ጃንሆይ በአሜሪካ! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)
64 አመታት አለፉ። ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት፤ እንደኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር በ1946 ዓ.ም ነበር። ከ64 ዓመታት በኋላ 7ኛው ንጉሥ ዶ/ር አብይ አህመድ በአሜሪካ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው። ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም… 64 አመታት ወደኋላ ተመልሰን ስለጃንሆይ የሰሜን አሜሪካ ጉብኝት እጅግ በጣም በጥቂቱ ልናወጋቹህ ወደድን። ይህን ለማድረግ የወደድነው በሁለት ምክንያት ነው። አንድም ይህ ታሪክ በመጽሃፍም ሆነ በዶክመንተሪ ፊልም ያልተሰራ እና የአሁኑ ትውልድ እምብዛም የማያውቀው በመሆኑ፤ ሁለትም ‘ታሪካችንን እኛ ካልተረክነው ማንም አይተርክልንም!’ በሚል ተነሳስተን ነው። ዋናው ቁምነገር ግን በዚህ ታሪክ ውስጥ የድሮው ገናና ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በውጭው አለም የነበራቸውን ተቀባይነት እናይበታለን። ይህ ብቻ አይደለም፤ ጃንሆይ ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ራዕይ ለማስታወስ እና በዚያውም ጥቂት እንድንማማር በማሰብ… እጅግ ከበዛው ታሪክ ትንሹን ጨልፈን እነሆ አበርክተናል… መልካም ቆይታ!
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ወደ አሜሪካ ከመምጣታቸው በፊት፤ በአዲስ አበባ በቤተ መንግስት ሽኝት ተደረገላቸው። አቡነ ባስልዮስም እንዲህ አሉ። “…የብሱን አቋርጠው፣አብህርትን ተሻግረው፣ አየራችንን አልፈው ሩቅ ወደሆነው ክፍለ አለም መሄድዎ ለሃገርዎ ለኢትዮጵያ እድገት፤ ለህዝቦችዎ የተሟላ ህይወት ለማግኘትና ቋሚ መሰረታዊ የሆነ አንድነት ለመመስረት ስለሆነ፤ የኢትዮጵያ አምላክ አሰቡበት እንዲያደርስዎና ከዚያም መልሶ በሰላም ወደ አገርዎ እንዲያስገባዎ… የኢትዮጵያም ህዝብ አጥቶ ላገኘበት፣ ወድቆ ለተነሳበት ግርማዊነትዎ በፍጹም ልቡ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት ያደርሳል” ግንቦት 10፣ 1946 ዓ.ም።
ጎበዝ ያን ግዜ የአሜሪካ መንገድ ሩቅ ነው። ዛሬ ተነስተን ነገ የምንገባበት አገር አልነበረም። ስለዚህ አንድ ሳምነት ለሚፈጀው ግዜ… ጃንሆይ እና ተከታዮቻቸው ከአዲስ አበባ ወደ ሊቢያ በአውሮፕላን ሄደው፤ ከዚያም ፈረንሳይ – ፓሪስ ደርሰው፤ ከፈረንሳይ ደግሞ በፈጣን መርከብ ተሳፍረው፤ ከስድስት ቀናት በኋላ ኒውዮርክ ከተማ ገቡ። ገና ከመርከብ ወርደው አቀባበል ሲደረግላቸው እንዲህ አሉ – ጃንሆይ። “ያገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ አድናቆትና በወዳጅነት ወደሚመለከተው ወደዚህ ታላቅ አገር አሜሪካ በመምጣቴ የሚሰማኝ ደስታ እጅግ የላቀ ነው። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አሜሪካንን ሲጎበኝ ዛሬ የመጀመሪያ ጊዜው ነው። የኛ አመጣጥ… ይህ ታላቅ አገር አሜሪካ በችግራችን ግዜ ላደረገልን እርዳታ፤ ለአሜሪካ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ምስጋናችንን ለማቅረብ ነው…” አሉ።
