ተበዳይ፣ የወንድ እና የሴት፣ የፈጣሪ እና የሰው መገናኘት እና ርቀታቸውን አቀራርቦ ማስማማት ነው ትርጉሙ፡፡ (ለኔ፡፡)
ይኼ ትርጉሙ ሆኖ እያለም፤ “መቆጣጠር” የሚለው ነገር፤ እዚህ ውስጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ፈጣሪ፤ የፈጣሪነት ባህሪውን መጥኖ ነው በሰው አካል መልክ፣ ወደ ምድር የመጣው፡፡ የክርስቶስ ለስላሳነት፤ ሃይል እና ስልጣኑን እንዴት በብቃት መቆጣጠር እንደቻለ ነው ለእኔ የሚያስገነዝበኝ። በምድራዊ/ ስጋዊ/ ሰዋዊ እይታ ከመዘንነው፤ አምላክ ወደ ምድር ይዞ የመጣው፤ ግራ ጉንጩን ሲመታ፣ ቀኙን የሚሰጥ ምስኪን ባህሪን ነው፡፡ ምስኪንነቱ ከደካማነት የመጣ ከመሰለን፣ ከፈጣሪ ጋር መገናኛ መሰላሉ አልገባንም ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ በምድር ያሳየው ባህሪው “ strength under control ” ተብሎ የሚጠራውን አይነት ነው፡፡ ጥንካሬው (strength )… ሰውነቱን ከወደቀበት ትቢያ ወደ አምላክነቱ እንዲጠጋ ማድረጉ ነው፡፡ መቆጣጠር ያስፈለገው ( control ) አምላክነቱ ወደ ሰውነት አቧራ እንዳይወርድ በመግዛት ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ሊቀራረቡ የማይችሉ ሁለት የማንነት/ ምንነት ጥጎችን ( Zenith& Nadir ) ወደ አንድ አመጣቸው። ይኼ ነጥብም “ፍቅር” ተብሎ ይጠራል፡፡ ክርስቶስ ማንም የምድር አካልን የተሸከመ ሰው፤ ሊቀበል የማይችለውን መከራ በቁሙ ተቀብሏል፡፡ ሲቀበል ደግሞ ትዕግስቱ ሳያልቅ፣ ሳይበሳጭ፣ ጣቱን በሌሎች ላይ ሳይቀስር ነው፡፡ ድምፁ በፍርሃት ሳይንቀጠቀጥ፡፡ አምላኩን ሳይራገም፡፡ የሰው ልጆች ላይ ጥርሱን ሳይነክስ ነው፡፡ ሰውን አምላክ ማድረግ ማለት፣ ስልጣንን መቆጣጠር ማለት ነው፡፡ የሰውነቱንም ሆነ የአምላክነቱን ስልጣን፡፡ ስለዚህ፤ በዛሬው ቀን የመጣልኝ መልዕክት - “Control” የሚል ነው፡፡
ስልጣንህን መቆጣጠር ትችላለህ? መቆጣጠር ማለት… ስልጣን ለሌላቸው ስልጣንን ማካፈል ሊሆን ይችላል፡፡ ደካሞቹን ከአደጋ መጠበቅ፡፡ እውቀት አለህ?... እውቀትህን ከራስወዳድ ፍላጎትህ ባሻገር ለጥሩ እንዲውል ማድረግ ትችላለህ? ፍርሃት አለብህ? የሚያስፈራህን ነገር በመረዳት/ በማፍቀር መቆጣጠር ትችላለህ? ህልም አለህ? ህልምህን ሁሉ ግብ ከማድረግ ራስህን መቆጣጠር ትችላለህ? እውነት አለህ? በእውነትህ የሌላውን እምነት ከመንጠቅ ራስህን መቆጠብ ትችላለህ?... ዐይን አለህ? “…ዓይን የተፈጠረው ሁሉን ለማየት ነው…” ብለህ፣ በዐይንህ የገባውን ጉድፍ ሁሉ፣ ለሃሳብህ ፈተና ከማድረግ ራስህን መቆጣጠር ትችላለህ? ወይንስ ራስህን መቆጣጠር አትችልም እንጂ ሌሎቹን መቆጣጠር ትፈልጋለህ? ድምፅ አለህ? ድምፅህን ዘፍነህም ሆነ ጮኸህ፣ ህዝብን የገደል ማሚቶህ ከማድረግ ራስህን መግዛት ትችላለህ?
እሺ በመጨረሻ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤ ፍቅር አለህ?... ፍቅር ካለህ መቆጣጠር አያስፈልግም፡፡ የራስ ፍቅር አይሁን እንጂ ፈፅሞ መቆጣጠር አያስፈልግም፡፡ ምክኒያቱም፤ የፍቅር ትርጉም፤ ሐዋሪያው ጳውሎስ እንዳለው ነው፦
“በሰዎች እና በመላእክት ልሳን ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ናስ ወይንም እንደሚንሿሿ ፀናፅል ሆኛለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ሚስጥርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፤ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነትም ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፡፡ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፡፡ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ አመፃ ደስ አይለውም፡፡ ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይፀናል፡፡”
“በሰዎች እና በመላእክት ልሳን ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ናስ ወይንም እንደሚንሿሿ ፀናፅል ሆኛለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ሚስጥርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፤ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነትም ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፡፡ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፡፡ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ አመፃ ደስ አይለውም፡፡ ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይፀናል፡፡”
ፍቅር ካለህ መቆጣጠር አያስፈልግም፡፡ ፍቅር ካለህ ሁሉም ነገር ተከትሎ ይመጣል፡፡ የተዛነፈው ሁሉ ተመልሶ መስመር ይይዛል፡፡ ከሚቆጣጠርህ ግን ከማትቆጣጠረው … የእውነትና የፍቅር ዋናው ምንጭ ጋር ያገናኝሃል፡፡ መስዋዕትነት ያስከፍላል፡፡ ፍቅር መስዋዕትነት ያስከፍላል። በፈጣሪ መስመር ገብቶ፣ ሰውነትን ከፈጣሪ ጋር በፍቅር ውስጥ ሆኖ ለመቀጠል፣ መስዋአትነት መክፈል ያስፈልጋል። ፈተናው ይሄ ነው፡፡
ሕይወት፤ ሰውነታችንን የማስተማሪያና ፈተናን የመፈተኛ ስፍራ ነው፡፡ መራመድን የመልመጃ፣ የመንገዳገጃ ቦታ ነው፡፡ መራመድ የምንለምደው በየብስ ላይ አይደለም። ወደ ፈጣሪ ነው፤ በፍቅር መንገድ ላይ፡፡ ፈተና አለው፡፡ እንንገዳገዳለን። መንገዱን ካገኘነው፣ እርምጃውን ከቻልነው በኋላ መስዋዕትነቱ ይመጣል፡፡ ሰውን ወደ አምላክ፣አምላክን ወደ ሰው ለማምጣት መስዋዕትነት የመገናኛው መንገድ ነው።
ፍሬድሪክ ዳግላስ፤ “ያለ ትግል መሻሻል የለም ” ቢልም፣ እኔ ግን ያለመስዋዕትነት ነፃነት የለም ነው የምለው፡፡ ነፃነት የሚለውን ቃል፤ ከዚህ በፊት በብዙ የተጣመሙ የትርጉም ፍቺዎች ሲያገለግል የቆየ ነው፡፡ የነፃነት እውነተኛ ትርጉም ግን ፦ ከሰው ግዛት በትክክለኛው የፍቅር ትግል አርነት ወጥቶ፣ ወደ አምላክ ግዛት መግባት ማለት ነው - ትርጉሙ፡፡
No comments