ጃንሆይ በንጋታው ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አመሩ። ዋሺንግተን ዲሲ በታላቅ ድምቀት ተቀበለቻቸው። ዲሲ በደረሱም ግዜ፤ የከተማው ከንቲባ የዋሺንግተን ዲሲ ከተማን ቁልፍ አበረከተላቸው። እሳቸውም እንዲህ አሉ፤ “የዋሺንግተን ከተማ ባደረገልኝ የወዳጅነት አቀባበል ተደስቻለሁ።…በክቡርነትዎ እጅ ለተሰጠኝ የከተማ ቁልፍ ከልብ የሆነ ምስጋናዬን እያቀረብኩ፤ ይህ ውብ የሆነ ዋና ከተማ ከዳር እስከዳር ክፍት ሆኖ ስላገኘሁት፤ የተሰጠኝ የከተማ ቁልፍ አያስፈልገኝም” በማለት የተሰበሰበውን ህዝብ ፈገግ አደረጉት።
የዚያኑ ቀን ወደ ኋይት ሃውስ ነበር ያመሩት። በቅድሚያ በወቅቱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዘዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን አቀባበል አደረጉላቸውና በክፍት መኪና፤ በመኪናቸውም ላይ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ እየተውለበለበ፤ ወደ ኋይት ሃውስ አመሩ። እዚያም የአሜሪካ የወቅቱ ፕሬዘዳንት የነበሩት አይዘን አወር ጃንሆይን በታላቅ ክብር ተቀበሏቸው። እነሆ የመጀመሪያው ጥቁር የአገር መሪ በኋይት ሃውስ ውስጥ ተስተናገደ።
በኋይት ሃውስ የእራት ግብዣም ላይ አይዘን ሃወር ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ንግግር ማድረግ ጀመሩ። “ግርማዊ ሆይ! ባለፉት መቶ አመታት በነዚህ ግንቦች በታጠረው ኋይት ሃውስ ውስጥ ብዙ የተመረጡ ሰዎች ተስተናግደውበታል። ከእነሱም ውስጥ አብዛኞቹ የአገራችን ሰዎች ሲሆኑ፤ የቀሩትም ጥቂት የውጭ አገር ሰዎች ናቸው። በየዘመኑ እዚህ ተሰብስበው ከተገኙት ወዳጆቻችን መካከል እንደዚህ ያለ የጋለ አቀባበል፤ ለአንዳቸውም ተደርጎላቸው አያውቅም። ግርማዊነታቸው በህዝባቸውና በእግዚአብሔር ከመታመን አንድ ደቂቃ እንኳን አቋርጠው አያውቁም።” ሲሉ ተጨበጨበ። ጭብጨባውንም ተከሎ ፕሬዘዳንቱ፤ ጽዋቸውን አነሱ፤ እንዲህም አሉ።
“ወይዛዝርት ክቡራን!ስለግርማዊነታቸው ክብር ከኔ ጋራ በመሆን ጽዋችሁን እንድታነሱ ይሁን!”
ጃንሆይም በኋይት ሃውስ ስለአገራቸውና ህዝባቸው ሰፋ አድርገው ተናገሩ። ከረዥሙ ንግግር ዋናው ፍሬ ሃሳብ በአጭሩ ይሄን ይመስላል፤ “ክቡር ፕሬዚደንት… በዛሬዋ ቀን በዚህ ቦታ ላይ ቆሜ፤ ለአሜሪካ ፕሬዚደንትና ህዝብ፤ እኔና ህዝቤ ያለንን ከፍ ያለ አድናቆት ስገልጽ በታላቅ ደስታ ነው። ክቡር ፕሬዘዳንት በጦር መሰናክሎች ምክንያት ታግዶ የነበረውን፤ አገሬን የማልማት ስራ እንድቀጥል በማበረታታትና በመደገፍ ላደረጉልኝ የወዳጅነት እርዳታ የኔና የህዝቤን ምስጋና እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ።”
ጃንሆይ በየደረሱበት ቦታ ከሚያደርጉት ንግግር፤ የህዝባቸውን መልካም ምኞት እና የአገራቸውን መልካም ስም በማስጠራት ይታወቃሉ። በዚያው መጠን ደግሞ የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ጨምሮ ሁሉም ባለስልጣናት ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር አልሸሸጉም፤ አልነፈጉም። ለምሳሌ በሚቀጥለው ቀን የአሜሪካ መንግስት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሔንሪ ባይሮድ፤ በባትለር ሆቴል ባደረገላቸው የእራት ግብዣ ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ እንዲህ አለ።
“…አለማችን በዚህ ሁሉ ብጥብጥ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ በአፍሪካ ውስጥ ነጻነት ያላት ጥንታዊና ሰላማዊ አገር የሆነች፤ ለ1ሺህ 600 አመታት የክርስትና ሃይማኖት ጠብቃ የኖረች አገር… ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ለኛ ለሁላችን ምሳሌ ሆና ትታያለች። …ኢትዮጵያ ከዘመን ዘመን እየተያያዘ የመጣውን ባህሏን ሳትለቅ፤ ወደ ዘመናዊው ጥበብ የሚወስዱ መንገዶችን ስትከተል ትታያለች።” በማለት ሰፊ ማብራሪያ ስለኢትዮጵያ ሰጥቶ ነበር።
በሚቀጥለው ቀን ጃንሆይ ለመላው የቴሌቪዥን፣ የሬድዮ እና የፕሬስ ጋዜጠኞች ንግግር አደረጉ። ጥያቄና መልሱም ቀጠለ። “ኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት አሰጣጣቹህ ምን ይመስላል? የአሜሪካንን Milk Shake ቀምሰዋል ወይ? ኢትዮጵያ ምን አይነት አገር ናት?” ለብዙ ጥያቄዎችን መልስ ሰጡ። የሚልክ ሼኩንም ጉዳይ፤ “አሜሪካ ከመጣሁ ሚልክ ሼክ አልጠጣሁም። ነገር ግን ኤርትራ ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ውስጥ እያለሁ ቀምሼው ነበር። ይጣፍጣል።” ሲሉ የአሜሪካ ጋዜጠኞች ስቀው ነበር። በዚህ ለህዝብ በተላለፈ ጥያቄና መልስ ዝግጅት ላይ ሁሉንም ጥያቄዎች በጥንቃቄና በጥሩ ሁኔታ መልሰው ሲያበቁ፤ በሚቀጥለው ቀን ወደ አሜሪካ ኮንግረስ ለመሄድ ተዘጋጁ።
በአሜሪካ ኮንግረስም እንዲህ ሆነ።የመላው አሜሪካውያን የህዝብ ተወካዮች በሚገኙበት በዚህ ኮንግረስ ውስጥ፤ ለመጀመሪያ ግዜ የጥቁር አገር መሪ ተገኘ። መገኘት ብቻ ሳይሆን የክብር አቀባበል ተደረገላቸው። የኮንግረሱ አፈ ጉባኤም እንዲህ ሲል ጀመረ። “ዛሬ ከኛ ጋር የምታዩዋቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ናቸው።” ሲል ጭብጨባው ከዳር እስከዳር አስተጋባ። በመቀጠልም ጃንሆይ ለኮንግረሱ እንዲህ አሉ።
“ምናልባት የኔ የአንድ ሩቅ የሆነች አገር መሪ፤ ከዚህ ምክር ቤታቹህ መካከል መገኘት፤ ለዩናይትድ ስቴትስ ምን ይጠቅማል ብላቹህ ታስቡ ይሆናል። …ኢትዮጵያ ለእናንተ አንዲት ታናሽና ሩቅ የሆነች አገር ናት። ነገር ግን ታናሽነትም ሆነ ርቀት አንዱን ከሌላው የማመዛዘን ጉዳይ ነው። በእውነቱ ግን ኢትዮጵያ በስፋትም ሆነ በህዝብ ብዛት፤ የካሊፎርንያን፣ ኦሬጎንን፣ ዋሺንግተን እና አይዳሆን አንድ ላይ አድርጎ፤ የፓሲፊክ ሰሜን ምዕራብን የምታክል አገር ናት። በቀይ ባህርና በተራሮቻችን ምሽግነት፤ በምስራቅ አፍሪቃ ክፍል ከማንኛውም አደጋ የተሰወርን ስለሆነ ርቀታችን በዚሁ መንፈስ ብቻ ነው።” ብለዋል።
ጃንሆይ ለአሜሪካ ኮንግረስ ባደረጉት በዚህ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያንና ባህሏን ቡናዋንና የቆዳ ምርቷን ሳይቀር ለኮንግረሱ አባላት አስተዋውቀዋል። ስለዘር መድልዎና የአፍሪቃ ነጻነት ድምጻቸውን አሰምተዋል። በዋናነት ግን የCollective Securityን አስፈላጊነት ደግመው ደጋግመው በመናገር፤ የአሜሪካ ኮንግረስ በዚህ ጉዳይ እንዲሰራበትና በአለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን አስገንዝበዋል።
እንዲህ እንዲህ እያልን… ጃንሆይ በአሜሪካ የፈጸሙትን ጉብኝት እና በያንዳንዱ ቀን ያደረጉትን ንግግር ዘርዝረን ልናበቃው አንችልም። ስለዚህ ከዚህ ቀጥሎ በሰሜን አሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት የተፈጸሙትን ዋና ዋና ነገሮች ብቻ እናውጋቹህ።
ግንቦት ሃያ ቀን በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ ተገኝተው በህግ የክብር ዶክተርነት ማዕረጋቸውን ተቀበሉ። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በህግ እና በህገ መንግስት እንድትመራ ያደረጉት አስተዋጽኦ ተነገረ። በተለይም አፍሪቃ በቅኝ ተገዝታ በነበረበት ወቅት፤ በተባበሩት መንግስታት አባላት ፊት ቆመው፤ ለአለም መሪዎች የሰጡት ማሳሰቢያ፤ ለትውስታ ያህል እንደገና ተነበበ። እንዲህ ይል ነበር።
“ወደ አፍሪቃ ምድር መጥታቹህ ብትረዱን በጣም ደስ ይለናል። ነገር ግን አመጣጣቹህ ህዝባችንን ለመግዛት፣ ለማዋረድ እና ለመዝረፍ ሳይሆን፤ በጤና፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ለማሰልጠን መሆኑን መገንዘብ ይገባችኋል።” ብለው ነበር – ጃንሆይ።
ሌላም ታሪክ እናክል። ለአሜሪካው ፕሬዘዳንት አይዘንሃወር፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ የእራት ግብዣ አድርገው ነበር – ጃንሆይ።
በሚቀጥሉት ቀናትም የቀድሞው ገናና የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ሩዝቬልት መቃብር ጋር የአበባ ጉንጉን ለማስቀመጥ፤ ሃይድ ፓርክ በሚገኘው የመቃብር ስፍራው ተገኙ። የሩዝቬልት ባለቤት በስፍራው ስለነበሩ፤ ጃንሆይ ይህንን አሉ። “ሚስስ ሩዝቬልት… እንደሚያውቁት ባለቤትዎ ወደ አሜሪካ እንድመጣ ከጋበዙኝ አስር አመታት አለፉ። ከዚያን ግዜ ጀምሮ አውቃቸዋለሁ። ዛሬ ግን እኚህን ታላቅ መሪ ከድሮው ይበልጥ በጣም የማቅበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ደስ ብሎኛል።”
ጃንሆይ የዋሺንግተን ዲሲ ቆይታቸው አብቅቶ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ አመሩ። በኒው ዮርክ ከተማ ዛሬም ድረስ ስሙ የገነነ አንድ ቤተክርስቲያን አለ – አቢሲንያ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል። ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያኑ ከአምልኮት ስርአት በተጨማሪ፤ እንደሙዚየም ይጎበኛል። ጃንሆይ ከ64 አመታት በፊት ወደዚህ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ እጅግ በጣም ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደረገላቸው። የቤተ ክርስቲያኑ አለቃ ብፁዕ አዳም ክሌይተንም እንዲህ አሉ።
“…ምንም እንኳን እኛ የአሜሪካ ጥቁሮች ከፍተኛውን የእውቀትና የኑሮ ደረጃ እስካሁን ድረስ ለማግኘት ባንችል፤ በቅርብ ግዜ ውስጥ አላማችንን ከግቡ እናደርሳለን። ግርማዊ ሆይ! መላው የአፍሪካ አገሮች እንደኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነታቸውን እንዲያገኙ የምናደርገው የጸሎት፣ የተስፋና የህልማችን ማህደር ግርማዊነትዎና ኢትዮጵያ ናት። ስለዚህ አሁን ግርማዊነትዎን ምንግዜም በጸሎትዎ እንዳይረሱን እንለምናለን። እኛም የጦርነት ዘመን አብቅቶ፤ የሰላም ቀን የሚመሰረትበት ቀን እንዲቀርብልን በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንማጸናለን።” ብለው ንግግራቸውን በጸሎት አሳረጉ።
በነገራቹህ ላይ… ወደዚህ የኒው ዮርክ አቢሲንያ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ፤ በቅድሚያ የሚታየው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የተበረከተው ትልቅ የኢትዮጵያ መስቀል ነው። የኒውዮርክ አቢሲንያ አባላት ከምስረታው ጀምሮ… እስካሁን ድረስ ለቀዳማዊ ኃይለ ስላሴና ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ቤተክርስቲያናቸውን “አቢሲኒያ” ያሉት ኢትዮጵያ በአድዋ ድል ጣልያንን ካሸንፈች በኋላ፤ “ጥቁር ህዝብ ያሸንፋል” በሚል እሳቤ፤ በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ የመንፈስ ጥንካሬን ለመፍጠር ጭምር ነው።
ጃንሆይ በሰሜን አሜሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት ቀጥሏል። ከኒውዮርክ ከተማ በኋላ ወደቦስተን አቀኑ። በዚያ ትንሽ ቆይታ አድርገዋል። ከቦስተን በኋላ የካናዳን ድንበር ተሻግረው ኦታዋ እና ሞንትሪያልን ጎብኝተዋል። ከዚያ ሲመለሱ በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ተጨማሪ የዶክትሬት ማዕረግ ተሸልመዋል። ቺካጎ እና ሜኒሲታ ላይ፣ ሲያትል ላይ ተመሳሳይ ጉብኝት አድርገዋል።
ከዚያም በሲያትል የሚገኘውን የብሬመርትን ጦር መርከብ ፋብሪካ ለቀድሞው የጦር መርከቦቻችን የግዢ እቅድ የያዙበት፣ የቦይንግ አውሮፕላን በመጎብኘት እና ለአሁኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሰረት የጣሉበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። እንግዲህ የሁሉንም ከተሞች ጉብኝት ዘርዝረን ለመጨረስ አንችልም፤ ሆኖም በሳንፍራንሲስኮ፣ በሎስ አንጀለስ፣ በኦክላሆማ፣ በሜክሲኮ፣ በሉዊዚያና ትልቅ የሚባል የስራ ጉብኝት አደረጉ። በየሄዱበትም ሁሉ ያማረና የደመቀ የክብር አቀባበል ይደረግላቸው ነበር። በመጨረሻም ወደ አውሮጳ ተሳፍረው ሲያበቁ፤ ወደ ኤርትራ በመብረር፤ አስመራ ከተማ ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበል እጅግ ደማቅ ነበር።
ይህን ሁሉ እንድናነሳ ያደረገን፤ የሰሞኑ የዶ/ር አብይ አህመድ ጉዞ ሲሆን፤ ጨዋታን ጨዋታ እያመጣው በታሪክ ወደኋላ ብዙ ሄድን። የዛሬ 64 አመት… ጃንሆይ አሜሪካን ሲጎበኙ የነበራቸው ህልም እና አሁን ያለንበትን ሁኔታ ለማነጻጸር ይህ ትርክት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል። ለማንኛውም የጃንሆይ የአሜሪካ ጉብኝትን በተመለከተ ክፍል ሁለትን በቅርብ ቀናት ውስጥ፤ ምናልባትም ከዶ/ር አብይ ጉብኝት በፊት ይዘንላቹህ እንቀርባለን።
ይህን ሁሉ እንድናነሳ ያደረገን፤ የሰሞኑ የዶ/ር አብይ አህመድ ጉዞ ሲሆን፤ ጨዋታን ጨዋታ እያመጣው በታሪክ ወደኋላ ብዙ ሄድን። የዛሬ 64 አመት… ጃንሆይ አሜሪካን ሲጎበኙ የነበራቸው ህልም እና አሁን ያለንበትን ሁኔታ ለማነጻጸር ይህ ትርክት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል። ለማንኛውም የጃንሆይ የአሜሪካ ጉብኝትን በተመለከተ ክፍል ሁለትን በቅርብ ቀናት ውስጥ፤ ምናልባትም ከዶ/ር አብይ ጉብኝት በፊት ይዘንላቹህ እንቀርባለን።
No comments